ዘረኝነት እጅግ ሊኮንን የሚገባ አፀያፊ አስተሳሰብና
ድርጊት ነው፡፡ ዘረኝነት የሚለውን ቃል ብዙ ሰዎች ለብዙ ነገር ሲጠቀሙበት ይስተዋላል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ዘረኝነት በትክክል ተርጉመው
ከሁኔታው ጋር አያየዝው ጥሩ የሆነ እውቀት ለሌሎች ሲያካፍሉ ይታያሉ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ዘረኝነት የሚለውን ቃል የሚጠቀሙበትን መንገድ
ስንመለከት በእውነት ሃሳቡን ተረድተውታል ወይ ብለን እንድንጠይቅ ያስገድደናል፡፡
አንዳንድ ሰዎች ዘረኝነት የሚለውን ቃል በትክክል
ባለመረዳት በተለያየ ንግግራቸው እና ፅሁፋቸው ውስጥ ሲጠቀሙት እና ሰዎችን ከማስተማርና ከማንቃት ይልቅ ሲያደናግሩ እናያለን፡፡
ዘረፅነት የሚለውን ቃል የሚጠቀሙት ቃሉ ታዋቂ ስለሆነ ብቻ እንጂ ምን ማለት እንደሆነ ተረድተውት እንዳይደለ አነጋገራቸው በግልፅ
ያሳያል፡፡ አንዳንድ ሰዎች የዘረኝነትን ቃሉን የሚጠቀሙት በቅጡ ተረድተውት ሳይሆን የራሳቸውን ሃሳብ ብቻ ለማስፈፀም ሲሉ ብቻ ነው፡፡
ዘረኝነት ብለው በብዛት የሚጮሁ አንዳንድ ሰዎች
ዘረኛ ነው ብለው ከሚኮንኑት ወገን ይልቅ እነርሱ ራሳቸው ዘረኛ ሆነው ይገኛሉ፡፡
ሁላችንም እኩል ተደርገን ተፈጥረን ሳለ ዘረኝነት
የሌላውን ዘር የመናቅ ፣ የመግፋትና የማንኳሰስ ክፉ በሽታ ነው፡፡ ከእኔ ዘር ያንሳል ብለህ የምታስብው ምንም ዘር ካለ ዘረኛ ለመፈለግ
ሌላ ቦታ መሄድ አይጠበቅብህም አንተው ዘረኛ ነህ፡፡
ዘረኝነት በምንም መልኩ ሊበረታታ የማይገባው ክፉ
ነው፡፡
ዘረኝነትን በሚገባ ካልተረዳነው መወገዝ የማይገባውን
እያወገዝን መበረታታት የማይገባውን እያበረታታን የመፍትሄው አካል መሆን ሲገባን የችግሩ አካል ሆነን በከንቱ ጊዜያችንን እናባክናለን፡፡
ዘረኝነት ከበታችነት ስሜት ይመጣል፡፡
በራሱ መተማመን የሌለው ሰው የሰው ወይም የአንድ
ወገን በራስ መተማን ያሰጋዋል፡፡ ዘረኝነት ከበታችነት ስሜት የተነሳ የበላይነት ስሜትን በማሳየት ይንፀባረቃል፡፡ ዘረኝነት ከተቻለ
በሃይል ካልተቻለ ደግሞ በንግግር ሌላውን ወገን ዝቅ ዝቅ ማድረግና ራስን ከፍ በማድረግ ሌላውን ማጥቃት ነው፡፡ ዘረኛ የሆነ ሰው
የራሱ ዘር ስኬት የሚደገፈው በሌላው ዘር ውድቀት ላይ ይመስለዋል፡፡ የአንተ ዘር እንዲሳካለት ሌላው ዘር መውደቅ የለበትም፡፡ ስግብግብነትና
ንፉግነት ካልሆነ በስተቀር ለሁሉም ዘር የሚበቃ ስኬት አለ፡፡
ሰው ክቡር ነው፡፡ ሰው ጠቃሚ ነው፡፡ ብዙ ዘር
በሚኖርባት አገር ውስጥ እየኖርክ የምትቀበለው ያንተን ዘር ብቻ ከሆነ አንተ ራስህ ዘረኛ ነህ፡፡ ከአንተ የተለየ ዘር በራሱ ቋንቋ
መናገር የሚያሳስብህ ከሆነ አንተው ዘረኛ ነህ፡፡
ሰውን እንደ ሀብት ሳይሆን እንደ እዳ ካየኸው
መለወጥ ያለብህ የራስህን የሽንፈት አስተሳሰብህን ነው፡፡ በተለይ ከአንተ የተለየን ሰው እንደ ውበት ካላየኸው በስተቀር እያነስክ
ትሄዳለህ እንጂ አትሰፋም፡፡
ኢትዮጲያ ውስጥ አንድ ዘርና እንድ ቋንቋ ብቻ
ካልኖረ በስተቀር ሰላም አይኖርም ብለህ የምታስብ ከሆንክ ዘረኛው አንተው ነህ፡፡ የኢትዮጲያ ችግር የመጣው ብሄሮች በራሳቸው ቋንቋ
መጠቀም ሲጀምሩ ነው ብለህ ካሰብክ ዘረኛው አንተው እንጂ በቋንቋቸው የሚማሩና ብሄሮች አይደሉም፡፡ ኢትዮጲያ ባለአንድ ቋንቋ ስትሆን
ብቻ ነው ሰላም የሚመጣው ብለህ የምታስብ ከሆንክ ልብህ በዘረኝነት ክፉ በሽታ አለመያዙን መርምር፡፡ እያንዳንዱ ዘር ቋንቋውን አክብሮ
ለኢትዮጲያ አንድነትና ብልፅግና መስራት አይችልም ብለህ ካመንክ ሃሳብህን መለወጥ ያለብህ አንተ ነህ፡፡
አንተ በሚመችህ ቋንቋ እየተናገርህ ሌላው በቋንቋው ስለተናገረ ዘረኛ የሆነ ከመሰለህ ራስህን
መርምር፡፡
የሌላው ብሄር ሰው ሲሰደድና ሲገፋ ምንም ካልመሰለህ
ያንተ ብሄር ሲገፋና ሲሰደድ ብቻ ስለዘረኝነት አስከፊነት የምታነሳ ከሆንክ አንተ ራስህ በዘረኝነት ወጥመድ ውስጥ አለመግባትህን
አረጋገጥ፡፡
በመከራ ቀን ብትላላ ጉልበትህ ጥቂት ነው። ወደ ሞት የሚነዱትን
ታደግ፤ ሊታረዱ የተወሰኑትን አድን። እነሆ፥ ይህን አላወቀውም ብትል፥ ልቦችን የሚመረምር እርሱ አያስተውልምን? ነፍስህንም የሚመለከት እርሱ አያውቅምን? ለሰውስ ሁሉ እንደ ሥራው አይመልስለትምን? መጽሐፈ ምሳሌ 24፡10-12
ዘረኝነት ዘር የለውም፡፡ ዘረኝነት የሁላችንም ፈተና ነው፡፡ ዘረኝነት ዘራችንን
በመውደድና የሌላውን ዘር በመጥላት መካከል ያለ ሚዛናዊነትን ያለመጠበቅ ችግር ነው፡፡ ዘረኝነት ዘራችንን በማክበርና ሌላውን ዘር
በመናቅ መካከል ያለ ሚዛናዊነትን አለመጠበቅ ችግር ነው፡፡ ዘረኛ ሰው ለአንተ ወይም ለዘርህ ያለው የንቀት አስተያየት አንተም መልሰህ
የእርሱን ዘር እንድትንቅ ይፈትንሃል፡፡
ዘረኝነት በሌላ በዘረኝነት አይስተካከልም፡፡ በዘረኛ
ሰው ንግግርና አካሄድ ተነሳስተህ አንተም ወደ ዘረኝነት ወጥመድ ውስጥ እንዳተወድቅ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ዘረኝነት ወደ አንተም
ህይወት እንዳይስፋፋ በአጭሩ የምትቀጨው ዘረኛን ዘረኛ የሚያደርገው የበታችነት ስሜት እንደሆነ አውቀህ ስታዝንለትና ስትራራለት ብቻ
ነው፡፡ ዘረኛነት እንዳይስፋፋ የምታደርገው በሌሎች ዘረኝነት ንግግርና ድርጊት ተሸንፈህ አንተም በዘረኝነት ወጥመድ ውስጥ ላለመውደቅ
ስታመልጥ ነው፡፡
ክፉውን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ። ወደ ሮሜ ሰዎች 12፡21
ከዘረኛ ሰው ጋር ፉክክር ውስጥ መግባት የዘረኞችን
ቁጥር ያሳድጋል እንጂ ዘረኝነትን ለመዋጋት መፍትሄ አይሆንም፡፡
ዘር በራሱ ክፉ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው ከቤተሰብ ጀምሮ በየደረጃው
በዘመድ በጎሳ በብሄር በሃገር አብሮና ተረዳድቶ በወገንተኝነት ስሜት እንዲኖር አድርጎ ነው፡፡ ማንም ሰው ስለተወለደበት ቤተሰብ
ጎሳ እና ዘር መሳቀቅና መጸጸት የለበትም፡፡
ከሌሎች ሰዎች ሁሉ ይልቅ ለምን ቤተሰብህን ወደድክ የሚል ሰው እንደሌለ ሁሉ ማንም
ዘርህን ለምን ወደድክና አከበርክ የሚል መኖር የለበትም፡፡ ለቤተሰብህ ማደግ ለምን ትተጋለህ የሚልህ እንደሌለ ሁሉ ለዘርህ ማደግ
ለምን ትተጋለህ የሚል ሰው አይኖርም፡፡ ቤተሰብህን ስትወድና ስታከብር ዘርህ ይከብራል ያድጋል፡፡ ዘርህ ሲከብርና ሲያድግ አገር
ትከብራለች ታደጋለች፡፡ ምድር ለሁላችን የሚበቃ በቂ ምንጭ አላት፡፡ እኔ ዘሬን ለመጥቀም የሌላውን ዘር መጉዳት የለብኝም፡፡ እኔ
አገሪቱን ለመጥቀም ዘሬን መጉዳት የለብኝም፡፡ ሁላችንም ከቤተሰባችን ጀምረን እስከ ዘራችንና ብንሰራ አገር ታድጋለች፡፡
ዘረኝነት ዘርን መውደድ ሳይሆን ሌላውን ዘር መጥላት ነው፡፡ ዘረኝነት የራስን ዘር
ማክበር ሳይሆን የሌላውን ዘር መናቅ ነው፡፡ ዘረኝነት የራስን ዘር መርዳት ሳይሆን የሌላውን ዘር መጉዳት ነው፡፡ ሌላውን ዘር እንድትጠላና
እንድትንቅ የሚያደርግህ ማንኛውም ንግግር በዘረኝነት መርዙ እየመረዘህ እንደሆነ አውቀህ ሽሽ፡፡ ዘረኛ የዘረኝነቱን ንቀትና ጥላቻ
ማስተላለፊያ ሊያደርግህ ሲሞክር ዘረኝነቱን ባለመከተልና ባለማስፋፋት ብለጠው፡፡
ከዘረኝነት ነፃ የወጣ ሰው ከራሱ ዘር አልፎ ሌሎችን ዘሮች በማክበርና በመውደድ
ይታወቃል፡፡ ዘረኝነት የሌለበት ሰው እያንዳንዱ ዘር እኩልና እኩል እድል ሊሰጠው እንደሚገባ ያምናል፡፡ ከዘረኝነት ነፃ የሆነ ሰው
ጭቆናና በደል ሲደርስ ለራሱ ዘር ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ዘሮች ጥብቅና ሲቆም ይታያል፡፡ አንዱ ዘር ለሌላው ዘር ሲከራከር የምንሰማው
ከዘረኝነት ነፃ በሆነ ህብረተሰብ ውስጥ ብቻ ነው፡፡
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች
https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች
https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #በክርስቶስ
#መንፈስ #ማንነት
#መልክ #አምሳል
#የእግዚአብሄርልጅ #ክብር #ብሔር #ቋንቋ #ወገን
#ነገድ #አፍሪካ
#ኢትዮጲያ #ነገድ
#ቤተሰብ #ቤተክርስትያን
#አማርኛ #ዘረኝነት
#የእግዚአብሄርመንግስት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ
#አቢይዋቁማዲንሳ #አዲስፍጥረት #ክርስቶስ #የእግዚአብሄርቤተሰብ #ማእረግ
#ስልጣን #ዘውግ