ሕግን ብታደርግ መገረዝስ ይጠቅማል፤ ሕግን ተላላፊ ብትሆን ግን መገረዝህ አለ መገረዝ ሆኖአል። እንግዲህ ያልተገረዘ ሰው የሕግን ሥርዓት ቢጠብቅ አለመገረዙ እንደ መገረዝ ሆኖ አይቈጠርለትምን? ከፍጥረቱም ያልተገረዘ ሕግን የሚፈጽም ሰው የሕግ መጽሐፍና መገረዝ ሳለህ ሕግን በምትተላለፈው በአንተ ይፈርድብሃል። በግልጥ አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ አይደለምና፥ በግልጥ በሥጋ የሚደረግ መገረዝም መገረዝ አይደለምና፤ ዳሩ ግን በስውር አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ ነው፥ መገረዝም በመንፈስ የሚደረግ የልብ መገረዝ ነው እንጂ በመጽሐፍ አይደለም፤ የእርሱ ምስጋና ከእግዚአብሔር ነው እንጂ ከሰው አይደለም። ሮሜ 2፡25-29
መፅሃፍ ቅዱስ ስለ ስጋ እና ስለልብ መገረዝ ይናገራል፡፡ በብሉይ ኪዳን ስጋቸውን ስለሚገረዙ ሰዎች ነገር ግን ልባቸው ስላልተገረዘ የእግዚአብሄርን ቃል ስለማይጠብቁ ሰዎች ይናገራል፡፡ ሰው ልቡ ካልተገረዘና በእግዚአብሄር መንገድ ካልሄደ የስጋው መገረዝ ለሰው ምንም አይጠቅመውም፡፡ ነገር ግን ስጋው ያልተገረዘ ልቡ የተገረዘ ሰው እግዚአብሄርን ያስደስተዋል፡፡ እግዚአብሄር የውጭውን ስርአት ሳይሆን የልብን ነገር ነው የሚመለከተው፡፡
አሁን ማንሳት የፈለግኩት ስለግርዘት ሳይሆን ሰለመስቀል ነው፡፡ የመስቀልን በአል በየአመቱ በደማቅ ሁኔታ ብናከብር ነገር ግን የመስቀል ህይወት ከሌለን ምንም አይጠቅመንም፡፡ ይልቁንም የመስቀልን በአል የማያከብር ነገር ግን መስቀልን በህይወቱ የሚለማመድ ሰው ይሻላል፡፡
የመስቀልን በአል በየአመቱ ብናከብር የመስቀል ቃል በህይወታችን ከሌለ ምንም አይጠቅመንም፡፡ የመስቀል ቅርፅ በአንገታችን ብናስር የመስቀል ህይወት ግን በልባችን ከሌለ ምንም አይጠቅመንም፡፡
1. መስቀል ኢየሱስ የሞተበት ነው፡፡
መስቀል ኢየሱስ ስለሃጢያችን የውርደትርን ሞት እንደሞተ ይናገራል፡፡ መስቀል ስለኢየሱስ መስዋእትነት ይናገራል፡፡ መስቀል ኢየሱስ በእኛ ምትክ በመስቀል ላይ እንደተሰቀለ ይናገራል፡፡
ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው። ማቴዎስ 26፡28
2. የመስቀሉ አሰራር ዘላለማችን የሚወስን ነው፡፡
ኢየሱስ በመስቀል ላይ የሰራው ስራ ለአንዳንዶች ሞኝነት ነው ለሌሎች የእግዚአብሄር የማዳኛ ሃይል ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች የመስቀሉን አሰራር በፍፁም አይቀበሉትም ሌሎቹ ደግሞ ሁለንተናቸው መስቀል ነው፡፡ ለኢየሱስ የመስቀል ስራ ያለን እምነት ዘላለማችንን ይወስነዋል፡፡ ኢየሱስ ወደምድር የመጣው ሰዎችን ከሃጢያት ሊያድን በመሆኑ የመስቀሉን ትምህርት የተቀበሉ ሰዎች ከሃጢያት ባርነት ነፃ ይወጣሉ፡፡
የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና። 1ኛ ቆሮንቶስ 1፡18
ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ። ማቴዎስ 1፡21
3. መስቀል ኢየሱስ ስለሃጢያታችን ደሙን እንዳፈሰሰ ይናገራል፡፡
መስቀል ሃጢያታችንን በደሙ ሊያጥብ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ደሙን እንዳፈሰሰ ይናገራል፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ ያለደም ስርየት የለም እንደሚል የሃጢያታችንን ይቅርታ የምናገኘው ሃይማኖታው ስርአት ስለፈፀምን ሳይሆን ኢየሱስ በመስቀል ላይ ያፈሰሰልንን ደም ለእኔ ነው ብለን ስንቀበል ነው፡፡
ነውር የሌለው ሆኖ በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ የክርስቶስ ደም እንዴት ይልቅ ሕያውን እግዚአብሔርን ልታመልኩ ከሞተ ሥራ ሕሊናችሁን ያነጻ ይሆን? ዕብራውያን 9፡14
4. መስቀል ከእግዚአብሄር ጋር ሰላምን እንዳገኘን ይናገራል፡፡
ኢየሱስ በሰውና በእግዚአብሄር መካከል ያለውን የጥል ግድግዳ በመስቀሉ እንደሻረው መፅሃፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ የሰውና የእግዚአብሄርን ጠላትነት ሻረ፡፡ ማንም ሰው ኢየሱስ በመስቀል ላይ የሰራለትን ስራ ቢቀበል እግዚአብሄር ወደቤተሰቡ ይቀበለዋል፡፡
እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፥ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው። ኤፌሶን 2፡14-16
5. መስቀል እኛም አብረነው እንደተሰቀል ይናገራል፡፡
መስቀል ስላለፈው ሃጢያት ይቅርታ ብቻ ሳይሆን በሃጢያት ላይ ሃይል ስላገኘንበት የእግዚአብሄር አሰራር ይናገራል፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሲሞት የእኛን የሃጢያተኛ ስጋ ወክሎ ነው የሞተው፡፡ በኢየሱስ ስጋ የእኛ የሃጢያት ስጋ ተገድሎዋል፡፡ ኢየሱስ ይቅር ያለው ያለፈውን ሃጢያታችንን ብቻ ሳይሆን ኢየሱስን ከተቀበልን በኋላ ሃጢያት እንዳንሰራ የሃጢያተኛ ባህሪያችንን በመስቀሉ ላይ ገድሎታል፡፡
ከሥጋ የተነሣ ስለ ደከመ ለሕግ ያልተቻለውን፥ እግዚአብሔር የገዛ ልጁን በኃጢአተኛ ሥጋ ምሳሌ በኃጢአትም ምክንያት ልኮ አድርጎአልና፤ እንደ መንፈስ ፈቃድ እንጂ እንደ ሥጋ ፈቃድ በማንመላለስ በእኛ የሕግ ትእዛዝ ይፈጸም ዘንድ ኃጢአትን በሥጋ ኰነነ። ሮሜ 8፡3-4
ከእንግዲህስ ወዲያ ለኃጢአት እንዳንገዛ የኃጢአት ሥጋ ይሻር ዘንድ አሮጌው ሰዋችን ከእርሱ ጋር እንደ ተሰቀለ እናውቃለን፤ የሞተስ ከኃጢአቱ ጸድቋልና። ሮሜ 6፡6
6. መስቀል ለሞተልን እንድንኖር ይናገራል፡፡
መስቀል ስለኢየሱስ ሞት ብቻ ሳይሆን ሰለእኛም ሞት ይናገራል፡፡ መስቀል ኢየሱስ ስለእኛ ስለመሞቱ ብቻ ሳይሆን እኛ ለአለም ስለመሞታችንን ይናገራል፡፡
ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ። ገላትያ 6፡14
7. መስቀል በየእለቱ ለስጋችን ፈቃድ ስለምንሞትበት የእግዚአብሄር አሰራር ይናገራል፡፡
መስቀል የስጋችንን ፈቃድ በየእለቱ እንቢ የምንልበት ነው፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ የሰራው ስራ በእያንዳንዱ ቀን የሃጢያተኛ ስጋችንን ፈቃድ እንቢ ለማለት ሃይልን የምናገኝበት የእግዚአብሄር አሰራር ነው፡፡
ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፥ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። ሮሜ 8፡36
8. የክርስትና ስብከት ልቡ ያለው መስቀል ላይ ነው፡፡
ሞት የሌለው መስቀል ጌጥ እንጂ ምንም አይደለም፡፡ መስቀል የሌለው ስብከትም ሆነ ትምህርት ክርስትና አይደለም፡፡ የመስቀል ህይወት የሌለው በአል ድግስ እንጂ ክርስትና አይደለም፡፡ ኢየሱስ ለእናንተ ሞቶዋል ለሃጢያትና ለአለም ሞታችኋል ለክርስቶስ ኑሩ የማይል ስብከት መፅሃፍ ቅዱሳዊ አይደለም፡፡
እኔም፥ ወንድሞች ሆይ፥ ወደ እናንተ በመጣሁ ጊዜ በቃልና በጥበብ ብልጫ ለእግዚአብሔር ምስክርነቴን ለእናንተ እየነገርሁ አልመጣሁም። በመካከላችሁ ሳለሁ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር እርሱም እንደተሰቀለ ሌላ ነገር እንዳላውቅ ቆርጬ ነበርና። 1ኛ ቆሮንቶስ 2፡1-2
ባገኘነው አጋጣሚ መስቀልን ማክበር አለብን ነገር ግን በህየወት የማይከበር መስቀል ለምንም አይጠቅምም፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #መስቀል #ስቅለት #ሃጢያት #ሞት #ስቅለት #ጠቦት #መጋረጃ #ደም #ትንሳኤ #ስርየት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ተፈፀመ #ቤተመቅደስ #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ