Popular Posts

Monday, June 10, 2019

ፍቃዱ ከደስታ ይበልጣል


ሰው የተፈጠረው ለእግዚአበሄር ክብር ነው፡፡ ሰው የተፈጠረው የእግዚአብሄርን ፈቃድ በምድር ላይ ለመፈፅም ነው፡፡ ኢየሱስ ወደምድር የመጣው የእግዚአብሄርን ፈቃድ እንዳንፈፅም ስላደረገን ስለሃጢያታችን በመስቀል ላይ ዋጋ ሊከፍልና ከአመጽና ካለመታዘዝ ሊያድነን እና ለእርሱ ፈቃድ እንድንኖር ነፃ ሊያወጣን ነው፡፡
በምድር ላይ ለነፍሳችን ደስታን ካገኘን መልካም ነው፡፡ ነገር ግን በምድር ላይ ለነፍሳችን ደስታን ማግኘት የህይወታችን ብቸኛ አላማ አይደለም፡፡
የህይወታችን ቀዳሚ ግብ የእግዚአብሄርንም ፈቃድ መፈፀም ነው፡፡ ካለእግዚአብሄር ፈቃድ በነፋስ ሁሉ እንደሚፍገመገም በውሃ ላይ ወዲያና ወዲህም እንደሚንሳፈፍ ነን፡፡
እንደ ስሕተት ሽንገላ ባለ ተንኮል በሰዎችም ማታለል ምክንያት በትምህርት ነፋስ ሁሉ እየተፍገመገምን ወዲያና ወዲህም እየተንሳፈፍን ሕፃናት መሆን ወደ ፊት አይገባንም፥ ወደ ኤፌሶን ሰዎች 4፡14
ኢየሱስ ክርስቶስን ጌታችን አድርገን የተቀበልን ሁላችን የራሳችን አይደለንም፡፡ ኢየሱስን የምንከተል ሁላችን በሁለንተናችን የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንድንፈፅም በዋጋ ተገዝተናል፡፡
በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 6፡19-20
የተጠራነው ነፍሳችንን ለማክበርና ለማስደሰት አይደለም፡፡ የተጠራነው የእግዚአብሄርን ፈቃድ በመፈፀም እግዚአብሄርን ለማክበር ነው፡፡
ነገር ግን ሩጫዬንና ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልሁትን አገልግሎት እርሱም የእግዚአብሔርን ጸጋ ወንጌልን መመስከር እፈጽም ዘንድ ነፍሴን በእኔ ዘንድ እንደማትከብር እንደ ከንቱ ነገር እቆጥራለሁ። የሐዋሪያት ሥራ 20:24
ቅድሚያ የምንሰጠው የእግዚአብሄርን ፈቃድ በህይወታችን መፈፀሙን እንጂ የነፍሳችንን ደስታን አይደለም፡፡ ነፍሳችንን የምናድነው የእግዚአብሄርን ፈቃድ በመፈፀም እንጂ ነፍሳችንን ለጊዜው በማስደሰት አይደለም፡፡
ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል። የማቴዎስ ወንጌል 16፡25
የእግዚአብሄርን ፈቃድ በመፈፀም ዘለቄታዊ ሰላምና ደስታ አለ፡፡ ደስታችን የእግዚአብሄርን ፈቃድ በመፈፀም የሚመጣ ብቻ ነው፡፡ በምድር ላይ በእግዚአብሄር ፈቃድ የምንለውጠው ወይም ከእግዚአብሄር ፈቃድ የምናስቀድመው ምንም አይነት ደስታ የለም፡፡ ደስታችን በእምነት እግዚአብሄርን ፈቃድ በመፈፀም እግዚአብሄርን ማስደሰት ነው፡፡  
ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። ወደ ዕብራውያን 11፡6
ብትፈቅድ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ አይሁን የአንተ እንጂ እያለ ይጸልይ ነበር። የሉቃስ ወንጌል 2242
ፀሎት
እግዚአብሄር ሆይ ፈቃድህን እፈልጋለሁ፡፡ ነፍሴ ብትጮህ ብታጉረመርምም ፣ ለጊዜው ደስ ባይልም ለጊዜው የሚስብ ባይሆንም ብዙ ሰዎች የሚመርጡት ባይሆንም ነገር ግን ለእኔ ፈቃድህ ይሻለኛል፡፡ ምንም ዋጋ ቢያስከፍል ፈቃድህ ይሻለኛል፡፡ ምንም ቢያሳምም ፈቃድህን እፈልጋለሁ፡፡ በህይወቴ ሁሉ ፈቃድህ ይሁንልኝ፡፡ በኢየሱስ ስም፡፡ አሜን
 አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር  share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #የእግዚአብሄርፈቃድ #ደስታ #ክብር #ነፍስ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #የእግዚአብሄርቃል #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #መጠየቅ #መንበርከክ #ምስጋና

No comments:

Post a Comment