ልጅነታችን ክብር አለው ልጅነታችን የእግዚአብሄር የቤተሰብነት አባል ታላቅ ክብር አለው፡፡ እንደ ልጅነታችን ክብር የማይስማማ ምንም ነገር ለማድረግ እንፈልግም፡፡ ከልጅነት ክብራችን ጋር የማይሄድ ማንኛውም ጥቅም እንንቀዋለን፡፡ ክብራችን ተነክቶ የምናገኘውን ጥቅም ከምናገኝ ሞት ይሻለናል፡፡
እኔ ግን ከእነዚህ ሁሉ ምንም አልተጠቀምሁም። እንዲህ እንዲሆንልኝ ይህን አልጽፍም፤ ማንም ትምክህቴን ከንቱ ከሚያደርግብኝ ሞት ይሻለኛልና። 1ኛ ቆሮንቶስ 9፡15
አንዳንድ ሰዎች ሃዋሪያው ጳውሎስ ጌታን የሚያገለግለው ስለሚጠቀም ነው ጥቅሙ ቢቀርነት አገልግሎቱን ያቆማል የሚል አመለካከት ለነበራቸው ሰዎች ለማሳየት ሰዎች የሚሰጡትን ስጦታ አልተቀበለም፡፡ ምክኒያም ለጥቅም ጌታን ማገልገል ክብራችን አይፈቅድም፡፡
አገልግሎታችንም እንዳይነቀፍ በአንዳች ነገር ማሰናከያ ከቶ አንሰጥም። ነገር ግን በሁሉ እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ራሳችንን እናማጥናለን፤ 2ኛ ቆሮንቶስ 6፡3-4
- ለመዋሸት ክብራችን እይፈቅድም
ውሸት ከፍርሃት ይመነጫል፡፡ እኛ ደግሞ በፍቅር የምንኖር ስለሆንንና ፍፁም ፍቅርም ፍርሃትን አውጥቶ ስለሚጥል አንዋሽም፡፡ ከምንዋሽ በውሸት የሚመጣው ጥቅምን ቢቀርብን ይሻለናል፡፡ የልጅነትን ክብራችንን እንዲነካ ለምንም ነገር አንፈቅድም፡፡ እውነትን የማንናገርለት ነገር የእኛ እንዳልሆነ እናምናለን፡፡
እግዚአብሔር ይቀድማችኋልና፥ የእስራኤልም አምላክ ይከተላችኋልና በችኰላ አትወጡም በመኰብለልም አትሄዱም። ኢሳይያስ 52፥12
- ለመለማመጥ ክብራችን አይፈቅድም በመሃላ በመለማመጥ በብዙ ቃልና በብዙ ጭንቅ ሰዎችን ልናሳምን አንጥርም፡፡ በእግዚአብሄር እንታመናለን፡፡ እግዚአብሄር ያላደረግልንን ነገር አንወስድም፡፡ የራሳችንን ሃይል ጨምረን የምናመጣው ነገር በእውነት የእኛ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ያላደረገልንን ነገር ሁሉ የእኛ እንዳልሆነ ነው የምንቆጥረው፡፡
በራስህም አትማል፥ አንዲቱን ጠጉር ነጭ ወይም ጥቁር ልታደርግ አትችልምና። ነገር ግን ቃላችሁ አዎን አዎን ወይም አይደለም አይደለም ይሁን፤ ከነዚህም የወጣ ከክፉው ነው። ማቴዎስ 5፡36-37
- ክብራችን ነውረኛን ረብ አይፈቅድም የቤተሰቡ ደረጃ ክብር የሌለበትን ጥቅም ያስንቃል፡፡ እግዚአብሄር በክብር እንደሚባርክ ነው የምናምነው፡፡ በነውር በወስላታነት በታማኝነት ያልሆነ ጥቅምን እንንቃለን፡፡ እግዚአብሄር በክብር እንደሚባርክ እናምናለን፡፡
ነውረኛ ረብ የማይወዱ፥ በንጹሕ ሕሊና የሃይማኖትን ምሥጢር የሚይዙ ሊሆኑ ይገባቸዋል። 1ኛ ጢሞቴዎስ 3፡9
አምላኬም እንደ ባለ ጠግነቱ መጠን በክብር በክርስቶስ ኢየሱስ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ ይሞላባችኋል። ፊልጵስዩስ 4፡19
- ለጥቅም ጌታን ማገልገል ክብራችን አይፈቅድም ፡፡ ሃዋሪያው ጳውሎስ መስራት ሲችል እራሱ እየሰራ የሚያስፈልገውን ያሟላ ነበር፡፡
ከእናንተ ዘንድ በአንዱ ስንኳ እንዳንከብድበት፥ ሌሊትና ቀን በድካምና በጥረት እየሠራን እንኖር ነበር እንጂ፥ ከማንም እንጀራን እንዲያው አልበላንም። 2ኛ ተሰሎንቄ ሰዎች 3፡8
- ከስስታም ሰው ለመቀበል ክብራችን አይፈቅድም፡፡
ሰው የሚያደርግልንና የሚሰጠን ደስ ብሎት ከልቡ ካልሆነ እየሰሰተ ከሚሰጠን ሰው ለመቀበል ክብራችን እይፈቅድም፡፡ ሰው በልቡ ባይበላ እያለ ከሚሰጠን መራብ ይሻለናል፡፡
የቀናተኛን ሰው እንጀራ አትብላ፥ ጣፋጩ መብልም አይመርህ፤ በልቡ እንዳሰበ እንዲሁ ነውና፤ ብላ ጠጣ ይልሃል፥ ልቡ ግን ካንተ ጋር አይደለም። የበላኸውን መብል ትተፋዋለህ፥ ያማረውንም ቃልህን ታጠፋዋለህ። ምሳሌ 23፡6-8
- ወንጌልን ዝቅ አድርጎ ለሚያይ ሰው ጋር መከራከር ክብራችን እይፈቅድም፡፡ የወንጌልን ክብር ከማይረዳ እንዲያውም ልንጎዳው እንደመጣን ከሚያስብ ሰው ጋር በክርክር ጊዜያችንንና ጉልበታችንን መጨረስ ክብራችን አይፈቅደውም፡፡
በእግራቸው እንዳይረግጡት ተመልሰውም እንዳይነክሱአችሁ፥ የተቀደሰውን ለውሾች አትስጡ፥ ዕንቁዎቻችሁንም በእሪያዎች ፊት አትጣሉ። ማቴዎስ 7፡6
- ከሰነፍ ጋር ለመመላስ ክብራችን አይፈቅድም፡፡ እውነትን ለማወቅ ፈልጎ ከሆነ እንረዳዋለን፡፡ እኛን ለማዋረድ ፈልጎ ከሆነ ለክርክር ጊዜ የለንም፡፡ አንተ ደግሞ እርሱን እንዳትመስል ለሰነፍ እንደ ስንፍናው አትመልስለት። ምሳሌ 26፡4
በክርክርና በጭቅጭቅ የሚገኘውን ጥቅም ለማግኘት ክብራችን አይፈቅድም፡፡ ከክርክር ይርቅ ዘንድ ለሰው ክብሩ ነው፤ ሰነፍ ሁሉ ግን እንዲህ ባለ ነገር ይጣመራል። ምሳሌ 20፡3
እንግዲህ ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል፤ . . . የማይጨቃጨቅ ነገር ግን ገር የሆነ፥ 1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 3፡3
- መስራት እየቻልን የሌላን ሰው እርዳታ አንጠብቅም፡፡
ለለበጸጥታም ትኖሩ ዘንድ ልትቀኑ፥ የራሳችሁንም ጉዳይ ልትጠነቀቁ፥ እንዳዘዝናችሁም፥ በውጭ ባሉት ዘንድ በአገባብ እንድትመላለሱ፥ አንዳችም እንዳያስፈልጋችሁ በእጃችሁ ልትሠሩ እንለምናችኋለን። 1ኛ ተሰሎንቄ 4፡11-12
- ቃልኪዳናችን ከእግዚአብሄር ጋር ስለሆነ ስለመባረካችን ስለማደጋችንና ስለመለወጣችን ማንም ስጋ የለበሰ ክብሩን አንዲወስድ አንፈቅድም፡፡ ስለስኬታችን ክብሩን ከጌታ ጋር የሚሻማ ከሆነ ጥቅሙን እንተዋለን፡፡ ሰው እኔ አነሳሁት ከሚለን የሚያደርግልን ይቅርብን፡፡
አብራምም የሰዶምን ንጉሥ አለው፦ ሰማይንና ምድርን ወደሚገዛ ወደ ልዑል እግዚአብሔር እጄን ከፍ አድርጌአለሁ፤ አንተ፦ አብራምን ባለጠጋ አደረግሁት እንዳትል፥ ብላቴኖቹ ከበሉት በቀር ከእኔ ጋር ከሄዱትም ድርሻ በቀር፥ ፈትልም ቢሆን የጫማ ማዘቢያም ቢሆን፥ ለአንተ ከሆነው ሁሉ እንዳልወስድ አውናን ኤስኮልም መምሬም እነርሱ ድርሻቸውን ይውሰዱ። ዘፍጥረት 14፡22-24
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#እግዚአብሔር #አምላክ #ክብር #ምሪት #ሰላም #ቃል #እረፍት #አምልኮ #ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ
No comments:
Post a Comment