Popular Posts

Follow by Email

Friday, June 7, 2019

ለአንዱ ችግር ለሌላው እድል


አለም በመልካም እድሎች የተሞላች ነች፡፡ የአለም ምንጭ እና ሃብት ለሁሉም ሰው ይበቃል፡፡
ምድር ለአንዱ እናት ለሌላው ጨቋኝ የእንጀራ እናት አይደለችም፡፡ እያንዳንዳችንን ከሌላችን የሚለየን አለምን የምንመለከትበት ሁኔታ ብቻ ነው፡፡
እያንዳንዱ ነገር የራሱ ጥቅም የራሱ ተግዳሮት አለው፡፡ ተግዳሮት የሌለው ጥቅም የለም፡፡ እድል የሌለው ተግዳሮት የለም፡፡
በችግር ላይ የሚያተኩር ሰው ከችግሩ በስተጀርባ ያለውን መልካም እድል ማየት አይችልም፡፡ ችግር በጊዜያዊነት መልስን አለማግኘት እንጂ ዘላለማዊ ተግዳሮት የለም፡፡ እያንዳንዱ የህይወት ጥያቄ መልስ አለው፡፡ መልስ የሌለው ጥያቄ የለም፡፡ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ለእያንዳንዱ የህይወት ጥያቄ መልስ ይገኝለታል፡፡ መውጫ የሌለው ፈተና የለም፡፡
ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፥ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10፡13
ሁሉም ሰው የራሱ ተግዳሮቶች አሉት፡፡ ተግዳሮቶችና ድካሞች የሌሉት ሰው በአለም ላይ የለም፡፡ ሰው የሌላውን ሰው ድካም ብቻ ካየ በዚያ ሰው ውስጥ የተቀመጠውን እምቅ ጉልበት መጠቀም ያቅተዋል፡፡ ሰው የሌላው የህይወት ተግዳሮቶች ላይ ብቻ ካተኮረ እና ከተግዳሮቶቹ ባሻገር ያለውን እድል ካልተመለከተ ሰውየውን እንዳለ አውጥቶ ለመጣል ይፈተናል፡፡ ሌላውን ሰው በደፈናው በጣልን ቁጥር አንድ የሰውነት ክፍላችንን እንጥላለን፡፡
ሃዋሪያው ጳውሎስ ጌታ ከመከተሉ በፊት ክርስትያኖችን አሳዳጅ ነበር፡፡ ሰው የጳውሎስ አደጋው ላይ ሲያተኩር  ጌታ ግን ትኩረቱ አምቅ ጉልበቱ ላይ ነበር፡፡ ሰው በጳውሎስ ጎርፍነት ሲፈራ እና ሲደናገር ጌታ ግን የጳውሎስን ጎርፍ እንዴት መንገድ እንደሚሰጠውና የጎርፉን እድል እንዴት እንደሚጠቀምበት ያውቅ ነበር፡፡ ሰው የጳውሎስን የሃይማኖት እሳት እንዴት እንደሚይዘው ስለማያውቅ እንደችግር ሲያየው ጌታ ግን የጳውሎስን እሳት እንዴት እንደሚመራውና ለእውነተኛው ለእግዚአብሄርን መንግስት ጥቅም እንደሚጠቀምበት ስለሚያውቅ ጥበቡ ስላለው የጳውሎስ ገዳይ ሃይማኖተኝነት ለጌታ ስጋት አልነበረም፡፡
አሁን የምናልፍባቸው ማንኛውም ችግሮች የራሳቸው እድል አላቸው፡፡ የሚያስፈልገን አይናችን ተከፍቶ ከተግዳሮቶቹ በስተጀርባ ያለውን እድል ማየት ብቻ ነው፡፡ ማንኛውም ጥያቄ መልስ አለው፡፡ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ማንኛውምን ፈተና መውጫ አለው፡፡
ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጎድለው፥ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፥ ለእርሱም ይሰጠዋል። የያዕቆብ መልእክት 1፡5
በተግዳሮት ወቅት ከምንም ነገር በላይ የሚያስፈልገን የልባችን አይኖች መከፈትና ከከበቡን ነገሮች በላይ እጅግ የሚበልጠውን እድል መመልከት ነው፡፡ ከተግዳሮት በስተጀርባ ያለውን እድል ሳይመለከቱ ተግዳሮቱ ላይ ብቻ በማተኮር ከተግዳሮቱ በፍጥነት ለመውጣት መሞከር በተግዳሮቱ ውስጥ የተሸሸገውን እድል እንዳናይና ወርቃማውን እድል በከንቱ እንድድናባክን ያደርገናል፡፡
በእይታ ልዩነት ምክንያት ለአንዱ የማሰናከያ ድንጋይ የሆነው ድንጋይ ለሌላው ወደከፍታ የመወጣጫ ደረጃ ነው፡፡   
የክብር አባት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እርሱን በማወቅ የጥበብንና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ እለምናለሁ። ይህም የልባችሁ ዓይኖች ሲበሩ የመጥራቱ ተስፋ ምን እንዲሆን በቅዱሳንም ዘንድ ያለው የርስት ክብር ባለ ጠግነት ምን እንዲሆን ለምናምን ከሁሉ የሚበልጥ የኃይሉ ታላቅነት ምን እንዲሆን ታውቁ ዘንድ ነው፤ ወደ ኤፌሶን ሰዎች 1፡17-19
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ፈተና #ፀጋ #የሚያስችልሃይል #ጥበብ #ክፉ #አሸንፍ #ብቃት #የእግዚአብሄርችሎታ #የእግዚአብሄርሃይል #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #እድል #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ተግዳሮት #እግዚአብሄርንመምሰል #ራስንመግዛት #ልብ #ምስክርነት

No comments:

Post a Comment