Popular Posts

Tuesday, October 4, 2016

ሞት - ድንገትኛ እንግዳ

ሞት ከስጋ መለየት ነው፡፡ ሰው በምድር ላይ ከሚኖርበት ምድራዊ መኖሪያ ስጋው ተለይቶ የሚወጣበት መንገድ ነው፡፡ ሞት መለየት ስለሆነና አንዳንዴም በድንገት ስለሚመጣና ህያውንና የተውን በድንገርት ስለሚለይ ሞትን በቀላሉ አንመለከተውም፡፡
ነገር ግን ወደድንም ጠላንም ግን ሞት አለ፡፡ ሞት ይጠብቀናል፡፡ ድንገተኛም ሞት ይሁን የተዘጋጀንበት ሞት ሁላችንንም ይጠብቀናል፡፡
ለሰዎችም አንድ ጊዜ መሞት ከእርሱ በኋላም ፍርድ እንደ ተመደበባቸው፥ ዕብራውያን 9፡27
ሰው በእግዚአብሄር አምሳል የተፈጠረ ዘላለማዊ ፍጥረት ነው፡፡ ሰው ከስጋም ከተለየም በኋላ መኖሩን አያቆምም፡፡ ሰው ከስጋ ከተለየም በኋላ ነፍሱና መንፈሱ ለዘላለም ይኖራል፡፡ ስለዚህ ነው ሞት መጥፊያ ማለቂያ መትነኛ ሳትይሆን ሞት ከተፈጥሮአዊው ወደመንፈሳዊው አለም መሸጋገሪያ ነው የሚባለው፡፡
ድሀውም ሞተ፥ መላእክትም ወደ አብርሃም እቅፍ ወሰዱት፤ ባለ ጠጋው ደግሞ ሞተና ተቀበረ። ሉቃስ 16፡22
ዋናው ነገር ግን ለሞት ተዘጋጅተናል ወይ የሚለውን ጥያቄ በሚገባ መመለስ ነው፡፡ ደግሞ ለሞት መዘጋጀት ምን አመጣው ትሉኝ ይሆናል፡፡ ወይም ደግሞ ሁላችንም መልካም ስራ ለመስራት እየሞከርን ነው ልትሉኝ ትችላላችሁ፡፡
ለሞት መዘጋጀት ማለት እግዚአብሄርን ለመገናኘት መዘጋጀት ማለት ነው፡፡ ሰው እግዚአብሄር ያዘጋጀለትን የመዳኛ መንገድ ኢየሱስን ከተቀበለ እግዚአብሄር ይቀበለዋል እግዚአብሄርን ለመገናኘት ተዘጋጅቷል፡፡
ሰው በእግዚአብሄር ተቀባይነት ለማግኘት በህይወቱ ሙሉ መስራትና መልፋት የለበትም፡፡ ገና ድሮ በሃጢያት ስለወደቅን እግዚአብሄርን ልናስደስትበት የምንችለው ምንም መልካም ምግባር የለም፡፡
አንድ ማድረግ የምንችለው ነገር ኢየሱስ ለሃጢያታችን የከፈለውን ሞት ለእኔ ነው ብለን በእምነት መቀበል ብቻ ነው፡፡
ሰው የሚዘጋጀው እግዚአብሄርን ለመገናኘት ነው፡፡ ሰው ከሃጢያት የሚድንበትን የመዳኛ መንገድ ከተቀበለ እግዚአብሄር ይቀበለዋል የዘላለምም ህይወት ይሰጠዋል፡፡ ይህ ሰው እግዚአብሄርን ለመገናኘት ተዘጋጅቶዋል እንላለን፡፡
ነገር ግን ሰውን ከእግዚአብሄር የለየውን የሃጢያቱን እዳ የከፈለውን እየሱስን ከጣለ እግዚአብሄር አይቀበለውም፡፡ ይህ ሰው ሳይዘጋጅ ሞተ እንላለን፡፡ መጨረሻውም ለዘላለም ከእግዚአብሄር መለየትና ጥፋት ነው፡፡
በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዮሃነስ 3፡16
ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ ዮሃንስ 1፡12
ሞት መቼ እንደሚመጣ ስለማናውቅ ማድረግ የምንችለው ብቸኛ ነገር እስትንፋሳችን እስካለ ድረስ ኢየሱስን መቀበልና ከእግዚአብሄር ጋር መታረቅ ነው፡፡ ያለን ቀን አሁን ነው፡፡
በተወደደ ሰዓት ሰማሁህ በመዳንም ቀን ረዳሁህ ይላልና፤ እነሆ፥ የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤ እነሆ፥ የመዳን ቀን አሁን ነው። 2ኛ ቆሮንቶስ 6፡2
ጥያቄው ዛሬ ብትሞት እግዚአብሄርን ለመገናኘት ተዘጋጅተሃል ወይ ? እግዚአብሄር የሚጠይቅህ አንድ እርግጠኛ ጥያቄ ለሃጢያትህ ያዘጋጀሁትን ልጄን ኢየሱስን ተቀበልከው? ይሆናል፡፡
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ራእይ #መዳን #እምነት #ሞት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #የዘላለምህይወት #ፅናት #ትግስት #መሪ

Sunday, October 2, 2016

አንድ መልስ የለውም - ሁሉም መልስ ነው

በአገራችን ስላለው የሰዎች መሞት ስናስብ ችግሩ አንድ መልስ እንደሌለው እናስተውላለን፡፡ ለጥያቄው አንድ መልስ ብቻ መመለስ አንችልም፡፡ አንዳንዱ ሰው መፀለይ ብቻ ነው መፍትሄው መናገር አያስፈልግም ይላል፡፡ ሌላው ደግሞ መቃወም ነው እንጂ መፀለይ ምን ያስፈልጋል ይላል፡፡ እንደ እኔ ግን አንድ መልስ የለውም እላለሁ፡፡ ይህን የመጣውን እንደ ክርስቲያን በተለያየ መልኩ መመለስ አለብን፡፡
እንደ ክርስቲያን የህዝብን እልቂት ስናይ በጣም እናዝናለን፡፡ ልባችን ይሰበራል፡፡ መፅሃፍ ቅዱስም ከሚያለቅሱም ጋር አልቅሱ ስለሚል ስለሞቱት የሃዘንተኞችን ሃዘን እንካፈላለን፡፡ ወንድማቸውን እህታቸውን አባታቸውን እናታቸውን ልጃቸውን ካጡት ጋር እናዝናለን ልባችን ያለቅሳል፡፡
ከሚያለቅሱም ጋር አልቅሱ። ሮሜ 12፡15
ይህም ብቻ አይደለም ባገኘነው አጋጣሚ በልባችን ያለውን ሃሳብ እንናገራለን፡፡ የተሳሳተውን ትክክል አይደለም እንላለን፡፡ ስለዚህ ሕዝቡን በብዙ ሌላ ምክር እየመከራቸው ወንጌልን ይሰብክላቸው ነበር፤ የአራተኛው ክፍል ገዥ ሄሮድስ ግን፥ ስለ ሄሮድያዳ ስለ ወንድሙ ስለ ፊልጶስ ሚስትና ሄሮድስ ስላደረገው ሌላ ክፋት ሁሉ ዮሐንስ ስለ ገሠጸው፥ ሉቃስ 3፡18-19
እንዲሁም እንፀልያለን፡፡ እንፀልያለን የሚለው ቃል ለአንዳንዶች የማይሰራና (passive) ገቢር እንዳይደለ ሊሰማቸው ይችላል፡፡ ነገር ግን የክርስቲያን ፀሎት በጣም ወሳኝ ነው፡፡ ክርስቲያንና ፀሎትን መለየት አይቻልም፡፡ ሰይጣን ስፍራን እንዳያገኝ አጥብቀን መፀለይ አለብን፡፡
በክርስቶስ ኢየሱስ ያመነ የፃዲቅ ሰው ፀሎት በስራው እጅግ ሃይል ያደርጋል፡፡
የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች። ኤልያስ እንደ እኛ የሆነ ሰው ነበረ፥ ዝናብም እንዳይዘንብ አጥብቆ ጸለየ፥ በምድርም ላይ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር አልዘነበም፤ ሁለተኛም ጸለየ፥ ሰማዩም ዝናብን ሰጠ ምድሪቱም ፍሬዋን አበቀለች። ያዕቆብ 5፡16-18
እንግዲህ እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር፥ ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ። ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው። 1ኛ ጢሞቴዎስ 2፡1-4
እግዚአብሄር ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነቱን እንዲያውቁ ይወዳል፡፡ ስለዚህ ዛሬ ነገ ሳንል ወንጌልን እንሰብካለን፡፡ ባገኘነው አጋጣሚ ኢየሱስ ለሰው ልጆች ሃጢያት እንደሞተ የምስራቹን እንናገራለን፡፡
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ፖለቲካ #ፀሎት #ተቃውሞ #ሃዘን #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ወንጌል #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

የወንድሞች ህብረት

እግዚአብሄር በመልኩና በምሳሌው ስለፈጠረን እግዚአብሄር እንደኛው ስሜት እንዳለው እንረዳለን፡፡ እግዚአብሄርን የሚያስደስቱን ነገሮች አሉ፡፡ እግዚአብሄርን የማያስደንቁት ነገሮች አሉ፡፡ እግዚአብሄር የሚወደው ነገር አለ፡፡ እግዚአብሄር የማይወደው ነገር ደግሞ አለ፡፡ ለእግዚአብሄር መልካም የሆነ ነገር አለ፡፡ እግዚአብሄር መልካም የማይለው ነገር አለ፡፡
እኛን የሚያስደንቁን ነገሮች ነገሮች ሁሉ እግዚአብሄርን አያስደንቁትም፡፡ እግዚአብሄርን የማያስደስቱት እኛን የሚያስደስቱን ነገሮች አሉ፡፡
በመፅሃፍ ቅዱስ እግዚአብሄር የሚደነቅባቸውና መልካም ነው ያማረ ነው ብሎ የሚናገረው ነገር አለ፡፡ እንዲያውም የወንድሞች ህብረት ለእግዚአብሄር የሚጣፍጥ ምርጥ ሽቱ እንደሆነ መፅሃፍ ቅዱስ በግልፅ ይናገራል፡፡ የወንድሞች መሰብሰብ ጥምን እንደሚያረካና እንደሚያለመልም ውሃ ወሳኝ እንደሆነ መፅሃፍ ቅዱስ ያስተምራል፡፡
ስንሰበሰብ እግዚአብሄር ደስ ይለዋል፡፡ በአንድነት ስንሆን ደስ ይረካል፡፡ የወንድሞች መሰብሰብ ለእግዚአበሄር እንደ ሽቱ ነው፡፡ ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ፥ እነሆ፥ መልካም ነው፥ እነሆም፥ ያማረ ነው።ከራስ እስከ ጢም እንደሚፈስስ፥ እስከ አሮን ጢም፥ በልብሱ መደረቢያ እንደሚወርድ ሽቱ ነው። በጽዮን ተራሮች እንደሚወርድ እንደ አርሞንዔም ጠል ነው፤ በዚያ እግዚአብሔር በረከቱን ሕይወትንም እስከ ዘላለም አዝዞአልና። መዝሙር 133:1-3 ይህንን ፅሁፍ ሼር ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ህብረት #ወንድሞች #ሽቱ #ያማረ #እምነት #አንድነት #ልብ #ቃል #ምስጉን #ሃሳብ #ማሰላሰል #ወንጌል #ደቀመዝሙር #ኢየሱስ #ጌታ #መዳን #አማርኛ #ኢትዮጲያ #አቢይዋቁማ #ፌስቡክ #አዋጅ

Saturday, October 1, 2016

ህልሜን እየኖርኩት ነው

እግዚአብሄር ይመስገን ህልሜን እየኖርኩት ነው፡፡ ይህንን ንግግር ስናገር ሰዎች በአንድ አቅጣጫ ብቻ ስለሚመለከቱት ህልሜ ውስንና ትንሽ እንደሆነ ያስባሉ፡፡ ህልሜን እየኖርኩት ነው ስል ማለም እንዳቆምኩኝና ህልሜ ያለቀ ይመስላቸዋል፡፡ ህልሜን አየኖርኩት ነው ስል አንዳንዶች ተስፋ የቆረጥኩ ከዚህ በላይ ማየት ያቃተኝም ሁሉ ይመስላቸዋል፡፡
በፍፁም አይደለም፡፡ ህልሜን እየኖርኩት ነው ስል ምን ማለቴ እንደሆነ እኔ ነኝ የማውቀው፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ አሁን ያለኝ ነገር ሁሉ የእኔ አይደለም፡፡ አሁን ያለኝ ነገር እኔጋ ስለቆየ የእኔ እንደሆነ አላስብም፡፡ አሁን ያለኝ ነገር ሁሉ ከእግዚአብሄር የተቀበልኩት ነው እንጂ የእኔ አይደለም፡፡
አንተ እንድትበልጥ ማን አድርጎሃል? ያልተቀበልኸውስ ምን አለህ? የተቀበልህ ከሆንህ ግን እንዳልተቀበልህ የምትመካ ስለ ምንድር ነው? 1ኛ ቆሮንቶስ 4፡7
ስለዚህ ህልሜን እየኖርኩት ነው ስል እግዚአብሄ ታማኝ አምላክ ነው እንደተራራ የከበደብኝን ነገር እርሱ ራሱ አድርጎልኛል ማለቴ ነው፡፡
በሁለተኛ ደረጃ አሁን የደረስኩበት ደረጃ ከአመታት በፊት ተራራ ሆኖብኝ የነበረ መንፈሳዊ ደረጃ ነው፡፡ አሁን ያለሁበት የአገልግሎት ደረጃ ላይ እንደምደርስ እኔን ለማሳመን እግዚአብሔር ብዙ ቃል መጠቀም ነበረበት፡፡ እግዚአብሄር ተስፋ ስቆርጥ አፅናንቶኛል፡፡ ህልሜን ለመጣል ስፈተን ይቻላል ይደረስበታል ብሎ አበረታቶኛል፡፡
ዳዊትን ከበግ እረኝነት ወደንግስና ያመጣው እግዚአብሄር ነው፡፡ ህልሙን እየኖረ እያለ እግዚአብሄር ከተጨማሪ ህልሞች ጋር ወደእርሱ ሲመጣ እግዚአብሄርን እየኖረ ስላለው ህልምና ሊፈፀም ስላለው ህልም አመሰገነ፡፡
ንጉሡ ዳዊትም ገባ፥ በእግዚአብሔርም ፊት ተቀምጦ እንዲህ አለ፦ ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ እስከዚህ ያደረስኸኝ እኔ ማን ነኝ? 2ኛ ሳሙኤል 7፡18
ስለዚህ ነው ህልሜን እየኖርኩት ነው የምለው፡፡ በፊት ያልነበረኝ አሁን የደረስኩበት የህይወትና የአገልግሎት ደረጃ ሰላለ ነው ህልሜን እየኖርኩት ነው የምለው፡፡
ሶስተኛ እግዚአብሄር ስለዚህ ስለደረስኩበት ደረጃ ሊመሰገን ስለሚገባው ነው፡፡ ይህ ማለት ከአሁን በኋላ ምንም ህልም የለኝም ማለት ግን አይደለም፡፡ አንዳንድ ሰዎች እግዚአብሄርን ስለደረሱበት ማመስገን የማይፈልጉት ሌላ የሚፈልጉት ነገር የሌለ ይመስልብናል ብለው በማሰብ ነው፡፡ ህልምን መኖርና ሌላ ህልም ማለም አብረው የሚሄዱ እንዲያውም የአንዱ እምነት ለሌላው ምስክር የሚሆንበት እንጂ የሚቃረኑ አይደሉም፡፡
አሁንም ብዙ የሚፈፀሙ ህልሞች አሉኝ፡፡ ወደፊት የማያያቸው ብዙ ደረጃዎች አሉኝ፡፡ ብዙ የምደርስባቸው ግቦች አሉኝ፡፡ ልደርስባቸው የምዘረጋባቸው ህልሞች ከፊቴ አሉ ማለት ግን አሁን የምኖረውን ኑሮና የመንፈሳዊ ህይወት ደረጃ ስለደረስኩበትር ብቻ አጣጥለዋለሁ ማለት አይደለም፡፡ የወደፊት ህልም አለኝ ማለት አሁን ስለደረስኩበት ጌታን አላመሰግንም ማለት አይደለም፡፡ ወደፊት ህልም አለኝ ማለት በደረስኩበት ህልም አልደሰትም ማለት አይደለም፡፡
የአሁኑም የህይወቴ ደረጃ ፣ አሁን በክርስቶስ ያለኝ የነፃነት ደረጃ ፣ አሁን ያለኝ መንፈሳዊ አርነት ፣ አሁን ያለኝ የአገልግሎት ደረጃ አንድ ቀን የፀለይኩበት ፣ አንድ ቀን በእጅጉ የፈለኩት ፣ አንድ ቀን ያወጅኩትና አንድ ቀን እንደተራራ የሆነብኝ ደረጃ ነበር፡፡ ስለእናንተን አላውቅም እኔ ግን ህልሜን እየኖርኩት ነው፡፡ እግዚአብሄ ይመስገን፡፡
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ራእይ #ህልም #ስምረት #መሰረታዊፍላጎት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

ወደር የለሽ ብልፅግና

በክርስትና ህይወታችን አድገን አድገን የመጨረሻው የስኬትና የብልፅግና ደረጃ ምን እንደሆነ ማወቅ ሁላችንም እንፈልጋለን፡፡ የመጨረሻው ደረጃ ላይ ስንደርስ እንድናውቀውና እንድንረካ "ይሄ ነው" እንድንል ሁላችንም እንፈልጋለን፡፡
ስለዚህ ደረጃ የተለያዩ ሰዎች የተለያዩ አስተያየት አላቸው፡፡ ይህንን ሁሉ አስተያየት ብንሰማ እንስታለን፡፡ የእግዚአብሄር ቃል የሚለውን ከሰማን ግን እናርፋለን፡፡
የክርስትና ህይወት ግቡ ምንድነው? የክርስትና ህይወት የስኬት ጣራው ምንድነው? የሚለውን ጥያቄ በሚገባ ሊመልስልን ሙሉ ስልጣን ያለው የእግዚአብሄር ቃል ብቻ ነው፡፡
የእግዚአብሄር ቃል ደግሞ እውነት ነው፡፡ የእግዚአብሄር ቃል ኦሪጂናል የእግዚአብሄር ሃሳብና ፈቃድ ነው፡፡
የእግዚአብሄር ሰው ደረሰበት የሚባለው ምን ሲኖረው ነው? የጌታ ሰው እንደው ህይወቱ ሲያስቀና የሚያስብለው ምንና ምን ሲኖረው ነው? የሚለውን ጥያቄ መፅሃፍ ቅዱስ በሚገባ ይመልሰዋል፡፡
ክርስቲያን በለፀገ የሚባለው ሚሊየነር ሲሆን አይደለም፡፡ ክርስቲያን ተሳካለት ደረሰበት የሚባለው ዝነኛ ሲሆን አይደለም፡፡ ክርስቲያን ደረሰበት ይህ የተሳካለት ሰው ነው የሚባለው መሰረታዊ ፍላጎቱን አሟልቶ ጌታን ሲከተል ነው፡፡ ክርስቲያን ደረሰበት የሚባለው እግዚአብሄር በህይወቱ ላስቀመጠው ሃላፊነት የሚያስፈልገው ነገር ካልጎደለበት ነው፡፡ ክርስቲያን ተሳካለት የሚባለው ለአገልግሎቱ የሚያስፈልገውን መሰረታዊ ፍላጎት ካሟላ ነው፡፡
ጌታ ከመከተል የተሻለ የስኬት ደረጃ የለም፡፡ ጌታን ከመውደድ ያለፈ የብልፅግና ደረጃ የለም፡፡ ጌታን ከማምለክና እግዚአብሄርን ከመምሰል የላቀ የስምረት ደረጃ የለም፡፡
ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤ ወደ ዓለም ምንም እንኳ አላመጣንምና፥ አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፥ እርሱ ይበቃናል። 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡6-8
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ብልፅግና #ስኬት #ስምረት #መሰረታዊፍላጎት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

ኃይላቸውን ያድሳሉ

አንዳንዴ የራሳችን ጉልበት ያልቃል፡፡ አቅም ያንሰናል፡፡ ማለዳ ብርቱና ሙሉ ሆነን ከሰአት በኋላ ውድቅ እንላለን፡፡ መሄድ እንፈልጋለን ግን ይደክመናል፡፡ ወደፊት መራመድና ነገሮችን መፈፀም ያቅተናል፡፡ ይህ እንግዳ ነገር አይደለም ፡፡ የሰው ጉልበት ያልቃል፡፡ ብርቱና ሃያል ሰው እንኳን ይደክማል ይታክታል፡፡ እግዚአብሄርም ስለዚህ እንዲህ ይላል፡፡
ብላቴኖች ይደክማሉ ይታክቱማል፥ ጐበዛዝቱም ፈጽሞ ይወድቃሉ፤ ኢሳያስ 40፡30
እግዚአብሄር ሊያድሰን ያስፈልጋል፡፡ እግዚአብሄር ደግሞ ማደስ ማስነሳት ልማዱ ነው፡፡ እግዚአብሄር ለደካማ ሃይልን መስጠት ይወዳል፡፡ እግዚአብሄር ብርታት ለሌለው ጉልበትን በደስታ ይጨምራል፡፡
ለደካማ ኃይልን ይሰጣል፥ ጕልበት ለሌለውም ብርታትን ይጨምራል። ኢሳያስ 40፡29
የማይደክመው እግዚአብሄር አምላካችን ሆኖ ሁልጊዜ እንበረታለን፡፡ ከማይደክመውና ከማይታክተው ከሃያሉ ከእግዚአብሄር ጋር ተገናኝተን የሚጎድልብንና የምናጣው ምንም ሃይል የለም፡፡
አላወቅህምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፥ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው፤ አይደክምም፥ አይታክትም፥ ማስተዋሉም አይመረመርም።
ሂድ አድርግ አትቁም አትዘግይ የሚሉ በራሳችን እንድንራመድ የሚያጣድፉ ብዙ ድምፆች አሉ፡፡ ከእኛ የሚጠበቀው አንድ ነገር እግዚአብሄርን በመተማመን መጠበቅ ነው፡፡ ጊዜ ያለፈብን ሊመስለን ይችላል፡፡ የተበለጥን ሊመስለን ይችላል፡፡ የሳትን ሊመስለን ይችላል፡፡ ማስተዋሉ የማይመረመረውን እግዚአብሄርን በመጠበቀ የምናጣውና የሚጎድልብን ነገር የለም፡፡
እግዚአብሔርን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፥ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፥ አይደክሙም። ኢሳያስ 40፡31
በራስህ ትደክማለህ ትካክታለህ፡፡ እግዚአብሄር ሲያድስ ግን ሄደህ ሄደህ አትደክምም፡፡ ሮጠህ ሮጠህ አትታክትም፡፡ እግዚአብሄር እድሳት ከፍ ያደርግሃል ከሁኔታው ሁሉ በላይ ያወጣሃል፡፡ ስለዚህ በምናደርገው ሁሉ እግዘዚአብሄርን በመተማመን እንጠብቅ፡፡ ለእግዚአብሄ እድሳት ስፍራ እንስጥ፡፡ እግዚአብሄርን በመጠባበቅ እንዲያድሰን እንፍቀድለት፡፡
ያዕቆብ ሆይ፥ እስራኤልም ሆይ፦ መንገዴ ከእግዚአብሔር ተሰውራለች ፍርዴም ከአምላኬ አልፋለች ለምን ትላለህ? ለምንስ እንዲህ ትናገራለህ? አላወቅህምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፥ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው፤ አይደክምም፥ አይታክትም፥ ማስተዋሉም አይመረመርም። ለደካማ ኃይልን ይሰጣል፥ ጕልበት ለሌለውም ብርታትን ይጨምራል። ብላቴኖች ይደክማሉ ይታክቱማል፥ ጐበዛዝቱም ፈጽሞ ይወድቃሉ፤ እግዚአብሔርን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፥ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፥ አይደክሙም። ኢሳያስ 40፡27-31
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #መጠበቅ #በመተማመን #ያድሳሉ #ይወጣሉ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ