Popular Posts

Wednesday, June 19, 2019

ሰውን ወይስ እግዚአብሔርን አሁን እሺ አሰኛለሁን?



ሰውን ወይስ እግዚአብሔርን አሁን እሺ አሰኛለሁን? ወይም ሰውን ደስ ላሰኝ እፈልጋለሁን? አሁን ሰውን ደስ ባሰኝ የክርስቶስ ባሪያ ባልሆንሁም። ወደ ገላትያ 1:10
ብዙ የሰውና የእግዚአብሔር ፍላጎት ጊዜ ይለያያሉ::
እርሱ ግን ዘወር ብሎ ጴጥሮስን፦ ወደ ኋላዬ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና ዕንቅፋት ሆነህብኛል አለው። የማቴዎስ ወንጌል 16፡23
በሰው ወርቅ የሆነው ሃሳብ በእግዚአብሄር ግን የተሳሳተ ሃሳብ ሊሆን ይችላል፡፡
ብዙ ጊዜ የእግዚአብሔር ፍላጎት ጥቁርና ነጭን ቀለም እንደ መለየት ቀላል ይመስለናል:: አንዳንድ ጊዜ በእግዚአብሄር አሰራር የምናዝነው ወይም የምንሰናከለው እንደጠበቅነው ስለማይሆ ነው፡፡ እግዚአብሔር መልካምን ነገር እንዳገኝ ይፈልጋል እንላለን ነገር ግን  ከማን አንፃር መልካም የሆነውን እግዚአብሄር እንደሚፈልግ አንርዳውም::
ብዙ ጊዜ የእግዚአብሔር ፍላጎት ምንድነው ብለን ከመጠየቅና ከመፈለግ ይልቅ እግዚአብሔር ይህ እንዲሆንልኝ ሳይፈልግ አይቀርም ብለን በግምት በስንፍና እግዚአብሔርን በራሳችን ትንሽ አእሮምሮ ልንወስነው እንፈልጋለን::
ክርስትና የሚጀምረው የአንተ እና የእኔ ሀሳብ የተለያየ ነው ብሎ ከማመን ነው:: ክርስትና ፍሬያማ የሚሆነው በትህትናና በየዋህነት የራሳችንን ሀሳብ እየጣልን የእርሱን ሃሳብ በተቀበልን መጠን ብቻ ነው:: ክርስትና የሚደመደመው ብእርሱ ሀስብ እርሱን ስንመስለው ነው:: ክርስትና የሚጣፍጠው አእምሮዋችንን በእግዚአብሄር ቃል አና በእግዚአብሄር ሀሳብ ካደስን ብቻ ነው፡፡
የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ። ወደ ሮሜ ሰዎች 12፡2
የእግዚአብሄርን ሃሳብ ለመቀበልና ለመተግበር የራሳችንንና የሌላውን ሰው ሀሳብ መተው ይጠይቃል::
ከምንስበው በላይ ብዙ ጊዜ የሰው ሃሳብና የእግዚአብሔር ሃሳብ በፊታችን እንደምርጫ ይቀርብልናል:: ክርስቶስን በመከተል ፍሬያማ ለመሆን ለእግዚአብሄር ቃል አዎ ለሰው ሃሳብ ደግሞ አይ ማለትን መማር አለብን፡፡
ከምናስበው በላይ ብዙ ጊዜ የእግዚአብሔርና የሰው ህሳብ ይራራቃሉ:: የሰውንና የእግዚአብሄርን ሀሳብ አንድ ላይ ማስኬድ ደግሞ በፍፁም አይቻልም::
ክፉ ሰው መንገዱን በደለኛም አሳቡን ይተው፤ ወደ እግዚአብሔርም ይመለስ እርሱም ይምረዋል፥ ይቅርታውም ብዙ ነውና ወደ አምላካችን ይመለስ። አሳቤ እንደ አሳባችሁ መንገዳችሁም እንደ መንገዴ አይደለምና፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡ ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፥ እንዲሁ መንገዴ ከመንገዳችሁ አሳቤም ከአሳባችሁ ከፍ ያለ ነው። ትንቢተ ኢሳይያስ 55፡7-9
ብዙ ጊዜ ሰውን ደስ ማሰኘት የእግዚአብሔርን ሃሳብ መጣል ይጠይቃል:: ብዙ ጊዜ እግዚአብሄርን ደስ ለማሰኘት የሰውን ሃሳብ መተው  ይጠይቃል::
ሰው ሊከበር ይገባዋል፡፡ ሰው ግን እንደ እግዚአብሄር ሊፈራ አይገባውም፡፡ ሰውን መፍራት ወጥመድ ያመጣል፡፡
ሰውን መፍራት ወጥመድ ያመጣል፤ በእግዚአብሔር የሚታመን ግን እርሱ ይጠበቃል። መጽሐፈ ምሳሌ 2925
አንዳንደ ጊዜ የእግዚአብሄርን ሃሳብ መርጠን የሰውን ቅያሜ ለመቀበል መዘጋጀት አለብን፡፡ የሰውን አስተያየት ሳንፈራ የእግዚአብሄርን ሃሳብ ለማድረግ ግንባራችንን የቡላድ ድንጋይ ማድረግ አለብን፡፡
ከቡላድ ድንጋይ ይልቅ እንዳለ አልማዝ ግምባርህን አጠንክሬአለሁ፤ እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ቢሆኑ አትፍራቸው፤ ከፊታቸውም የተነሣ አትደንግጥ። ትንቢተ ሕዝቅኤል 39
የእግዚአብሄርን ሃሳብ ለማድረግ ሰዎች ነውር ነው የሚሉትን ነገር እንኳን ለማድረግ መዘጋጀት አለብን፡፡ እንደ ኢየሱስ እንደ ወንበዴ ተይዞ መሰቀል በብዙዎች ሰዎች ዘንድ ነውር ነው፡፡ ብዙዎች እንደወንበዴ ተይዘው ከሚሰቀሉ በእግዚአብሄር ሃሳብ ላይ ቢያመቻምቹ ይሻላቸዋል፡፡ ምሳሌያችን ኢየሱስ ግን ነውርን ናቀው እንጂ ከእግዚአብሄር ፈቃድ በላይ ነውርን አላከበረውም፡፡
እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና። ወደ ዕብራውያን 12፡2
የብዛት ጉዳይ አይደለም፡፡ ከእግዚአብሄር ፈቃድ ጋር አብሮ የሚቆም አንድ ሰው አብላጫ ነው፡፡  
ይህ ሕዝብ፦ ዱለት ነው በሚሉት ሁሉ፦ ዱለት ነው አትበሉ፤ መፈራታቸውንም አትፍሩ፥ አትደንግጡ። ትንቢተ ኢሳይያስ 8፡12
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ጌታ #ኢየሱስ #ፍቅር #ፍርሃት #ሃይል #ራስንመግዛት #አላማ #መዳን #ነፃነት #ቅድስና #ሰላም #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ብርሃን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  #የዋህነት #ንፁህ

No comments:

Post a Comment