Popular Posts

Thursday, February 13, 2020

በጋብቻ እመኑ



ስለጋብቻ በእግዚአብሔር እመኑ፡፡
ጋብቻ የእግዚአብሄር እንጂ የሰው ሃሳብ አይደለም፡፡ የጋብቻን ሃሳብ ያመነጨው ሰው አይደለም፡፡ የጋብቻን ሃሳብ ያመጣው ራሱ እግዚአብሄር ነው፡፡ እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው አስቀድሞ ጋብቻን አስቦ ነው፡፡ እግዚአብሄር ሰውን ሲፈጥር ወንድና ሴት አድርጎ የፈጠረው ስለዚህ ነው፡፡
እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አለ፦ ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አደረጋቸው፥ የማቴዎስ ወንጌል 19፡4
አስቦ አስቦ ማግባት አለብኝ ብሎ ከጊዜ በኋላ የጋብቻን አሳብ ያመጣው ሰው አይደለም፡፡ የፈጠረው ሰው ሚስት ማግባት እንዳለበትና ሰው ብቻውን መኖሩ መልካም እንዳይደለ የተናገረው እግዚአብሄር ራሱ ነው፡፡
ሰው የጋብቻን ሃሳብ ባላሰበበት ጊዜ ሰው ማግባት እንዳለበት ያሰበው እና ያቀደው ሚስትም የፈጠረለት እግዚአብሄር ነው፡፡ ከሰው በላይ ለሰው ምን እንደሚያስፈልገው የሚያውቀው እግዚአብሄር ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም በማለት ሰው ማግባት እንዳለበት ተናገረ፡፡
በእግዚአብሄር የሚያመን ሰው በጋብቻ ማመን አለበት፡፡ በጋብቻ ከማመን ውጭ መንም አማራጭ የለም፡፡ በጋብቻ ማመን መፅሃፍ ቅዱሳዊ እውነት ነው፡፡ ሰው በሌላ ነገር ሊሳሳት ይችላል ነገር ግን በጋብቻ አምኖ አይሳሳትም፡፡
ኢየሱስ በምድር ላይ በተመላለሰበት ጊዜ የጋብቻ ቃልኪዳን እስከመጨረሻው እንደሆነ ሲያስተምር ነበር፡፡ ደቀመዛሙርቱም የጋብቻ ሥርዓት ይህ ከሆነማ መጋባት አይጠቅምም ወደሚል መደምደሚያ ደረሱ፡፡ ኢየሱስ ግን ሰው ጃንደረባ ካልሆነ በስተቀር በጋብቻ ማመንና ራስን መስጠት እንጂ ሌላ ምንም አማራጭ እንደሌለው አስተማራቸው፡፡
ደቀ መዛሙርቱም፦ የባልና የሚስት ሥርዓት እንዲህ ከሆነ መጋባት አይጠቅምም አሉት። እርሱ ግን፦ ይህ ነገር ለተሰጣቸው ነው እንጂ ለሁሉ አይደለም፤ የማቴዎስ ወንጌል 19፡10-11
ጋብቻ የእግዚአብሄር ስርአት ነው፡፡ ጋብቻ የህይወት ሃላፊነት ነው፡፡ ጋብቻ የህይወት የቤት ስራ ነው፡፡
ጋብቻ ይጠቅማል አይጠቅምም ከሚለው ባለፈ ልናልፍበት የሚገባ የህይወት ሃላፊነት ነው፡፡
ጋብቻ በእግዚአብሄር ዘንድ የተከበረ ነው፡፡
መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹሕ ይሁን፤ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል። ወደ ዕብራውያን 13፡4
የጋብቻ ቃልኪዳን እግዚአብሄር ራሱ የሚካተትበት ክቡር ነገር ነው፡፡ 
እናንተም፦ ስለ ምንድር ነው? ብላችኋል። ሚስትህ ባልንጀራህና የቃል ኪዳንህ ሚስት ሆና ሳለች እርስዋን አታልለሃታልና እግዚአብሔር በአንተና በልጅነት ሚስትህ መካከል ምስክር ስለ ሆነ ነው። ትንቢተ ሚልክያስ 2፡14
እግዚአብሄር ከጋብቻ መቀጠል ጋር በትጋት የሚሰራው የእሱ የራሱ ተቋም ስለሆነ ነው፡፡ ትዳሩን መገንባት የሚፈልግ ሰውን እግዚአብሄር በመንፈሱ እና በሃይሉ የሚረዳው ትዳር የራሱ እቅድ ስለሆነ ነው፡፡ እግዚአብሄር ከጋብቻ መቀጠል ጋር አብሮ የሚቆመው እና መፋታትን የሚጠላው መፋታት የራሱን እግዚአብሄርን ተቋም ስለሚቃወም ነው፡፡ በትዳር ላይ ታላቁ የእግዚአብሄር እጅ ያለበት ትዳር የእግዚአብሄር እቅድ እና አላማ ስለሆነ ነው፡፡
ከፍጥረት መጀመሪያ ግን እግዚአብሔር ወንድና ሴት አደረጋቸው፤ ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፥ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ፤ ስለዚህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ወደ ፊት ሁለት አይደሉም። እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው። የማርቆስ ወንጌል 10፡6-9
ትዳርን ባቀደው ፣ በመሰረተው እና በሚደግፈው በእግዚአብሄር ስለትዳራችሁ አመኑ፡፡
ልባችሁ አይታወክ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፥ በእኔም ደግሞ እመኑ። የዮሐንስ ወንጌል 14፡1
 ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ህይወት #ጋብቻ #ትዳር #መጋባት #ባል #ሚስት #ፍቅር #መውደድ #ይተዋል #ይጣበቃል #አንድስጋ #እውነት #ትህትና #ትንሳኤ #ህይወት #ወንጌል #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ  #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ 

No comments:

Post a Comment