Popular Posts

Follow by Email

Friday, June 14, 2019

እንደ ህፃናት ካልሆናችሁሕፃንም ጠርቶ በመካከላቸው አቆመ እንዲህም አለ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ካልተመለሳችሁ እንደ ሕፃናትም ካልሆናችሁ፥ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም። የማቴዎስ ወንጌል 18፡2-3
ሰው የተፈጠረው እንደ ህፃን የዋህ ተደርጎ ነው፡፡ አዳምና ሄዋን በሰይጣን ተንኮል አእምሮዋቸው ከመበላሸቱ በፊት እንደህፃን እግዚአብሄርን ሙሉ ለሙሉ ያምኑት ነበር፡፡ ከውድቀታቸው በፊት ለአዳምና እና ለሄዋን እግዚአብሄር አንድን ነገር አለ ማለት ሆነ ተደረገ ማለት ነበር፡፡ ከሃጢያት በኋላ ግን ሰው የህጻንነት የዋህነቱንና ገርነቱ አጥቷል፡፡
በእግዚአብሔር ቅንዓት እቀናላችኋለሁና፥ እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና፤ ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 11፡2-3
ህፃናት ከአዋቂዎች የተለየ ባህሪ አላቸው፡፡ ይህ ባህሪ በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ በጣም የሚፈልግ ባህሪ ነው፡፡ የእግዚአብሄር መንግስት ስርአት እንደ ህፃናት የሆኑ ሰዎች ብቻ እንዲከናወኑበት የተሰራ ስርአት ነው፡፡ እንደ ህፃን ለማይሆኑ ሰዎች የእግዚአብሄር መንግስት ለማደግና ለማፍራት ተስማሚ ስፍራ አይደለም፡፡ የህፃንነት ባህሪ በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ ሁኔታዎችን ተቋቁመን እንድናልፍ የሚያደርግ ወሳኝ ባህሪ ነው፡፡ የህጻንነት ባህሪ በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ ሙሉ ተጠቃሚ የሚያደርገን እግዚአብሄር ወዳየልን የህይወት ከፍታ የምንወጣበት ባህሪ ነው፡፡
አንድ አዋቂ ሰው የልጆች አለም ውስጥ ገብቶ እንደ ልጆቹ መጫወቻውን ቦታ ሊደሰትበት ፣ ሊዝናናበት እና ሊጠቀምበት እንደማይችል ሁሉ እንደህፃን የማይሆን ሰው በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ ደስተኛ ሊሆን ፣ በሚገባ ሊኖርና ፍሬ ሊያፈራ አይችልም፡፡ ከዋህነትና ከገርነት ጉድለት በአጠቃላይ እንደህፃናት ካለመሆን እንድንመለስና እንደ ህፃናት እንድንሆን እግዚአብሄር ይፈልጋል፡፡
በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ እጅግ ወሳኝ የሆነው የህፃናት ባህሪ ምን እንደሆነ ከእግዚአብሄር ቃል እንመልከት፡፡
1.      ህፃናት ቀጥተኛ ናቸው
ህፃናት በልባቸው የሚያስቡትና በአፋቸው የሚናገሩት የተለያየ አይደለም፡፡ ህፃናት በልባቸው አንድ ነገር በአፋቸው ሌላ ነገር የለም፡፡ ህፃናት አንድ ናቸው፡፡ ህፃናት በተንኮል ወይም በድብቅ ሃሳብ አእምሮዋቸው አልተበላሸም፡፡ ህፃናት ቀጥተኛና ንፁህ ናቸው፡፡ ህፃናት ቅን ናቸው፡፡
በእግዚአብሔር ቅንዓት እቀናላችኋለሁና፥ እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና፤ ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ። 2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 11፡2-3
2.       ህፃናት  ለማመን ፈጣን ናቸው
ህፃናት ለማመን ይፈጥናሉ፡፡ ህፃናት በቀላሉ ራሳቸውን ይሰጣሉ፡፡ እኛም በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ ቃሉን እንድናምን እግዚአብሄር ይፈልጋል፡፡ በተስፋ ቃሉ ሙሉ ለሙሉ እንድንደገፍ እግዚአብሄር ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሄር ለቃሉ ህጻናት እንድንሆንና በቃሉ የተናገረውን ነገር ሳንጠራጠር በፍጥነት እርምጃ እንድንወስድ እግዚአብሄር ይፈልጋል፡፡  
ስለዚህ ርኵሰትን ሁሉ የክፋትንም ትርፍ አስወግዳችሁ፥ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በየዋህነት ተቀበሉ። የያዕቆብ መልእክት 1፡21
እንግዲህ ክፋትን ሁሉ ተንኰልንም ሁሉ ግብዝነትንም ቅንዓትንም ሐሜትንም ሁሉ አስወግዳችሁ፥ ጌታ ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እንደ ሆነ፥ ለመዳን በእርሱ እንድታድጉ አሁን እንደ ተወለዱ ሕፃናት ተንኰል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ። 1 የጴጥሮስ መልእክት 2፡1-3
3.       ህፃናት በደልን አይቆጥሩም
እስከምትደነግጡ ድረስ ህፃናት በደልን በቶሎ ይረሳሉ፡፡ ህፃናት በደልን አያጠራቅሙም፡፡ ህፃናት ክፉን በክፉ ለመመለስ አያቅዱም፡፡ ህፃናት በደልን ይተዋሉ፡፡
ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ፤ በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን አስቡ። ወደ ሮሜ ሰዎች 12፡17
የማይገባውን አያደርግም፥ የራሱንም አይፈልግም፥ አይበሳጭም፥ በደልን አይቆጥርም፤ 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 13፡5
4.     ህፃናት ትንሽ ስጦታ ያስደንቃቸዋል
ህግፃናት ያመሰግናሉ፡፡ ህፃናት ትንሽ ነገርን ማድነቅ ይችላሉ፡፡ ህፃናት ያላቸው ነገር ላይ እንጂ ያላገኙት ነገር ላይ አያተኩሩም፡፡
በአንድ አካልም የተጠራችሁለት ደግሞ የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይግዛ፤ የምታመሰግኑም ሁኑ። ወደ ቆላስይስ ሰዎች 3፡15
5.     ህፃናት አይጨነቁም
ህፃናት የሚኖሩት በዛሬ ውስጥ ነው፡፡ ህፃናት በትላንት ወይም በነገ ውስጥ አይኖሩም፡፡ ህፃናት የሚኖሩት እያንዳንዱን ቀን አንድ በአንድ ነው፡፡
ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል። የማቴዎስ ወንጌል 6፡34
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ልብ #ህፃንነት #ብስለት #ጥበብ #ማስተዋል #አላማ #ቅንነት #የዋህነት #አለመጨነቅ #እምነት #ማድነቅ #ማመስገን #በደልንአይቆጥርም ##መሰረታዊፍላጎት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ጥሪ #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አንድነት #ትህትና #አክብሮት #ስልጣን #መሪ

No comments:

Post a Comment