Popular Posts

Wednesday, February 5, 2020

እግዚአብሔር አላከበደውም



እግዚአብሔር ሰውን የማይቻል ነገር ጠይቆ አያውቅም፡፡ እግዚአብሄር ከጠየቀ ይቻላል ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር ካዘዘ መፈፀኽ የሚቻል ትእዛዝ ነው ማለት ነው፡፡  
እግዚአብሄር እርሱን መታዘዝንና ማስደሰትን ሰው ብዙ ጊዜ እንደሚያስበው ከባድ አላደረገውም፡፡
የእግዚአብሄርን ነገር ከባድና ውስብስብ የሚያደርገው የሰው የሃይማኖት መልክ ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ነገር ሩቅና በፍፁም ሊረዱት የማይችሉት ረቂቅ የሚያደርገው የሰው ከንቱ የሃይማኖትኝነት አስተሳሰብ ነው፡፡
እግዚአብሔር ሰዎችን ቅኖች አድርጎ እንደ ሠራቸው፥ እነሆ፥ ይህን ብቻ አገኘሁ፤ እነርሱ ግን ብዙ ብልሃትን ፈለጉ። መጽሐፈ መክብብ 7፡29
እግዚአብሄር እርሱን መከተልን አላከበደውም፡፡ አንዳንድ ሰው በራሱ የሰው ጥበብ የእግዚአብሄርን ነገር ካላወሳሰበው በስተቀር እግዚአብሄርን ያመለከ አይመስለውም፡፡  
እግዚአብሄር የሰው ደስታ ጠላት አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ሰውን በትንሽ በትልቁ ማዘዝ አይፈልግም፡፡ እግዚአብሄር የሚፈልገው ሰው በነፃነት እንዲኖርና የሚያደርገውን ነገር ሁሉ በእግዚአብሄር ፍርሃት እንዲያደርገው ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄር ከሰው የሚፈልገው ብቸኛው ነገር እግዚአብሄር አንድ ቀን ሰው የሚሰራውን ስራ ወደፍርድ እንደሚያመጣው በማወቅ ብቻ በነፃነት እንዲኖር ነው፡፡
የነገሩን ሁሉ ፍጻሜ እንስማ፤ ይህ የሰው ሁለንተናው ነውና፤ እግዚአብሔርን ፍራ፥ ትእዛዙንም ጠብቅ። መጽሐፈ መክብብ 12፡13
ሰው ሲታለል እግዚአብሄርን ለማስደስት ብዙ ነገር የሚያስፈልግ ይመስለዋል፡፡ እግዚአብሄር ከሰው የሚፈልገው አንድ ነገር ቃሉን እንዲሰማና እንዲከተል ብቻ ነው፡፡
ኢየሱስም መልሶ፦ ማርታ፥ ማርታ፥ በብዙ ነገር ትጨነቂአለሽ ትታወኪማለሽ፥ የሚያስፈልገው ግን ጥቂት ወይም አንድ ነገር ነው፤ ማርያምም መልካም ዕድልን መርጣለች ከእርስዋም አይወሰድባትም አላት። የሉቃስ ወንጌል 10፡41-42
እግዚአብሄር ሰው በምድር ላይ ብዙ ነገር እንዲፈልግ አልፈለገም፡፡ እግዚአብሄር ሰው እንዲፈልግ የፈለገው ብቸኛ በነገር የእግዚአብሄርን ፅድቁንና መንግስቱን ብቻ ነው፡፡
ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። የማቴዎስ ወንጌል 6፡33
እግዚአብሄር በትላንት በዛሬና በነገ ውስጥ እንድንኖር እና ህይወታችንን እንድናወሳስብ አልጠየቀም፡፡ እግዚአብሄር በዛሬ ላይ ብቻ ኖረን እንድናስደስተው ኑሮን ቀላል አድርጎታል፡፡
ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል። የማቴዎስ ወንጌል 6፡34
ሰው እግዚአብሄር ብዙ ነገሮች የሚፈልግ ይመስለዋል፡፡ እግዚአብሄር ከሰው የሚፈልገው የሰውም ትህትና ብቻ ነው፡፡  
ሰው ሆይ፥ መልካሙን ነግሮሃል፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? ፍርድን ታደርግ ዘንድ፥ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፥ ከአምላክህም ጋር በትሕትና ትሄድ ዘንድ አይደለምን? ትንቢተ ሚክያስ 6፡8
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ስፋት #እርካታ #ፍሬያማነት #ክንውን #አሸናፊነት #በጎነት #ቅን #እምነት #ፅድቅ #ደስታ #ሰላም #ኢየሱስ #ጌታ #ሃይል #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መጋቢ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment