Popular Posts

Wednesday, October 25, 2017

ልብ ይጠይቃል!


1.      ከእኛ የተለየውን ሰው ለመቀበል ልብ ይጠይቃል
ማንም መንገደኛ የሚመስለውንና የሚስማማውን ብቻ ይቀበላል፡፡ የሚወደውን ለመውደድ የሚጠላውን ደግሞ ለመጥላት ብዙ ጥረት አይጠይቅም፡፡ ከእርሱ የተለየውን ሰው ለመጣል ራስ ወዳድነት በቂ ነው፡፡ ከእኛ የተለየውን እንደ አካለ ብልት ለመቁጠርና ከማይመስለን ሰው ጋር ለአንድ ግብ ለመስራት እና እና ሌላውን ለመታገስ ልብ ይጠይቃል፡፡ ደካማ ሰዎች ሁሉንም እሺ የሚሉዋቸውን ፣ የማይጋፈጡዋቸውን ፣ የሚፈሩዋቸውንና እንዲለወጡ የማይገዳደሩዋቸውን ሰዎች በዙሪያቸው ይሰበስባሉ፡፡ እውነተኛ ሰዎች ሌላ የተደበቀ የስስት አላማ ስለሌላቸው ለመታረም ለመለወጥ ክፍት በመሆናቸው የሚያርሙዋቸውን ከእነርሱ የተለየተ ሃሳብ ያላቸውን እንዲያድጉና እንዲዘረጉ የሚያበረታቱዋቸውን ሰዎች ያከብራሉ፡፡  ሌሎችን የማያምን ራሱን ብቻ የሚያምን ሰው በህይወት እያነሰና እየቆረቆዘ ይሄዳል፡፡ ሁሉንም እንደሚያውቅ ሌላው የተሻለ እንደሚያውቅ የማያስብ ሰው እያነሰ ይሄዳል፡፡ ከእርሱ የተለየውን ሰው ውበት ማየት የሚችልና ሳያሻሽል የሚቀበለው ሰው ግን እየበዛ እየጠነከረ ይሄዳል፡፡ ከሰው ድካም ባሻገር ጥንካሬንና ውበትን ማየት መቻል ልብ ይጠይቃል፡፡  
የጸጋም ስጦታ ልዩ ልዩ ነው መንፈስ ግን አንድ ነው፤ አገልግሎትም ልዩ ልዩ ነው ጌታም አንድ ነው፤ አሠራርም ልዩ ልዩ ነው፥ ሁሉን በሁሉ የሚያደርግ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው። 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡1-3
ዓይን እጅን፦ አታስፈልገኝም ልትለው አትችልም፥ ወይም ራስ ደግሞ እግሮችን፦ አታስፈልጉኝም ሊላቸው አይችልም። 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡21
2.     ለሌላው ቅድሚያ መስጠትና ለራስ ብቻ አለማሰብ ልብ ይጠይቃል
ለሌላው ቅድሚያ መስጠት ክብር መሆኑን ማወቅ ትልቅነት ነው፡፡ ለራሱ ብቻ የሚያስብ ሰው ፣ ራሱ ላይ ብቻ የሚሰራ ሰው ፣ ለራሱ ብቻ የሚያከማች ሰው የተፈጠረበትን አላማ ስቶዋል፡፡ ሰው በእግዚአብሄር መወደዱን ሲያውቅ ሰዎችን ይወዳል ለሰዎች ቅድሚያን ይሰጣል፡፡ እግዚአብሄር እንዴት በፍቅር እና በርህራሄ እንደሚያየው የሚያውቅ ስው ሌሎችን በፍቅር ያያል፡፡ እግዚአብሄር አባቱ እንደሆነ የተረዳ ሰው ለሌሎች አባት ይሆናል፡፡ በእግዚአብሄር አባትነት የማይተማመን ሰው ግን የራሱን ፍሎጎት ብቻ ለማሙዋላት ሲደሳክር ዘመኑን ይፈጃል፡፡ የተፈጠረው ለሌላው ሰው በጎነት እንደሆነ ያለተረዳ ሰው ሳያካፋል ያለውን ነገር ሁሉ ራሱ ላይ ብቻ አፍስሶ ህይወቱን በከንቱ ያሳልፋል፡፡
ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፥ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር፤ እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፥ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ። ፊልጵስዩስ 2፡3-4
3.     በምድር ከፉክክር ነፅቶ እንደ እንግዳ መኖርና በዘላለም እይታ መኖር ልብ ይጠይቃል
የምድር ፉክክር የአላማ ጠላት ነው፡፡ የምድር ፉክክር በተንኮል ወደህይወታቸን እየገባ ከመንገዳችን የሚያስወጣ የህይወት አላማ ጠር ነው፡፡ የምድር ፉክክር ለእግዚአብሄር ሳይሆን ለሰው እንድንኖር የሚያታለል ክፉ በሽታ ነው፡፡ ይህን የምድር ፉክክር ጥሎ መውጣትና እግዚአብሄር ለእያንዳንዳችን በሰጠን ሃላፊነት ላይ ማተኮር ድፍረት ይጠይቃል፡፡ ማንም ሰው በምድር ፉክክር ውስጥ ገብቶ እንደሰው መሆን ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሄር ግን እንደ እግዚአብሄር ልጆች የእግዚአብሄርን ፅድቅና መንግስቱን እንድንፈልግ ጠርቶናል፡፡ ሰው ከምድር ፉክክር በራሱ ፈቃድ ካላቋረጠ እግዚአብሄር በህይወቱ ያስቀመጠውን አላማ መፈፀም አይችልም፡፡
ነገር ግን እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሥራ ይፈትን፥ ከዚያም በኋላ ስለ ሌላው ሰው ያልሆነ ስለ ራሱ ብቻ የሚመካበትን ያገኛል፤ ገላትያ 6፡4
4.     ከራስ አልፎ ለሚቀጥለው ትውልድ ማሰብ ልብ ይጠይቃል
ማንም ሰው ለዛሬ መኖር ይፈልጋል፡፡ ነገር ግን የዛሬን ደስታ አዘግይቶ ለሚመጣው ትውልድ መሰረት መጣል የተለየ መንፈስ ይጠይቃል፡፡ ዛሬ እንብላ ነገ እንሞታለን ማለት ቀላል ነው፡፡ የሚመጣው ትውልድ ሸክም በእኔ ትከሻ ላይ ነው ብሎ ለሚመጣው ትውልድ መልካም ምሳሌ ሆኖ ማለፍ ልብ ይጠይቃል፡፡ ከራስ ትውልድ አልፎ የእግዚአብሄርን ቃል ምሳሌነት ለሚመጣው ትውልድ ማድረስ የየእለት ጥረት ይጠይቃል፡፡  
እንደ ሰው በኤፌሶን ከአውሬ ጋር ከታገልሁ፥ ሙታንስ የማይነሡ ከሆነ፥ ምን ይጠቅመኛል? ነገ እንሞታለንና እንብላና እንጠጣ። 1ኛ ቆሮንቶስ 15፡32
5.     አለመጨነቅ ልብ ይጠይቃል፡፡
መጨነቅ ውጤት የሌለው ነገር ግን ከውጤት የሚያሰናክል ነገር ነው፡፡ እንድንጨነቅ የሚገፋፋ ብዙ ምክኒያቶች እያሉ አለመጨነቅ እምነት ይጠይቃል፡፡ ብዙ ሰዎች ሲጨነቁ ስራ የሰሩ ይመስላቸዋል፡፡ ብዙ ሰዎች መጨነቅ መብታቸው እንደሆነ ይሰማቸዋል፡፡ ብዙ ሰዎች የጭንቀትን ጉዳት አይረዱትይም፡፡ ጭንቀት ማቀድ ይመስላቸዋል፡፡ ጭንቀት ግን ማቀድ አይደለም፡፡ ጭንቀት ማለት ማድረግ የማንችለውን ነገር ለማድረግ መፍጨርጨር ነው፡፡ ጭንቀት ማለት የማናውቅውን ነገር አሁኑኑ ለማወቅ መላላጥ ነው፡፡ ጭንቀት ማለት ቆይተን የምንረዳውን ነገር አሁኑኑ ለመረዳት አእምሮን ማጣበብ ነው፡፡ ጭንቀት ማለት ወደፊታችን ምን እንደሚሆነ ካሁኑ አውቆ ለመጨረስ የመሞከር ከንቱ ድካም ነው፡፡ የሚያስጨንቀንን ነገር ለእኛ በሚያስበው በጌታ ላይ መጣል ልብ ይጠይቃል፡፡
እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት። 1ኛ ጴጥሮስ 5፡7 
6.      አለመፍረድ ልብ ይጠይቃል፡፡
ማንም መንገደኛ በማንም ላይ ሊፈርድ ይችላል፡፡ አለመፍረድና ይልቁንም ሌላውን መርዳት ልብ ይጠይቃል፡፡ አለመፍረድ ይልቁንም ራስን በሌላ ሰው ቦታ አድርጎ መመልከትና ለሌላው መራራት ልብ ይጠይቃል፡፡ አለመፍረድና ይልቁንም የሰዎችን ስሜት መረዳት ጥረት ይጠይቃል፡፡ አለመፍረድ ይልቁንም ወደሰዎች ደረጃ ወርዶ ማገዝ ምሳሌ መሆን ልብ ይጠይቃል፡፡ 
ወንድሞች ሆይ፥ ሰው በማናቸውም በደል ስንኳ ቢገኝ፥ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ እንደዚህ ያለውን ሰው በየውሃት መንፈስ አቅኑት፤ አንተ ደግሞ እንዳትፈተን ራስህን ጠብቅ። ገላትያ 6፡1
ወንድሞች ሆይ፥ እርስ በርሳችሁ አትተማሙ። ወንድሙን የሚያማ በወንድሙም የሚፈርድ ሕግን ያማል በሕግም ይፈርዳል፤ በሕግም ብትፈርድ ፈራጅ ነህ እንጂ ሕግን አድራጊ አይደለህም። ያዕቆብ 4፡11
7.     ጠላትን መውደድ የሚረግሙንን መባረክ ልብ ይጠይቃል፡፡
በራሱ ሃይል የማይታመን በእግዚአብሄር ብቻ የሚታመን ሰው ነው ጠላቱን የሚወድ፡፡  በእግዚአብሄር ፈራጅነት የሚታመን ሰው ብቻ ነው እራሱ የማይፈርደው፡፡ እግዚአብሄር እንደሚባርክ የተረዳ ሰው ብቻ ነው የሰውን እርግማን ተከትሎ የማይራገም፡፡ አስቀድሞ እንደተባረከ የሚያምን ብቻ ነው ሰውን የማይረግመው፡፡ ለእርሱ መባረክ የሌላው መረገም አንደማያስፈልግ የሚያምን ሰው ብቻ ነው ሰውን የማይራገም፡፡  
ክፉን በክፉ ፈንታ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ በዚህ ፈንታ ባርኩ እንጂ፥ በረከትን ልትወርሱ ለዚህ ተጠርታችኋልና። 1ኛ ጴጥሮስ 3፡9
እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፥ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ፤ እርሱ በክፎዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፥ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና። ማቴዎስ 5፡44-45
8.     ነገሮች ሁሉ በተቃራኒው ሲሰሩ እግዚአብሄርን ማመን ልብ ይጠይቃል፡፡
በሁኔታዎች ውስጥ ማረጋገጫ እንፈልጋለን፡፡ ነገር ግን በሁኔታዎች ውስጥ ማረጋገጫ ሲጠፋና የሚታየው ነገር ሁሉ እግዚአብሄር ከተናገረን ተቃራኒ ሲሆን እግዚአብሄርን ለማመን ልብ ይጠይቃል፡፡ ሌላው ሰው ሁኔታውን አይቶ እጅ ሲሰጥ ለመቀጠል ልብ ይጠይቃል፡፡
ዘርህ እንዲሁ ሊሆን ነው እንደ ተባለ፥ ተስፋ ባልሆነው ጊዜ የብዙ አሕዛብ አባት እንዲሆን ተስፋ ይዞ አመነ። የመቶ ዓመትም ሽማግሌ ስለ ሆነ እንደ ምውት የሆነውን የራሱን ሥጋና የሳራ ማኅፀን ምውት መሆኑን በእምነቱ ሳይደክም ተመለከተ፤ ሮሜ 4፡18-19
ሰዎች በፊታቸው እንበጣ ነን ሲል እንደ እንጀራ ይሆኑልናል ማለት ልብ ይጠይቃል፡፡
ነገር ግን በእግዚአብሔር ላይ አታምፁ፤ እንደ እንጀራ ይሆኑልናልና የምድሪቱን ሰዎች አትፍሩ፤ ጥላቸው ከላያቸው ተገፍፎአል፥ እግዚአብሔርም ከእኛ ጋር ነው፤ አትፍሩአቸው ብለው ተናገሩአቸው። ዘኍልቍ 14፡9
9.     ምንም ነገር የማይበቃ በሚመስልበት ያለኝ ይበቃኛል ማለት ልብ ይጠይቃል
የሰው ፍላጎት አያልቅም፡፡ እኛ ለፍላጎታቸን ገደብ ካላበጀንና በመሰረታዊ ፍላጎታችን ላይ ብቻ ካላተኮርን የማያልቅ ፈላጎታችንን ከማሙዋላት አልፈን እግዚአብሄርን ማገልገል አንችልም፡፡ ሰው ለመሰረታዊ ፍላጎቱ እግዚአብሄርን ካልታመነና ያለኝ ይበቃኛል ካላለ የማያባራውን የሰውን ፍላጎት ማሙዋላት ብቻ የህይወት ዘመን ይጠይቃል፡፡ አህዛብ ሌላ የህይወት አላማ ስለሌላቸው የመጀመሪያውም የመጨረሻውም ፍላጎታቸው የሚበላና የሚለበስ ነው፡፡ ሰው ያለኝ ይበቃኛል ባለ መጠን ብቻ ነው እግዚአብሄርን ማገልገል የሚችለው፡፡ ያለኝ አይበቃኝም ባለ መጠን ሁሉ ህይወቱ ይባክናል፡፡   
ይህን ስል ስለ ጉድለት አልልም፤ የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል ማለትን ተምሬአለሁና። ፊልጵስዩስ 4፡11
ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ማቴዎስ 6፡32-33
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ፀጋ #ምህረት #ቃል #መባረክ #አገልግሎት #መዋረድ #ፉክክር #መርካት #ፀጋ #እውቀት #ኢየሱስንተመልክተን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና #እምነት #ታላቅነት #ማገልገል #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment