Popular Posts

Tuesday, June 23, 2020

በምድራዊ እውቀት የማይደረስበት መንፈሳዊ ክልል



ይህችም የአብርሃም ልጅ ሆና ከአሥራ ስምንት ዓመት ጀምሮ ሰይጣን ያሰራት በሰንበት ቀን ከዚህ እስራት ልትፈታ አይገባምን? አለው። የሉቃስ ወንጌል 13፡16

በህይወታችን ላይ የሚነጣጠሩ ብዙ ጥቃቶች ከምናስበው በላይ መንፈሳዊ ናቸው፡፡

ለምሳሌ የጤና መታወክ ሲደርስብን ቶሎ የሚመጣልን የሳይንሱ እውቀትና የሳይንሱ መፍትሄ ነው፡፡ ብዙ ነገር ሲደርስብን ቁሳዊ እናደርገዋለን፡፡ ብዙ ነገር ሲደርስብን በህክምና እውቀት ብቻ ልንተረጉመው እንፈተናለን፡፡

የበላሁት ምግብ ነው ወይም ቫይረስ ነው ብለን እንደሰው ልማድ ብቻ ጥቃቱን ልንዋጋው እንፈልጋለን፡፡ እንደሰው ልማድ ተዋግተን ከተሳካልን እሰየው፡፡ የሰይጣን ስራ ለማፍረስ ያለንን ነገር ሁሉ እምነታችን እና እውቀታችንን ሁሉ እንጠቀማለን፡፡

እንደሰው ልማድ ብቻ ከመዋጋት ያለፈ ነገር የሚጠይቅ ብዙ የዲያቢሎስ ጥቃት አለ፡፡  

የሰው ልጆች ጥቃት በቀጥታ ባይሆንም ቢያንስ በተዘዋዋሪ ከሰይጣን ነው፡፡ ሰይጣን ሌላ ራእይ የለውም፡፡ ራእዩ መስረቅ ማረድና ማጥፋት ብቻ ነው፡፡

ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም እንጂ ስለ ሌላ አይመጣም፤ እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ። የዮሐንስ ወንጌል 10፡10

አንዳንዴ ሰይጣን በመንፈሱ በቀጥታ ባያጠቃንም ማድረግ ያለብንን ነገር በቸልተኝነት እንዳናደርግ በአእምሮዋችንም ቢሆን ያጠቃናል፡፡ ወይም የእግዚአብሄርን አላማ በምድር ላይ እንዳንፈፅም በፍርሃት ሽባ ያደርገናል፡፡ ሌላም ጊዜ በፀጋ ከተቀበልነው በሽታን በእኛ ላይ ሊያደርግ ይሞክራል፡፡

ተዘዋዋሪ የሰይጣን አላማ ቢሆኑም ንፅህናን ባለመጠበቅ የሚመጡ በሽታዎች ከሰይጣን አላማ ናቸው፡፡ እግዚአብሄር ጥንቃቄያችንንም ተጠቅሞ ከጠላት ጥቃት ያስመልጠናል፡፡

ተጠንቅቀንም እግዚአብሄር አስመለጠን ነው የምንለው እንጂ ጥንቃቄያችንም ፍፁም በማይሆነው በጥንቃቄያችንም አንታመንም፡፡

እግዚአብሄር ለእኛ ነው፡፡ እግዚአብሄር ለደህንታችን ያለውንም ነገር ሁሉ ይጠቀማል፡፡ እግዚአብሄር የዶክተሮችን ጥበብ ተጠቅሞ በሽታን ይዋጋልናል፡፡ የዲያቢሎስን ስራ ለማፍረስ ያለንን ምድራዊ እውቀት እና መንፈሳዊ እውቀርት ሁሉ እንጠቀማለን፡፡ ሰይጣን በህይወታቸን በጤናችን ምንም ስፍራ እንዳያገኝ እስከመጨረሻው ፀንተን እንቃወመዋለን፡፡

በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት። 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 5፡9

ኃጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው፥ ዲያብሎስ ከመጀመሪያ ኃጢአትን ያደርጋልና። 1ኛ የዮሐንስ መልእክት 3፡8

ከዶክተሮች እውቀት በላይ ያለ ነገር ደግሞ አለ፡፡ ዶክተሮች በምድራዊ ጥበባቸው የማይደርሱበት መንፈሳዊ ክልል አለ፡፡

ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም።  1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 2፡14

እግዚአብሄር እምነታችንን ተጠቅሞ ከበሽታው ጀርባ ያለውን መንፈሱን በኢየሱስ ስም እንድንቃወመው አይናችንን ይከፍታል ይመራናል፡፡

ይህችን ሴት በወቅቱ ዶክተሮች ጋር ብትታይ ዶክተሮች በምድራዊ እውቀታቸው የማይረዱት መንፈሳዊ ክልል ስላለ ስለበሽታዋ አንድ ምክኒያት ይሰጧታል፡፡  

ኢየሱስ ግን ከዚህ በሽታ ጀርባ ያለውን ሊሰርቅ ሊያርድና ሊያጠፋ የሚመጣውን ሰይጣንን አየው፡፡ ኢየሱስ በሽታውን ሳይሆን ከበሽታው በስተጀርባ ያለውን የበሽታውን ምንጭ አደረቀው፡፡

ይህችም የአብርሃም ልጅ ሆና ከአሥራ ስምንት ዓመት ጀምሮ ሰይጣን ያሰራት በሰንበት ቀን ከዚህ እስራት ልትፈታ አይገባምን? አለው። የሉቃስ ወንጌል 13፡16

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #ፈውስ #ስጋ #ጤንነት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #ተስፋ #አሁን #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ


No comments:

Post a Comment