ትንቢት ፍፁም አይደለም፡፡ ነቢያትም ፍፁም አይደሉም፡፡ ፍፁሙ የእግዚአብሔር ፈቃድ ግን ሊሳሳት በሚችል ሰው ውስጥ ነው የሚተላለፈው፡፡ እግዚአብሔር ግን ከማይተላለፍ ፍፁም ባልሆነ ሰው ውስጥ ቢተላለፍ ይሻላል ብሎ ነው ነቢያትን የሰጠን፡፡
በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር መንፈስ የሚኖረው በነቢያት በካህናትና በነገስታት ላይ ብቻ ስለነበረ የእግዚአብሔር ህዝብ ቃሉን ከመቀበል ውጭ በውስጡ ባለው መንፈስ ትንቢቱን የሚመዝንበት እድል አልነበረውም፡፡
ሰዎች በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ቃል የሚገኝበት ነቢይ እዚህ ይኖራል? በማለት ችግር ሲገጥማቸው ነቢያትን ይፈልጉ ነበር፡፡
በአዲ ኪዳን ግን መንፈስ ቅዱስ በአማኞች ሁለ ውሰጥ አለ፡፡ እንዲያውም በውስጡ መንፈስ ቅዱስ ከሌላ አማኝ አይደለም፡፡
የክርስቶስ መንፈስ የሌለው ከሆነ ግን ይኸው የእርሱ ወገን አይደለም። ሮሜ 8፡9
ትንቢትን የመፈተን ትልቁ ሃላፊነት ያለው እኛ ጋር ነው፡፡ ነቢይ ስላሳሳተኝ ነው ብለን የምንሰጠው ሰበብ ሊኖር አይችልም፡፡
ነቢይ በጉባኤ ሲናገር ሌሎች ነቢያት የሚናገረውን ነገር እንዲፈትኑት መፅሃፍ ቅዱስ ያስተምራል፡፡
ነቢያትም ሁለት ወይም ሦስት ሆነው ይናገሩ ሌሎችም ይለዩአቸው፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 14፡29
በጉባኤም ይሁን በግል የተሰጡትን ትንቢቶች መቀበል ወይም አለመቀበል ሃላፊነቱ ያለው አማኙ ጋር ነው፡፡ እኔ ታላቅ ነቢይ ነኝና የምናገረውን ሁሉ ሳትጠራጠረሩ ዋጡ የሚል ነቢይ እኛም አማኞች እያንዳንዳችን እንደ ነቢይ የምንለይበት መንፈስ እንዳለን ማወቅ ይገባዋል፡፡
ትንቢት የሚፈተሽባቸው ስድስት መንገዶች
1. ትንቢት ከእግዚአብሔር ቃል ጋር መስማማት አለበት፡፡
ትንቢት ከእግዚአብሔር ቃል ከተቃረነ በቃሉ ላይ ከጨመረ ወይም ከቀነሰ ስህተት መሆኑን አውቆ መጠንቀቅ ይገባል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ሰባት ጊዜ የተፈተነ ራሱ የትንቢት ቃል ነው፡፡ እያንዳንዱ ትንቢት ከተፈተነው ከእግዚአብሔር ቃል ካለተስማማ ትንቢቱ ተሳስቷል ያሳስታልም፡፡
ወንድሞች ሆይ፥ ስለ አንዱ በአንዱ ላይ አንዳችሁም እንዳይታበዩ፦ ከተጻፈው አትለፍ የሚለውን በእኛ ትማሩ ዘንድ፥ ይህን በእናንተ ምክንያት ስለ ራሴና ስለ አጵሎስ እንደ ምሳሌ ተናገርሁ። 1ኛ ቆሮንቶስ 4፡6
ማንም ሰው የሚናገር ቢሆን፥ እንደ እግዚአብሔር ቃል ይናገር፤ 1ኛ ጴጥሮስ 4፡11
2. ትንቢት ከመንፈሳችን ምሪት ጋር መስማማት አለበት
አንዳንድ ጊዜ ትንቢት ከአጠቃላይ የእግዚአብሔር ምክር ጋር ተስማምቶ ነገር ግን አግዚአብሔር በጊዜው ያልሰጠን ሬማ ቃል አይደለም ይሆናል፡፡ ምንም እንኳን ነቢዩ ከመፅሃፍ ቅዱስ ጠቅሶ ቢተነብይም ለጊዜው እግዚአብሔር ለእኛ የሰጠን መልእክት መሆኑን ማመረጋገጥ አለብን፡፡ ነቢይ ለግል ህይወታችን የሚናገረው ነገር ጉሉ እግዚአብሔር ለግላችን በመንፈሱ የሚያተረጋገጥልን ካልሆነ አለመቀበል እንችላለን፡፡ እግዚአብንሔርን በልባችን ለግላችን ያልመራንን ነቢዩ ስለተናገረ ብቻ ለምን አልፈፀሙትም አይለንም፡፡
በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና። የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል። ሮሜ 8፡14፣16
እናንተም ከቅዱሱ ቅባት ተቀብላችኋል፥ ሁሉንም ታውቃላችሁ። እናንተስ ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በእናንተ ይኖራል፥ ማንም ሊያስተምራችሁ አያስፈልጋችሁም፤ ነገር ግን የእርሱ ቅባት ስለ ሁሉ እንደሚያስተምራችሁ፥ እውነተኛም እንደ ሆነ ውሸትም እንዳልሆነ፥ እናንተንም እንዳስተማራችሁ፥ በእርሱ ኑሩ። 1ኛ ዮሐንስ 2፡20፣27
3. ትንቢት የሰው ፈቃድ መሆን የለበትም
ትንቢት የሚናገረው ከራሱ ፍላጎት ብቻ ከሆነ ትንቢቱ ትክክል አይሆንም፡፡ ትንቢትን የሚናገረው ሰው ከኪሱ አውጥቲ እንደሚሰጥ ከሆነ ትንቢቱ እውነተኛ ላይሆን ይችላል፡፡ ትንቢት በሰው ፈቃድ አይመጣም፡፡
እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፦ ነቢያቱ ውሸት በስሜ ትንቢት ይናገራሉ፤ አላክኋቸውም፥ አላዘዝኋቸውም፥ አልተናገርኋቸውም፤ የውሸቱን ራእይ ምዋርትንም ከንቱንም ነገር የልባቸውንም ሽንገላ ይሰብኩላችኋል። ኤርሚያስ 14፡14
የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ትንቢት የሚናገሩላችሁን የነቢያትን ቃል አትሰሙ፤ ከንቱነትን ያስተምሩአችኋል፤ ከእግዚአብሔር አፍ ሳይሆን ከገዛ ልባቸው የወጣውን ራእይ ይናገራሉ። ኤርምያስ 23፡16
ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ። 2ኛ ጴጥሮስ 1፡21
4. ትንቢት መፈፀም አለበት
ትንቢቱ ካለተፈፀመ ትንቢቱን እንደተሳሳተ እንረዳለን፡፡ በተለይ በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ህዝብ ትንቢትን በመንፈስ የመለየት ምንም እድል ስላልነበረው የትንቢትን እውነተኝነት የሚያረጋግጡት መፈፀሙንና አለመፈፀሙን ጠብቀው አይተው ነበር፡፡ ነቢይ እንደማንም ሰው ሊሳሳት ይችላል፡፡ ነቢዩም ትንቢይ ካመጣ ደግሞ ተሳስቻለሁ ብሎ ይቅርታ መጠየቅ አለበት፡፡
በልብህም፦ እግዚአብሔር ያልተናገውን ቃል እናውቅ ዘንድ እንዴት ይቻለናል? ብትል፥ ነቢዩ በእግዚአብሔር ስም በተናገረ ጊዜ የተናገረው ነገር ባይሆን ባይመጣም፥ ያ ነገር እግዚአብሔር ያልተናገረው ነው፤ ነቢዩ በድፍረቱ ተናግሮታል እርሱን አትፍራው። ዘዳግም 18፡21-22
5. የነቢዩን አጠቃላይ የህይወት ባህሪ በመመልከት
ሰው ነቢይ ነኝ ቢል ነገር ግን ገንዘብን መውደድ የተሞላ ከሆነ እግዚአብሔር ለነቢይነት ቢጠራውም አንኳን ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ስር ነው እንደሚል ነቢይነቱን ለራሱ የግል ጥቅም ለክፋት ሊጠቀምበት ስለሚችል ከዚህ አይነት ሰው ትንቢት መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡
የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውሥጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኵላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ። ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። ከእሾህ ወይን ከኩርንችትስ በለስ ይለቀማልን? ማቴዎስ 7፡15-16
6. የነቢዩን አምልኮ እና ለእግዚአብሔር ያለውን መሰጠት በመመልከት
በብሉይ ኪዳን እንዲያውም ሰው የተናገረው እንኳን ቢፈፀም እንኳን ነገር ግን ባእዳን አማልክትን እናመልክ ካለ ስቷል፡፡ ከተፈጥሮ በላይ ሃይል ነው ማለት ከእግዚአብሔር ብቻ ነው ማለት አይደለም፡፡ ከተፈጥሮ በላይ የሆነ ነገር ግን የእግዚአብሔር መንፈስ ግን ያልሆነ ሃይል በአለም ላይ አለ፡፡
በመካከልህም ነቢይ ወይም ሕልም አላሚ ቢነሣ፥ ምልክትም ተአምራትም ቢሰጥህ፥ እንደ ነገረህም ምልክቱ ተአምራቱም ቢፈጸም፥ እርሱም፦ ሔደን የማታውቃቸውን ሌሎች አማልክት እንከተል እናምልካቸውም ቢልህ፥ አምላካችሁን እግዚአብሔርን በፍጹም ልባችሁ በፍጹምም ነፍሳችሁ ትወድዱት እንደ ሆነ ያውቅ ዘንድ አምላካችሁ እግዚአብሔር ሊፈትናችሁ ነውና የዚያን ነቢይ ቃል ወይም ያን ሕልም አላሚ አትስማ። ዘዳግም 13፡1-3
ወዳጆች ሆይ፥ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፥ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደ ሆነ መርምሩ፤ ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና። 1ኛ ዮሐንስ 4፡1
እግዚአብሔር በነቢያት ቢጠቀምም እግዚአብሔር አብዛኛውን ጊዜ የሚናገረው በልባችን ነው፡፡ እግዚአብሔር በልባችን እንደሚናገረን አስተማማኝ መልእክት የለም፡፡ እግዚአብሔር በግላችን እንዲናገረን ጊዜ እንስጠው፡፡ እግዚአብሔር በነቢያቱ የሚናገረንን አንናቅ ነገር ግን ሁሉን እንፈትን መልካሙን እንያዝ፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #የመንፈስፍሬ #ቅባት #መንፈስቅዱስ #የእግዚአብሔርመንፈስ #መሪ #ቤተመቅደስ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ነቢያት #ነቢይ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ
No comments:
Post a Comment