Popular Posts

Friday, December 23, 2016

ኢየሱስ ብቻ አይደለም የተወለደው !

ለብዙ ሰዎች የኢየሱስ መወለድ ከእለታት አንድ ቀን የተፈፀመ ታሪክ ብቻ ነው፡ ለእነዚህ ሰዎች የኢየሱስ መሞት በህይወታቸው ያመጣው ምንም ነገር የለም፡፡ በኢየሱስ መወለድ ህይወታቸው አልተለወጠም፡፡ በኢየሱስ መወለድ ህይወታቸው የተወለደ ነገር የለም፡፡
ኢየሱስ በቤተልሄም እንደተወለደ በህይወታችን ሊወለድና ሊኖር ይገባዋል፡፡
ኢየሱስ የተወለደው ታሪክ ሊሰራ አይደለም፡፡ ኢየሱስ የተወለደው ለገድል አይደለም፡፡
ኢየሱስ የተወለደው ለእውነት ሊመሰክር ነው፡፡
እውነትን መፈለግ አቁመናል፡፡ በኢየሱስ እውነትን አግኝተነዋል፡፡
ጲላጦስም፦ እንግዲያ ንጉሥ ነህን? አለው። ኢየሱስም መልሶ፦ እኔ ንጉሥ እንደ ሆንሁ አንተ ትላለህ። እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ዮሃንስ 18፡37
ኢየሱስ የተወለደው ለዓለም ብርሃን ሊሆን ነው፡፡
ዓለም በጨለማ በተያዘበት ጊዜ ወዴት እንደሚሄድ ምን እንደሚያደናቅፈው ባለወቀ ጊዜ ኢያስ በጨለማ የሚያበራ ብርሃን ሆኖ መጣ፡፡  
በእኔ የሚያምን ሁሉ በጨለማ እንዳይኖር እኔ ብርሃን ሆኜ ወደ ዓለም መጥቻለሁ። ዮሃንስ 12፡46
ደግሞም ኢየሱስ፦ እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም ብሎ ተናገራቸው። ዮሃንስ 8፡12
ኢየሱስ የተወለደው በመስቀል ላይ ሊሞት ነው፡፡
ኢየሱስ የተወለደው እኛ ከእግዚአብሄር እንድንወለድ ነው፡፡ ኢየሱስ የተወለደው እኛ ወደ እግዚአብሄር ቤተሰብ ውስጥ አንድንገባ ነው፡፡ ኢየሱስ የተወለደው እኛ የእግዚአብሄር የቤተሰብ አባላት የመሆን ስልጣን እንድናገኝ ነው፡፡
የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም። ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ ዮሃንስ 1፡11-12
ኢየሱስ የተወለደው ከሃጢያት ሊያድነን ነው
ከሃጢያት ካልዳንን ኢየሱስ የተወለደበትን አላማ ስተነዋል ማለት ነው፡፡ ከሃጢያት ሃይል ነፃ ካልወጣን የኢየሱስ መሞት ታሪክ ብቻ ነው ማለት ነው፡፡  
ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ። ማቴዎስ 1፡21
ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና። ሉቃስ 2፡11
ኢየሱስ የተወለደው ሰላምን ሊሰጠን ነው
በምንም ምድራዊ ሁኔታ የማይለዋወጥ እውነተኛ ሰላም ፣ ምንም ነገር የማያደፈርሰው ሰላም ከሌለን ኢየሱስ የተወለደበትን አላማ ተጠቃሚ አልሆንም ማለት ነው፡፡
ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና። . . . እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ፦ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ። ሉቃስ 2፡11-14
ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም። ዮሐንስ 14፡27
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ወልድ #ልጅ #አዳኝ #መድሃኒት #ሰላም #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ብርሃን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #መንገድ #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

Thursday, December 22, 2016

ለክብሬም የፈጠርሁት


ክርስቲያን ሁሉ በህይወትህ የምትፈልገው አንድ ነገር ምንድነው ተብሎ ሲጠየቅ የሚመልሰው "እግዚአብሄርን ማክበር" የሚል ነው፡፡ ምንም እንኳን እግዚአብሄርን ማክበር የሚለው ንገግር ሰፊ ፣ ግልፅ ያልሆነና ተጨማሪ ማብራሪያ የሚያስፈልገው መልስ ቢሆንም ትክክለኛ መልስ ነው፡፡ የተሰራነውና የተፈጠርነው ለእግዚአብሄር ክብር ነው፡፡  
በስሜ የተጠራውን ለክብሬም የፈጠርሁትን፥ የሠራሁትንና ያደረግሁትን ሁሉ አምጣ እለዋለሁ። ኢሳይያስ 43፡7
ሁላችንም ልባችን የሚቃጠልለት እግዚአብሄርን የማክበር አላማ ግን ምንድነው ? በህይወታችን የምንፈልገው ምንድነው? እግዚአብሄር ማክበራችንንና አለማክበራችንን እንዴት እናውቃለን? እግዚአብሄርን ማክበራችን እንዴት ይመዘናል? እግዚአብሄርን ማክበራችን እንዴት እናሳካዋለን፡፡ እግዚአብሄርን ማክበር በተግባር ምን ማድረግ ነው? እግዚአብሄርን ማክበራችን እንዴት ይለካል? የሚሉትን ጥያቄዎች መመለስ እግዚአብሄር የማክበር አላማችንን ለማሳካት እጅግ ይጠቅመናል፡፡  
ለእግዚአብሄር ክብር መኖር ማለት
·         ለሌሎች መልካምን ማድረግ ነው

በምናደርገው መልካምነት የእግዚአብሄርን መልካምነት ማሳየት ማንፀባረቅ ነው፡፡ ከምድራዊ ሰዎች የእንካ በእንካ አሰራር የተለየ ከእግዚአብሄር ብቻ የሚገኝን በሁኔታዎች ላይ ያልተደገፈ መልካምነት በመኖር ለሰዎች ወደ እግዚአብሄር ማመልከት ነው፡፡ ሰዎች የእኛን ኑሮ አይተው ይህ የሰው ስራ አይደለም ብለው እግዚአብሄርን ራሱን እንዲያመሰግኑት ማድረግ ነው፡፡ ለሁሉም ሰው መልካምነትን በማሳየት የእግዚአብሄርን ታላቅ ችሎታ ማሳየት ነው፡፡

መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ። ማቴዎስ 5፡16

እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ፤ 1ኛ ጴጥሮስ 2፡9

·         የእግዚአብሄርን ስም መሸከም ማለት ነው

የእግዚአብሄር ስም በመልካም ሁሉ እንዲነሳ ሰዎች በእኛ ህይወት የእግዚአብሄርን ፍቅር እንዲያዩ ማድረግ ነው፡፡ በእኛ ምክኒያት የእግዚአብሄር ስም በክፉ አንዳይነሳ መጠንቀቅ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ስም ከፍ ብሎ እንዲታይ የሚያስፈልገውን መስዋእትነት ሁሉ መክፈል ነው፡፡ እግዚአብሄርን በሚገባ መወከል ማለት ነው፡፡

ጌታም፦ ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና ሂድ፤ ስለ ስሜ ስንት መከራ ሊቀበል እንዲያስፈልገው እኔ አመለክተዋለሁና አለው።ሐዋርያት 20፡15-16

·         ቃሉን በመታዘዝ ፍሬ ማፍራት ነው

ጌታን የምናከብርበትን መመሪያ የእግዚአብሄርን ቃል በመስማትና በመታዘዝ በዚያም ፍሬ በማፍራት ለእግዚአብሄርን ያለንን ፍቅርና አክብሮት ማሳየት ነው፡፡

በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ ይሆንላችሁማል። ብዙ ፍሬ ብታፈሩና ደቀ መዛሙርቴ ብትሆኑ በዚህ አባቴ ይከበራል። ዮሐንስ 15፡7-8

·         ሃጢያትን መፀየፍ ከክፋት መሸሽ ነው፡፡

እግዚአብሄርን ማክበር ሃጢያትን በመፀየፍና በመሸሽ ቅዱስ የሆነውን እግዚአብሄርን በመምሰል ለቅዱሳን እንደሚገባ መኖር ነው፡፡ እግዚአብሄርን ማክበር ስጋችንን ሃጢያት በመከልከል እግዚአብሄርን ደስ ማሰኘት ነው፡፡

ለቅዱሳን እንደሚገባ ግን ዝሙትና ርኵሰት ሁሉ ወይም መመኘት በእናንተ ዘንድ ከቶ አይሰማ፤ ኤፌሶን 5፥3

ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ 6፡19-20

·         የእግዚአብሄርን ፍላጎት መፈፀም ማለት ነው

ከፍላጎታችን በላይ የእግዚአብሄርን ፍላጎት ማሟላት ፣ የእኛን ፍላጎት ወደጎን በማድረግ የእርሱን ፍላጎት ማስቀደም ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለማድረግ ራሳችንን መስጠት ማለት ነው፡፡ ከምንም ስሜታችን በላይ እግዚአበሄርን ለማስደሰት ቅድሚያ መስጠት ነው፡፡

ብትፈቅድ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ አይሁን የአንተ እንጂ እያለ ይጸልይ ነበር። ሉቃስ 22፡42

·         እግዚአብሄርን ብቻ መፍራት ማለት ነው

እንድንፈራቸው የሚፈልጉ በጣም ብዙ ነገሮች ባሉበት አለም ውስጥ እግዚአብሄርን ብቻ መፍራት ፣ እግዚአብሄርን ከሌሎች ጌቶች ጋር አለመቀላቀል ፣ ብቻውን መያዝና በህይወታችን የመጀመሪያውን ስፍራ መስጠት እግዚአብሄርን ከፍ ማድረግ ነው፡፡

ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ አትናወጡም፥ ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት። 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 3፡14-15

·         እግዚአብሄርን ማመን ማለት ነው

በአካባቢያችን ያሉትን ነገሮች ባለማየት የማይታየውን እግዚአብሄርን በቃሉ ማመንና መታዘዝ ነው፡፡ ይህ በተፈጥሮ አይን የማይታየውን እግዚአብሄር በእኛ እንዲታይና እንዲከበር ያደርገዋል፡፡  

እንግዲህ ሁልጊዜ ታምነን፥ በእምነት እንጂ በማየት አንመላለስምና በሥጋ ስናድር ከጌታ ተለይተን በስደት እንዳለን የምናውቅ ከሆንን፥ 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡6-7

·         ገንዘብን አለመውደድ ነው

ገንዘብን ሁሉንም ነገር ሊገዛ እንደማይችል በጣም ውስን እንደሆነ መረዳታችን ፣ መኖሪያችን እግዚአብሄር እንጂ ገንዘብ እናዳይደለ ማወቃችን ፣ ከገንዘብ ይልቅ ወደጌታ መጠጋታችንና ገንዘብን መናቃችን እግዚአብሄርን ያከብረዋል፡፡
ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም። ማቴዎስ 6፡24

·         የነፍሳችንን ጥያቄ መርሳት ነው

ነፍሳችን ብዙ ጥያቄ አላት ፡፡ ጥያቄዋን ሁሉ ከሰማንና ከቃሉ በላይ ካከበርናት እግዚአብሄርን አናከብረውም፡፡ እግዚአብሄርን ለማክበር የነፍሳችንን ጥያቄና ጩኸት መርሳት ይጠይቃል፡፡ ከነፍሳችን በላይ ቃሉን መስማትና መታዘዝ እግዚአብሄርን በህይወታችን ያከብረዋል፡፡

የእግዚአብሄርን ነገር አክብዶ ለመያዝ የራስን ነገር ቀለል አድርጎ መያዝ ይጠይቃል፡፡ ለእግዚአብሄር ስራ ቅድሚያ ለመስጠት የነፍሳችንን ጥያቄ አለመስማትና ቸል ማለት ይኖርብናል፡፡

ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታልና፤ ስለ እኔ ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ግን እርሱ ያድናታል። ሉቃስ 9፡24

ነገር ግን ሩጫዬንና ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልሁትን አገልግሎት እርሱም የእግዚአብሔርን ጸጋ ወንጌልን መመስከር እፈጽም ዘንድ ነፍሴን በእኔ ዘንድ እንደማትከብር እንደ ከንቱ ነገር እቆጥራለሁ። ሐዋርያት 20፥24
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ክብር #ራእይ #አላማ #ግብ #ውሳኔ #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ብርሃን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #መንገድ #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

Saturday, December 17, 2016

የቱ ይቀድማል ውሳኔ ወይስ ራእይ?

ብዙ ሰዎች በአመቱ መጀመሪያ ላይ ውሳኔን ይወስናሉ፡፡ በዚህ አመት እንደዚህ አደርጋለሁ ፣ እንደዚህ እሆናለሁና እንደዚህ አገኛሁ በማለት ለራሳቸው ቃል ይገባሉ፡፡ አንዳንዶቹ እንዳሉትም ማድረግም ይጀምራሉ ነገር ግን አይዘልቁበትም፡፡
ይህ በየአመቱ እየተደጋገመ የሚመጣ በውሳኔ አለመፅናትና የህይወት ለውጥ እጦት ታዲያ የውሳኔ እጥረት ነው ወይስ የሌላ ያሰኛል፡፡
ፍላጎት ብቻውን የሚያመጣው ነገር የለም፡፡ የዚህ ሁሉ ችግር የፍላጎት እጥረት ሳይሆን የራእይ እጥረት ነው፡፡ ፍላጎት በእውቀትና በመረዳት ሲሆን ወደ ፍሬያማነት ያደርሳል፡፡
ሰው የተፈጠረበትን አላማ ሲረዳ ፣ ራእይ ሲኖረውና ሰው የሚሄድበትን ሲያውቅ ሁል ቀን የውሳኔ ቀን ነው ሁል ቀን የተግባር ቀን ነው ሁልጊዜ የፍያማነት ቀን ነው፡፡
ሰው እግዚአብሄር ለምን እንደፈጠረው ከመፅሃፍ ቅዱስ ፈልጎ ሲረዳ ለመኖር ፣ ለመስራትና ለመለወጥ በቂ አቅም ይኖረዋል፡፡  ለተለየ አላማ እግዚአብሄር ወደ ምድር እንዳመጣው የተረዳ ሰው አላማውን ለመፈፀም የማይከፍለው ዋጋ አይኖርም፡፡ በህይወቱ ያለውን የእግዚአብሄርን አላማ የተረዳ ሰው ራእዩ እንዳይተኛ ይጎተጉተዋል፡፡
ለእግዚአብሔር እንደ ማለ፥ ለያዕቆብም አምላክ እንደ ተሳለ፦ በእውነት ወደ ቤቴ ድንኳን አልገባም፥ ወደ ምንጣፌም አልጋ አልወጣም፥ ለዓይኖቼም መኝታ ለሽፋሽፍቶቼም እንቅልፍ፥ ለጕንጮቼም ዕረፍትን አልሰጥም፥ ለእግዚአብሔር ስፍራ፥ ለያዕቆብ አምላክ ማደሪያ እስካገኝ ድረስ ብሎ። እነሆ፥ በኤፍራታ ሰማነው፥ በዱር ውስጥም አገኘነው። መዝሙር 132፡2-6
ሰው ለምን አገልግሎትና ስራ ወደ ምድር እንደመጣ ሲረዳ ስራውን ጨርሶ እግዚአብሄርን እስከሚያከብር አያርፍም፡፡
የቀረውንም ነገር ሳልቆጥር፥ ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው። 2ኛ ቆሮንቶስ 11፡28
በምድር ያለበትን አላማ የተረዳ ሰው ከአላማው ሊያስተጓጉለው የሚመጣውን ማንኛውንም ነገር ይንቃል፡፡
የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና። ዕብራውያን 12፡1-2
ሰው የተፈጠረበትን አላማ ከእግዚአብሄር ሲያገኝ የኋላውን በመርሳት ሁልጊዜ ወደፊት ይዘረጋል፡፡
ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ገና እንዳልያዝሁት እቈጥራለሁ፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ፥ በክርስቶስ ኢየሱስ ከፍ ከፍ ያለውን የእግዚአብሔርን መጥራት ዋጋ እንዳገኝ ምልክትን እፈጥናለሁ። ፊልጵስዩስ 3፡13-14
ህይወታችንን እግዚአብሄር በልቡና በሃሳቡ እንዳለ ለመምራት ራእይ ያስፈልገናል፡፡ ራእይ ሲኖረን የት እንደምንሄድ ስናውቅ ለህይወታችን ጉልበት ይሆነዋል፡፡ ህይወታችንን ለመለወጥ አቅም የሚሰጠን ጥሩ ነገር መፈለጋችን ሳይሆን እግዚአብሄር በህይወታችን ሊሰራ ያለውን መረዳትና ለተፈፃሚነቱ ከእግዚአብሄር ጋር አብሮ መስራት ነው፡፡
ኢየሱስ ግን፦ አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ ብሎ መለሰላቸው። ዮሃንስ 5፡17
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እይታ #ራእይ #አላማ #ግብ #ውሳኔ #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ብርሃን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #መንገድ #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

Friday, December 16, 2016

ሁሉ የእናንተ ነው

1 ቆሮንቶስ 3:21 ሁሉ የእናንተ ነው፡፡
·         የሰጠኸኝን ክብር እኔ ሰጥቻቸዋለሁ
እግዚአብሄር ለኢየሱስ የሰጠውን ክብር ኢየሱስ ለእኛ ሰጥቶናል፡፡ ይህንንም ክብር የሰጠን ኢየሱስ እና አብ አንድ እንደሆኑ እኛም በኢየሱስ አንድ እንድንሆን ነው፡፡   
እኛም አንድ እንደ ሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ፤ እኔም በእነርሱ አንተም በእኔ ስትሆን፥ በአንድ ፍጹማን እንዲሆኑ፥ የሰጠኸኝን ክብር እኔ ሰጥቻቸዋለሁ፤ ዮሐንስ 17፡22
·         መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ በጎ ፈቃድ ነውና
አንተ ታናሽ መንጋ፥ መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ በጎ ፈቃድ ነውና አትፍሩ። ሉቃስ 12፡32
·         ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ ስለ ሰጠን
በህይወት ጌታን ለመከተልና እግዚአብሄር በህይወታችን ያዘጋጀውን መልካሙን ስራ ጨርሰን እንድናከብረው የሚያስፈልገው ወጭ ሁሉ ተሰጥቶናል፡፡  
የመለኮቱ ኃይል፥ በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ፥ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ ስለ ሰጠን፥ በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ። 2ኛ ጴጥሮስ 1፡2-3
·         እግዚአብሄር እረኛችን ነው
መልካም ነገር የሚባል ነገር ሁሉ ተሰጥቶናል፡፡ የሚያስፈልገን ነገር ሁሉ ተሰጥቶናል፡፡ መልካም ከሚባል ነገር አንጎድልም፡፡
እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፥ የሚያሳጣኝም የለም። መዝሙር 1፡23
. . . እግዚአብሔርን የሚፈልጉት ግን ከመልካም ነገር ሁሉ አይጐድሉም። መዝሙር 34፡10
·         መግባት የእኛ ነው፡፡
እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ በመረቀልን በአዲስና በሕያው መንገድ ወደ ቅድስት በኢየሱስ ደም በመጋረጃው ማለት በሥጋው በኩል እንድንገባ ድፍረት ስላለን፥ ዕብራውያን 10፡19-20
·         ንግስና የእኛ ነው
በአንዱም በደል ሞት በአንዱ በኩል ከነገሠ፥ ይልቁን የጸጋን ብዛትና የጽድቅን ስጦታ ብዛት የሚቀበሉ በአንዱ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሕይወት ይነግሣሉ። ሮሜ 5፡17
·         በወደድኸኝም መጠን እነርሱን እንደ ወደድሃቸው
እግዚአብሄር አብ ኢየሱስን በሚወደው መጠን ይወደናል፡፡
እንዲሁም ዓለም አንተ እንደ ላክኸኝ በወደድኸኝም መጠን እነርሱን እንደ ወደድሃቸው ያውቃል። ዮሐንስ 17፡23
ነገር ሁሉ የእናንተ ነውና፤ ጳውሎስ ቢሆን አጵሎስም ቢሆን ኬፋም ቢሆን ዓለምም ቢሆን ሕይወትም ቢሆን ሞትም ቢሆን ያለውም ቢሆን የሚመጣውም ቢሆን፥ ሁሉ የእናንተ ነው፥ እናንተም የክርስቶስ ናችሁ ክርስቶስም የእግዚአብሔር ነው። 1ኛ ቆሮንቶስ 3፡21-23
ይህ ሁሉ የሚሆነው ግን ለሁሉም ሰው አይደለም፡፡ ሁሉ የእናንተ ነው የተባሉት ኢየሱስን የህይወታቸው አዳኝና ጌታ አርገው  የተቀበሉትን ብቻ ነው፡፡
ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ ዮሃንስ 1፡12
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ሁሉየእናንተነውና #መንግስት #ፍቅር #እረኛእግዚአብሄር #ክርስቶስ #የሚያስፈልገውን #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ብርሃን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  #የዋህነት #ንፁህ

Thursday, December 15, 2016

ይህን ያውቁ ኖሯል? የክሪስማስ እውነተኛ ትርጉም

ብዙ ሰው ክሪስማስን ሲያስብ እውነተኛ ትርጉሙን በፍፁም አያስበውም፡፡ ለአንዳንዱ የበአል ሰሞን ነው፡፡ ለሌላው አዲስ አመትን የሚቀበልበት የመጨረሻው ወር ነው፡፡ ለሌላው የክሪስማስ ስርአቶች የሚታዩበት ፣ ቤቶችና ሱቆች በክሪስማስ ዛፍ የሚያሸበርቁበት ፣ ቤትና አካባቢው በክሪስማስ መብራቶች የሚሽቆጠቆጥበት ወቅት ነው፡፡ ለሌላው ክሪስማስ የሚበላበትና የሚጠጣበት ከቤተሰብ ጋር የሚገናኙበት የአመቱ መዝናኛ ጊዜ ነው፡፡ እንዲሁ ለሌላው ክሪስማስ ልብስና ቁሳቁስ የሚለወጥበትና በአዲስ የሚተካበት ጊዜ ነው፡፡
ግን ክሪስማስ ይህ ብቻ ነው? ክሪስማስን ስናስብ ይህን ብቻ የምናስብ ከሆነ የክሪስማስን ዋናውን አላማ ስተነዋል፡፡ ክሪስማስ በዚህ ብቻ ካሰብነው ዋና ነገር በህይወታችን ጎድሏል ማለት ነው፡፡
እውነት ነው አለም ክሪስማስን ዋናው የንግድ ጊዜና የአመቱ ዋናው ንግድ ወቅት አድርጋዋለች፡፡ ክሪስማስ ዋናውን መልክቱን ከመሳቱ የተነሳ የክሪስማስ ዋናው ባለቤት አይጠቀስም፡፡
እወነት የክሪስማስ ትርጉሙና አላማው ይህ ነው? እኛ የምናከብረው ክሪስማስና ለልጆቻችን የምናስተላልፈው ክሪስማስ ይህ ነው?
እውነተኛውን የክሪስማስ ትርጉም እንመልከት፡፡  
ክሪስማስ የምስራች ነው
ሰው በሃጢያት ምክኒያት ከእግዚአብሄር ክብር ወድቆ በሃዘን በነበረበት ጊዜ የኢየሱስ መወለድ ታላቅ የምስራች ነው፡፡  
መልአኩም እንዲህ አላቸው፦ እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና።  ሉቃስ 2፡10-11
ክሪስማስ  ስለተስፋ ይናገራል
ሰው ሁሉ በሃጢያት ከተስፋ ርቆ በነበረበት ጊዜ ለሰው ልጆች ብርሃን ሊሆን ኢየሱስ ወደምድር የመጣበት ኢየሱስ የተወለደበት በአል ነው፡፡ ክሪስማስ ኢየሱስ በመወለዱ የሰው ልጆች የመዳን ተስፋ እንደገና የለመለመበት ነው፡፡
ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ። ማቴዎስ 1፡21
ክሪስማስ  ስለደህንነት ያውጃል
ለሃጢያት መድሃኒት የተወለደበት ጊዜ በመሆኑ ክሪስማስ መድሃኒት ነው፡፡
ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና። ሉቃስ 2፡11
ክሪስማስ ፍቅር ነው
ኢየሱስ ወደምድር የተወለደው ለእኛ ነፍሱን አሳልፎ ለመስጠት ነው፡፡
ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም። ዮሃንሰ 15፡13
ክሪስማስ ስጦታ ነው
የሰው ልጆች በሃጢያታቸው ምክኒያት ለዘላለም ከእግዚአብሄር እንዳይለያዩ ለሃጢያታቸው እዳ እንዲከፍል እንድያ ልጁን ለአለም በስጦታ የሰጠበት በዓል ነው፡፡
በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዮሐንስ 3፡16
ክሪስማስ የብርሃን ጊዜ ነው
የአለም ብርሃን የሆነው የኢየሱስ መወለድ ለአለም በጨለማ ውስጥ የበራ ብርሃን ነው፡፡
በነቢዩም በኢሳይያስ፦ የዛብሎን ምድርና የንፍታሌም ምድር፥ የባሕር መንገድ፥ በዮርዳኖስ ማዶ፥ የአሕዛብ ገሊላ፤ በጨለማ የተቀመጠው ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ፥ በሞት አገርና ጥላ ለተቀመጡትም ብርሃን ወጣላቸው የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሆነ። ማቴዎስ 4፡14-16
ክሪስማስ መስዋእትነት ነው
ኢየሱስ በእግዚአብሄር መልክ ሲኖር ሳለ ስለእኛ ሃጢያት ሰው ሆነ፡፡ ኢየሱስ እኛን ከበደል ለማዳን ከሰው ተወለደ፡፡
ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ፊልጵስዩስ 2፡7-8
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ገና #በዓል #ፍቅር #ተስፋ #ደስታ #መስዋእት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ብርሃን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  #የዋህነት #ንፁህ

Wednesday, December 14, 2016

መንፈሳዊ ቤት

ቤት በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ሰው የሚያርፍበትና የሚያድርበት ቤት ከሌለው አያርፍም፡፡ ሰው ቤት ካለው ደግሞ ነፃነቱ ይበዛል፡፡
እንዲሁም እግዚአብሄር የሚንቀሳቀስበት ፣ የሚናገርበት ፣ የሚገኝበት ፣ የሚያርፍበትና በጎነቱን የሚያስተላልፍበት ቤት ይፈልጋል፡፡ ቤት ሰፋ ባለ ቁጥር ፣ ቤት ንፁህ በሆነ መጠንና ቤት ጠንካራ በሆነ መጠን ለመኖርም ፣ እንግዳን ለመቀበልም ፣ ለማረፍም እንዲሁም ለማደር ያበረታታል፡፡ ቤት ግን በደንብ ካልተሰራ ፣ ንፅህናው በደንብ ካልተጠበቀ ፣ ጠንካራ መሰረት ላይ ካልተመሰረተ ፣ ውበት ከሌለው ለመኖር ፣ ለማረፍና እንግዳ ለመቀበል አይመችም፡፡
እኛም ንፁህ ሰፊ ጠንካራ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ራሳችንን ሰጠንና በተሰራን መጠን እግዚአብሄር በቀላሉ ፣ በደስታና በእረፍት በእኛ ይኖራል በእኛ ይታያል ፣ በእኛ ይናገራል ፣ በእኛ ይወቅሳል ፣ በእኛ ሌሎችን ይደርሳል ፣ በእኛ ያርፋል ፡፡  
እናንተ ደግሞ እንደ ሕያዋን ድንጋዮች ሆናችሁ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕትን ታቀርቡ ዘንድ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ። 1ኛ ጴጥሮስ 2፡5
ቤት ማረፊያና መደሰቻ እንደመሆኑ መጠን የእግዚአብሄር ማረፊያና መደሰቻ ለመሆን እለት በእለት በእግዚአብሄር ቃል መሰራት ይኖርብናል፡፡ ሰው ሌላ ቦታ ቢያዝን ቤቱ ግን ማዘን የለበትም፡፡ ሰው ሌላ ቦታ ቢታመፅበት በቤቱ የሚነገረው ነገር ሁሉ እርሱን የሚያከብርና እርሱን የሚያስደስተው ብቻ መሆን አለበት፡፡   
. . . ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ። ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ። ኤፌሶን 4፡29-30
ቤት መገኛ አድራሻ እንደመሆኑ መጠን የእግዚአብሄር በጎነት የሚገኝበት ፣ የእግዚአብሄር ምህረት የማይታጣበት ፣ የእግዚአብሄር ይቅርታ በልግስና የሚከፋፈልበት ፣ የእግዚአብሄር ፍቅር የማይጠፋበት መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሰሩ፡፡
እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፥ እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ። ኤፌሶን 4፡32
ቤት ንፁህ ነገር ብቻ የሚገኝበት እንደመሆኑ መጠን የእግዚአብሄር ነገር ብቻ የሚገኝበት ከሰይጣን ሃሳብና ከሃጢያት ምኞት የፀዳ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሰሩ፡፡
የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን? ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ።1ኛ ቆሮንቶስ 3፡16-17
ቤት ከምንም አስቀድሞ አስተማማኝ በሆነ አለት መሰረት ላይ እንደሚገነባ ሁሉ በቃሉ መሰረት የእግዚአብሄር ቤት ለመሆን ተሰሩ፡፡
ስለዚህ ይህን ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው ሁሉ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራ ልባም ሰውን ይመስላል። ማቴዎስ 7፡24
ሰው ከምንም በላይ ቤቱን በከበረ ነገር እንደሚያስውበው መጠን በየዋህነትና በዝግተኝነት የተዋበ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሰሩ፡፡
ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ። 1ኛ ጴጥሮስ 3፡4
ቤት የሚስብ ትህትና የሚታይበት ቦታ እንደመሆኑ መጠን በትህትናና በተሰበረ ልብ ለእግዚአብሄር መኖሪያ ቤት ለመሆን ተሰሩ፡፡ 
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሰማይ ዙፋኔ ነው፥ ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት፤ የምትሠሩልኝ ቤት ምን ዓይነት ነው? የማርፍበትስ ስፍራ ምንድር ነው? እነዚህን ሁሉ እጄ ሠርታለችና እነዚህ ሁሉ የእኔ ናቸው፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ነገር ግን ወደዚህ ወደ ትሑት፥ መንፈሱም ወደ ተሰበረ፥ በቃሌም ወደሚንቀጠቀጥ ሰው እመለከታለሁ። ኢሳይያስ 661-2
ኢየሱስም መለሰ አለውም፦ የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን። ዮሃንስ 14፡23
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ትህትና #የእግዚአብሔርቤት #በቃሉመንቀጥቀጥ #ማረፊያ #መኖሪያ #የተሰበረልብ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ማደሪያ #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  #የዋህነት #ንፁህ