ሰው ሁሉ ነገር ቢኖረው ነገር ግን ምንም መነሳሳትና መቀጣጠል ከሌለውና ልቡ ከቀዘቀዘ ምንም አይጠቅምም፡፡ ስለዚህ ነው መፅሃፍ ቅዱስ ሁሌ እንድንቀጣጠል የሚያዘን፡፡
ለሥራ ከመትጋት አትለግሙ፤ በመንፈስ የምትቃጠሉ ሁኑ፤ ለጌታ ተገዙ፤ ሮሜ 10፡11
ሰው ምንም ያህል የመውረስ የመውጣት የማገልገል እድሉም ቢኖረው እሳቱ ከተዳፈነና ልቡ ከሞተ ምንም ማድረግ ያቅተዋል፡፡
ኢያሱም ሸመገለ በዕድሜም አረጀ እግዚአብሔርም አለው፦ አንተ ሸመገልህ፥ በዕድሜህም አረጀህ፤ ያልተወረሰች እጅግ ብዙ ምድር ገና ቀርታለች፤ ኢያሱ 13:1
ኢያሱ እንኳን እድሜው አርጅቶ ነው ነገር ግን እድሜያቸው ሳያረጅ በውስጣቸው የታመቀ ሃይል እያለ ልባቸው ያረጀ ሰዎች ለእግዚአብሄር መንግስት ያላቸው ጠቀሜታ በእጅጉ ይቀንሳል፡፡ ለመንግስቱ ስራ ያላቸው ምንም የማይጠቅሙ ሰዎች ይሆናሉ፡፡ ይህንን የሚያወርሰንን እሳት የሚበሉትን ነገሮችን ካወቅን እሳታችንን በሚገባ እንጠብቃለን፡፡
ቀድሞ የነበረንን እሳትን መቀጣጠልን ግለትን የሚያጠፉት አራት ነገሮችን ተግተን ከጠበቅን እግዚአብሄር እስከመጨረሻው የምንጠቅም ውድ እቃዎች እንሆናለን፡፡
- የኑሮ ሃሳብን መቀበል
የህይወት ዘመን ሃሳብ ፊት ከሰጠነው አሽመድምዶ ሽባ ሊያደርገን የሚችል አፍራሽ ሃይል ነው፡፡ ስለአቅርቦታችን እግዚአብሄርን በማመን መንግስቱንና ፅድቁን በመፈለግ ላይ ካላተኮርን የአለም ሃሳብ መቀጣጠላችንን ለመብላትና ከአገልግሎት ውጭ ለማድርግ የማይናቅ ሃይል አለው፡፡
የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት ማታለል የሌላውም ነገር ምኞት ገብተው ቃሉን ያንቃሉ፥ የማያፈራም ይሆናል። ማርቆስ 4፡19
በእሾህ መካከልም የወደቀ እነዚህ የሚሰሙት ናቸው፤ መንገዳቸውንም ሄደው በሕይወት ዘመን በአሳብና በባለ ጠግነት ምቾት ይታነቃሉ፥ ሙሉ ፍሬም አያፈሩም። ሉቃስ 8፡14
2. የአመለካከታችን መበላሸት
አመለካከታችን በእግዚአብሄር ቃል በየጊዜው ካልታደሰ ሊበላሽና ለክርስቶስ ካለን ቅንነት ሊለወጥ ይችላል፡፡ ሳናስበው ለጌታ የነበረንን እሳት ለጌታ ስራ መስዋእት ለማድርግ የነበረንን ግለት ከቦታው ልናጣው ልንቀዘቅዝ እንችላለን፡፡
ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ። 2ኛ ቆሮንቶስ 11፡3
ለእግዚአብሄር ያለን ቅንነት ሲለወጥና በመንፈስ መቀጣጠላችን ሲቀንስ ራሳችንን ከእግዚአብሄር መጠበቅ እንጀምራለን፡፡ ጊዜያችንን ጉልበታችንን እቅውቀታችንን ከእግዚአብሄር ስራ መሰሰት እንጀምራለን፡፡ እኔ የእርሱን ቤት ስሰራ እግዚአብሄር የኔን ቤት ይሰራል የሚለውን የዋህነታችንን ጥለን እኛ ለራሳችን መስራት እንጀምራለን፡፡
አንድ መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ፦ ጌታ ሆይ፥ ካልዘራህባት የምታጭድ ካልበተንህባትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፤ ማቴዎስ 25፡24
3. ከንቱ ውድድር
ሰው እግዚአብሄር ያዘጋጀለትን ስራ ትቶ ለሌላ ስራ ለከተጠራው ከጎረቤቱ ጋር መወዳደር ሲጀምር እሳቱን ያጣዋል፡፡ ሰው እግዚአብሄር የሰጠውን ስራ ለመፈፀም አይኑን ጌታ ላይ ካደረገ ብቻ ነው እሳቱን በልቡ የሚጠብቀው፡፡ ስለውድድር ብሎ እግዚአብሄር ያልጠራው ቦታ ላይ ሲገኝ እሳቱና ግለቱ አብሮት አይሆንም፡፡ ስለዚህ የባሰ ተስፋ ይቆርጣል፡፡ ሰው ግን ከውድድር በራሱ ፈቃድ ተሰናብቶ እግዚአብሄር በሰጠው የአገልግሎት ስራ ላይ ካተኮረ እሳቱ እይጨመረ እየጨመረ ይሄዳል፡፡
4. የሰዎች አመለካከት
በክርስቶስ ማን እንደሆንን በደንብ ካልተረዳንና የሰዎች አመለካከት እኛን ዝቅ አድርጎ መመልከታቸውን ከተቀበልነው እሳቱ ይዳፈናል፡፡ ሰዎች ከተለያየ ነገር ተነስተው አንተ ምንም ማድረግ አትችልም ያሉንን ካመንንና እንደዛው መኖር ከጀመርን ለእግዚአብሄ ስራ ለመሮጥ ወሳኝ የሆነውን እሳቱን እናዳፍነዋለን፡፡ ራሳችንን በክርስቶስ ማየት ካቃተን እሳቱ እየደበዘዘ ለእግዚአብሄር ለመትጋት ጉልበት እያጠረን ይሄዳል፡፡
በቃልና በኑሮ በፍቅርም በእምነትም በንጽሕናም ለሚያምኑቱ ምሳሌ ሁን እንጂ፥ ማንም ታናሽነትህን አይናቀው። 1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 4፡11-12
እሳቱን የመጠበቅ ጉዳይ እኔን አይመለከተኝም የሚል ሰው የለም፡፡ ጌታን ለማገልገል እሳቱ ሙሉ የነበረው ኤልያስ የኤልዛቤልን ዛቻ ሰምቶ ወደልቡ ስለከተተው ከአባቶቼ አልበልጥም ብሎ ተስፋ ቆረጠ፡፡ የእግዚአብሔር ነቢይ የልቡ እሳት ተዳፈነ፡፡
እርሱም አንድ ቀን የሚያህል መንገድ በምድረ በዳ ሄደ፤ መጥቶም ከክትክታ ዛፍ በታች ተቀመጠና፦ ይበቃኛል አሁንም፥ አቤቱ፥ እኔ ከአባቶቼ አልበልጥምና ነፍሴን ውሰድ ብሎ እንዲሞት ለመነ። 1ኛ ነገሥት 19:4
ስለዚህ ነው መፅሃፍ አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ የህይወት መውጫ ከእርሱ ነውና የሚለው፡፡
አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ፣ የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና ምሳሌ 4:23
No comments:
Post a Comment