Popular Posts

Tuesday, September 28, 2021

የሰይጣን መሳሪያ

 


የሰይጣን አላማው መስረቅ ማረድና ማጥፋት ነው፡፡ ሰይጣን ከመስረቅ ከማረድና ከማጥፋት ውጭ ሌላ ምንም አላማ የለውም፡፡

ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም እንጂ ስለ ሌላ አይመጣም፤ የዮሐንስ ወንጌል 10፡10

ይህንን የመስረቅ የማረድና የማጥፋት አላማውን የሚያሳካው ደግሞ በውሸት ነው፡፡ ሰይጣን አለማማውን የሚያሳካው በመዋሸት እና በማታለል ነው፡፡

እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፥ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና። የዮሐንስ ወንጌል 8፡44

ሰይጣን የራሱ ነገር የለውም፡፡  ሰይጣን የእግዚአብሄርን እውነትን አይቀበለም፡፡ ሰይጣን ከራሱ ሃሰትን ይናገራል፡፡ ሰይጣን ይዋሻል፡፡ ሰይጣን እውነትን ለውጦ ያቀርባል፡፡ ሰይጣን የሚያምኑትን ሰዎች ያታልላል፡፡

ሰይጣን ከመጀመሪያ ጀምሮ ውሸታም ነው፡፡ ከሰይጣን ውሸት እንጂ ምንም ሌላ ነገር አይጠበቅም፡፡ ሰይጣን ተንኮለኛ ነው፡፡ የሰይጣን ሃይል ማታለል ስለሆነ ሰይጣን ሃሰቱን እውነት አስመስሎ ለማቅረብ የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም፡፡

ሰይጣን በተለይ በእግዚአብሄር ፊት ያለን ቦታ ላይ ይዋሻል፡፡ እግዚአብሄር እንዴት በክብር እንደሚያየን በእግዚአብሄር ፊት ያለንን የክብር ቦታ ላይ በልባችን ጥርጥር ማስገባት ከተሳካለት ሰይጣን ህይወታችንን በቀላሉ ሊሰርቅ ሊያርድና ሊያጠፋ እንደሚችል ያውቃል፡፡

ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ። 2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 11፡3

ሰይጣን ዲያብሎስ በእግዚአብሄር ልጅነታችን ላይ እንዲዋሽ ካልፈቀድንለት ግን ህይወታችንን የሚያጠቃበት ምንም ፈንታ እና ስፍራ ሊያገኝ አይችልም፡፡ ለሰይጣን በፍርሃት ስፍራን የምንሰጠው ወይም በእምነት ስፍራን የምናሳጣው እኛው ራሳችን ነን፡፡

ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 4፡27

ሰይጣን ሔዋንን ያሳሳታት በእግዚአብሄር ፊት ባላት ስልጣን በማንነትዋ ላይ በመዋሸት ነው፡፡ እግዚአብሄር በመልኩና በአምሳሉ ፈጥሮአት እያለ ልጅነትዋ ምንም እንዳይደለ ፣ ምንም ሊጠቅማት እንደማይችል ፣ ከንቱ እንደሆነ እና የጎደላት ብዙ ነገር እንዳለ በውሸት በማሳመን በአመፃ ከእግዚአብሄር ክብር እንድትወድቅ አታለላት፡፡

እባብም ለሴቲቱ አላት፦ ሞትን አትሞቱም፤ ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ። ኦሪት ዘፍጥረት 3፡5

ዲያቢሎስ ኢየሱስን በምድር ላይ ሲፈትነው የሰይጣን የውሸትና የንቀት ስልቱ ተመሳሳይ ነበር፡፡ ሰይጣን "የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ" በሚለው የማናናቂያ እና የማጣጣያ የንቀት ንግግሩ በኢየሱስ ማንነት ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ሞክሮዋል፡፡ የሰይጣን "የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ" የሚለው ንግግር ኢየሱስ በእግዚአብሄር ፊት ያለውን ልጅነት የሚያንቋሽሽ ምን ታመጣለህ? ዝም ብለህ ነው ! ምንም አይደለህም! ከማንም አትበልጥም! የሚል መልእክት ነበረው፡፡

ዲያብሎስም፦ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ ይህን ድንጋይ፦ እንጀራ ሁን ብለህ እዘዝ አለው። የሉቃስ ወንጌል 4፡3

ኢየሱስ ግን የልጅነት ቦታውንና ስልጣኑን አጥብቆ ያውቅ ስለነበር ለሰይጣን ማንቋሸሽ እና ማጣጣል አልተንበረከከም፡፡ ኢየሱስ የሰይጣንን የውሸት ንግግር በልቡ አላስተናገደውም፡፡ ኢየሱስ የሰይጣንን የማንቋሸሽ ንግግር ተቀብሎ እግዚአብሄር ከሰጠው አላማ ወጥቶ ለአንድም ሰአት ለሰይጣን ሃሳብ አልተገዛም፡፡ ኢየሱስ የሰይጣንን የንቀትና የፍርሃት ንግግር ንቆ እግዚአብሄር የሰጠውን አላማ በድፍረት ፈፀመ፡፡

የሰይጣን የፍርሃት አላማ ሰውን ከአላማው ማስቆም እንደመሆኑ መጠን የሰይጣን ፍርሃት እና ጥርጥር የሚጭር ንግግር ኢየሱስን ከአላማው እና ከእርምጃው አላቆመውም፡፡ የፍርሃት አላማ እኛን ለምንም የማንጠቅም ፣ ሽባ ማድረግ እንደመሆኑ መጠን ኢየሱስን በፍርሃት ሽባ ሊያደርገው እና ከአላማው ሊያስቆመው አልቻለም፡፡  

አሁንም ሰይጣን እኛን የሚፈትነን ልጅነታችንን እና በልጅነታችን ያገኘነውን ነገር ጥርጣሬ ውስጥ በመክተት ነው፡፡ አሁንም የእግዚአብሄር ልጅ ከሆንክ እስኪ ከዚህ ሁኔታ አምልጥ ፣ የእግዚአብሄ ልጅ ከሆንሽ ይህ ለምን ደረሰብሽ? የእግዚአብሄር ልጅ ከሆንክ እንዲህ እና እንዲያ ለምን ሆነ? በማለት በእግዚአብሄር ፊታ ያለንን ልጅነት ሊያጣጥል ይጥራል፡፡

እህህ ብለን ውሸቱ ከሰማነውና በማጣጣል ወጥመዱ ውስጥ ከገባንለት የእግዚአብሄር ልጅ አይደላችሁም ፣ ዝም ብላችሁ ነው ፣ ከእኔ ሃይል አታመልጡም ብሎ ሊያሳምነን ይፈልጋል፡፡

ሰይጣን የህይወት ጠላት ነው፡፡ ሰይጣን ውሸታም ነው፡፡ ሰይጣን የሚጠቀመው በማታለል ነው፡፡ በህይወታችን አሸናፊ ለመሆን ከሰይጣን ንግግር በላይ እና ከሁኔታ በላይ የእግዚአብሄርን ቃል ልናምን ይገባናል፡፡

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ዲያቢሎስ #ጠላት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ሐሰት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ውሸት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ማታለል #የተሸነፈ #በረከት #ትግስት #መሪ


No comments:

Post a Comment