ስለሰው ማንነት የእግዚአብሄር ቃል ምን እንደሚያስተምር መረዳታችን ስለፍጥረታችን እንድንረዳና ከአፈጣጠራችን ጋር አብረን እንድንፈስ ያስችለናል፡፡ ስለሰው ማንነት የእግዚአብሄር ቃል የሚያስተምረውን መረዳታችን ሶስቱን የሰው ሁለንተና በትክክል እንድናስተዳደርና በቅድስና እንድንጠበቅ ይረዳናል፡፡
የሰላምም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ መንፈሳችሁም ነፍሳችሁም ሥጋችሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለ ነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ። 1ኛ ተሰሎንቄ 5፡23
የሰውን ማንነት ከእግዚአብሄር ቃል ማወቃችን የቱ የቱን እንደሚያዝና እንደሚያስተዳደር በመረዳት ራሳችንን ለመግዛት ይጠቅመናል፡፡ የሰውን ማንነት መረዳታችን በመንፈስ ለመመራት ብርሃንን ይሰጠናል፡፡
የሰው ተፈጥሮ መንፈስ ነው፡፡ ሰው የተሰራው ከመንፈስ ነው፡፡ ሰው የተፈጠረው መንፈስ ተደርጎ ነው፡፡
ሰው እንዴት እንደተፈጠረ ከእግዚአብሄር ቃል እንመልከት፡፡
ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሄር መልክና አምሳል ነው፡፡
እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። ዘፍጥረት 1፡27
እኛ እግዚአብሄርን የምንመስለው ደግሞ በስጋችን አይደለም፡፡ እኛ እግዚአብሄርን የምንመስለው በቁመታችን አይደለም፡፡ እኛ እግዚአብሄርን የምንመስለው በቆዳ ቀለማችን አይደለም፡፡ እኛ እግዚአብሄርን የምንመስለው በመንፈሳችን ነው፡፡
እግዚአብሄር መንፈስ እንደሆነ መፅሃፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡ ሰው በእግዚአብሄር አምሳል ከተፈጠረ በእግዚአብሄር መልክና አምሳል የተፈጠረው መንፈስ እንጂ ስጋው አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ስጋ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ነፍስም አይደለም፡፡ እግዚአብሄር መንፈስ ነው፡፡ በመልኩና በአምሳሉ የፈጠረው ሰው በስጋ ውስጥ የሚኖር ነፍስ ያለው መንፈስ ነው፡፡
እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል። ዮሃንስ 4፡24
እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ። ዘፍጥረት 2፡7
መፅሃፍ ቅዱስ እግዚአብሄር ሰውን እንዴት እንደፈጠረ ሲያስረዳ እግዚአብሄር መጀመሪያ የሰውን መኖሪያ ቤት ከምድር አፈር እንዳበጀው ይናገራል፡፡
ስጋ የሰው መኖሪያ ቤት እንጂ ሰው ስጋ አይደለም፡፡
ድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ፥ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘላለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን እናውቃለንና። 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡1
እግዚአብሄር የሰውን መኖሪያ ቤቱን ከምድር አፈር ካበጀው በኋላ የተበጀው የሰው ስጋ ህይወት አልነበረውም፡፡ የሰው ስጋ ስሜትም ፣ ፈቃድም ፣ ሃሳብም ፣ ያልነበረው የማይንቀሳሰቅ የማይሰማው የጭቃ ቅርፅ ነበር፡፡ ሰው በስጋ ውስጥ ይኖራል እንጂ ሰው ስጋ አይደለም፡፡
እግዚአብሄር የህይወት እስትንፋስ እፍ አለበት፡፡ እግዚአብሄር መንፈስ ነው፡፡ እግዚአብሄር የሚተነፍሰው ኦክስጅንና ካርቦንሞኖክሳይድ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር እፍ ያለበት መንፈስን ነው፡፡ እግዚአብሄር የሰውን አካል ከምድር አፈር ከሰራው በኋላ ሰውን በሰራው አካል ውስጥ ከተተው፡፡
እስከዚያን ጊዜ የሰው አካል ስሜት ያለው ፣ ፈቃድ ያለው ፣ ሃሳብ ያለው አልነበረው፡፡ እግዚአብሄር በአበጀው አካል ውስጥ መንፈስ ሲጨምርበት ብቻ ነው ሰው ነፍስ ያለው ፣ የሚንቀሳሰቅ ፣ የሚሰማው ፣ ሃሳብ ያለው ፣ ፈቃድ ያለው ፣ ስሜት ያለው ፣ ህያው ነፍስ ሆነ የተባለው፡፡
ከምድር የተበጀው ስጋው መንፈስ ባይገባበት ኖሮ የሰው አካል የጭቃ ቅርፅ ሆኖ ይቀር ነበር፡፡ ስለዚህ ነው የሰው ተፈጥሮ መንፈስ ነው የሚባለው፡፡ ስለዚህ ነው የሰው ዋናው ክፍል መንፈስ ነው የሚባለው ፡፡ ስለዚህ ነው የሰው ማንነት መንፈስ ነው የሚባለው፡፡ ስጋው ለመኖሪያ ከምድር አፈር የተበጀ ነው እንጂ ስጋ ሰው አይደለም፡፡
ሰውም ሲሞት መንፈሱ ነው ከስጋው የሚለየው፡፡ ሰው ልክ ሲሞት ወይም መንፈስ ከስጋ ሲለያይ ስጋው አስከሬን ይባላል፡፡ ስለዚህ ነው መንፈስ የሆነው ሰው ከስጋው ከተለያ በኋላ ስሙ እከሌ ሳይሆን እስከሬን የሚባለው፡፡ የሰው ስጋ ለመኖሪያነት ብቻ እንጂ ለምንም ስለማይጠቅም መንፈስ ከስጋው ሲለይ መኖሪያው ስጋው ወደመቃብር ይሄዳል፡፡
ስለዚህ ነው ሃዋሪያው ከስጋ ብለይ ፣ ልሄድ ፣ በስጋ መኖሬ እያለ መንፈሱ እንጂ ስጋው ጊዜያዊ መኖሪያው እንደሆነ የሚናገረው፡፡
ነገር ግን በስጋ መኖር ለእኔ የሥራ ፍሬ ቢሆን፥ ምን እንድመርጥ ኣላስታውቅም። በእነዚህም በሁለቱ እጨነቃለሁ፤ ልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፥ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና፤ ነገር ግን በሥጋ መኖሬ ስለ እናንተ እጅግ የሚያስፈልግ ነው። ፊልጵስዩስ 1፡22-24
የሰው ማንነት መንፈሱ ነው፡፡ ሰውን ህያው ያደረገው ፣ ስሜት እንዲኖረው ፣ ፈቃድ እንዲኖረው እና ሃሳብ እንዲኖረው ያደረገው መንፈሱ ነው፡፡ የሰው መንፈስ ሲለይ ስጋው ይቀበራል፡፡
በሚቀጥለው ፅሁፌ ደግሞ የሰውን አወዳደቅ እንመለከታለን፡፡
ለተመሳሳይ ፅሁፍ መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውም https://www.facebook.com/notes/abiy-wakuma-dinsa/%E1%88%98%E1%8A%95%E1%8D%88%E1%88%B5-%E1%88%A5%E1%8C%8B%E1%8A%93-%E1%8A%A0%E1%8C%A5%E1%8A%95%E1%89%B5-%E1%8B%A8%E1%88%88%E1%8B%8D%E1%88%9D/10155475631979255/
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #በክርስቶስ #መንፈስ #ነፍስ #መልክ #አምሳል #የእግዚአብሄርልጅ #ስጋ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ማየት #የእግዚአብሄርመንግስት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አዲስፍጥረት #ክርስቶስ #የእግዚአብሄርቤተሰብ #ማእረግ #ስልጣን #ዳግመኛመወለድ
No comments:
Post a Comment