Popular Posts

Follow by Email

Saturday, March 9, 2019

የልቡ አሳብ ምኞትም ሁልጊዜ ፈጽሞ ክፉ እንደ ሆነ


እግዚአብሔርም የሰው ክፉት በምድር ላይ እንደ በዛ፥ የልቡ አሳብ ምኞትም ሁልጊዜ ፈጽሞ ክፉ እንደ ሆነ አየ። ኦሪት ዘፍጥረት 6፡5
እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው በመልካም ልብና ለመልካም ልብ ነበር፡፡ ነፃ ፈቃዱን ተጠቅሞ እግዚአብሄር አታድርግ ያለውን ያንኑ ነገር ካደረገ በኋላ ሰው ከእግዚአብሄር ክብር ወደቀ፡፡ የሰው ልቡ ተበላሸ፡እግዚአብሄር የፈጠረው ሰው የተፈጠረበትን አላማ ስቷል፡፡
የሰው ልብ ከእግዚአብሄር መንገድ እንደወጣና ሰው ክፉ ልብ እንዳለው የሚያሳየው ነገር ምንድነው ብለን መጠየቅ ጥበብ ነው፡፡ የሰውን ልብ ክፉ የሚያደርግውን ነገር ወይም የክፉ ልብ ምልክቶችን ከእግዚአብሄር ቃል እንመልከት፡-
1.      የሰውን ልብ ክፉ እንደሆነ የሚያሳየው ራስ ወዳድ በመሆኑ ነው
የሰው ልብ ከእግዚአብሄር ሲርቅ ራስ ወዳድ ይሆናል፡፡ ሁሉንም ነገር ከራሱ ጥቅም አንፃር እንጂ ከሌላው ጥቅም አንፃር መመልከት አይችልም፡፡ ክፉ ልብ ያለው ሰው ለራሱ ሙሉውን ድርሻ ወስዶ ሌላውን ባዶውን ሲልክ አይሰማውም፡፡
ሰዎችም ሊያደርጉላችሁ እንደምትወዱ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው። የሉቃስ ወንጌል 6፡31
2.     የሰውን ልብ ክፉ እንደሆነ የሚያሳየው በአድልዎ መፍረዱ ነው
የሰው ልብ ክፉ እንደሆነ የሚያሳየው ፍርዱ በመርህ ላይ ያልተመሰረተ ነገር ግን በስሜቱ ላይ የተመሰረተ መሆኑ ነው፡፡ ክፉ ሰው በተመሳሳይ ጉዳይ ለአንዱ የሚፈርደው ፍርድና ለሌላው የሚፈርደው ፍርድ ይለያያል፡፡ ክፉ ልብ ያለው ሰው የሚፈረርደው ፊትን አይቶ ነው፡፡ ክፉ ልብ ያለው ሰው ወጥ የሆነ በመርህ ላይ የተመሰረተ ፍርድ የለውም፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ተመሳሳይ ጥፋት ላጠፉ ሁለት ሰዎች ያለው ምዘና የተለያየ ነው፡፡ ፍርዱ የሚወሰነው በሰዎቹ ላይ እንጂ በመርህ ላይ አይደለም፡፡ ክፉ ልብ ያለው ሰው ሰዎቹን ሳያይ በመርህ ብቻ መፍረድ አይችልም፡፡ አንዱ ሲሰራው ትክክል ነው የሚለውን ነገር ሌላው ሲሰራው ስህተት ነው ይለዋል፡፡
3.     የሰው ልብ ክፉ እንደሆነ የሚያሳየው ለሌላው ባለው ንቀት ነው  
ሌላውን የሚንቅ እና ዝቅ ዝቅ አድርጎ የሚመለከት ሰው ክፉ ልብ ያለው ሰው ነው፡፡ ሌላው ሰው ሁሉ የእርሱ ታናሽ እርሱ ብቻ ታላቅ እንደሆነ በትእቢት የሚያስብ ሰው ልቡ ክፉ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ የሌላውን ችግርና መከራ እንደራሱ አድርጎ የማያይ እና የሰው መከራና ችግር የማይሰማው ሰው ክፉ ልብ ያለው ሰው ነው፡፡ ራሱን በሌሎች ቦታ የማስቀምጥ እኔ ብሆን ኖሮ ምን እሆን ነበር ብሎ የሌሎችን መጎዳት ለማየት የማይፈልግ ሰው ክፉ ልብ ያለው ሰው ነው፡፡ አላግባብ ከተጠቃ ሰው ጋር ራሱን ለማስተባበር የሚፀየፍ እና የትህትናን ነገር ለማደርግ የማይፈልግ ሰው ክፉ ልብ ያለው ሰው ነው፡፡
እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማሙ፤ የትዕቢትን ነገር አታስቡ፥ ነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ። ልባሞች የሆናችሁ አይምሰላችሁ። ወደ ሮሜ ሰዎች 12፡16
4.     የሰውን ልብ ክፉ እንደሆነ የሚያሳየው ሰውን በሰውነቱ ሳይሆን በሃብቱ በዝናውና በሃይሉ ሲያከብር ነው
ክፉ ልብ ያለው ሰው አክብሮቱ በሰው ሃብትና ዝና ላይ ይመሰረታል፡፡ ክፉ ልብ ያለው ሰው ሰውን የሚያከብረው ሃብቱን አይቶ በእበላ ባይነት ነው፡፡ ክፉ ልብ ያለው ሰው ዝነኛን ሰው የሚያከበርው ሃያል ስለሆነ ክፉ ሊያደርግብኝ ይችላል በሚል ፍርሃት እንጂ በእግዚአብሄር መልክና አምሳል ስለተፈጠረ ስለ ሰውነቱ ብቻ አይደለም፡፡ ክፉ ልብ ያለው ሰው ሰውን በሰውነቱ ስለማያከብር ድሃን ይንቃል ደካማው ላይ ይበረታል፡፡
የወርቅ ቀለበት ያደረገና የጌጥ ልብስ የለበሰ ሰው ወደ ጉባኤአችሁ ቢገባ፥ እድፍ ልብስም የለበሰ ድሀ ሰው ደግሞ ቢገባ፥ የጌጥ ልብስም የለበሰውን ተመልክታችሁ፦ አንተስ በዚህ በመልካም ስፍራ ተቀመጥ ብትሉት፥ ድሀውንም፦ አንተስ ወደዚያ ቁም ወይም ከእግሬ መረገጫ በታች ተቀመጥ ብትሉት፥ ራሳችሁን መለያየታችሁ አይደለምን? ክፉ አሳብ ያላቸውም ዳኞች መሆናችሁ አይደለምን? የያዕቆብ መልእክት 2፡2-4
5.     ክፉ ልብ ያለው ሰው ወገንተኛ ነው
ክፉ ልብ ያለው ሰው የሚያዳላው ለራሱ ወይም ለእኔ ስለሚለው ሰው ነው፡፡ ክፉ ልብ ያለው ሰው የእኔ ወገኔ  ነው ስለማይለው ሰው ምንም ግድ የለውም፡፡ ክፉ ልብ ያለው ሰው ሌላው ሲጎዳ ሲያይ አይቶ እንዳላየ ያልፋል እንጂ ለሌላው ወገን አይናገርም አይከራከርም፡፡
ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፥ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር፤ ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 2፡4
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ህይወት #የሚፈርድ #የሚያማ #ወንጌል #መውደድ #ፍቅር #የህይወትምስክርነት #መታዘዝ #ማገልገል #መውደድ #እውነት #ትህትና #ትንሳኤ #ህይወት #ወንጌል #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ  #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment