ሰውን ሁሉ የፈጠረው እግዚአብሔር ነው፡፡ ሰውን እግዚአብሔር የፈጠረው በመልኩና በአምሳሉ ነው፡፡ እግዚአብሔር ሰውን በመልኩና በአምሳሉ የፈጠረው ሰው የእግዚአብሔር የቤተሰቡ አባል እንዲሆንና ከእግዚአብሔር ጋር ህብረት እንዲኖረው ነው፡፡ ሰው ከእርሱ ጋር ለዘላለም በአባትና በልጅ ግንኙነት እንዲኖር ስለፈለገ እግዚአብሔር ሰውን በመልኩና በአምሳሉ ፈጠረው፡፡ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ያለው የአባትና ልጅ ግንኙነት እንዳይበላሽ ስለፈለገ ሰውን ካልተፈቀደለት ፍሬ እንዳይበላና እንዳይሞት አዘዘው፡፡
እግዚአብሔር አምላክም ሰውን እንዲህ ብሎ አዘዘው፦ ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና። ዘፍጥረት 2፡16-17
ሰው ግን በሰይጣን አማካኝነት አትብላ የተባለውን ፍሬ በላ፡፡ ሰው በበላም ቀን ሞተ፡፡ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር የነበረው የአባትነትና የልጅነት ግንኙነት ተቋረጠ፡፡ ሰው በመንፈሱ ከእግዚአብሔር ተለየ ሞተም፡፡
ሰውን ሁሉ የፈጠረው እግዚአብሔር እንጂ ሰይጣን የፈጠረው ሰው የለም፡፡ ሰይጣን ሰውን አሳመፀ፡፡ ያመፀውም የሰው ልጅ እንኳን የእግዚአብሔር ፍጥረት ነው፡፡
የእግዚአብሔር ፍጥረት መሆን ማለት ግን የእግዚአብሔር ልጅ መሆን ማለት አይደለም፡፡ በምድር ላይ የምታዩት ሰው ሁሉ የእግዚአብሔር ፍጥረት ነው፡፡ በምድር ላይ የምታዩት ሰው ሁሉ ግን የእግዚአብሔር ልጅ ላይሆን ይችላል፡፡
የእግዚአብሔር ልጅ ለመሆን መመዘኛ አለው፡፡ መመዘኛው ስራ አይደለም፡፡ መመዘኛው እምነት ብቻ ነው፡፡ መመዘኛው በእምነት የኢየሱስን የመስቀል ላይ እዳ መክፈል መቀበል ነው፡፡
ኢየሱስ ለሰው ልጆች ሃጢያት ሁሉ በመስቀል ላይ ስለሞተ የእግዚአብሔር ፍጥረት የሆነ ሰው ሁሉ መመዘኛውን ካሟላ የእግዚአብሔር ልጅ መሆን ይችላል፡፡ ኢየሱስ ስለሃጢያታችን ስለሞተ ብቻ ሰው ሁሉ የእግዚአብሔር ልጅ አይሆብንም፡፡ ኢየሱስ የሃጢያታችንን እዳ ሁሉ ስለከፈለ ኢየሱስ የከፈለው ለእኔ ነው ብሎ የኢየሱስን አዳኝነት የተቀበለ ሁሉ እግዚአብሔር ልጅ ይሆናል፡፡
ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ ዮሃንስ 1፡12
የእግዚአብሔ ፍጥረት የሆነ ሰው ኢየሱስ ስለሃጢያቱ በመስቀል ላይ የከፈለለትን ለእኔ ነው ብሎ ባይቀበል ግን ለዘላለም ይጠፋል፡፡ ሰው ኢየሱስን ባይቀበል የዘላለም ቅጣት ይጠብቀዋል፡፡
በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም። ዮሃንስ 3፡36
የእግዚአብሔር ፍጥረት የሆኑ ሁሉ ኢየሱስን እንደ አዳኝና ጌታ አድርጎ በመቀበል ብቻ የእግዚአብሔር ልጅ መሆን ይችላሉ፡፡ እግዚአብሔር ወደ ቤተሰቡ ሊቀበላቸው ይፈልጋል ኢየሱስን ተቀበሉ እንላለን፡፡
የእግዚአብሄር ልጅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ ይህን ፀሎት አብሮ ይፀልይ፡፡
እግዚአብሔር ሆይ ስለላክልኝ ቃል አመሰግንሃለሁ፡፡ ልጅህን ኢየሱስ ስለሃጢያቴ በመስቀል ላይ ስለተሰቀለልኝና ስለሞተልኝ አመሰግንሃለሁ፡፡ ኢየሱስ በሶስተኛው ቀን ከሙታን እንደተነሳ አምናለሁ፡፡ እንደሁም ኢየሱስ ጌታ እንደሆነ እመሰክራለሁ፡፡ ኢየሱስ ጌተ ነው፡፡ እግዚአብሔር ሆይ ልጅህ አድርገህ ስለተቀበልከኝ አመሰግንሃለሁ፡፡ በኢየሱስ ስም፡፡ አሜን ፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ልጅነት #ደህንነት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ቃል #ፍጥረት #ልጅነት #ስራ #እምነት #አምባሳደር #ብርሃን #ጨው #ልጅነት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ
No comments:
Post a Comment