ዓመት በራሱ አዲስ አይሆንም፡፡ ያው የተለመደው
ሰኞ ማክሰኞ ሮብ ሃሙስ አርብ ቅዳሜ እሁድ ነው፡፡ በቀኖቹ የምናደርጋቸው ነገሮች ናቸው አመቱን በእውነት አዲስ የሚያደርጉት፡፡
አመቱ በእርግጥ አዲስ አመት እንዲሆን አዲስ ሰው
ይጠይቃል፡፡ አዲስን ወይንጠጅ በአሮጌ አቁማዳ ውስጥ እንደማይጨምሩት አዲሱና አሮጌው እንደማይስማሙ ሁሉ ሰው በአዲስነት ካልተቀበለው
አዲስ አመት አይጠቅመውም፡፡ ሰው ህይወቱን በመለወጥ የሚኖር ከሆነ ደግሞ ሁሉም ቀን አዲስ ቀን ሁሉም ወር አዲስ ወር ሁሉም አመት
አዲስ አመት ይሆንለታል፡፡
በአረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚያኖር የለም፤ መጣፊያው ልብሱን ይቦጭቀዋልና፥ መቀደዱም የባሰ ይሆናል። በአረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን፥ አቁማዳው ይፈነዳል፥ የወይን ጠጁም ይፈሳል አቁማዳውም ይጠፋል፤ ነገር ግን አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ያኖረዋል፥ ሁለቱም ይጠባበቃሉ። ማቴዎስ 9፡16-17
አመቱን
አዲስ የሚያደርጉ አምስት ዋና ዋና ነገሮች፡-
1.
ንስሃ
የቀደመውን የክፋት ሃሳብ
መተው፡፡ ከእግዚአብሔር ቃል ውጭ የሆነውን አካሄድ መለወጥ፡፡ ከሃጢያት መንገድ ቀኝ ኋላ ዙር ብሎ መመለስ ህይወታችንን ያድሳል፡፡
በቀጣይነትም ከመፅሃፍ ቅዱስ ውጭ የምንኖረውን ኑሮ በንስሃ እና ሃሳብን በመለወጥ ስንለውጠው በንስሃ ህይወታችንን እናድሰዋለን፡፡
እንግዲህ
ኃጢአታችሁ እንዲደመሰስ ንስሐ ግቡ፣ ከመንገዳችሁም ተመለሱ፣ ከጌታም ዘንድ የመታደስ ዘመን ይመጣላችኋል፡፡ ሐዋርያት 3፡19
2.
አዲስ ፍጥረት መሆን
ሰው ክርስቶስን በመቀበል
አዲስ ፍጥረት ካልሆነ በስተቀር በየአመቱ አዲስ ይሆናል ብሎ ይጓጓል ጠብ የሚል አዲስ ነገር የለም፡፡ እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ
ያዘጋጀውን የመዳኛ መንገድ ሳይቀበሉ በአዲስ አመት አዲስን ነገር ለማግኘት መጓጓት ከንቱ ነው፡፡ የእግዚአብሄርን አላማ ስተው ነገሬ
አዲስ ይሆናል ማለት ዘበት ነው፡፡ እውነተኛው አዲስ ነገር በክርስቶስ የሚገኘው አዲስ ፍጥረትነት ነው፡፡ የሚጠቅመው አዲስ ፍጥረትነት
እንጂ በአዲስ አመት አዲስን ነገር መመኘት አይደለም፡፡
ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል። 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡17
በክርስቶስ ኢየሱስ አዲስ ፍጥረት መሆን ይጠቅማል እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና። ገላትያ 6፡15
3.
አእምሮን በእግዚአብሔር ቃል
ማደስ
ክርስቶስ ኢየሱስን
እንደአዳኝ ከተቀበልን በሁዋላ አእምሮዋችንን በእግዚአብሄር ቃል እውቀት መለወጥ አለብን፡፡ የተለወጠ አእምሮ የተለወጠን ህይወት
ያስገኛል፡፡ የአባታችንን ፈቃድ በምድር ላይ መፈፀም የምንችለው በቃሉ በተለወጠ አእምሮ ብቻ ነው፡፡
የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ። ሮሜ 12፡2
4.
አዲሱን ሰው መልበስ
በህይወታችንም በየጊዜው
የሚፈትነንን የአሮጌውን ሰው ማንነት አውልቀን በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረውን አዲሱን ሰው መልበስ ይገባናል፡፡
በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ፥ ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ። ኤፌሶን 4፡23-24
የፈጠረውንም ምሳሌ እንዲመስል እውቀትን ለማግኘት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችሁታል፤ ቆላስይስ 3፡10
5.
የእግዚአብሔርን ቃል ሰምቶ
ማድረግ
የእስራኤል ህዝብ የእግዚአብሔርን
ቃል ሰምተው ያደረጉበትና በዚያም ነፃ የወጡበትን ቀን ነበር የወሩ የመጀመሪያው ቀን እንዲሁም የአመቱ የመጀመሪያው ወር ይሁንላችሁ
የተባሉት፡፡
እግዚአብሔርም በግብፅ አገር ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ ይህ ወር የወሮች መጀመሪያ፤ የዓመቱም መጀመሪያ ወር ይሁናችሁ። ዘጸአት 12፡1-2
እግዚአብሔር ለእስራኤል
አዲስ አመትን የሰየመላቸው ነፃ የወጡበትን ቀን ነው፡፡ ነፃ የወጣችሁበት ቀን ሁሉ አዲስ ወራችሁ ነው፡፡ ነፃ የወጣችሁበት ወር ሁሉ አዲስ አመታችሁ ነው፡፡ እስራኤል የእግዚአብሄርን
የነፃነት መንገድ ተቀብለው የዳኑበትን ቀን ነው አዲስ አመት ይሁንላችሁ የተባለው፡፡
እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል አላቸው። ዮሃንስ 8፡32
#አዲስፍጥረት #አዲስ #መዋጀት #መዳን #ኢየሱስ #ጌታ
#እግዚአብሔር #ንስሃ #አቁማዳ #መታዘዝ #መሪነት #ቤተክርስትያን
#አማርኛ #ስብከት
#መዳን #መፅሃፍቅዱስ
#መጋቢ #እምነት
#ተስፋ #ፍቅር
#ጌታ #ሰላም
#ደስታ #አቢይ
#አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ
#እወጃ #መናገር
#ፅናት #ሰላም
ትግስት #ልጅ
No comments:
Post a Comment