Popular Posts

Monday, June 15, 2020

እግዚአብሔር የሚቀጣው እንዲበድል ያደረገውን ስጋዊ ፍላጎት ነው


ብዙ ሰዎች በደልን እንዴት እንደሚይዙ ስላማያውቁ በህይወታቸው ዘመን ይሰቃያሉ፡፡ ገንዘባችንን እንዴት እንድምንይዝ ፣ ጤናችንን እንዴት እንድምንጠበቅ ፣ ስራችንን እንዴት እንደምንሰራ የመሳሰሉትን ከምናውቀው እውቀት በላይ ከሰው ጋር እንዴት እንድምንኖር ማወቅ ከብዙ ኪሳራ ከብዙ የስሜት በሽታ ብሎም ከብዙ ችግሮች ይጠብቀናል፡፡

ሰውን እንድናምን ከሰው ጋር እንድንኖር ተፈጥረናል፡፡ ሰው ጠቃሚ እንደመሆኑም መጠን ግን በተለያየ ጊዜም ይበድለናል፡፡

ሰው አውቆም ይሁን ሳያውቅ ሰውን ስለሚበድል ሰው ሰውን የመበደሉ እውነት የማይቀር ነገር ነው፡፡ ዋናው ነገር ሰው ሰው ሰውን ይበድላለ ወይ የሚለው ጥያቄ አይደለም፡፡ ዋናው ነገር የተበደለው ሰው በደሉን እንዴት ይይዘዋል የሚለው ጥያቁ ነው፡፡ ሰው ለበደል እንዴት እንደሚመልስ ካወቀ ያርፋል፡፡

ሰው በደሉን በትክክል ከያዘው ይማርበታል ያድግበታል የተሻለ ሰው ሆኖ ይለወጥበታል፡፡ ሰው በደሉን በትክክል ካልያዘው ይሰቃይበታል ህይወቱን ያባክንበታል፡፡

ሰው ሲበድለን በመጀመሪያ ደረጃ ነፃ የሚያወጣን ነገር ስለበደሉ የተቻለንን ያህል ሃላፊነት መውሰዳችን ነው፡፡ እርሱ 100 % ጥፋተኛ ነው እኔ 0% ጥፋተኛ ነኝ የሚለው ነገር አያዋጣም፡፡ ቢያንስ ሲያጠፋ እኛ ጥፋቱን የመለስንበት መንገገድ ትክክል ላይሆን ይችላል፡፡

ሁለተኛ እግዚአብሄር የሚቀጣው የበደለውን ሰውዬ ሳይሆን እንዲበድል ያደረገውን ስጋዊ ፍላጎት ነው፡፡

ሶስተኛ ማወቅ ያለብን እርሱን እንዲበድል ያደረገው ያው ስጋዊ ፍላጎት እኛም ውስጥ እንደሚኖር አውቀን ትምህርትና ግሳፄ መውሰድ ነው፡፡ እኔ እንደዚህ መበደል አልችልም ማለት ሞኝነት ነው፡፡ በበዳዩ ውስጥ ያየነውን የስጋ አስከፊነት ካየን እኛ ውስጥ ያለው ስጋ በሌሎች ላይ ተመሳሳይ በደል እንዳያደርግ እንጨክንበታለን፡፡

አራተኛ የበደለን ሰው እስኪወድቅ አለመጠበቅ ነው፡፡ ሰው ስራውን ትቶ የበደለኝ ሰው ከመቼ መቼ ይቀጣል እያለ ስለበደለው ሰው የሚከታተል ከሆነ የራሱን የህይወት አላማ ትቶ ስቶዋል ማለት ነው፡፡ ከበደለው ሰው ጋር በመፎካከር የህይወት አላማውን አሽቀንጥሮ የሚጥል ሰው የህይወት አላማው ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ የማያውቅ ሰው ነው፡፡

የበደለ ሰው ስጋ በአስቸጋሪ ነገር ውስጥ በማለፍ የስጋ ፍላጎቱ ሊገደል ይችላል፡፡ በደል ያስደረገው ያ ስጋዊ ፍላጎት ዛሬ ነገ ወይም ከነገ ወዲያ በምን መጠን በምን ሁኔታ ይቀጣ አታውቅምና ትተኸው ህይወትህን ኑር፡፡

ተወዳጆች ሆይ፥ ራሳችሁ አትበቀሉ፥ ለቍጣው ፈንታ ስጡ እንጂ፤ በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና። ወደ ሮሜ ሰዎች 12፡19

አንተን ስለበደለህ እንዲጠፋ ከመፈለግ ይልቅ ሰው እንዲለወጥ እንዲሻሻል እንዲመለስ ፀልይለት፡፡ አንተን ስለበደለ እንዲቀጣ ብቻ ሳይሆን በዚህ አጋጣሚ እንዲመለስ እንዲስተካከል ፈልግ፡፡

ወንድሞች ሆይ፥ ሰው በማናቸውም በደል ስንኳ ቢገኝ፥ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ እንደዚህ ያለውን ሰው በየውሃት መንፈስ አቅኑት፤ አንተ ደግሞ እንዳትፈተን ራስህን ጠብቅ። ወደ ገላትያ ሰዎች 6፡1

አንተ የበደለህ ሰው እርዳታህን በሚፈልግበት ጊዜ መርዳትህ እንዳልበደለህ አይናገርምና እርዳው፡፡ የበደለ ሰው ይታዘንለታል እንጂ አይቀናበትም፡፡

ጠላትህ ግን ቢራብ አብላው፤ ቢጠማ አጠጣው፤ ይህን በማድረግህ በራሱ ላይ የእሳት ፍም ትከምራለህና። ወደ ሮሜ ሰዎች 12፡20

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ህይወት #የሚፈርድ #የሚያማ #ወንጌል #መውደድ #ፍቅር #ምህረት #መታዘዝ #ማገልገል #መውደድ #እውነት #ትህትና #ትንሳኤ #ህይወት #ወንጌል #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ  #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ 


No comments:

Post a Comment