Popular Posts

Follow by Email

Saturday, September 2, 2017

ሚስትህ በደስታ እንድትታዘዝህ የምትረዳበት መንገድ

ለእያንዳንዳችሁ በክርስቶስ ፍርሃት የተገዛችሁ ሁኑ። ሚስቶች ሆይ፥ ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁ ተገዙ፤ ክርስቶስ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደ ሆነ እርሱም አካሉን የሚያድን እንደ ሆነ ባል የሚስት ራስ ነውና። ዳሩ ግን ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትገዛ እንዲሁ ሚስቶች ደግሞ በሁሉ ለባሎቻቸው ይገዙ። ኤፌሶን 5፡21-24
ባል የቤተሰቡን ለመምራት አገልግሎት ተጠርቷል፡፡ ቤተሰቡን የመምራት ሃላፊነትና ሸክም የወደቀበት እንደመሆኑ መጠን ለባል የሚስት መታዘዝ እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ እግዚአብሄር የሰጠውን የራስነትን ሚና ለመጫወትና ቤተሰቡን እግዚአብሄር ወዳየለት የክብር ቦታ ለመምራት የሚስት በነገር ሁሉ መታዘዝ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ባል እግዚአብሄር የሰጠውን የመሪነት ሚና ለመጫወት  ከሚስት እንደመታዘዝ የሚያስፈልገው ነገር የለም፡፡ የባል እርካታ የቤተሰብ መሪነትን ሃላፊነት መወጣት እንደመሆኑ መጠን እንደ ሚስት አለመታዘዝ ተስፋ የሚያስቆርጠው ነገር የለም፡፡ እግዚአብሄር የሰጠኝን የመሪነት አገልግሎቴን ስፈፅም ሚስቴ እንዴት ነው የምትታዘዝልኝ የሚለውን ጥያቄ መመለስ ወሳኝ ነው፡፡  
በክርስትና ስለምትበላውና ስለምትጠጣው መጨነቅ ካልፈልግክ አስቀድመህ የእግዚአብሄርን ፅድቅና መንግስቱን ፈልግ ሌላ ሁሉ ይጨመርልሃል፡፡
ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ማቴዎስ 6፡31፣33
ክርስትና አገልግሎት ነው፡፡ ክርስትና መስጠት ነው፡፡ ክርስትና መዝራት ነው፡፡ ያገለገልከው ይንከባከብሃል፡፡ የሰጠኸው ይሰጥሃል፡፡ የዘራህበት ያበቅልልሃል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ ሚስቴ እንዴት ነው የምትገዛልኝ ብሎ መጨነቅና መጨቅጨቅ ሚስትህ በደስታ እንድትታዘዝህ ትክክለኛው መንገድ አይደለም፡፡ ሚስትህ እንድትታዘዝህ ያንተ የራስህ የመውደድ ሃላፊነት ላይ ከማተኮር የተሻለ መንገድ የለም፡፡ እግዚአብሄር በህይወትህ በሰጠህ የመውደድ ሃላፊነት ላይ ስታተኩር እግረ መንገድህን ሚስትህ እንድትታዘዝህ እያመቻቸህላት ነው፡፡ ለቤተሰቡ በምታደርገው የመውደድ ሃላፊነትህ ላይ ተጠንቀቅ ሌላው ነገር ለራሱ ይጠነቀቃል፡፡ ትዳሬ ከእኔ ምን ይፈልጋል በሚለው ላይ ስታተኩር ሃላፊነትህን እንድትወጣ የሚያስችልህን የሚስትህን መታዘዝ ታተርፋለህ፡፡  
ሚስት ትገዛ ተብሎ ተፅፏል የሚለው ጭቅጭቅ ልክ እንደ ብሉይ ኪዳን ህግ መረጃ ይሰጥ ይሆናል እንጂ ትእዛዙን ለመፈፀም የሚያስችል ጉልበት አይሆንም፡፡
ፊደል ይገድላልና መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል። 2ኛ ቆሮንቶስ 3፡6
ለቤተሰብ አንድነት እና ጥንካሬ ለባል የሚስት የመታዘዝን አስፈላጊነት የምትክድ ሴት አትገኝም፡፡ ባልን መታዘዝ ትክክል እንደሆነ ባላቸውን በሚታዘዙ ሰዎች የሚቀኑ ሴቶች ህያው ምስክር ናቸው፡፡ ባልን መታዘዝ የእግዚአብሄርን መታዘዝ በመሆኑ ባልዋን በመታዘዝ ጌታን ማስደሰት የማትፈልግ ሚስት አትገኝም፡፡ ባልን መታዘዝ እግዚአብሄር ለቤተሰብ ጥቅም ያስቀመጠውን ስልጣንን እንደመታዘዝ አስፈላጊ እንደሆነ የማትረዳ ሚስት አትገኝም፡፡ 
ሰውን መታዘዝ አንዳንዴ ሊቀል ይችላል፡፡ ሰውም ሁልጊዜ መታዘዝ ግን ቀላል አይደለም፡፡
ይህን ቀላል ያልሆነውን መታዘዝ ሚስትህ እንድታደርገው አንተም እንደባል የምታደርገው አስተዋፅኦ አለ፡፡ ትዳር የህብረት ስራ ነው፡፡ ሚስትህ ደስ ብሎዋት እንድትታዘዝ የምታግዛት አንተ ነህ፡፡ የሚስት መታዘዝ የሚስት ብቻ ሃላፊነት ቢሆንም ሚስትህ ደስ ብሎዋት እንድትታዘዝ አንተም የምታበረክተው አስተዋፅኦ እንዳለ አለመዘንጋት ይገባል፡፡ ያም ሆነ ይህ ሚስት መታዘዝ ቢኖርባትም መታዘዝዋን ለማቅለል ባል የሚወስደው ወሳኝ እርምጃ አለ፡፡
ሚስትህን ስትወዳት ሚስትህ እንድትታዘዝህ በተዘዋዋሪ እየጠየቅካት ነው፡፡ ሚስትህን ስትወድ ሚስትህ እንድትታዘዝህ እየረዳሃት ነው፡፡ ሚስትህ ስትወዳት እንድትታዘዝህ ሸክሟን እያገዝካት ነው፡፡ ሚስትህን ስትወድ እንድትታዘዝህ እያመቻቸህላትና እያቀለልክላት ነው፡፡
እግዚአብሄርን በእውነት ማስደሰት የምትፈልግ ሚስትህ ለእርስዋ ያለህን ፍቅርና መስዋእትነት ስታይ አንተን መታዘዝ ከአቅም በላይ ከባድ ሸክም አይሆንባትም፡፡ ሚስትህ ፍቅርህን ስታይ አንተን ለማስደሰት የማትሄደው መንገድ አይኖርም፡፡
ኢየሱስም እኛ እንድንታዘዘው በመጀመሪያ ያደረገው እኛን መውደድ ነው፡፡ ኢየሱስ እንድንታዘዘው የጠየቀው በፍቅር ነው፡፡ ኢየሱስ ራሳችንን እንድንሰጥ ከመጠየቁ በፊት ራሱን ሰጠን፡፡ ፍቅሩን በተረዳን ቁጥር መታዘዝ እየቀለለን ይሄዳል፡፡ ፍቅሩን በተረዳነውና ባወቅነው መጠን ምን ላድርግለት ፣ ምን ልሁንለንት ምኔን ልስጠው እንላለን፡፡  
እርሱ አስቀድሞ ወዶናልና እኛ እንወደዋለን። 1ኛ ዮሐንስ 4፡19
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ህይወት #ጋብቻ #ትዳር #ባል #ሚስት #ፍቅር #መውደድ #መታዘዝ #ይተዋል #ይጣበቃል #አንድስጋ #እውነት #ትህትና #ትንሳኤ #ህይወት #ወንጌል #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ  #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

No comments:

Post a Comment