Popular Posts

Tuesday, June 11, 2019

የህይወት ከንቱነት



በኢየሩሳሌም የነገሠ የሰባኪው የዳዊት ልጅ ቃል። ሰባኪው፦ ከንቱ፥ ከንቱ፥ የከንቱ ከንቱ፤ ሁሉ ከንቱ ነው ይላል። መጽሐፈ መክብብ 1፡1-2
ሰው በእግዚአብሔር መልክና አምሳል ተፈጥሮአል፡፡ እግዚአብሔር ሰውን በክብሩ ፈጥሮታል፡፡ የሚያሳዝነው ነገር ግን ይህን የከበረ ህይወት በክብር የሚይዘው ሁሉም ሰው አይደለም፡፡
እንግዲህ አሕዛብ ደግሞ በአእምሮአቸው ከንቱነት እንደሚመላለሱ ከእንግዲህ ወዲህ እንዳትመላለሱ እላለሁ በጌታም ሆኜ እመሰክራለሁ።  ወደ ኤፌሶን ሰዎች 4፡17
እግዚአብሔር በሰው ላይ ከፍ ያለ ዋጋ ቢያደርግም ለህይወቱ የሚገባውን ዋጋ የሚሰጠው ሰው ግን ሁሉም አይደለም፡፡ ይህ ከእግዚአብሔር የተሰጠ የከበረው ህይወት እንደ እግዚአብሔር መንገድ ካልተኖረ ከንቱ፥ ከንቱ፥ የከንቱ ከንቱ፤ ሁሉ ከንቱ ሊሆን ይችላል፡፡
ሰው የራሱ ፈቃድ አለው፡፡ ሰው ህይወቱን በፈለገው መንገድ የመምራት ሙሉ ፈቃድ ያለው ተደርጎ ተፈጥሮአል፡፡ ሰው ህይወቱን አክብሮ ህይወቱን በክብር ሊመራ ወይም ሰው ህይወቱን ሊንቅ የተፈጠረበትን አላማ ሊስትና የማይገባውን ኑሮ ሊኖር ይችላል፡
ህይወትን ከንቱ፥ ከንቱ፥ የከንቱ ከንቱ፤ ሁሉ ከንቱ ሊያደርጉ የሚችሉ አምስት ነገሮችን ከመፅሃፍ ቅዱስ እንመልከት
1.      አላማ ቢስ ህይወትን መኖር
ለእግዚአብሔር አላማ ተፈጥሮ እያለ ሰው ለህይወቱ የእግዚአብሄርን አላማ የማይፈልግና የማይከተል ከሆነ ህይወቱ ከንቱ የከንቱ ከንቱ ነው፡፡ ሰው አላማ በእግዚአብሔር ቃል በኩል የተፈጠረለትን የእግዚአብሔርን አላማ ካልፈፀመ ህይወት ከንቱ የከንቱ ከንቱ ነው፡፡
ጩኽ የሚል ሰው ቃል፤ ምን ብዬ ልጩኽ? አልሁ። ሥጋ ለባሽ ሁሉ ሣር ነው፥ ክብሩም ሁሉ እንደ ምድረ በዳ አበባ ነው። የእግዚአብሔር እስትንፋስ ይነፍስበታልና ሣሩ ይደርቃል አበባውም ይረግፋል፤ በእውነት ሕዝቡ ሣር ነው። ሣሩ ይደርቃል አበባውም ይረግፋል፥ የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች። ትንቢተ ኢሳይያስ 40፡6-8
2.     በፍቅር አለመኖር
ሰው በፍቅር ለመኖር ተፈጥሮአል፡፡ ከፍቅር ያነሰ ምንም አይነት ህይወት ለሰው ከንቱ ነው፡፡ ህይወት ዋጋ የሚኖረው በፍቅር ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ሰው ምንም ዝነኛ ፣ ጥበበኛ ፣ ሃያል እና ባለጠጋ ቢሆን ፍቅር ግን ከሌለው ከንቱ ነው፡፡
ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ፥ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፥ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 13፡2-3
3.     በጥንቃቄ አለመኖር
ሰው ዘመኑን በጥንቃቄ ካልያዘው ያባክነዋል፡፡ እግዚአብሔር የሰጠን ህይወት አጭርና በጥንቃቄ መኖር ያለበት ነው፡፡ ትንሽ ጥንቃቄ ጉድለት ለብዙ ክፋት ሊያጋልጠን ይችላል፡፡ 
እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፤ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 5፡15-16
በቀን እንደምንሆን በአገባብ እንመላለስ፤ በዘፈንና በስካር አይሁን፥ በዝሙትና በመዳራት አይሁን፥ በክርክርና በቅናት አይሁን፤ ነገር ግን ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት፤ ምኞቱንም እንዲፈጽም ለሥጋ አታስቡ። ወደ ሮሜ ሰዎች 13፡13-14
ሰው በምድር ላይ ለዘላለም እንደሚኖር አድርጎ በጥንቃቄ ካልኖረ ህይወት ከንቱ፥ ከንቱ፥ የከንቱ ከንቱ፤ ሁሉ ከንቱ ነው፡፡
4.     እንደ እንግዳ አለመኖር  
የምድር ህይወት አጭር ነው፡፡ የምድር ህይወት የእንግድነት ህይወት ነው፡፡ የምድር ህይወት ጊዜያዊ መተላለፊያ ህይወት ነው፡፡ አንድ ቀን በፈጠረን በጌታችን ፊት እንቀርባለን፡፡ አንድ ቀን በእግዚአብሔር ፊት ቅርቦ እንደሚጠየቅ ተደርጎ ካልተኖረ ህይወት ከንቱ፥ ከንቱ፥ የከንቱ ከንቱ ነው፡፡ 
በዚች ሕይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ ያደረግን ከሆነ፥ ከሰው ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ነን። እንደ ሰው በኤፌሶን ከአውሬ ጋር ከታገልሁ፥ ሙታንስ የማይነሡ ከሆነ፥ ምን ይጠቅመኛል? ነገ እንሞታለንና እንብላና እንጠጣ። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 15፡19፣32
5.     በእምነት አለመኖር 
ሰው የተፈጠረው የእግዚአብሔር ቃል ሰምቶ እንደእግዚአብሔር ቃል እና እንደፈቃዱ በእምነት እንዲኖር ነው፡፡ ሰው በእምነት ካልኖረ ከእግዚአብሔር ጋር ሊገናኝ እና በምንም መልኩ እግዚአብሔርን ሊያስደስት አይችልም፡፡ ሰው በአምስቱ የስሜት ህዋሳቶቹ ብቻ በሚያየውና በሚሰማው ብቻ ከተመላለሰ ከእግዚአብሄር ጋር የሚያገናኘው ምንም መስመር ስለሌለ ህይወቱን ከንቱ ያደርገዋል፡፡
ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። ወደ ዕብራውያን 11፡6
ሰው እግዚአብሔርን በቃሉ ካላመነ ሊከተለው ፣ እራሱን ለጌታ ሊሰጥና እግዚአብሔር ወደአየለት የክብር ደረጃ ሊደርስ አይችልም፡፡
ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል። የማቴዎስ ወንጌል 16፡25
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ፍቅር #አላማ #እምነት #ጥንቃቄ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #ምሪት #ድምፅ #ፍቅር #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #መውደድ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment