እግዚአብሔር ምን እንደምናደርግ ብቻ ሳይሆን ለምን እንደምናደረገው ምክኒያታችንን ማወቅ ይፈልጋል፡፡ የምንሰራውን ነገር ብቻ ሳይሆን ለምን እንደምንሰራው ግድ ይለዋል፡፡ እግዚአብሔር ንግግራችንን ብቻ ሳይሆን ልባችንንም ይመዝናል፡፡ እግዚአብሔር ድርጊታችንን ብቻ ሳይሆን ለድርጊቱ ያነሳሳንን ነገር ያያል፡፡
አንድን ነገር ስናደርግ በትህትና ይሁን በትእቢት እንዳደረግነው እግዚአብሔር የልባችንን ሃሳብ ይመዝናል፡፡ ስለዚህ ነው ሰዎች ትእቢተኛ ያሉትን ኢየሱስን እግዚአብሔር በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ እርሱ ነው እርሱን ነው እርሱን ስሙት ያለው፡፡ (ማቴዎስ 3፡17) ለዚህም ነው መልካም የመሰለን የሰው ሃሳብ ያመጣው ጴጥሮስ አንተ ሰይጣን ተብሎ በኢየሱስ የተገሰፀው፡፡ (ማቴዎስ 16፡23)
ገንዘባችንን ስንሰጥ ለምን እንደሰጠን አግዚአብሔር ልባችንን ይመዝናል፡፡ ገንዘባቸውን ለታይታ ፣ ሰዎችን ጉድ ለማሰኘትና ከሰው ክብርን ለማግኘት የሚሰጡትን ፈሪሳዊያን ልባቸውን እንዲያጠሩ ኢየሱስ አስተምሮዋልል፡፡
ለሰዎች ትታዩ ዘንድ ምጽዋታችሁን በፊታቸው እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ፤ ያለዚያ በሰማያት ባለው አባታችሁ ዘንድ ዋጋ የላችሁም። ማቴዎስ 6፡1
በሰዎች ፊት ቅዱስ ሃሳብ የሚባል ሃይማኖታዊ ነገር እንኳን ስናደርግ እግዚአብሔር ግን ለምን እንዳደረግነው ልባችንን ይመዝናል፡፡
ለሰውም እንዲታዩ ሥራቸውን ሁሉ ያደርጋሉ፤ ስለዚህ አሽንክታባቸውን ያሰፋሉ ዘርፉንም ያስረዝማሉ፥ በምሳም የከበሬታ ስፍራ፥ በምኵራብም የከበሬታ ወንበር፥ በገበያም ሰላምታና፦ መምህር ሆይ መምህር ሆይ ተብለው እንዲጠሩ ይወዳሉ። ማቴዎስ 23፡5-7
ለእግዚአብሔር ብለን የምናደርገውን ነገር እግዚአብሔር ይመዝነዋል፡፡ ለታይታ ወይም በፉክክር ያደረግነው ነገር እግዚአብሔር በእሺታ አይቀበለውም፡፡
የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንደሚያደርጉ እንደ ክርስቶስ ባሪያዎች እንጂ ለሰው ደስ እንደምታሰኙ ለታይታ የምትገዙ አትሁኑ። ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምትገዙ በትጋትና በበጎ ፈቃድ ተገዙ፤ ኤፌሶን 6፡6-7
ምንም ያህል መልካም ነገር ቢሆን በፍቅር ያልተደረገ ነገር ከንቱ ነው ምንም አይጠቅመንም፡፡ ከፍቅር ውጭ ያለ መነሻ ሃሳብ ከንቱ ነው፡፡ በጥላቻ በፉክክር በትእቢት ከማን አንሼ በማለት የተደረገ ምንም መልካም ነገር ፍሬ ቢስ ከንቱ ድካም ነው፡፡
በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ ጸናጽል ሆኜአለሁ። ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ፥ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፥ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም። 1ኛ ቆሮንቶስ 13፡1-3
በመጨረሻም ምን ሰራን ብቻ ሳይሆን ለምን ሰራነው የሚለውም ይፈተናል፡፡ እግዚአብሔር ምን ሰራን ከሚለው ያለነሰ ለምን ሰራነው የሚለው ግድ ይለዋል፡፡
ማንም ግን በዚህ መሠረት ላይ በወርቅ ቢሆን በብርም በከበረ ድንጋይም በእንጨትም በሣርም ወይም በአገዳ ቢያንጽ፥ የእያንዳንዱ ሥራ ይገለጣል፤ በእሳት ስለሚገለጥ ያ ቀን ያሳያልና፥ የእያንዳንዱም ሥራ እንዴት መሆኑን እሳቱ ይፈትነዋል። ማንም በእርሱ ላይ ያነጸው ሥራ ቢጸናለት ደመወዙን ይቀበላል፤ የማንም ሥራ የተቃጠለበት ቢሆን ይጎዳበታል፥ እርሱ ራሱ ግን ይድናል ነገር ግን በእሳት እንደሚድን ይሆናል። 1ኛ ቆሮንቶስ 3፡12-15
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#እምነት #ሃሳብ #መነሻሃሳብ #ልብ #ንፁህ #ፍቅር #ፉክክር #ቃል #ክብር #የእግዚአብሔርቃል #ቃሉንመስማት #እወጃ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ
No comments:
Post a Comment