Popular Posts

Sunday, February 9, 2020

የዘላለም መነፅር



ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ አዳኛችን እና ጌታችን አምነን የተቀበልንና የዳንን ሁላችን ማንኛውምን ነገር በዘላለም መነፅር አይተን ካልመዘንን በስተቀር እግዚአብሄር ወደአየልን የህይወት ግብ አንደርስም፡፡ በህይወታችን የሚቀርብልንን ምርጫዎች በዘላለም መነፅር አይተን ካልመዘንን እንሳሳታለን፡፡
ህይወት በምርጫ የተሞላ ነው፡፡ ትክክለኛ ምርጫን ለመምረጥ የከበረውን ከተዋረደው መለየት ግዴታ ነው፡፡
የከበረውን ከተዋረደው ለመለየት ነገሮችን እውነተኛ መልካቸውን የሚያሳይ መነፅር ማግኘት ወሳኝ ነው፡፡ በምድራዊ መነፅር ነገሮችን የምናይ እና የምንወስን ከሆንን እግዚአብሄር ካዘጋጀልን የክብር ህይወት እንጎድላለን፡፡ እግዚአብሄር እንደሚያያቸው በሰማይ መነፅር በትክክል አይተን ከወሰንን ህይወታችን ያብባል፡፡
ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ብትመለስ እመልስሃለሁ በፊቴም ትቆማለህ፤ የከበረውንም ከተዋረደው ብትለይ እንደ አፌ ትሆናለህ፤ እነርሱ ወደ አንተ ይመለሳሉ፥ አንተ ግን ወደ እነርሱ አትመለስም። ትንቢተ ኤርምያስ 15፡19
የምንወስነው ውሳኔ በእግዚአብሄር ዘለዓለማዊ እቅድ ውስጥ ያለውን ቦታ መረዳት ትክክለኛውን ውሳኔ እንድንወስን ያደርገናል፡፡
የምንወስነው ውሳኔ ለሚመጣው አለም የሚጠቅም እንደሆነ አውቀን ካልወሰንን የምድር ልፋታችን ከንቱ ነው፡፡
ሰውነትን ለሥጋዊ ነገር ማስለመድ ለጥቂት ይጠቅማልና፤ እግዚአብሔርን መምሰል ግን የአሁንና የሚመጣው ሕይወት ተስፋ ስላለው፥ ለነገር ሁሉ ይጠቅማል። 1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 4፡8
በምድር ላይ ስንኖር ከእግዚአብሄር እንደመጣን ወደእግዚአብሄር እንደምንሄድ አድርገን በዘላለም መነፅር ነገሮችን መመልከት አለብን እንጂ እንብላ እንጠጣ ነገ እንሞታለን በማለት በምድራዊ መነፅር ብቻ ነገሮችን እንደሚያዩት ከንቱ ኑሮ መኖር የለብንም፡፡
በዘላለም እይታ ነገሮችን ስናይ በምድር ላይ ለጌታ የምንቀበለው መከራ ዋጋ እንዳለው እንረዳለን፡፡
እንደ ሰው በኤፌሶን ከአውሬ ጋር ከታገልሁ፥ ሙታንስ የማይነሡ ከሆነ፥ ምን ይጠቅመኛል? ነገ እንሞታለንና እንብላና እንጠጣ። ፡1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 15፡32
የምናደርገውን ሁሉ እንደእግዚአብሄር ቃል በዘለላም መነፅር አይተን ካደረግን በከንቱ ለሚጠፋ መብል ከመስራት ይጠብቀናል፡፡
ለሚጠፋ መብል አትሥሩ፤ ነገር ግን ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር መብል የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ሥሩ፤ እርሱን እግዚአብሔር አብ አትሞታልና። የዮሐንስ ወንጌል 6፡27
በዘላለማዊ መነፅር የማያዩትን ሁሉንም ነገር በምድራዊ አስተሳሰብ የሚያስቡትን ሰዎች መፅሃፍ ቅዱስ መጨረሻቸው እንደማያምር ይናገራል፡፡
መጨረሻቸው ጥፋት ነው፥ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፥ ክብራቸው በነውራቸው ነው፥ አሳባቸው ምድራዊ ነው። እኛ አገራችን በሰማይ ነውና፥ ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን፤ ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 3፡19-20
በምድር እንዳሉት የእግዚአብሄርን የዘላለም እቅድ እንደማይረዱት ሰዎች በምድራዊ እይታ ብቻ ኖረን ኖረን መሞት ለእግዚአብሄር ልጅ የሚገባ አይደለም፡፡  
እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ፥ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ እሹ፤ በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም። ወደ ቆላስይስ ሰዎች 3፡1-2
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #እይታ #ተስፋ #መፀለይ #መንፈስ #በረከት #መዝገብ #ሰማይ #እንግዶች #ዘላለም #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #እምነት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እይታ #ምድራዊ #ሰማያዊት #ማየት #ቅርብ

No comments:

Post a Comment