Popular Posts

Tuesday, October 31, 2017

SUNDAY WITH DEBBIE

40 የእምነት ጥቅሞች (ክፍል ሁለት) ዕብራውያን 11፡21-40

እግዚአብሄር መንፈስ ነው፡፡ እግዚአብሄር በስጋ አይን አይታይም፡፡ እግዚአብሄር ምን እንደሚሰራ ለማየትና ከእርሱ ጋር ለመስማማትና ለመተባበር የመንፈስ አይን ይጠይቃል፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር በሚገባ ለመኖር በተፈጥሮአዊ አይን የማይታየውን ማየት ይጠይቃል፡፡ ወደ እግዚአብሄር ለመድረስ እግዚአብሄርን ማመን ይጠይቃል፡፡ ወደ እግዚአብሄር ለመድረስ እምነት ይጠይቃል፡፡ እግዚአብሄርን ለመንካት እምነት ይጠይቃል፡፡ ከእግዚአብሄር ሃይል ጋር ለመገናኘት እምነት ይጠይቃል፡፡ የእግዚአብሄር አቅርቦት ተጠቃሚ ለመሆን እምነት ይጠይቃል፡፡
በአጠቃላይ ያለእምነት እግዚአብሄርን ማስደሰት አይቻልም፡፡ ያለእምነት ከእግዚአብሄር ጋር ያለው ግንኙነታችን ትክክል ሊሆን በፍፁም አይችልም፡፡ ካለእምነት ከእግዚአብሄር ጋር ልንገናኝ አንችልም፡፡  
እምነት በተፈጥሮአዊ አይናችን የማናየውን ተስፋ ለማረጋገጥ ይጠቅማል፡፡ እምነት በተፈጥሮ አይናችን ስለማናየው ነገር ያስረዳል፡፡
እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው። ዕብራውያን 11፡1
ሰው ስለተለያየ ነገር ሊመሰክር ይችላል፡፡ የእግዚአብሄር እውነተኛው ምስክርነት የሚገኘው ግን በእምነት ከመኖር ነው፡፡ እምነት የእግዚአብሄር ምስክርነት እንዲኖረን ያደርጋል፡፡
ለሽማግሌዎች የተመሰከረላቸው በዚህ ነውና። ዕብራውያን 11፡2
ስለማናየው ስለወደፊቱ የበረከትን ቃል የምንለቀው በእምነት ብቻ ነው፡፡ የበረከታችን ቃል እንደሚደርስ አውቀን የምናመሰግነው በእምነት ነው፡፡
ያዕቆብ ሲሞት በእምነት የዮሴፍን ልጆች እያንዳንዳቸው ባረካቸው፥ በዘንጉም ጫፍ ተጠግቶ ሰገደ። ዕብራውያን 11፡21
ስለወደፊት ህይወታችንና ስለትውልዳችን የምናየው እና የምንናገረው በእምነት ነው፡፡
ዮሴፍ ወደ ሞት ቀርቦ ሳለ በእምነት ስለ እስራኤል ልጆች መውጣት አስታወሰ፥ ስለ አጥንቱም አዘዛቸው። ዕብራውያን 11፡22
ካለፍርሃት የምድራዊውን ህግ ሽረን እግዚአብሄርን የምንታዘዘው በእምነት ነው፡፡
ሙሴ ከተወለደ በኋላ ወላጆቹ ያማረ ሕፃን መሆኑን አይተው በእምነት ሦስት ወር ሸሸጉት የንጉሥንም አዋጅ አልፈሩም። ዕብራውያን 11፡23
ስለ ጥሪያችን ስንል የምድራዊውን ጥቅም የምንንቀው በእምነት ነው፡፡ ራሳችንን ከምድራዊ ፉክክር የምናገለው በተፈጥሮ አይን የማይታየውን በማየት በእምነት ነው፡፡
ሙሴ ካደገ በኋላ የፈርዖን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እምቢ አለ፤ ዕብራውያን 11፡24
እግዚአብሄር ክብደት ለሰጠው ነገር ክብደት የምንሰጠውና የናቀውን ነገር ደግሞ የምንንቀው በእምነት ነው፡፡ ከጊዜያዊ ደስታ ይልቅ የዘላለሙን ብድራት የምናየው በእምነት ብቻ ነው፡፡ በእግዚአብሄር ፈቃድ ውስጥ ያለ ማንኛውም ነገር የሚበልጥ ባለጠግነት እንደሆነ የምናስተውለው በእምነት ብቻ ነው፡፡ በምድር ላይ ትኩረታችን ለሚፈልጉ ነገሮችን እንቢ የምንለውና ክርስቶስን ብቻ ተመልክተን ሩጫችንን በትእግስት የምንጨርሰው በእምነት ነው፡፡
ከግብፅም ብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለ ጠግነት እንዲሆን አስቦአልና ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ፤ ብድራቱን ትኵር ብሎ ተመልክቶአልና። ዕብራውያን 11፡25-26
በምድር ላይ የሚያስፈራሩትንና የሚያስጨንቁትን ነገሮች ሳንፈራ እግዚአብሄርን የምናገለግለው በእምነት ነው፡
የንጉሡን ቍጣ ሳይፈራ የግብፅን አገር የተወ በእምነት ነበር፤ የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ ጸንቶአልና። ዕብራውያን 11፡27
ለሩሮዋችን ሳንጨነቅ የእግዚአብሄርን መንግስትና ፅድቅ የምንፈልገው በእምነት ነው፡፡

ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ማቴዎስ 6፡33
በመውጣት በመግባታችን ከክፉ የምንጠበቀው በእምነት ነው፡፡ በአእምሮ የማይመስለውን የእግዚአብሄርን ቃል በሞኝነት የምንታዘዘው በእምነት ነው፡፡
አጥፊው የበኵሮችን ልጆች እንዳይነካ ፋሲካንና ደምን መርጨትን በእምነት አደረገ። ዕብራውያን 11፡28
ከከበበን ነገር የምናልፈው በእምነት ነው፡፡
በደረቅ ምድር እንደሚያልፉ በኤርትራ ባሕር በእምነት ተሻገሩ፥ የግብፅ ሰዎች ግን ሲሞክሩ ተዋጡ። ዕብራውያን 11፡29
ከእኛ ሃየለ የሚበልጠውን በሰው ጉልበት የማይቻለውን አስፈሪውን የጠላትን ግዛት የምንወርሰው በእምነት እርምጃ በመውሰድ ነው፡፡
የኢያሪኮ ቅጥር ሰባት ቀን ከዞሩበት በኋላ በእምነት ወደቀ። ዕብራውያን 11፡30
የእግዚአብሄር ፈቃድ የምንታዘዘው በተፈጥሮአዊ አይናችን አይተን ሳይሆን ቃሉን ብቻ ሰምተን በእምነት በመታዘዝ ነው፡፡
ጋለሞታይቱ ረዓብ ሰላዮችን በሰላም ስለ ተቀበለቻቸው ከማይታዘዙ ጋር በእምነት አልጠፋችም። ዕብራውያን 11፡31
በምናልፍበት አስቸጋሪ ህይወት ድልን የምናገኘው በእምነት ነው፡፡ የተሰጠንን የተስፋ ቃል የምናገኘው በእምነት ነው፡፡
እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ፥ ጽድቅን አደረጉ፥ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አገኙ፥ ዕብራውያን 11፡33
ከሰው ሃይልና ችሎታ በላይ የሆኑ ታእምራት በህይወታችን የሚሆኑት በእምነት ነው፡፡ የእሳት ሃይል የማይጎዳን በችሎታችን ሳይሆን በእግዚአብሄ ችሎታ ላይ በመታመን ነው፡፡ ከድካም የምንበረታው በእምነት ነው፡፡ ከእኛ እጅግ የሚበረቱትን ድል የምንረታው በእምነት ነው፡፡  
የአንበሶችን አፍ ዘጉ፥ የእሳትን ኃይል አጠፉ፥ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፥ ከድካማቸው በረቱ፥ በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ፥ የባዕድ ጭፍሮችን አባረሩ። ዕብራውያን 11፡34
ክርስትና ህይወታችንን መስዋእት እስከምናደርግ ድረስ ለጥሪያችን የምንታዘዘው በእምነት ነው፡፡
ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ፤ ሌሎችም መዳንን ሳይቀበሉ የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ፤ ዕብራውያን 11፡35
ሰው የሚጋደልለትን ነገር በደስታ የምናጣው የተሻለ ነገር እንዳለ በእምነት አይናችን አይተን ነው፡፡
የሚበልጥና ለዘወትር የሚኖር ገንዘብ በሰማይ ራሳችሁ እንዳላችሁ አውቃችሁ፥ በእስራቴ ራራችሁልኝ የገንዘባችሁንም ንጥቂያ በደስታ ተቀበላችሁ። ዕብራውያን 10፡34
የሰዎች መሳለቂያ የምንሆነው በእምነት ነው፡፡ ክብራችንን የምንተወው በእምነት ነው፡፡ ሰው የሚያከብረውን እንዳይደርስበት ሁሉንም ነገር የሚያደርገለትን ነውር የምንንቀው በእምነት ነው፡፡
ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ፤ ዕብራውያን 11፡36
የእግዚአብሄርን ስራ ለመስራት መዋረድን የማንፈራው በእምነት ነው፡፡ እግዚአብሄርን ለመታዘዝ መሳለቂያ መሆንን የምንንቀው በእምነት ነው፡፡  
. . . የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና። ዕብራውያን 12፡1-2
ማጣትን የምንንቀው በእምነት ነው፡፡ ላለማጣት ማንኛውንም ነገር የማናደርገው በእምነት ነው፡፡
በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፥ ተፈተኑ፥ በመጋዝ ተሰነጠቁ፥ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ፥ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤ዕብራውያን 11፡37
ማጣት እንደማያዋርደን ማግኘት እንደማያከብረን የሚያኖረን እግዚአብሄር እንደሆነ የምንረዳው በእምነት ነው፡
መዋረድንም አውቃለሁ መብዛትንም አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም መብዛትንና መጉደልን ተምሬአለሁ። ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ። ፊልጵስዩስ 4፡12-13
የአለምን ጥቅም የምንንቀው ፣ በአለም የማንጠቀመውና በአለም ጥቅም ላይ የሙጥኝ የማንለው በእምነት ነው፡፡
ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጕድጓድ ተቅበዘበዙ። ዕብራውያን 11፡38
የሚገዙም ምንም እንደሌላቸው፥ በዚችም ዓለም የሚጠቀሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙባት ይሁኑ፤ የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነውና። 1ኛ ቆሮንቶስ 7፡31
በእምነታቸው የተመሰከረላቸው አባቶች ያመኑትን ነገር ሳያገኙ የሞቱት በእምነት ነው፡፡
እነዚህም ሁሉ በእምነታቸው ተመስክሮላቸው ሳሉ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አላገኙም፥ ያለ እኛ ፍጹማን እንዳይሆኑ እግዚአብሔር ስለ እኛ አንዳች የሚበልጥ ነገርን አስቀድሞ አይቶ ነበርና። ዕብራውያን 11፡39-40
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #መናገር #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #ቃል #ማሰላሰል #ማድረግ #ሁሉይቻላል #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

Monday, October 30, 2017

ሰው በስጋ ውስጥ የሚኖር ነፍስ ያለው መንፈስ ነው

ስለሰው ማንነት የእግዚአብሄር ቃል ምን እንደሚያስተምር መረዳታችን ስለፍጥረታችን እንድንረዳና ከአፈጣጠራችን ጋር አብረን እንድንፈስ ያስችለናል፡፡ ስለሰው ማንነት የእግዚአብሄር ቃል የሚያስተምረውን መረዳታችን ሶስቱን የሰው ሁለንተና በትክክል እንድናስተዳደርና በቅድስና እንድንጠበቅ ይረዳናል፡፡
የሰላምም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ መንፈሳችሁም ነፍሳችሁም ሥጋችሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለ ነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ። 1ኛ ተሰሎንቄ 5፡23
የሰውን ማንነት ከእግዚአብሄር ቃል ማወቃችን የቱ የቱን እንደሚያዝና እንደሚያስተዳደር በመረዳት ራሳችንን ለመግዛት ይጠቅመናል፡፡ የሰውን ማንነት መረዳታችን በመንፈስ ለመመራት ብርሃንን ይሰጠናል፡፡  
የሰው ተፈጥሮ መንፈስ ነው፡፡ ሰው የተሰራው ከመንፈስ ነው፡፡ ሰው የተፈጠረው መንፈስ ተደርጎ ነው፡፡
ሰው እንዴት እንደተፈጠረ ከእግዚአብሄር ቃል እንመልከት፡፡
ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሄር መልክና አምሳል ነው፡፡
እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። ዘፍጥረት 1፡27
እኛ እግዚአብሄርን የምንመስለው ደግሞ በስጋችን አይደለም፡፡ እኛ እግዚአብሄርን የምንመስለው በቁመታችን አይደለም፡፡ እኛ እግዚአብሄርን የምንመስለው በቆዳ ቀለማችን አይደለም፡፡ እኛ እግዚአብሄርን የምንመስለው በመንፈሳችን ነው፡፡
እግዚአብሄር መንፈስ እንደሆነ መፅሃፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡ ሰው በእግዚአብሄር አምሳል ከተፈጠረ በእግዚአብሄር መልክና አምሳል የተፈጠረው መንፈስ እንጂ ስጋው አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ስጋ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ነፍስም አይደለም፡፡ እግዚአብሄር መንፈስ ነው፡፡ በመልኩና በአምሳሉ የፈጠረው ሰው በስጋ ውስጥ የሚኖር ነፍስ ያለው መንፈስ ነው፡፡
እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል። ዮሃንስ 4፡24
እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ። ዘፍጥረት 2፡7
መፅሃፍ ቅዱስ እግዚአብሄር ሰውን እንዴት እንደፈጠረ ሲያስረዳ እግዚአብሄር መጀመሪያ የሰውን መኖሪያ ቤት ከምድር አፈር እንዳበጀው ይናገራል፡፡  
ስጋ የሰው መኖሪያ ቤት እንጂ ሰው ስጋ አይደለም፡፡
ድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ፥ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘላለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን እናውቃለንና። 2 ቆሮንቶስ 5፡1
እግዚአብሄር የሰውን መኖሪያ ቤቱን ከምድር አፈር ካበጀው በኋላ የተበጀው የሰው ስጋ ህይወት አልነበረውም፡፡ የሰው ስጋ ስሜትም ፣ ፈቃድም ፣ ሃሳብም ፣ ያልነበረው የማይንቀሳሰቅ የማይሰማው የጭቃ ቅርፅ ነበር፡፡ ሰው በስጋ ውስጥ ይኖራል እንጂ ሰው ስጋ አይደለም፡፡
እግዚአብሄር የህይወት እስትንፋስ እፍ አለበት፡፡ እግዚአብሄር መንፈስ ነው፡፡ እግዚአብሄር የሚተነፍሰው ኦክስጅንና ካርቦንሞኖክሳይድ አይደለም፡፡  እግዚአብሄር እፍ ያለበት መንፈስን ነው፡፡ እግዚአብሄር የሰውን አካል ከምድር አፈር ከሰራው በኋላ ሰውን በሰራው አካል ውስጥ ከተተው፡፡
እስከዚያን ጊዜ የሰው አካል ስሜት ያለው ፣ ፈቃድ ያለው ፣ ሃሳብ ያለው አልነበረው፡፡ እግዚአብሄር በአበጀው አካል ውስጥ መንፈስ ሲጨምርበት ብቻ ነው ሰው ነፍስ ያለው ፣ የሚንቀሳሰቅ ፣ የሚሰማው ፣ ሃሳብ ያለው ፣ ፈቃድ ያለው ፣ ስሜት ያለው ፣ ህያው ነፍስ ሆነ የተባለው፡፡
ከምድር የተበጀው ስጋው መንፈስ ባይገባበት ኖሮ የሰው አካል የጭቃ ቅርፅ ሆኖ ይቀር ነበር፡፡ ስለዚህ ነው የሰው ተፈጥሮ መንፈስ ነው የሚባለው፡፡ ስለዚህ ነው የሰው ዋናው ክፍል መንፈስ ነው የሚባለው ፡፡ ስለዚህ ነው የሰው ማንነት መንፈስ ነው የሚባለው፡፡ ስጋው ለመኖሪያ ከምድር አፈር የተበጀ ነው እንጂ ስጋ ሰው አይደለም፡፡
ሰውም ሲሞት መንፈሱ ነው ከስጋው የሚለየው፡፡ ሰው ልክ ሲሞት ወይም መንፈስ ከስጋ ሲለያይ ስጋው አስከሬን ይባላል፡፡ ስለዚህ ነው መንፈስ የሆነው ሰው ከስጋው ከተለያ በኋላ ስሙ እከሌ ሳይሆን እስከሬን የሚባለው፡፡ የሰው ስጋ ለመኖሪያነት ብቻ እንጂ ለምንም ስለማይጠቅም መንፈስ ከስጋው ሲለይ መኖሪያው ስጋው ወደመቃብር ይሄዳል፡፡
ስለዚህ ነው ሃዋሪያው ከስጋ ብለይ ፣ ልሄድ ፣ በስጋ መኖሬ እያለ መንፈሱ እንጂ ስጋው ጊዜያዊ መኖሪያው እንደሆነ የሚናገረው፡፡
ነገር ግን በስጋ መኖር ለእኔ የሥራ ፍሬ ቢሆን፥ ምን እንድመርጥ ኣላስታውቅም። በእነዚህም በሁለቱ እጨነቃለሁ፤ ልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፥ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና፤ ነገር ግን በሥጋ መኖሬ ስለ እናንተ እጅግ የሚያስፈልግ ነው። ፊልጵስዩስ 1፡22-24
የሰው ማንነት መንፈሱ ነው፡፡ ሰውን ህያው ያደረገው ፣ ስሜት እንዲኖረው ፣ ፈቃድ እንዲኖረው እና ሃሳብ እንዲኖረው ያደረገው መንፈሱ ነው፡፡ የሰው መንፈስ ሲለይ ስጋው ይቀበራል፡፡
በሚቀጥለው ፅሁፌ ደግሞ የሰውን አወዳደቅ እንመለከታለን፡፡
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #በክርስቶስ #መንፈስ #ነፍስ  #መልክ #አምሳል #የእግዚአብሄርልጅ #ስጋ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ማየት #የእግዚአብሄርመንግስት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አዲስፍጥረት #ክርስቶስ #የእግዚአብሄርቤተሰብ #ማእረግ #ስልጣን #ዳግመኛመወለድ

Saturday, October 28, 2017

ለራሳቸው እንዳይኖሩ

ከእኛ አንድ ስንኳ ለራሱ የሚኖር የለምና፥ ለራሱም የሚሞት የለም፤ ሮሜ 14:7
በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ። 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡15
ኢየሱስ የሞተልን ንስሃ ገብተን የራሳችንን ህይወት ካቆምንበት እንድንቀጥል አይደለም፡፡ ኢየሱስ የሞተው እኛ ለራሳችን እንድንሞት ነው፡፡ ኢየሱስ የሞተው ለእርሲ እንድንኖርለት ነው፡፡
በክርስትና ስኬታማ የምንሆነው ለራሳችን ስንኖር ሳይሆን ለራሳችን ስንሞት ነው፡፡ በክርስትና የምንከናወነው ለሞተልን ለእርሱ ስንኖር ነው፡፡
ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታልና፤ ስለ እኔ ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ግን እርሱ ያድናታል። ሉቃስ 9፡24
ነፍሱን ሊያስደስት የሚወድ ፣ ለነፍሱ ስሜት ቅድሚያ የሚሰጥና ነፍሱን በዋነኝነት የሚያከብር ሰው ለሞተለት ለክርስቶስ መኖር አይችልም፡፡
ነገር ግን ሩጫዬንና ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልሁትን አገልግሎት እርሱም የእግዚአብሔርን ጸጋ ወንጌልን መመስከር እፈጽም ዘንድ ነፍሴን በእኔ ዘንድ እንደማትከብር እንደ ከንቱ ነገር እቆጥራለሁ። ሐዋርያት 20፡24
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እምነት #ማየት #ነፍሱን #የሚያጠፋ #ሞተ #እንዲኖሩ #እንዳይኖሩ #የሚኖር #የሚሞት #መከተል #ቃል #የእግዚአብሄርሃይል #መንፈስቅዱስ #ቃሉንመስማት #ደቀመዝሙር #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ነፍስንመካድ #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

ዘይት መሸጥ ችግሩ ምንድነው ?

ኢየሱስን የምንከተል ሁላችን ከተባረክናባቸው በረከቶች አንዱ የስጋ ፈውስ ነው፡፡ እግዚአብሄር በክርስቶስ በኩል የሃጢያታችንን እዳ እንደከፈለና ነፍሳችን ከሃጢያት ነፃ እንዳወጣ ሁሉ እንዲሁ ኢየሱስ በመገረፉና ለስጋችን ፈውስና ጤንነት ሙሉ ዋጋ በመክፈሉ ፈውስ የእኛ ነው፡፡
ስለዚህ ነው የቤተክርስቲያን ሽማግሌዎች በታመመ ሰው ላይ ዘይትት ቀብተው እንዲፀልዩለት መፅሃፍ ቅዱስ የሚያስተምረው፡፡
የቤተክርስትያን ሽማግሌዎች ሃላፊነት በቤተክርስትያናቸው ስለፈውስ ማስተማር ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል ስናስተምር የእግዚአብሄ ህዝብ እግዚአብሄር ለእርሱ ያለውን የፈውስ አላማ ሲረዳ ይፈወሳል፡፡ እምነት የእግዚአብሄርን ቃል ከመስማት ይመጣልና፡፡  
እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው። ሮሜ 1017
የቤተክርስትያን ሽማግሌዎች በግልፅ እንደተፃፈው የእግዚአብሄር ቃል ትእዛዝ ለታመመ ሰው ዘይት ቀብተው መፀለይ ነው፡፡ ሽማግሌዎች በታመመ ላይ ዘይት ቀብተው በመፀለይ የእግዚአብሄርን ቃል መታዘዝ አለባቸው፡፡  
ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤተ ክርስቲያንን ሽምግሌዎች ወደ እርሱ ይጥራ፤ በጌታም ስም እርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት። ያዕቆብ 5፡14
ያም ሆነ ይህ የእምነት ፀሎት ነው በሽተኛውን የሚፈውሰው፡፡ ሰው እግዚአብሄር ስለእርሱ ያለውን የፈውስ አላማ ከእግዚአብሄር ቃል ሰምቶ ሲያምን ይፈወሳል፡፡ ሐዋርያት 14፡9
ይህም ሰው ጳውሎስ ሲናገር ይሰማ ነበር፤ እርሱም ትኵር ብሎ ተመለከተውና ይድን ዘንድ እምነት እንዳለው ባየ ጊዜ፥
ሰወ የእግዚአብሄርን ቃል ሲሰማ እምነት ይኖረዋል፡፡ እምነት ሲኖረው እምነቱ ይፈውሰዋል፡፡
እርሱም፦ ልጄ ሆይ፥ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ ከሥቃይሽም ተፈወሽ አላት። ማርቆስ 5፡34
አንዳንድ አገልጋዮች ዘይት ቀብተው ለበሽተኞች ይፀልያሉ፡፡ ዘይቱን ወደቤቱ ወስፈዶ መፀለይ ለሚፈልግ ሰው ዘይትን ይሰጣሉ ወይም ይሸጣሉ፡፡ አንዳንድ ሰው ዘይቱን የሚገዛው መምጣት ላልቻለ ለታመመ ሰው ላይ ወስዶ ለመፀለይ ነው፡፡
ድውዮችን ፈውሱ፤ ሙታንን አስነሡ፤ ለምጻሞችን አንጹ፤ አጋንንትን አውጡ፤ በከንቱ ተቀበላችሁ፥ በከንቱ ስጡ። ማቴዎስ 10፡8
ዘይቱን ስለመሸጥ ስናስብ የመሸጥ ችግሩ ምንድነው ዘይት ብለን እንደ እግዚአብሄር ቃል ማሰብ ይኖርብናል፡፡ ዘይት ገዝተው በሰው ላይ ለመቀባትና ለመፀለይ ወይም በራሳቸው ላይ ለመቀባትና ለመፀለይ ለሚፈልጉ ሰዎች ዘይቱን መሸጥ ችግሩ ምንድነው የሚለውን ጥያቄ መመለስ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡
በደንብ ብናስበው ዘይቱ የሚገኘው በገንዘብ ነው፡፡ ትንሽም ቢሆን ማሸጊያና ሌሎች ወጭዎች ይኖሩታል፡፡ ያንን ወጪ ማን ይሸፍን ነው ጥያቄው? አገልጋዩ ያንን ወጭ ሸፍኖ በነፃ መስጠት ቢችል እሰየው ነው፡፡ ካልቻለ ግን ዘይቱን ለመግዛትና ለማሸግ ያወጣውን ወጭ ቢመልስ ችግሩ ምንድነው? ሰው በዘይቱ ከሚያገኘው መንፈሳዊ ጥቅም አንፃር የዘይቱን መጋና´ማሸጊያ ለጥቃቅን ወጪዎችን ቢከፍል ትልቅ ነገር ነውን?
እኛ መንፈሳዊን ነገር የዘራንላችሁ ከሆንን የእናንተን የሥጋዊን ነገር እኛ ብናጭድ ትልቅ ነገር ነውን? 1ኛ ቆሮንቶስ 9፡11
እውነት ነው ፀጋው ነፃ ነው፡፡ የፈውስ ስጦታው ነፃ ነው፡፡ ነገር ግን ዘይቱን ለመግዛትና ለማሸግ ነፃ አይደለም ገንዘብ ያስወጣል፡፡
በቅንነት ካየነው አገልጋዮች ለዘይቱና ለማሸጊያው ያወጡትን ተመጣጣኝ ዋጋ ቢመልሱ ምንም ችግር የለበትም፡፡
ይህ ማለት አገልጋዩ ስስታም አይሆንም ማለት አይደለም፡፡ ይህ ማለት አገልጋዩ በዚያ አጋጣሚ ተጠቅሞ ብዙ ገንዘብ ለማግኘት አይሞክርም እያልኩ አይደለም፡፡ አገልጋዩ ራስ ወዳድ ሊሆንና ከሰዎች መፈወስ በላይ የራሱን ጥቅም ሊያስቀድምና ካለምንም ምክኒያት ካወጣው ወጭ በላይ ብዙ እጥፍ ሊያስከፍል ይችላል፡፡ ይህ በፍፁም ተቀባይነት የሌለው ነገር ነው፡፡ ሰው ለዘይቱና ለማሸጊያው ያወጣውን ወጭ አስታኮ በነፃ የተቀበለውን የእግዚአብሄርን ነገር መሸጥ ስግብግብነት ነው፡፡
ኢየሱስን በግልፅ የተቃወመው መንፈሳዊ ነገርን ፈልገው የመጡ ሰዎችን ላይ አላግባብ መጠቀምን ነው፡፡
እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ በጸሎት ርዝመት እያመካኛችሁ የመበለቶችን ቤት ስለምትበሉ፥ ወዮላችሁ፤ ስለዚህ የባሰ ፍርድ ትቀበላላችሁ። ማቴዎስ 23፡14
የእግዚአብሄርን ፈውስ ፈልገው የመጡን ሰዎች ይህን ያህል ገንዘብ ካልከፈላችሁ ብሎ የተጋነነ ገንዘብ መጠየቅና ማስጨነቅ ስጋዊነት ነው፡፡
በመጀመሪያይቱም ቤተክርስትያን መንፈስ ቅዱስን ለመሙላት ለሃዋሪያት ብር ሊሰጣቸው የሞከረውን ሰው ሃዋሪያት አጠንክረው ሲገስፁት እንመለከታለን፡፡ የእግዚአብሄርን ስጦታ በገንዘብ መቸርቸር በነፃ ተቀብላችሁዋልና በነፃ ስጡ የሚለው መፅሃፍ ቅዱሳዊ መርህ ይቃወማልና፡፡
ሲሞንም በሐዋርያት እጅ መጫን መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጥ ባየ ጊዜ፥ ገንዘብ አመጣላቸውና። እጄን የምጭንበት ሁሉ መንፈስ ቅዱስን ይቀበል ዘንድ ለእኔ ደግሞ ይህን ሥልጣን ስጡኝ አለ። ጴጥሮስ ግን እንዲህ አለው፦ የእግዚአብሔርን ስጦታ በገንዘብ እንድታገኝ አስበሃልና ብርህ ከአንተ ጋር ይጥፋ። ሐዋርያት 8፡18-20
አገልጋዮች ስለኑሮዋቸው በእግዚአብሄርን መታመን አለባቸው፡፡ እግዚአብሄር የሰጣቸውን ነፃ ስጦታ በነፃ መስጠት አለባቸው፡፡ አገልጋዮች እግዚአብሄር የሰጣቸው ስጦታ ብዙ ገንዘብ ማግኛ መንገድ ለማድረግ ያለባቸውን ስጋዊ ፈተና ማሸነፍ እግዚአብሄን በስኬት እንዲየገለግሉት ያስችላቸዋል፡፡ አገልጋዮች የእግዚአብሄር ህዝብ መባረክ ፣ መጠቀምና መፈወስ ላይ ማተኮር አለባቸው፡፡ አገልጋዮች የእግዚአብሄርን መንግስትና ፅድቁን ሲፈልጉ እግዚአብሄር ደግሞ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ አንደሚያሟላላቸው በእግዚአብሄር መታመን አለባቸው፡፡
እንግዲህ፦ ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ማቴዎስ 6፡ 31-33  
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ፈውስ #እምነት #ቁስል #ህመም #ደዌ #ጤንነት #በነፃ #ዘይት #ቅባት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #በመገረፉ #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

Friday, October 27, 2017

በፍቅሬ ኑሩ

አብ እንደ ወደደኝ እኔ ደግሞ ወደድኋችሁ፤ በፍቅሬ ኑሩ። እኔ የአባቴን ትእዛዝ እንደ ጠበቅሁ በፍቅሩም እንደምኖር፥ ትእዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ። ዮሐንስ 15:9-10
ኢየሱስ እንዲህ እያለ ነው፡፡ በፍቅሬ ብሉ ፣ በፍቅሬ ጠጡ ፣ በፍቅሬ ግቡ ፣ በፍቅሬ ውጡ ፣ በፍቅሬ ጠንክሩ ፣ በፍቅሬ ተከናወኑ ፣ በፍቅሬ ጥግቡ ፣ በፍቅሬ በርቱ ፣  በፍቅሬ ተደገፉ ፣ በፍቅሬ ተማመኑ ፣ በፍቅሬ ተስፋ አድርጉ ፣ በፍቅሬ እረፉ ፣ በፍቅሬ ስሩ . . .
ሰው ለመኖር መኖሪያ ያስፈልገዋል፡፡ ሰው መኖሪያ ከሌለው መኖር አይችልም፡፡ ሰው ለመኖር ህይወት የሚጠይቃቸውን ሁኔታዎችን ተቋቁሞ ማለፍ አለበት፡፡ ሰው በምድር ላይ ለመኖር አቅራቦት ያስፈልገዋል፡፡ ሰው ለመኖር ሃይል ያስፈልገዋል፡፡ ሰው ለመኖር ጥንካሬ ያስፈልገዋል፡፡ ሰው ለመኖር ምሪት ያስፈልገዋል፡፡ ሰው ለመኖር ፍቅር ያስገፈልገዋል፡፡
አብ ኢየሱስን ይወደዋል፡፡ ኢየሱስ በምድር ላይ የኖረው በአብ ፍቅር ነው፡፡ ኢየሱስ በምድር ላይ የተከናወነው በአብ ፍቅር ነው፡፡ ኢየሱስ በምድር ላይ የወጣውና የገባው አላማውንም የፈፀመው በአብ ፍቅር ነው፡፡ ኢየሱስ በምድር ላይ የረካው በአብ ፍቅር ነው፡፡ ኢየሱስ በምድር ላይ መከራን የተጋፈጠው በአብ ፍቅር ነው፡፡
ኢየሱስ እኔን ምሰሉ እያለን ነው፡፡ እኔ በአብ ፍቅር እንደኖርኩና እንዳሸነፍኩ እናንተም በእኔ ፍቅር ኑሩ ውጡ ግቡ አሸንፉ እያለን ነው፡፡
ለመኖር ለመውጣት ለመግባት የህይወት አላማን ለማሳካት እግዚአብሄር ፍቅር መሆኑን ከማወቅ በላይ የሆነ እውቀት የለም፡፡ ማስተዋሉ የማይመረመር እግዚአብሄር ፍቅር ነው፡፡ ሁሉን ቻይ የሆነው እግዚአብሄር ይወደናል፡፡ የዘላለም አምላክ አቅራቢያችን ነው፡፡
በእግዚአብሄር ፍቅር መኖር ካልቻልን በምንም ነገር መኖር አንችልም፡፡ በእግዚአብሄር ፍቅር ከኖርን ደግሞ የማናደርገው ነገር አይኖርም፡፡ በእግዚአብሄር ፍቅር ከኖርን የማንደርስበት ከፍታ የለም፡፡ በእግዚአብሄር ፍቅር ከኖርን የማናገኘው መልካም ነገር የለም፡፡ በእግዚአብሄር ፍቅር ከኖርን የማንሆነው ነገር የለም፡፡
አብ እንደ ወደደኝ እኔ ደግሞ ወደድኋችሁ፤ በፍቅሬ ኑሩ። ዮሐንስ 15:9
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ፍቅር #መውደድ #ኑሩ #ህይወት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #ቸርነት #ትግስት #ፍርሃት #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #መውደድ #ትግስት #መሪ

Thursday, October 26, 2017

ልጅ ስለሆንክ ብቻ

እግዚአብሄር የሚንከባከበን ስለሰራንና ወይም ስላልሰራን አይደለም፡፡ እግዚአብሄር የሚንከባከበን ልጅ ስለሆንን ብቻ ነው፡፡ የትኛው ወላጅ ነው በቤቱ የተወለደ ልጁ ስራ ሲሰራ የሚመግበው ካልሰራ ደግሞ ምግብን የሚከለክለው? ልጅ መሰረታዊ ፍላጎቱ የሚሟላው ልጅ ስለሆነና በቤተሰቡ ውስጥ ስለተወለደ ብቻ ነው፡፡  
ታዲያ የምንሰራው ለምድነው?
የምንሰራው የልጅነት መብታችንን ከእግዚአብሄር ለመቀበል አይደለም፡፡ የምንሰራው እግዚአብሄር ልጄን ምን አበላዋለሁ ብሎ ስለተጨነቀ እግዚአብሄርን ለመርዳት አይደለም፡፡ የምንሰራው ስራና በእግዚአብሄር ዘንድ ያለን የልጅነት መብት  ምንም የሚያገናኛቸው ነገር የለም፡፡ እግዚአብሄር ወፎችን የሚመግበው መስሪያ ቤት ሄደው ስለሰሩ አይደለም፡፡ የእግዚአብሄ ፍጥረት ስለሆኑ ብቻ ነው፡፡
ወደ ሰማይ ወፎች ተመልከቱ፤ አይዘሩም አያጭዱምም በጎተራም አይከቱም፥ የሰማዩ አባታችሁም ይመግባቸዋል፤ እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን? ማቴዎስ 6፡26
የምንሰራው የክህንነት ሃላፊነታችንን ለመወጣት ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄር በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን በኋላ እኛን ካህናት አድርጎናል፡፡ ስለእግዚአብሄር ለሰዎች እንመሰከራለን፡፡ በድርጊትም በቃልም ሰዎችን ከእግዚአብሄር ጋር ታረቁ ብለን እንለምናለን፡፡ የእግዚአብሄር የምስራች ወንጌል መልክተኞች ነን፡፡  
የምንሰራው ለክርስቶስ ምስክርነታችን ሃይል እንዲሰጠን ነው፡፡ ክርስትያን ሰነፍ እንዳልሆነ እንዲያውም ጠንካራ ሰራተኛ እንደሆነና በእግዚአብሄር ፀጋ ተጨማሪ ምእራፍ የሚሄድ እንደሆንን በማሳየት በውስጣችን ስከለሚሰራወ የእግዚአብሄር ፀጋ ምስክር ለመሆን ነው፡፡
እንዲሁ በመቄዶንያ ሁሉ ላሉት ወንድሞች ሁሉ ታደርጋላችሁና። ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ከፊት ይልቅ ልትበዙ፥ በጸጥታም ትኖሩ ዘንድ ልትቀኑ፥ የራሳችሁንም ጉዳይ ልትጠነቀቁ፥ እንዳዘዝናችሁም፥ በውጭ ባሉት ዘንድ በአገባብ እንድትመላለሱ፥ አንዳችም እንዳያስፈልጋችሁ በእጃችሁ ልትሠሩ እንለምናችኋለን። 1ኛ ተሰሎንቄ 4፡10-12
ማንም ሰው አንድ ምዕራፍ ትሄድ ዘንድ ቢያስገድድህ ሁለተኛውን ከእርሱ ጋር ሂድ። ማቴዎስ 5፡41
የምንሰራው በስራ ቦታችን ላሉት ሰዎች ብርሃን ለመሆን ነው፡፡ የምንንሰራው ከፍ ያለ የእግዚአብሄር ህይወት እንዳለ ለማሳየት ነው፡፡ የምንሰራው የእግዚአብሄር ቃል ሊፈፅሙት የሚቻልና የሚገባ ክቡር ቃል እንደሆነ በህይወታችን ምሳሌ ለመሆን ነው፡፡ የምንሰራው በአካባቢያችን ላሉ ሰዎች የእግዚአብሄር መንግስትን መረዳት ለማካፈል ነው፡፡
እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም። መብራትንም አብርተው ከዕንቅብ በታች አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያኖሩታል በቤት ላሉት ሁሉም ያበራል። ማቴዎስ 5፡14-15
የምንሰራው በስራ ለምንገናኛቸው ሰዎች የምድር ጨው ለመሆን ነው፡፡
የምንሰራው በስራ ለሚገናኙን ሰዎች በህይወታችን የእግዚአብሄር መልካምነትን ጣእም ለማቅመስ ነው፡፡
ለእያንዳንዱ እንዴት እንድትመልሱ እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ሁልጊዜ፥ በጨው እንደ ተቀመመ፥ በጸጋ ይሁን። ቆላስይስ 4፡6
ስራም ስንሰራ የመጀመሪያው ስራችን ለሰዎች የእግዚአብሄር መልካምነት ምስክር መሆን ነው፡፡ እንደ ክርስትያን የመጀመሪያ ጥሪያችን በህይወታችን ስለክርስትና መመስከር እንደመሆኑ መጠን ቀጣሪያችን የምድር ጌታችን ሳይሆን ቀጣሪያችን ጌታ ክርስቶስ ነው፡፡
እንደ ክርስትያን የመጀመሪያ ጥሪያችን ክርስቶስን በመምሰል ለሌሎች መመስከር እንደመሆኑ መጠን ቀጣሪያችንም ከፋያችንንም ጌታ ክርስቶስ ነው፡፡
ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉ፥ የምታደርጉትን ሁሉ በትጋት አድርጉት፥ ከጌታ የርስትን ብድራት እንድትቀበሉ ታውቃላችሁና፤ የምታገለግሉት ጌታ ክርስቶስ ነውና። ቆላስይስ 4፡23-24
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ጭንቀት #ልጅነት #ብርሃን #ጨው #ምስክርነት #ጌታክርስቶስ #ርስት #ብድራት #ስራ #የኑሮሃሳብ #የእለትእንጀራ #የባለጠግነትምቾት #አቅርቦት #መሰረታዊፍላጎት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

Wednesday, October 25, 2017

ልብ ይጠይቃል!


1.      ከእኛ የተለየውን ሰው ለመቀበል ልብ ይጠይቃል
ማንም መንገደኛ የሚመስለውንና የሚስማማውን ብቻ ይቀበላል፡፡ የሚወደውን ለመውደድ የሚጠላውን ደግሞ ለመጥላት ብዙ ጥረት አይጠይቅም፡፡ ከእርሱ የተለየውን ሰው ለመጣል ራስ ወዳድነት በቂ ነው፡፡ ከእኛ የተለየውን እንደ አካለ ብልት ለመቁጠርና ከማይመስለን ሰው ጋር ለአንድ ግብ ለመስራት እና እና ሌላውን ለመታገስ ልብ ይጠይቃል፡፡ ደካማ ሰዎች ሁሉንም እሺ የሚሉዋቸውን ፣ የማይጋፈጡዋቸውን ፣ የሚፈሩዋቸውንና እንዲለወጡ የማይገዳደሩዋቸውን ሰዎች በዙሪያቸው ይሰበስባሉ፡፡ እውነተኛ ሰዎች ሌላ የተደበቀ የስስት አላማ ስለሌላቸው ለመታረም ለመለወጥ ክፍት በመሆናቸው የሚያርሙዋቸውን ከእነርሱ የተለየተ ሃሳብ ያላቸውን እንዲያድጉና እንዲዘረጉ የሚያበረታቱዋቸውን ሰዎች ያከብራሉ፡፡  ሌሎችን የማያምን ራሱን ብቻ የሚያምን ሰው በህይወት እያነሰና እየቆረቆዘ ይሄዳል፡፡ ሁሉንም እንደሚያውቅ ሌላው የተሻለ እንደሚያውቅ የማያስብ ሰው እያነሰ ይሄዳል፡፡ ከእርሱ የተለየውን ሰው ውበት ማየት የሚችልና ሳያሻሽል የሚቀበለው ሰው ግን እየበዛ እየጠነከረ ይሄዳል፡፡ ከሰው ድካም ባሻገር ጥንካሬንና ውበትን ማየት መቻል ልብ ይጠይቃል፡፡  
የጸጋም ስጦታ ልዩ ልዩ ነው መንፈስ ግን አንድ ነው፤ አገልግሎትም ልዩ ልዩ ነው ጌታም አንድ ነው፤ አሠራርም ልዩ ልዩ ነው፥ ሁሉን በሁሉ የሚያደርግ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው። 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡1-3
ዓይን እጅን፦ አታስፈልገኝም ልትለው አትችልም፥ ወይም ራስ ደግሞ እግሮችን፦ አታስፈልጉኝም ሊላቸው አይችልም። 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡21
2.     ለሌላው ቅድሚያ መስጠትና ለራስ ብቻ አለማሰብ ልብ ይጠይቃል
ለሌላው ቅድሚያ መስጠት ክብር መሆኑን ማወቅ ትልቅነት ነው፡፡ ለራሱ ብቻ የሚያስብ ሰው ፣ ራሱ ላይ ብቻ የሚሰራ ሰው ፣ ለራሱ ብቻ የሚያከማች ሰው የተፈጠረበትን አላማ ስቶዋል፡፡ ሰው በእግዚአብሄር መወደዱን ሲያውቅ ሰዎችን ይወዳል ለሰዎች ቅድሚያን ይሰጣል፡፡ እግዚአብሄር እንዴት በፍቅር እና በርህራሄ እንደሚያየው የሚያውቅ ስው ሌሎችን በፍቅር ያያል፡፡ እግዚአብሄር አባቱ እንደሆነ የተረዳ ሰው ለሌሎች አባት ይሆናል፡፡ በእግዚአብሄር አባትነት የማይተማመን ሰው ግን የራሱን ፍሎጎት ብቻ ለማሙዋላት ሲደሳክር ዘመኑን ይፈጃል፡፡ የተፈጠረው ለሌላው ሰው በጎነት እንደሆነ ያለተረዳ ሰው ሳያካፋል ያለውን ነገር ሁሉ ራሱ ላይ ብቻ አፍስሶ ህይወቱን በከንቱ ያሳልፋል፡፡
ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፥ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር፤ እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፥ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ። ፊልጵስዩስ 2፡3-4
3.     በምድር ከፉክክር ነፅቶ እንደ እንግዳ መኖርና በዘላለም እይታ መኖር ልብ ይጠይቃል
የምድር ፉክክር የአላማ ጠላት ነው፡፡ የምድር ፉክክር በተንኮል ወደህይወታቸን እየገባ ከመንገዳችን የሚያስወጣ የህይወት አላማ ጠር ነው፡፡ የምድር ፉክክር ለእግዚአብሄር ሳይሆን ለሰው እንድንኖር የሚያታለል ክፉ በሽታ ነው፡፡ ይህን የምድር ፉክክር ጥሎ መውጣትና እግዚአብሄር ለእያንዳንዳችን በሰጠን ሃላፊነት ላይ ማተኮር ድፍረት ይጠይቃል፡፡ ማንም ሰው በምድር ፉክክር ውስጥ ገብቶ እንደሰው መሆን ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሄር ግን እንደ እግዚአብሄር ልጆች የእግዚአብሄርን ፅድቅና መንግስቱን እንድንፈልግ ጠርቶናል፡፡ ሰው ከምድር ፉክክር በራሱ ፈቃድ ካላቋረጠ እግዚአብሄር በህይወቱ ያስቀመጠውን አላማ መፈፀም አይችልም፡፡
ነገር ግን እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሥራ ይፈትን፥ ከዚያም በኋላ ስለ ሌላው ሰው ያልሆነ ስለ ራሱ ብቻ የሚመካበትን ያገኛል፤ ገላትያ 6፡4
4.     ከራስ አልፎ ለሚቀጥለው ትውልድ ማሰብ ልብ ይጠይቃል
ማንም ሰው ለዛሬ መኖር ይፈልጋል፡፡ ነገር ግን የዛሬን ደስታ አዘግይቶ ለሚመጣው ትውልድ መሰረት መጣል የተለየ መንፈስ ይጠይቃል፡፡ ዛሬ እንብላ ነገ እንሞታለን ማለት ቀላል ነው፡፡ የሚመጣው ትውልድ ሸክም በእኔ ትከሻ ላይ ነው ብሎ ለሚመጣው ትውልድ መልካም ምሳሌ ሆኖ ማለፍ ልብ ይጠይቃል፡፡ ከራስ ትውልድ አልፎ የእግዚአብሄርን ቃል ምሳሌነት ለሚመጣው ትውልድ ማድረስ የየእለት ጥረት ይጠይቃል፡፡  
እንደ ሰው በኤፌሶን ከአውሬ ጋር ከታገልሁ፥ ሙታንስ የማይነሡ ከሆነ፥ ምን ይጠቅመኛል? ነገ እንሞታለንና እንብላና እንጠጣ። 1ኛ ቆሮንቶስ 15፡32
5.     አለመጨነቅ ልብ ይጠይቃል፡፡
መጨነቅ ውጤት የሌለው ነገር ግን ከውጤት የሚያሰናክል ነገር ነው፡፡ እንድንጨነቅ የሚገፋፋ ብዙ ምክኒያቶች እያሉ አለመጨነቅ እምነት ይጠይቃል፡፡ ብዙ ሰዎች ሲጨነቁ ስራ የሰሩ ይመስላቸዋል፡፡ ብዙ ሰዎች መጨነቅ መብታቸው እንደሆነ ይሰማቸዋል፡፡ ብዙ ሰዎች የጭንቀትን ጉዳት አይረዱትይም፡፡ ጭንቀት ማቀድ ይመስላቸዋል፡፡ ጭንቀት ግን ማቀድ አይደለም፡፡ ጭንቀት ማለት ማድረግ የማንችለውን ነገር ለማድረግ መፍጨርጨር ነው፡፡ ጭንቀት ማለት የማናውቅውን ነገር አሁኑኑ ለማወቅ መላላጥ ነው፡፡ ጭንቀት ማለት ቆይተን የምንረዳውን ነገር አሁኑኑ ለመረዳት አእምሮን ማጣበብ ነው፡፡ ጭንቀት ማለት ወደፊታችን ምን እንደሚሆነ ካሁኑ አውቆ ለመጨረስ የመሞከር ከንቱ ድካም ነው፡፡ የሚያስጨንቀንን ነገር ለእኛ በሚያስበው በጌታ ላይ መጣል ልብ ይጠይቃል፡፡
እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት። 1ኛ ጴጥሮስ 5፡7 
6.      አለመፍረድ ልብ ይጠይቃል፡፡
ማንም መንገደኛ በማንም ላይ ሊፈርድ ይችላል፡፡ አለመፍረድና ይልቁንም ሌላውን መርዳት ልብ ይጠይቃል፡፡ አለመፍረድ ይልቁንም ራስን በሌላ ሰው ቦታ አድርጎ መመልከትና ለሌላው መራራት ልብ ይጠይቃል፡፡ አለመፍረድና ይልቁንም የሰዎችን ስሜት መረዳት ጥረት ይጠይቃል፡፡ አለመፍረድ ይልቁንም ወደሰዎች ደረጃ ወርዶ ማገዝ ምሳሌ መሆን ልብ ይጠይቃል፡፡ 
ወንድሞች ሆይ፥ ሰው በማናቸውም በደል ስንኳ ቢገኝ፥ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ እንደዚህ ያለውን ሰው በየውሃት መንፈስ አቅኑት፤ አንተ ደግሞ እንዳትፈተን ራስህን ጠብቅ። ገላትያ 6፡1
ወንድሞች ሆይ፥ እርስ በርሳችሁ አትተማሙ። ወንድሙን የሚያማ በወንድሙም የሚፈርድ ሕግን ያማል በሕግም ይፈርዳል፤ በሕግም ብትፈርድ ፈራጅ ነህ እንጂ ሕግን አድራጊ አይደለህም። ያዕቆብ 4፡11
7.     ጠላትን መውደድ የሚረግሙንን መባረክ ልብ ይጠይቃል፡፡
በራሱ ሃይል የማይታመን በእግዚአብሄር ብቻ የሚታመን ሰው ነው ጠላቱን የሚወድ፡፡  በእግዚአብሄር ፈራጅነት የሚታመን ሰው ብቻ ነው እራሱ የማይፈርደው፡፡ እግዚአብሄር እንደሚባርክ የተረዳ ሰው ብቻ ነው የሰውን እርግማን ተከትሎ የማይራገም፡፡ አስቀድሞ እንደተባረከ የሚያምን ብቻ ነው ሰውን የማይረግመው፡፡ ለእርሱ መባረክ የሌላው መረገም አንደማያስፈልግ የሚያምን ሰው ብቻ ነው ሰውን የማይራገም፡፡  
ክፉን በክፉ ፈንታ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ በዚህ ፈንታ ባርኩ እንጂ፥ በረከትን ልትወርሱ ለዚህ ተጠርታችኋልና። 1ኛ ጴጥሮስ 3፡9
እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፥ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ፤ እርሱ በክፎዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፥ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና። ማቴዎስ 5፡44-45
8.     ነገሮች ሁሉ በተቃራኒው ሲሰሩ እግዚአብሄርን ማመን ልብ ይጠይቃል፡፡
በሁኔታዎች ውስጥ ማረጋገጫ እንፈልጋለን፡፡ ነገር ግን በሁኔታዎች ውስጥ ማረጋገጫ ሲጠፋና የሚታየው ነገር ሁሉ እግዚአብሄር ከተናገረን ተቃራኒ ሲሆን እግዚአብሄርን ለማመን ልብ ይጠይቃል፡፡ ሌላው ሰው ሁኔታውን አይቶ እጅ ሲሰጥ ለመቀጠል ልብ ይጠይቃል፡፡
ዘርህ እንዲሁ ሊሆን ነው እንደ ተባለ፥ ተስፋ ባልሆነው ጊዜ የብዙ አሕዛብ አባት እንዲሆን ተስፋ ይዞ አመነ። የመቶ ዓመትም ሽማግሌ ስለ ሆነ እንደ ምውት የሆነውን የራሱን ሥጋና የሳራ ማኅፀን ምውት መሆኑን በእምነቱ ሳይደክም ተመለከተ፤ ሮሜ 4፡18-19
ሰዎች በፊታቸው እንበጣ ነን ሲል እንደ እንጀራ ይሆኑልናል ማለት ልብ ይጠይቃል፡፡
ነገር ግን በእግዚአብሔር ላይ አታምፁ፤ እንደ እንጀራ ይሆኑልናልና የምድሪቱን ሰዎች አትፍሩ፤ ጥላቸው ከላያቸው ተገፍፎአል፥ እግዚአብሔርም ከእኛ ጋር ነው፤ አትፍሩአቸው ብለው ተናገሩአቸው። ዘኍልቍ 14፡9
9.     ምንም ነገር የማይበቃ በሚመስልበት ያለኝ ይበቃኛል ማለት ልብ ይጠይቃል
የሰው ፍላጎት አያልቅም፡፡ እኛ ለፍላጎታቸን ገደብ ካላበጀንና በመሰረታዊ ፍላጎታችን ላይ ብቻ ካላተኮርን የማያልቅ ፈላጎታችንን ከማሙዋላት አልፈን እግዚአብሄርን ማገልገል አንችልም፡፡ ሰው ለመሰረታዊ ፍላጎቱ እግዚአብሄርን ካልታመነና ያለኝ ይበቃኛል ካላለ የማያባራውን የሰውን ፍላጎት ማሙዋላት ብቻ የህይወት ዘመን ይጠይቃል፡፡ አህዛብ ሌላ የህይወት አላማ ስለሌላቸው የመጀመሪያውም የመጨረሻውም ፍላጎታቸው የሚበላና የሚለበስ ነው፡፡ ሰው ያለኝ ይበቃኛል ባለ መጠን ብቻ ነው እግዚአብሄርን ማገልገል የሚችለው፡፡ ያለኝ አይበቃኝም ባለ መጠን ሁሉ ህይወቱ ይባክናል፡፡   
ይህን ስል ስለ ጉድለት አልልም፤ የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል ማለትን ተምሬአለሁና። ፊልጵስዩስ 4፡11
ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ማቴዎስ 6፡32-33
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ፀጋ #ምህረት #ቃል #መባረክ #አገልግሎት #መዋረድ #ፉክክር #መርካት #ፀጋ #እውቀት #ኢየሱስንተመልክተን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና #እምነት #ታላቅነት #ማገልገል #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ