Popular Posts

Wednesday, September 7, 2016

በዝምታ ያፈራል!



መጠበቅ ሁል ጊዜ ለስጋ አይመችም፡፡ ስጋ የሚፈልገው ሁሉ ነገር ወዲያው እንዲሆንለት ነው፡፡ ረጋ ብሎ ጠብቆ የሚሆንን ነገር የሚመርጠው ጥቅሙን የሚረዳ የበሰለ ሰው ብቻ ነው፡፡ ተፈጥሮአዊው ሰው ቢችል ሳይለፋ ሳይሰራ ሳይጠብቅ ሁሉ ነገር እንዲሁ ቢሆንለት ይመርጣል፡፡
እግዚአብሄርን መጠበቅ የእግዚአብሄርን አሰራር በትግስት መጠበቅና የእግዚአብሄርን እርምጃን መታገስ ለስጋዊ ተፈጥሮ አይመችም፡፡ የሰው ህይወት በመሰረታዊ ደረጃ የሚለወጠው የእግዚአብሄር ቃል ነው፡፡ የእግዚአብሄር ቃል ደግሞ ሲሰራ በቅፅበት ላይሰራ ይችላል፡፡ የእግዚአብሄር ቃል በሂደት ጊዜ ወስዶ ነው የሚሰራው፡፡
የእግዚአብሄር ቃል እንደዘር ነው፡፡ ዘር ተዘርቶ ፍሬ እስከሚያፈራ ጊዜ ይወስዳል፡፡ የእግዚአብሄር ቃል ፍሬ ትግስትን ይጠይቃል፡፡
ስለዚህ ነው ይህንን የእግዚአብሄ አሰራር የማይረዱ ሰዎች ሁሉ ነገር በአስቸኳይ እንዲሆንላቸውና ህይወታቸው በትንቢት በአንድ ቀን እንዲለወጥ የሚፈልጉት፡፡ እነዚህ አይነት ሰዎች በህይወታቸው መሰረታዊ ለውጥ ለሚያመጣው ቀስ ብሎ ከሚሰራው ከእግዚአብሄር ቃል ትምህርት ይልቅ ድንገተኛ በረከት ይፈልጋሉ፡፡
ነገር ግን እውነተኛና የእኛ የምንለው ቋሚ የህይወት ለውጥ የሚያመጣው የእግዚአብሄርን ቃል ሰምተን የምናደርገውና ፍሬን የምናፈራበት አሰራር ነው፡፡
የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፥ የሚሠራም፥ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፥ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፥ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል፤ ዕብራውያን 4፡12
አንድ እርግጠኛ መሆን ያለብን ነገር የእግዚአብሄር ቃል በህይወቴ አለ ወይ የሚለውን ጥያቄ መመለስ ነው፡፡ ፍሬ ለማፍራት የእግዚአብሄርን ቃል መስማታችንና መታዘዛችን ወሳኝ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ቃል በውስጣችን ከሌለ ምንም የለም ማለት ነው፡፡ የእግዚአብሄር ቃል በውስጣችን ካለ ግን ለውጥንና ፍሬን መምጣቱ እርግጥ ነው፡፡
በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ ይሆንላችሁማል። ብዙ ፍሬ ብታፈሩና ደቀ መዛሙርቴ ብትሆኑ በዚህ አባቴ ይከበራል። ዮሃንስ 15፡7-8
የእግዚአብሄርን ቃል ካደረግን በኋላ መፅናት ይጠበቅብናል፡፡ ዘር ተዘርቶ ባንዴ ፍሬ እንደማያፈራ ሁሉ የእግዚአብሄር ቃልን ከሰማንና ከታዘዝን በኋላ እንዲያድግ ለማፍራት ጊዜ ይወስዳል፡፡
የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ መጽናት ያስፈልጋችኋልና። ዕብራውያን 10፡36
እርሱም አለ፦ በምድር ዘርን እንደሚዘራ ሰው የእግዚአብሔር መንግሥት እንደዚህ ናት ሌሊትና ቀን ይተኛልም ይነሣልም፥ እርሱም እንዴት እንደሚሆን ሳያውቅ ዘሩ ይበቅላል ያድግማል። ምድሪቱም አውቃ በመጀመሪያ ቡቃያ ኋላም ዛላ ኋላም በዛላው ፍጹም ሰብል ታፈራለች። ፍሬ ግን ሲበስል መከር ደርሶአልና ወዲያው ማጭድ ይልካል። ማርቆስ 4፡26-29

No comments:

Post a Comment