ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም እንጂ ስለ ሌላ አይመጣም፤ እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ። ዮሐንስ ወንጌል 10፡10
እየሱስ ደግሞ የመጣው ህይወት እንዲሆንልን እንዲበዛልንም ነው፡፡ እንግዲህ በህይወታችን ስፍራ የምንሰጠው አለማውን ይፈፅማል፡፡ ስለዚህ ነው ለዲያቢሎስ ስፍራን አትስጡት ብሎ መፅሃፍ ቅዱስ የሚያስጠነቅቀው፡፡ ለዲያቢሎስ ስፍራን ከሰጠነው የመስረቅ የማረድና የማጥፋት አላማውን በእኛ ላይ ይፈፅማል፡፡
ሰይጣን በህይወታችን ከሰረቀ ካረደና ካጠፋ ስፍራን ሰጥተነዋል ማለት ነው፡፡ እኛ ስፍራን ካልሰጠነው ሊሰርቀን ሊያርድና ሊያጠፋ የማይችል የተሸነፈ ጠላት ነው፡፡ ኢየሱስ በመስቀሉ ስራ ሰይጣንን ፈፅሞ ስላሸነፈው ካልፈቀድንለትና በህይወታችን ስፍራ ካልሰጠነው በስተቀር በሃይል ምንም ሊያደርግ አይችልም፡፡
አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው። ቆላስይስ 2፡15
ሰው አንዴ ለዲያቢሎስ ስፍራ ከሰጠው ስራውን እየጨመረ ህይወትን መስረቅ ማረድና ማጥፋቱን እያበዛውና ፈፅሞ እስከሚያጠፋ ድርስ እያስፋፋው ይሄዳል፡፡ በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፥ ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት። ኤፌሶን 4፡27 ለዲያቢሎስ ስፍራ የምንሰጥበት መንገዶች ምንድናቸው
- ቁጣን አለመቆጣጠር ፣ ይቅር አለማለትና ምሬት
መቆጣት አግባብ ነው፡፡ ነገር ግን ከልክ ሲያልፍ ምሬት ይሆናል፡፡ ቶሎ ይቅር ካላልን በስተቀር በህይወታችን ለዲያቢሎስ ስፍራን እንሰጠዋለን፡፡
ተቆጡ ኃጢአትንም አታድርጉ፤ በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፥ ኤፌሶን 4፡26-27
የሰው ቁጣ የእግዚአብሄርን ፅድቅ አይሰራም፡፡ የሰው ቁጣ መጠኑ ስለማይታወቅ አደገኛ ነው፡፡ የሰው ቁጣ ጥበብ ስለሚጎድለው የቁጣን ትክክለኛ አላማ ግቡን እንዲመታ አያደርገውም፡፡ የሰው ቁጣ የራስን ስሜት ከመግለፅ ውጭ አለምን በፅድቅ የማስተዳደር አቅም የለውም፡፡
የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ ይሁን ፣ የሰው ቁጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አይሰራምና" ይላል ። ያዕቆብ 1 : 19 – 20
ስለዚህ ነው ሁልጊዜ ለእግዚአብሄር አገዛዝ ስፍራ መስጠት ያለብንና ራሳችን መበቀል የሌለብን፡፡ አለምን የምንመራው እግዚአብሄር እንጂ እኛ ስላይደለን ከሰው ጋር ስንጣላ የሁለታችንም ጌታ በሰማይ አንዳለ እውቅና መስጠት አለብን፡፡ ተወዳጆች ሆይ፥ ራሳችሁ አትበቀሉ፥ ለቍጣው ፈንታ ስጡ እንጂ፤ በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና። ሮሜ 12፡19
- ጥላቻ
በህይወት ዘመናችን የምንጠላው ዲያቢሎስን ብቻ ነው፡፡ በምድር ላይ አንዱንም የእግዚአብሄር ፍጥረት እንድንጠላ ፈቃድ የለንም፡፡ ጥላቻ ለሰይጣን በርን የምንከፍትበት መንገድ ነው፡፡ ጥላቻ የሰይጣን ለም መሬት ነው፡፡ ሰይጣን በጥላቻ ልብ ውስጥ ዘርቶት የማይበቅልለት የመስረቅ የማረድና የማጥፋት ዘር የለም፡፡ ጥላቻ ለሰይጣን ምቹ ቦታ ነው፡፡ ጥላቻ በሌለበት ልብ ውስጥ ሰይጣን መስራት አይችልም፡፡ እኛ ወንድሞችን የምንወድ ስለ ሆንን ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገርን እናውቃለን፤ ወንድሙን የማይወድ በሞት ይኖራል። ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፥ ነፍሰ ገዳይም የሆነ ሁሉ የዘላለም ሕይወት በእርሱ እንዳይኖር ታውቃላችሁ። 1ኛ ዮሐንስ 3፡14-15
- ትእቢት
ሌላው ኢየሱስ ሰይጣንን አሸንፎት ሳለ ሰይጣን ህይወታችንን የሚሰርቅበት የሚያርድና የሚያጠፋበት መንገድ በትእቢት ለሰይጣን ስፍራ መስጠት ነው፡፡ ትእቢት ከሆኑት በላይ ራስን ከፍ አድርጎ ማየት ነው፡፡ ትእቢት እግዚአብሄር ያልሰጠቅውን ደረጃ መውሰድ ነው፡፡
እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ የእምነትን መጠን እንዳካፈለው፥ እንደ ባለ አእምሮ እንዲያስብ እንጂ ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ በተሰጠኝ ጸጋ እናገራለሁ። ሮሜ 12፡3
ትእቢት ሁሉንም ከእግዚአብሄር ተቀብለነው ሳለ የእኛ እንደሆነ ምንጩ እኛ ራሳችን እንደሆንን ማሰብ ነው፡፡
አንተ እንድትበልጥ ማን አድርጎሃል? ያልተቀበልኸውስ ምን አለህ? የተቀበልህ ከሆንህ ግን እንዳልተቀበልህ የምትመካ ስለ ምንድር ነው? 1ኛ ቆሮንቶስ ሰዎች 4፡7
ሰይጣንን የምንቃወመው በእግዚአብሄር ፀጋ ሲሆን እግዚአብሄር ደግሞ ፀጋን የሚሰጠው ለትሁታን ብቻ ነው፡፡ ለትእቢተኛ ፀጋን አይሰጥም፡፡ እንዲያውም ትእቢተኛን ይቃወመዋል፡፡ የእግዚአብሄርን ተቃውሞ የሚቋቋሞ ማንም የለም፡፡
ነገር ግን ጸጋን አብልጦ ይሰጣል፤ ስለዚህ፦ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል ይላል። ያዕቆብ 4፡6
ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት! ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ጠላት #ዲያቢሎስ #ስፍራ #ኢየሱስ #ጥላቻ #ትእቢት #መራርነት #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ
No comments:
Post a Comment