Popular Posts

Sunday, June 28, 2020

ብዙ ጊዜ እንደምናስበው እጅግ በጣም አስፈላጊ አይደለንም በአእምሮዋችን ከምናስበው በላይ ግን ተወደናል



የእግዚአብሄር ልጆች ነን፡፡ አስፈላጊነታችን አጠያያቂ አይደለም፡፡
ነገር ግን ብዙ ጊዜ አስፈላጊነታችንን ከመጠን በላይ እናጋንነዋለን፡፡ ብዙ ነገሮች ካለእኛ መሰራት እንደማይችሉ በከንቱ እናስባለን፡፡
በህይወታችን ሁሉንም ነገር ማድረግ አንችልም፡፡ ማድረግ የምንችለው በጣም ውስን ነገር ነው፡፡ ማድረግ የምንችለውን ውስኑን ነገር በትክክል ከሰራነው ስኬታማ ነን፡፡
እኔ ካለ እግዚአብሄር ምንም ማድረግ አልችልም፡፡ እግዚአብሄር ግን ካለእኔ ሁሉን ሊያደርግ ይችላል ብሎ ትሁት መሆን ይጠቅማል፡፡ በእኛ መጠቀም ሲፈልግ ይጠቀማል እንጂ እኛን ላይጠቀም ሌላውን ሊጠቀም ይችላል፡፡   
አንገስ ቡከን የሚባል የእግዚአብሄር ሰው ሲናገር ራሳችንን በጣም ከማጋነናችን የተነሳ ስንሞት መልከአ ምድር ሁሉ የሚለወጥ ይመስለናል፡፡ እኛ ስለሞትን የሚለወጥ መንም መልከአ ምድር አይኖርም፡፡ ለብዙ ሺዎች አመታት ምድር ቀጥላለች እኛም ስንሞት ምድር እንዳለች ትቀጥላለች፡፡
ውስን እንደሆነን በመረዳት ራሳችንን ትሁት ማድረግ እና እጅግ አስፈላጊ በሆነው በእግዚአብሄር ላይ መደገፍ በምድር ላይ ባለን ቆይታ ውጤታማ እንድንሆን ያስችለናል፡፡
ግንድ ሳንሆን ቅርንጫፍ እንደሆንን ስንረዳ ከእግዚአብሀጌር ጋር በሰላም እንኖራለን፡፡
እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል። የዮሐንስ ወንጌል 15፡5
አካል ሳንሆን የአካል ብልቶች እንደሆንን ስንረዳ ውጤታማነታእችን ይበዛል፡፡
አካልም አንድ እንደ ሆነ ብዙም ብልቶች እንዳሉበት ነገር ግን የአካል ብልቶች ሁሉ ብዙዎች ሳሉ አንድ አካል እንደ ሆኑ፥ ክርስቶስ ደግሞ እንዲሁ ነው፤ 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 12፡12
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጠቢብ በጥበቡ አይመካ፥ ኃያልም በኃይሉ አይመካ፥ ባለ ጠጋም በብልጥግናው አይመካ፤ ነገር ግን የሚመካው፦ ምሕረትንና ፍርድን ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን በማወቁና በማስተዋሉ በዚህ ይመካ፤ ደስ የሚያሰኙኝ እነዚህ ናቸውና፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡ ትንቢተ ኤርምያስ 9፡23-24
ውስን እንደሆንን በትክክል ስንረዳ ማሰብ ከሚገባን አልፈን በትእቢት እንዳናስብ ይጠብቀናል፡፡
እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ የእምነትን መጠን እንዳካፈለው፥ እንደ ባለ አእምሮ እንዲያስብ እንጂ ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ በተሰጠኝ ጸጋ እናገራለሁ። ወደ ሮሜ ሰዎች 12፡3
ውስን እንደሆንን ስንረዳ ሌላውን በትህትና ከእኛ እንደሚሻል አድርገን መቁጠር እና ማድነቅ እንጀምራለን፡፡  
ውስን እንደሆንን ስንረዳ በሁለንተናችን እኛ እግዚአብሄር ለእኛ እንደሚያስፈልገን በትህትና ማየት እንጀምራለን፡፡
እንደምናስበው ከሚገባው በላይ በጣም አስፈላጊ አለመሆናችን ብቻ ሳይሆን ከምናስበው በላይ ተወደናል፡፡
እግዚአብሄር ፍቅር ነው፡፡ እግዚአብሄር ለእኛ ያለውን ፍቅር ተረድተን አንጨርሰውም፡፡
ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም፥ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና። 1ኛ የዮሐንስ መልእክት 4፡8
በእኛ ላይ ያለው አላማ ፍቅር ነው፡፡
በእኔ ላይ ያለው ዓላማውም ፍቅር ነው። መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን 2፡4
ጠላቶች ሳለን ወደደን፡፡
ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል። ወደ ሮሜ ሰዎች 5፡8
ሃጢያተኞች ሳለን አንድ ልጁን እስኪሰጠን ድረስ ወዶናል፡፡
በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። የዮሐንስ ወንጌል 3፡16
እራሱ ፍቅር በሆነው በእግዚአብሄር ተወደናል፡፡
ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ስፋቱና ርዝመቱ ከፍታውም ጥልቅነቱም ምን ያህል መሆኑን ለማስተዋል፥ ከመታወቅም የሚያልፈውን የክርስቶስን ፍቅር ለማወቅ ትበረቱ ዘንድ፥ ወደ ኤፌሶን ሰዎች 3፡18-19
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ፍቅር #ትህትና #መዋረድ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #ቸርነት #ትግስት #ከቅዱሳንሁሉጋር #መታበይ #መመካት #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment