ሰው ሰው የራሱ ፈቃድ ያለውና የተከበረ ፍጡር ስለሆነ ከሰው ጋር ያለ ግንኙነት እጅግ ጥበብን የሚጠይቅ ችሎታ ነው፡፡ ሰው ምንም ያህል የጠፈር እውቀት ቢኖረው ሰውን መያዝ ችሎታ ከጎደለው ብዙ ነገር ሊያደርግ አይችልም፡፡ ሰው ምንም ያህል የፊዚክስ ችሎታ ቢኖረው ከጓደኛ ጋር እንዴት እንደሚኖር ካላወቀ ህይወቱን ሊደሰትበት ያቅተዋል፡፡
ካለግንኙነትና ካለ ህብረት ሰው በራሱ ውስን ነው ፍሬ ሊያፈራ በህይወቱም ሊከናወን አይችልም፡፡
ከጠቢባን ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ ምሳሌ 13፡20
ለሰዎች የህይወት ስኬት የሚያስፈልገውን ነገር እግዚአብሄር ያስቀመጠው በሰው ውስጥ ነው፡፡
ብረት ብረትን ይስለዋል፥ ሰውም ባልንጀራውን ይስላል። ምሳሌ 27፡17
ከዚህ አንፃር ስለጓደኝነት ወይም ስለ ባለንጀራነት የተረዳሁትን ጥቂት ምክሮች ላካፍላችሁ
- ግንኙነት በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ሰው ይፈልገናል እኛም ሰውን እንፈልጋለን፡፡ እኛ ሰውን ለጓደኝነት መፈለጋችን ሰውም እኛን ለጓደኝነት መፈለጉ ትክክለኛ ነገር ጤናማነት ነው፡፡
- በጓደኝነት የሌላውንም ፍላጎት ማሟላት ያስፈልጋል፡፡ እኛን ብዙም የማያስደስተንን ነገር ስለጓደኝነት ብለን የማድረግ ትህትናን ይጠይቃል፡፡ ጓደኝነት የሚሰምረው ሌላውን ለማስደሰት በማተኮር ላይ ነው፡፡
እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፥ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ። ፊልጵስዩስ 2፡4
- በጓደኛችን ላይ የምንወደውና የምናከበረው ባህሪ ይኖራል፡፡ የጓደኛዬን ሁለንተና እወዳለሁ ማለት ውሸት ነው፡፡ የምንወደውና የምንጠቀምበት ባህሪና ጥንካሬ እንዳለ ሁሉ የምንሸከመው ባህሪም ይኖራል፡፡
- በጓደኛችን ላይ የማንወደውን አመል እንዲስተካከል በፍቅር የራሳችንን አስተዋፅኦ እናደርጋለን፡፡ እንዲሁም ያንን የማንወደውን ነገር ደግሞ እኛም ተቀብለነው እንዳናደርገው መልካም አመላችን እንዳይጠፋ መጠንቀቅ አለብን፡፡ እንዲያውም ክፉ አመል እንደሚጋባብን ካየን የወዳጅነቱን ድንበር ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡
ከቍጡ ሰው ጋር ባልንጀራ አትሁን፥ ከወፈፍተኛም ጋት አትሂድ፥ መንገዱን እንዳትማር ለነፍስህም ወጥመድ እንዳታገኝህ። ምሳሌ 22፡24-25
- ፈጥኖ ወደ ወዳጅነት ውስጥ መግባት አደገኛ ነው፡፡ ግንኙነት ጠቃሚ እንደመሆኑ መጠን በሚገባ ካልያዝነው አፍራሽ ሊሆን ይችላል፡፡
አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል። 1ኛ ቆሮንቶስ 15፡33
- ከሌላው ጓደኛ ጋር መሰጠት ጋር የተመጣጠነ መሰጠት ይኑርህ፡፡ ከአንዱ ወገን ብቻ የሚመጣ በጣም ያልተመጣጠነ መሰጠት ጤናማ ግንኙነትን አያመለክትም፡፡ እግዚአብሄር እንኳን ልጁን ኢየሱስን በመስቀል ላይ እንዲሞት ከሰጠን በኋላ እስክንቀበለው ጠበቀን እንጂ ራሱን በአንድ ለሊት ሁሉንም ዝርግፍ አድርጎ አልሰጠንም፡፡
ኢየሱስም መለሰ አለውም፦ የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን።ዮሃንስ 14፡23
- ወዳጅነታችን ለሁልጊዜ ቢሆን መልካም ነው፡፡ ካልተቻለ ግን ወዳጅነታችን ጊዜው ሲያልቅ በቀስታ መለየት መልካም ነው፡፡ ከጓደኝነት ተጣልቶና ተበጣብጦ መለያየት አያስፈልግም፡፡
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #መሪ #ወዳጅነት #ጓደኛ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ጓደኝነት #መንፈስቅዱስ #ባልንጀራ #ልብ #ስለሁሉሞተ