Popular Posts

Friday, March 22, 2019

የጥላቻን ዜና በማስፋፋት ለጊዜው የሚጠቀሙ የተሸነፉ ፖለቲከኞች ብቻ ናቸው



ፖለቲካ የህዝብ አስተዳደር ስርአት ነው፡፡ ፖለቲካ በራሱ ክፉ አይደለም፡፡ ማንኛውም ሙያ በክፉ ሰዎች እንደሚበላሽ ሁሉ ግን ፖለቲካም በክፉ ሰዎች ሊበላሽ አላማውንም ሊስት ይችላል፡፡
ይህ ደግሞ በመንግስት አካላት ያሉትን ፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆን በህዝብ መገናኛ ዘዴዎች በማህበራዊ ሚዲያዎች የራሳቸውን ትንተና የሚሰጡትንና አክቲቪስቶችን ሁሉ ያጠቃልላል፡፡
ፖለቲካ ወቅታዊውን የህዝብን ፍላጎት መረዳት መተንነተንና የተሻለ አማራጭን ማቅረብን ይጠይቃል፡፡ ፖለቲካ ህዝብን ወደ እረፍት ሰላም እና ብልፅግና የሚያደርስን የተሻለ ሃሳብን ማምጣት ይጠይቃል፡፡ እውነተኛ ፖለቲከኝነት ቀላል ስራ አይደለም፡፡ እውነተኛ ፖለቲከኝነት በጠለቀ እውቀት ፖሊሲ መቅረፅን በዚያ ዙሪያ ህዝብን ማንቃትና በአንድ አላማ ስር ማንቀሳስን ወደልማትና ብልፅግና መምራትን ይጠይቃል፡፡
ፖለቲከኛ ያለው ብቸኛ መሳሪያ የተሻለ ሃሳብ ነው፡፡ ፖለቲከኛ የተሻለ ሃሳብን ለማምጣት የሚተጋና በተሻለው ሃሳብ ዙሪያ ሰዎችን ለማንቀሳቀስ የሚያስተምር የሚያነቃና የሚሰራ ነው፡፡
እውነተኛም የፖለቲካ ስልጣን የሚገኘው አንድን የተሻለ ሃሳብ ከተቀበለ ህዝብ ነው፡፡ የፖለቲካ ስልጣን ሃሳብ በህዝብ ተቀባይነት በማግኘት ብቻ ይመጣል፡፡ የፖለቲካ ስልጣን በረብሻ አይመጣም፡፡ የፖለቲካ ስልጣን ሰዎችን ለብጥብጥ በማነሳሳት አይመጣም፡፡ የፖለቲካ ስልጣን ጥላቻን በመንዛት አይመጣም፡፡
አገራችን ኢትዮጲያ በብዙ እውነተኛ ፖለቲከኞች የተሞላች አገር ነች፡፡ ህዝባቸውን የሚወዱና ለህዝባቸው የሚሰሩ ብዙ ፖለቲከኞችን አፍርታለች፡፡
ነገር ግን የፖለቲከኝነትን ስራውን የማይፈልጉ ነገር ግን በአቋራጭ የፖለቲካ ስልጣንን የሚፈልጉ ፖለቲከኞችም አንዳንዴ ይታያሉ፡፡ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ሃሳብን ከማምጣት እና የህዝብን ልብ በተሻለ ሃሳብ ከማሸነፍ ይልቅ የሰውን አለማወቅ ተጠቅመው በውሸት ዜናዎች የራሳቸውን የግል አላማ ሊያሳኩ የሚጥሩ ፖለቲከኞችም አሉ፡፡
የአገሪቱን ሁኔታ በእውቀት በመረዳትና በመተንተን ሳይሆን የሰዎችን ችግር እየነካኩ በዚያም የፖለቲካ ነጥብ ሊያስመዘግቡ የሚፈልጉ ስነምግባር የጎደላቸው ፖለቲከኞች ከመንግስትም ከመገናኛ ብዙሃንም እንዲሁም ከአክትቪስቶችም አልጠፉም፡፡
የተሻለ ሃሳብ በማቅርብ በሃሳብ ውድድር ለማሸነፍ አቅቷቸው ጥላቻን በመዝራት የሰውን ስሜት የሚቀሰቅሱና በህዝቦች መካከል ጥርጣሬና አለመተማመን የሚፈጥሩ ይገኙበታል፡፡ የፖለቲካ እውቀታቸውን ለማሳደግ እና ለማስፋት በማንበብና በመመርመር ፋንታ ጊዜያቸውን ሁሉ ረብሻ ሊያስነሳ የሚችልን ወቅታዊ ወሬን የሚፈላለጉ የፖለቲካ ስነምግባር የጎደላቸው ይታያሉ፡፡
በተሻለ ሃሳብ የማሸነፍ አቅም ሲያጥራቸው ህብረተሰቡን ስጋቱን በማባባስ በችግረኛው ህብረተሰብ ላይ ተረማመደው የተሻለ ጥቅም ለማግኘት የሚፈልጉ የፖለቲካ ስነምግባር የማይገዳቸውንም ተመልክተናል፡፡
በተሻለ ሃሳብ ህዝቦችን ከማቀራረብና ለአንድ አገር ሰላም ልማትና አንድነት ከመስራት ይልቅ አገር በህዝቦች አለመተማመን ብትታመስ ምንም ደንታ የማይሰጣቸው የተሸነፉ ፖለቲከኞችም ይታዩባታል፡፡ የሚናገሩት የስድብ እና የንቀት ንግግር በህዝቦች መካከል ለሚያመጣው መቃቃር ግድ የሌላቸው ለጊዜያዊ ታዋቂነታቸው ብቻ የሚያስቡ ፖለቲከኞች አሉ፡፡ ህዝቡ በጥቃቅን ነገሮች ላይ ድንጋርይ መወራወሩት ትቶ ድህነትን በመዋጋት ወደልማትና ብልፅግና የሚሄድበትን መንገድ ለመፈለግ የሚያስችልን ከፍ ያለን ሃሳብ ማምጣት የማይችሉ ሰዎችን በማናቆር ብቻ ፖለቲከኞች እንደሆኑ የሚሰማቸው ይገኛሉ፡፡ ህዝቡ እርስ በእርሱ መፎካሩንና መወዳደሩን ትቶ ለአገር እንዲሰራ የሚያሳሙበት ሃሳብ ስለሚያጥራቸው በወቅታዊ ችግሮች ላይ ተጠምደው ጊዜያዊ ጥቅምን ያሳድዳሉ፡፡
ከራሳቸው ጥቅም በላይ የአገር እና የህዝብን ጥቅም የሚያስቀድሙ ፖለቲከኞች እንዳሉ መጠን ፖለቲካ እንደ ማንኛውም ሙያ ትምህርትና እውቀት የማይፈልግ የሚመስላቸው ይገኛሉ፡፡ እንወክለዋለን ከሚሉት ህዝብ ውጪ ላለውን ለሌላው ህዝብ የፍቅርና የርህራሄ ልብ የሌላቸው ከእነርሱ የተለየውን ህዝብ ሲሰድቡ እና የንቀትን ንግግር ሲናገሩ የሚውሉ ፖለቲከኞች ይገኛሉ፡፡   
በህዝቦች መካከል መቀራረብን መደራደርን የማይፈልጉ እና የማያበረታቱ የራሴ መንገድ ብቻ የሚሉ ፖለቲከኞች ያላቸው አንድ መሳሪያ ጥላቻን ማስፋፋት እና በህዝቦች መቃቃርና መናቆር በጊዜያዊነት ተጠቃሚ መሆን ብቻ ነው፡፡ በግልፅ በአደባባይ ሊሉት የማይፈልጉትን በማህበራዊ ሚዲያዎች ጀርባ እየተደበቁ ጥላቻን የሚያስፋፉ ስርአት አልበኛ ሰዎች አልታጡም፡፡
ለጊዜው የተሳካላቸው ይመስላችው ይሆናል እንጂ ሃሰተኛ ፖለቲከኞች መጋለጣቸው አይቀርም፡፡ ህዝብን የሚያቀራረብ ፍትሃዊ የሆነ የተሻለ ሃሳብን ማቅረብ እንጂ ጥላቻን በማስፋፋት የሚጎዳ እንጂ የሚጠቀም ማንም ሰው አይኖርም፡፡
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #በክርስቶስ #መንፈስ #ማንነት #መልክ #አምሳል #የእግዚአብሄርልጅ #ክብር #ብሔር #ቋንቋ #ወገን #ነገድ #አፍሪካ #ኢትዮጲያ #ነገድ #ቤተሰብ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ዘረኝነት #የእግዚአብሄርመንግስት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አዲስፍጥረት #ክርስቶስ #የእግዚአብሄርቤተሰብ #ማእረግ #ስልጣን #ዘውግ

No comments:

Post a Comment