Popular Posts

Monday, September 18, 2017

ሰዎች ለምን መዳን አይፈልጉም ?

ብዙ ሰዎች ጌታ ኢየሱስ ስለሃጢያታቸው በመስቀል ላይ የከፈለላቸውን ዋጋ ለእኔ ነው በማለት ጌታን ለመከተል ይወስናሉ፡፡ እግዚአብሔርም በኢየሱስ ያዘጋጀውን የመዳኛ መንገድ ስለተቀበሉ ልጆች አድርጎ ወደ ቤተሰቡ ይቀበላቸዋል፡፡
አንዳንድ ሰዎች ግን ቢያንስ ቢያንስ እስካሁን ኢየሱስን አልተቀበሉም፡፡ ሰዎች ኢየሱስን ተቀብለው የማይድኑበትን ምክኒያቶች እንመልከት፡-
1.      ሰዎች የደህንነት ነፃ ስጦታነት ስለማይረዱት ነው፡፡
እግዚአብሄር በነፃ ሊያድናችሁ ይፈልጋል ሲባሉ በጣም የተጋነነ ከእውነት የራቀ አባባል ይመስላቸዋል፡፡ ስለዚህ ነፃውን ስጦታ ከመቀበል ይልቅ በራሳቸው ስለሃጢያታቸው ዋጋን ለመክፈል መልካምን ለማድረግ በዚያም ደህንነትን ለማግኘት ይጥራሉ፡፡ ሃጢያተኛ ሰው በቅዱሱ በእግዚአብሄ ፊት መልካምን ነገር በማድረግ ስለሃጢያቱ ዋጋን ሊከፍል አይችልም፡፡ ሰዎች ግን በራሳቸው ለሃጢያታቸው ዋጋ ለመክፈል ከፈለጉ ለዘላለም ከእግዚአብሄር በመለያየት ነው የሚከፍሉት፡፡ ስለሃጢያት ሊከፍል የሚችለው ሰው ሃጢያት ያልሰራ ብቻ ነው፡፡ ሃጢያት የሌለበት ኢየሱስ ስለሃጢያታችን ፈፅሞ ከፍሎዋል፡፡ እኛ መክፈል አንችልምም አይገባንምም፡፡ እኛ ማድርግ የሚገባን በእምነት ይህንን ስጦታ መቀበል ብቻ ነው፡፡
ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም። ኤፌሶን 2፡8-9
2.     አንዳንድ ሰዎች የደህንነትን መልእክት የማይቀበሉት ለደህንነት የሃይማኖት ስርአትን መፈፀም የሚበቃ ስለሚመስላቸው ነው፡፡
አንዳንድ ሰዎች እግዚአብሄር በክርስቶስ ያዘጋጀውን የመዳኛ መንገድ የማይቀበሉት የአንድ ሃይማኖት ተከታይ መሆን የሚያድን ስለሚመስላቸው ነው፡፡ እውነተኛ ሃይማኖት ኢየሱስ በመስቀል ላይ የከፈለውን የሃጢያት መስዋእትነት የሚሰብክ ነው፡፡ ያንን እግዚአብሄር ያዘጋጀውን ብቸኛ የመዳኛ መንገድ መቀበል እንጂ የሃይማኖት ስርአትን መፈፀም ብቻ ማንንም ሊያድን አይችልም፡፡ የሃይማኖትን ስርአት መፈፀም የሚያድን ቢሆን ኖሮ ኢየሱስ ወደ ሃይማኖተኞች መጥቶ ስለ ዳግመኛ መወለድ አይሰብክላቸውም ነበር፡፡
ኢየሱስም መልሶ፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው። ዮሃንስ 3፡3
በየትኛውም ሃይማኖት ውስጥ ያለን ሰው ኢየሱስ ካላዳነው የየትኛውም ሃይማኖት ተከታይ መሆኑ በራሱ አያድነውም፡፡ የኢየሱስን አዳኝነት ከመቀበል ውጭ የየትኛውም ሃይማኖት ተከታይነት ለመዳን በቂ አይደለም፡፡ 
3.     አንዳንድ ሰዎች መዳን የማይፈልጉት ሃጢያትን ስለሚወዱ ነው፡፡
ሰዎች ኢየሱስን መከተል የማይፈልጉት ሃጢያትን ስለሚወዱ ነው፡፡ በሃጢያት የሚገኝ ጊዜያዊ ደስታ የዘላለም ህይወትን ያሳጣቸዋል፡፡ በሃጢያት ስለሚገኝ ደስታ በጌታ ኢየሱስ የሚገኘውን ሰላምና እረፍት ይለውጡታል፡፡ ሰዎች ኢየሱስን እንዲቀበሉ ሲነገራቸው ብዙ ምክኒያት የሚዘረዝሩት በጨለማ ስለሚመላለሱና ወደብርሃን መውጣት ስለማይፈልጉ ነው፡፡
ብርሃንም ወደ ዓለም ስለ መጣ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለ ወደዱ ፍርዱ ይህ ነው። ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፥ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም፤ ዮሃንስ 3፡19-20
4.     አንዳንድ ሰዎች መዳን የማይፈልጉት በመልካም ባህሪያቸው ስለሚመኩ ነው
አንዳንድ ሰዎች የደህንነትን መልእክት የማይቀበሉት ደህንነት የባህሪ ለውጥ ስለሚመስላቸው ነው፡፡ "እኔ በተቻለ ህሊናዬን ጠብቄ እኖራለሁ ስለዚህ ምንም አያስፈልገኝም" ብለው ያስባሉ፡፡ ነገር ግን ደህንነት የባህሪ ለውጥ ሳይሆን የመጥፋትና የመዳን ጉዳይ ነው፡፡ ደህንነት ጥሩ ሰው የመሆን ጉዳይ ሳይሆን ከእግዚአብሄር ለዘላለም መለያየትና ከእግዚአብሄር ጋር   የመታረቅ ጉዳይ ነው፡፡ ደህነንነት የመልካም ስነምግባር ጥሪ ሳይሆን የሞትና የህይወት ምርጫ ጥሪ ነው፡፡
ልጁ ያለው ሕይወት አለው፤ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም። 1ኛ ዮሃንስ 5፡12
ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን፥ ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን፤ ሮሜ 5፡10
በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም። ዮሃንስ 3፡36
5.     አንዳንድ ሰዎች መዳን የማይፈልጉት በቂ ጊዜ ያላቸው ስለሚመስላቸው ነው፡፡
አንዳንድ ሰዎች መዳን በኢየሱስ ብቻ እንዳለ ያምናሉ ነገር ግን በሌሎች ነገሮች በጣም ባተሌ ከመሆናቸው የተነሳ የደህንነታቸውን ነገር ሁሌ ለሌላ ጊዜ ያስተላልፉታል፡፡ አፍላ ህይወታቸውን ለጌታ መስጠት ይሳሳሉ፡፡ ህይወትን ለጌታ ከመስጠት በላይ አስፈላጊ ነገር እንዳለ ያስባሉ፡፡ ለእግዚአብሄር የህይወታቸውን ጭላጭ ሊሰጡት ይቀጥራሉ፡፡
ሌላውንም፦ ተከተለኝ አለው። እርሱ ግን፦ ጌታ ሆይ፥ አስቀድሜ ልሂድና አባቴን እቀብር ዘንድ ፍቀድልኝ አለ። ኢየሱስም፦ ሙታናቸውን እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው፤ አንተስ ሄደህ የእግዚአብሔርን መንግሥት ስበክ አለው። ደግሞ ሌላው፦ ጌታ ሆይ፥ እከተልሃለሁ፤ ነገር ግን አስቀድሜ ከቤቴ ሰዎች እንድሰናበት ፍቀድልኝ አለ። ኢየሱስ ግን፦ ማንም ዕርፍ በእጁ ይዞ ወደ ኋላ የሚመለከት ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይደለም አለው። ሉቃስ 9፡59-62
በተወደደ ሰዓት ሰማሁህ በመዳንም ቀን ረዳሁህ ይላልና፤ እነሆ፥ የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤ እነሆ፥ የመዳን ቀን አሁን ነው። 2 ቆሮንቶስ 6፡2
ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤ ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና። ሮሜ 10፡9-10
ፀሎት
አሁን ኢየሱስን ለመቀበል ከወሰንክ ይህንን ፀሎት ከልብህ ወደ እግዚአብሔር ፀልይ
እግዚአብሄር ሆይ የመዳንን እውቀት ስለላክልኝ አመሰግንሃለሁ፡፡ ሃጢያተኛ እንደሆንኩ አውቃለሁ፡፡ በሃጢያቴ ካንተ እንደተለሁ አውቃለሁ፡፡ ኢየሱስ ስለሃጢያቴ በመስቀል ላይ በመሞት የሃጢያቴን ዋጋ ሁሉ እንደከፈለ አውቄያለሁ፡፡ ኢየሱስ በሶስተኛው ቀን ሞትን ድል አድርጎ እንደተነሳ አምናለሁ፡፡ ኢየሱስ ጌታ ነው፡፡ ልጅህ አድርገህ ወደ ቤተሰብህ ስለተቀበልከኝ አመሰግንሃለሁ፡፡ በኢየሱስ ስም፡፡ አሜን፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ልጅነት #ደህንነት #መልካምስራ #መልካምምግባር #ሞት #አላማመሳት #ሐጢያት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ቃል #ፍጥረት #ልጅነት #ስራ #እምነት #አምባሳደር #ብርሃን #ጨው #ልጅነት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment