Popular Posts

Thursday, March 28, 2019

ትንፋሽህንና መንገድህን ሁሉ በእጁ የያዘውን አምላክ


የፈጠረን እግዚአብሄር ነው፡፡ ህይወትንና ትንፋሽን የሰጠን እግዚአብሄር ነው፡፡
አፈርም ወደ ነበረበት ምድር ሳይመለስ፥ ነፍስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ ፈጣሪህን አስብ። መጽሐፈ መክብብ 12፡7
የእያንዳንዳችንን ትንፋሽ የያዘው እግዚአብሄር ነው፡፡
ምድርን አደራ የሰጠው ማን ነው? ዓለምንስ ሁሉ በእርሱ ላይ ያኖረ ማን ነው? እርሱ ልቡን ወደ ራሱ ቢመልስ፥ መንፈሱንና እስትንፋሱን ወደ ራሱ ቢሰበስብ፥ ሥጋ ለባሽ ሁሉ በአንድነት ይጠፋል፥ ሰውም ወደ አፈር ይመለሳል።  መጽሐፈ ኢዮብ 34፡13-15
በመፅሃፍ ቅዱስ በትንቢተ ዳንኤል ምእራፍ 5 ከቁጥር 18 እስከ 23 የምንመለከተው ታሪክ የንጉስ አባት የናቡከደነፆር የልጁ የብልጣሶር ታሪክን ነው፡፡
ልጁ ብልጣሶር እግዚአብሄርን ስላልፈራና ስላላከበረ እግዚአብሄር የተናገረውን ንግግር እንመለከታለን፡፡
እግዚአብሄር ለአባቱ ለንጉስ ናቡከደነፆር እንዴት ታላቅ ክብርን እንደሰጠው መፅሃፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡ ናቡከደነፆር በምድር ላይ የነበረው ታላቅነት ሁሉ ከእግዚአብሄር የተሰጠው ክብር ነበር፡፡  
ንጉሥ ሆይ፥ ልዑል አምላክ ለአባትህ ለናቡከደነፆር መንግሥትንና ታላቅነትን ክብርንና ግርማን ሰጠው። ስለ ሰጠው ታላቅነት ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩም ቋንቋ የሚናገሩ ሁሉ በፊቱ ይንቀጠቀጡና ይፈሩ ነበር፤ የፈቀደውን ይገድል፥ የፈቀደውንም በሕይወት ያኖር ነበር፤ የፈቀደውንም ያነሣ፥ የፈቀደውንም ያዋርድ ነበር። ትንቢተ ዳንኤል 5፡18-19
አባቱ ግን በራሱ እንዴት እንደተመካና የማይገባውን ነገር እንዳደረገ እግዚአብሄርን እንደናቀው ያስታውሰዋል፡፡
ልቡ ግን በታበየ በኵራትም ያደርግ ዘንድ መንፈሱ በጠነከረ ጊዜ፥ ከመንግሥቱ ዙፋን ተዋረደ፥ ክብሩም ተለየው። ትንቢተ ዳንኤል 5፡20
በዚህ ምክኒያት ያ አለም ሁሉ ይገዛለትና ያከብረው ንጉስ እንዴት ከንጉስነት ደረጃ ወርዶ ከሰው በታች እንደተዋረደና ለእግዚአብሄር አምላክነት እውቅና እስሰጥ ድረስ እንደ እንስሳ ሳር እንደበላ ይናገረዋል፡፡
ልዑል አምላክም በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሠለጥን፥ የሚወድደውንም እንዲሾምበት እስኪያውቅ ድረስ ከሰው ልጆች ተይለቶ ተሰደደ፥ ልቡም እንደ አውሬ ልብ ሆነ፥ መኖሪያውም ከምድረ በዳ አህዮች ጋር ነበረ፤ እንደ በሬ ሣር በላ፥ አካሉም በሰማይ ጠል ረሰረሰ። ትንቢተ ዳንኤል 5፡21
ይህን ሁሉ የእግዚአብሄርን አሰራር ትእቢተኛን ማዋረዱን ያየው ልጁ ብልጣሶር ከዚያ እንዳልተማረ ፣ እግዚአብሄርን እንዳልፈራ እና እርሱም እንደታበየ ያስታውሰዋል፡፡
ብልጣሶር ሆይ፥ አንተ ልጁ ስትሆን ይህን ሁሉ እያወቅህ በሰማይ ጌታ ላይ ኰራህ እንጂ ልብህን አላዋረድህም። ትንቢተ ዳንኤል 5፡22
የመቅደሱንም ዕቃዎች በፊትህ አመጡ፥ አንተም መኳንንትህም ሚስቶችህም ቁባቶችህም የወይን ጠጅ ጠጣችሁባቸው ከብርና ከወርቅም ከናስና ከብረትም ከእንጨትና ከድንጋይም የተሠሩትን የማያዩትንም የማይሰሙትንም የማያውቁትንም አማልክት አመሰገንህ፤ ትንፋሽህንና መንገድህን ሁሉ በእጁ የያዘውን አምላክ አላከበርኸውም። ትንቢተ ዳንኤል 5፡23
መፅሃፍ ቅዱስ የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሄርን መፍራት ነው የሚለው ለዚህ ነው፡፡
የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤ ሰነፎች ግን ጥበብንና ተግሣጽን ይንቃሉ። መጽሐፈ ምሳሌ 1፡7
ትንፋሹንና መንገዱን የያዘውን እግዚአብሄርን ከማያከብር ሰው በላይ ሞኝ የለም፡፡ እግዚአብሄር መኖርና አለመኖርህን ይወስናል፡፡ እግዚአብሄርን በምድር ላይ መንገድህን ይወስናል፡፡ መንገድህን በእጁ የያዘውን እግዚአብሄርን ከማክበር የበለጠ ጥበብ የለም፡፡
ትንፋሽህንና መንገድህን ሁሉ በእጁ የያዘውን አምላክ አላከበርኸውም ትንቢተ ዳንኤል 5፡23
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ትህትና #መዋረድ #ባህሪ #ዝቅታ #ትዕቢት #ትምክህት #መመካት #ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መጋቢ #እምነት #ተስፋ #ፍቅር #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment