Popular Posts

Friday, March 15, 2019

የማንቂያ ደውል


እግዚአብሄርን ለሚወዱ ሰዎች ነገር ሁሉ ለበጎ ይደረጋል፡፡
ለምሳሌ እግዚአብሄርን ስንፈልግ ሰው ቢበድለን በደሉ እኛን የሚጥለን ሳይሆን የሚያነቃን ደውላችን ነው፡፡  
ሰው ሲበድለን ስለበደለን ሰው እንድናውቅ እና እንድንረዳ የማንቂያ ደውል ነው፡፡
ሰው ሲበድለን ስለበደለን ሰው እንድናዝን እንድንራራ የማንቂያ ደውል ነው፡፡
ባይበድለን እንድንፀልይለት ትዝ የማይለን ሰው ቢበድለን ስለበደለን ሰው እንድንፀልይና እንድንማልድ የማንቂያ ደውል ነው፡፡
ባይረግመን ጊዜ ወስደን የማንባርከው ሰው ቢረግመን እንድንባርከው ስለእርሱ መልካም እንድድናስብ መልካም እንድንናገርና መልካም እንድናደርግ የማንቂያ ደውል ነው፡፡
እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፥ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ፤ የማቴዎስ ወንጌል 5፡44
ሰዎች ሲበድሉን የእግዚአብሄርን መልካምነትና ልበ ሰፊነት ስንቱን እንደቻለ እንድናስብ የሚያደርግ የማንቂያ ደውል ነው፡፡
እርሱ በክፎዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፥ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና። የማቴዎስ ወንጌል 5፡45
ሰዎች ሲበድሉን ያሉበትን የህይወት ሁኔታ ችግር ላይ መሆናቸውን ማወቅና አንድ ነገር ማድረግ አለብን፡፡ ሰዎች ሲበድሉን የእኛን ፀሎትና በረከት እንደሚያስፈልጋቸው የማንቂያ ደውሉን መስማትና መረዳት አለብን፡፡ የበደሉንን ሰዎች መልሰን ለመበደል ስንፈተን ይልቁንም በደሉን መልካም ለማድረግ እንደማንቂያ ደውል ልንጠቀምበት ይገባል፡፡
ክፉን በክፉ ፈንታ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ በዚህ ፈንታ ባርኩ እንጂ፥ በረከትን ልትወርሱ ለዚህ ተጠርታችኋልና። 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 3፡9
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #መሪ #ፀጋ #የሚያስችልሃይል #መልካም #ክፉ #አሸንፍ #ብቃት #የእግዚአብሄርችሎታ #የእግዚአብሄርሃይል #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ፅድቅ #እግዚአብሄርንመምሰል #ራስንመግዛት #ልብ #ምስክርነት

Thursday, March 14, 2019

ከፀሎት ወደ ምስጋና ካላደረስክ እምነትህ ለውጤት አልደረሰም


በእግዚአብሄር መልክና አምሳል ለተፈጠረ ሰው እምነት በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ እግዚአብሄር በተፈጥሮአዊ አይን ስለማይታይ ከእግዚአብሄር ጋር የምናደርጋቸው ነገሮች ሁሉ የሚደረጉት በእምነት ነው፡፡ እምነት በተፈጥሮአዊ አይን ማየት የማይታየውንና የማይያዘውን ነገር ማየትና መያዝ ነው፡፡
ከለእምነት ከእግዚአብሄር ጋር ምንም ነገር ማድርግ አይቻለም፡፡ ካለእምንት አግዚአብሄርን ማስደሰት አይቻልም፡፡ ወደ ዕብራውያን 11፡6
ሰው ከእግዚአብሄር እንዲደረግለት በሚፈልገው ነገር ከፀሎት ወደማመስገን ካልተሸጋገረ አላመነም ማለት ነው፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር የሚፈልገው ነገር እንደተደረገለት ማመን አለበት፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር የሚፈልገው ነገር እንደተሰራለት ማወቅ አለበት፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር የሚጠይቀው ነገር እንደተሰጠው መቁጠር አለበት፡፡
ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የጸለያችሁትን የለመናችሁትንም ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ፥ ይሆንላችሁማል። የማርቆስ ወንጌል 11፡24
የእምነት አባታችን አብርሃም የተስፋ ቃሉን ያገኘው አምኖ ማመስገን ሲጀምር ብቻ ነው፡፡
ለእግዚአብሔርም ክብር እየሰጠ፥ የሰጠውንም ተስፋ ደግሞ ሊፈጽም እንዲችል አጥብቆ እየተረዳ፥ በእምነት በረታ እንጂ በአለማመን ምክንያት በእግዚአብሔር ተስፋ ቃል አልተጠራጠረም። ወደ ሮሜ ሰዎች 4፡20-21
ወደማመስገን ያልደረስንበት ነገር አላመንም ማለት ነው፡፡ እንዳመንን የሚመሰክረው ወሳኙ ነገር ማመስገንና ለእግዚአብሄር ክብር መስጠት መጀመራችን ነው፡፡ ከእግዚአብሄር እንዲደረግልን የፈለግነው ነገር እንዳገኘነው ደስ ደስ ካላለን አላመንንም ማለት ነው፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ልብ #ምስጋና #ክብር #ማመን #ቃል #መናገር #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ማሰላሰል #ማድረግ #ሁሉይቻላል #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

Monday, March 11, 2019

ስድብን በስድብ


ከልብ ክፉ አሳብ፥ መግደል፥ ምንዝርነት፥ ዝሙት፥ መስረቅ፥ በውሸት መመስከር፥ ስድብ ይወጣልና። የማቴዎስ ወንጌል 1519
አሁን ግን እናንተ ደግሞ ቍጣንና ንዴትን ክፋትንም፥ ከአፋችሁም ስድብን የሚያሳፍርንም ንግግር እነዚህን ሁሉ አስወግዱ፤ ወደ ቆላስይስ ሰዎች 38
ክፉን በክፉ ፈንታ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ በዚህ ፈንታ ባርኩ እንጂ፥ በረከትን ልትወርሱ ለዚህ ተጠርታችኋልና። 1 የጴጥሮስ መልእክት 39
ስድብ ከስጋ የሃጢያት ስራዎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ስድብ በንግግር ሌላውን ዝቅ ዝቅ ማድረግ ነው፡፡ ስድብ በንቀት ንግግር መናገር ነው፡፡ ስድብ ራስን ከፍ ማድረግና ሌላውን ማዋረድ ነው፡፡ ስድብ ሌላውን በማሳነስ የራስን የራስ ወዳድንት ሃሳብ ለማስፈፀም መሞከር ነው፡፡ ስድብ ሌላውን በማጣጣል የራስን ምሰል መገንባት ነው፡፡
ስድብ ከጥላቻ የሚመነጭ የምድር ፥ የሥጋና የአጋንንትም ጥበብ ነው፡፡  
ከእናንተ ጥበበኛና አስተዋይ ማን ነው? በመልካም አንዋዋሩ ስራውን በጥበብ የዋህነት ያሳይ። ነገር ግን መራራ ቅንዓትና አድመኛነት በልባችሁ ቢኖርባችሁ፥ አትመኩ በእውነትም ላይ አትዋሹ። ይህ ጥበብ ከላይ የሚወርድ አይደለም፤ ነገር ግን የምድር ነው፥ የሥጋም ነው፥ የአጋንንትም ነው፤ ቅንዓትና አድመኛነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ስራ ሁሉ አሉና። የያዕቆብ መልእክት 3፡13-16
ስድብ ሰው ሌላውን በሃሳብ ብልጫ ለማሸነፍ እንደማይችል ተስፋ የቆረጠ የተሸነፈ ሰው ስልት ነው፡፡ ስድብን የሰነፍ መሳሪያ ነው፡፡ ስድብ በአቋራጭ አላማን የማስፈፀሚያ መንገድ ነው፡፡
የሚሳደብ ሰው የሚያሳዝን ሰው ነው፡፡ የሚሳደብ ሰው በጥላቻ እስራት ውስጥ ስላለ ሊታዘንለት የሚገባ ሰው ነው፡፡ የሚሳደብ ሰው ርህራሄ ሊደረግለት የሚገባ ግራ የገባው ሰው ነው፡፡ የሚሳደብ ሰው የበታችነት ስሜቱን በበላይነት ስሜት ሊያካክስ የሚፈልግ ምስኪን ሰው ነው፡፡ የሚሳደብ ስው እውነተኛ የሚለውጥ እና የሚሰራ ሃይልና አቅም ያጠረው ሰው ነው፡፡
በሚሳደብ ሰው ለንቀና አይገባም፡፡ ከሚሳደብ ሰው ጋር በስድብ ፉክክር ውስጥ መግባት የለብንም፡፡ ለተሳዳቢው ማዘንና መራራት እንጂ ሰው የሚሰድበውን ሰው መልሶ ከሰደበ ወደሚሳደበው ሰው ደረጃ ይወርዳል፡፡ የሚሳድብ ሰው ካየን እንድንራራለት እና እንድንፀልይለት እግዚአብሄር እያስታወስን ማለት ነው፡፡ ሰው ሲሳደብ ሁኔታውን በሚገባ መያዝ እንዳቃተው እና ግራ እንደገባው ተረድተን ልናዝንለት ይገባል፡፡ ሰው ሲሳደብ ልንታገሰው መልሰን በመሳደብ ተሳዳቢው ያለው እስራት ውስጥ ላለመግባት ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡
ክፉን በክፉ ፈንታ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ በዚህ ፈንታ ባርኩ እንጂ፥ በረከትን ልትወርሱ ለዚህ ተጠርታችኋልና። 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 3፥9
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ባርኩ #ክፉ #መልካም #በረከት #ልትወርሱ #ትህትና #መልካምነት #መከባበር #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና  #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አንደበት #ከንፈር #ስድብ

Saturday, March 9, 2019

የልቡ አሳብ ምኞትም ሁልጊዜ ፈጽሞ ክፉ እንደ ሆነ


እግዚአብሔርም የሰው ክፉት በምድር ላይ እንደ በዛ፥ የልቡ አሳብ ምኞትም ሁልጊዜ ፈጽሞ ክፉ እንደ ሆነ አየ። ኦሪት ዘፍጥረት 6፡5
እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው በመልካም ልብና ለመልካም ልብ ነበር፡፡ ነፃ ፈቃዱን ተጠቅሞ እግዚአብሄር አታድርግ ያለውን ያንኑ ነገር ካደረገ በኋላ ሰው ከእግዚአብሄር ክብር ወደቀ፡፡ የሰው ልቡ ተበላሸ፡እግዚአብሄር የፈጠረው ሰው የተፈጠረበትን አላማ ስቷል፡፡
የሰው ልብ ከእግዚአብሄር መንገድ እንደወጣና ሰው ክፉ ልብ እንዳለው የሚያሳየው ነገር ምንድነው ብለን መጠየቅ ጥበብ ነው፡፡ የሰውን ልብ ክፉ የሚያደርግውን ነገር ወይም የክፉ ልብ ምልክቶችን ከእግዚአብሄር ቃል እንመልከት፡-
1.      የሰውን ልብ ክፉ እንደሆነ የሚያሳየው ራስ ወዳድ በመሆኑ ነው
የሰው ልብ ከእግዚአብሄር ሲርቅ ራስ ወዳድ ይሆናል፡፡ ሁሉንም ነገር ከራሱ ጥቅም አንፃር እንጂ ከሌላው ጥቅም አንፃር መመልከት አይችልም፡፡ ክፉ ልብ ያለው ሰው ለራሱ ሙሉውን ድርሻ ወስዶ ሌላውን ባዶውን ሲልክ አይሰማውም፡፡
ሰዎችም ሊያደርጉላችሁ እንደምትወዱ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው። የሉቃስ ወንጌል 6፡31
2.     የሰውን ልብ ክፉ እንደሆነ የሚያሳየው በአድልዎ መፍረዱ ነው
የሰው ልብ ክፉ እንደሆነ የሚያሳየው ፍርዱ በመርህ ላይ ያልተመሰረተ ነገር ግን በስሜቱ ላይ የተመሰረተ መሆኑ ነው፡፡ ክፉ ሰው በተመሳሳይ ጉዳይ ለአንዱ የሚፈርደው ፍርድና ለሌላው የሚፈርደው ፍርድ ይለያያል፡፡ ክፉ ልብ ያለው ሰው የሚፈረርደው ፊትን አይቶ ነው፡፡ ክፉ ልብ ያለው ሰው ወጥ የሆነ በመርህ ላይ የተመሰረተ ፍርድ የለውም፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ተመሳሳይ ጥፋት ላጠፉ ሁለት ሰዎች ያለው ምዘና የተለያየ ነው፡፡ ፍርዱ የሚወሰነው በሰዎቹ ላይ እንጂ በመርህ ላይ አይደለም፡፡ ክፉ ልብ ያለው ሰው ሰዎቹን ሳያይ በመርህ ብቻ መፍረድ አይችልም፡፡ አንዱ ሲሰራው ትክክል ነው የሚለውን ነገር ሌላው ሲሰራው ስህተት ነው ይለዋል፡፡
3.     የሰው ልብ ክፉ እንደሆነ የሚያሳየው ለሌላው ባለው ንቀት ነው  
ሌላውን የሚንቅ እና ዝቅ ዝቅ አድርጎ የሚመለከት ሰው ክፉ ልብ ያለው ሰው ነው፡፡ ሌላው ሰው ሁሉ የእርሱ ታናሽ እርሱ ብቻ ታላቅ እንደሆነ በትእቢት የሚያስብ ሰው ልቡ ክፉ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ የሌላውን ችግርና መከራ እንደራሱ አድርጎ የማያይ እና የሰው መከራና ችግር የማይሰማው ሰው ክፉ ልብ ያለው ሰው ነው፡፡ ራሱን በሌሎች ቦታ የማስቀምጥ እኔ ብሆን ኖሮ ምን እሆን ነበር ብሎ የሌሎችን መጎዳት ለማየት የማይፈልግ ሰው ክፉ ልብ ያለው ሰው ነው፡፡ አላግባብ ከተጠቃ ሰው ጋር ራሱን ለማስተባበር የሚፀየፍ እና የትህትናን ነገር ለማደርግ የማይፈልግ ሰው ክፉ ልብ ያለው ሰው ነው፡፡
እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማሙ፤ የትዕቢትን ነገር አታስቡ፥ ነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ። ልባሞች የሆናችሁ አይምሰላችሁ። ወደ ሮሜ ሰዎች 12፡16
4.     የሰውን ልብ ክፉ እንደሆነ የሚያሳየው ሰውን በሰውነቱ ሳይሆን በሃብቱ በዝናውና በሃይሉ ሲያከብር ነው
ክፉ ልብ ያለው ሰው አክብሮቱ በሰው ሃብትና ዝና ላይ ይመሰረታል፡፡ ክፉ ልብ ያለው ሰው ሰውን የሚያከብረው ሃብቱን አይቶ በእበላ ባይነት ነው፡፡ ክፉ ልብ ያለው ሰው ዝነኛን ሰው የሚያከበርው ሃያል ስለሆነ ክፉ ሊያደርግብኝ ይችላል በሚል ፍርሃት እንጂ በእግዚአብሄር መልክና አምሳል ስለተፈጠረ ስለ ሰውነቱ ብቻ አይደለም፡፡ ክፉ ልብ ያለው ሰው ሰውን በሰውነቱ ስለማያከብር ድሃን ይንቃል ደካማው ላይ ይበረታል፡፡
የወርቅ ቀለበት ያደረገና የጌጥ ልብስ የለበሰ ሰው ወደ ጉባኤአችሁ ቢገባ፥ እድፍ ልብስም የለበሰ ድሀ ሰው ደግሞ ቢገባ፥ የጌጥ ልብስም የለበሰውን ተመልክታችሁ፦ አንተስ በዚህ በመልካም ስፍራ ተቀመጥ ብትሉት፥ ድሀውንም፦ አንተስ ወደዚያ ቁም ወይም ከእግሬ መረገጫ በታች ተቀመጥ ብትሉት፥ ራሳችሁን መለያየታችሁ አይደለምን? ክፉ አሳብ ያላቸውም ዳኞች መሆናችሁ አይደለምን? የያዕቆብ መልእክት 2፡2-4
5.     ክፉ ልብ ያለው ሰው ወገንተኛ ነው
ክፉ ልብ ያለው ሰው የሚያዳላው ለራሱ ወይም ለእኔ ስለሚለው ሰው ነው፡፡ ክፉ ልብ ያለው ሰው የእኔ ወገኔ  ነው ስለማይለው ሰው ምንም ግድ የለውም፡፡ ክፉ ልብ ያለው ሰው ሌላው ሲጎዳ ሲያይ አይቶ እንዳላየ ያልፋል እንጂ ለሌላው ወገን አይናገርም አይከራከርም፡፡
ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፥ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር፤ ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 2፡4
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ህይወት #የሚፈርድ #የሚያማ #ወንጌል #መውደድ #ፍቅር #የህይወትምስክርነት #መታዘዝ #ማገልገል #መውደድ #እውነት #ትህትና #ትንሳኤ #ህይወት #ወንጌል #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ  #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Friday, March 8, 2019

ፍራ


ፍራ እንጂ የትዕቢትን ነገር አታስብ። ወደ ሮሜ ሰዎች 1120
በህይወት የወደቁ ሰዎች ሁሉ ከመውደቃቸው በፊት እኔ አልወድቅም ብለው አስበው ነበር፡፡ በህይወት የወደቁ ሰዎች ሁሉ ከመውደቃቸው በፊት በኩራት አስበው ነበር፡፡ በህይወት የወደቁ ሰዎች ሁሉ ከመውደቃቸው በፊት ይህ ውድቀት በእኔ ላይ አይደርስም ብለው በኩራት አስበው ነበር፡፡ ከመውደቃቸው በፊት ይህን እንዳሰቡ ማረጋገጫው ላለመውደቅ አለመፍራታቸውና ብሎም በመጨረሻም መውደቃቸው ነው፡፡
ሰው መፍራቱን ሲተውና ሃሳቡን በእርጋታ ከመቆጣጠር ይልቅ ሃሳቡን እንደፈለገ ሲለቀው ለውድቀት ይጋለጣል፡፡ ሰው ከመጠን በላይ ሲዝናናና ሃሳቡን መቆጣጠር ሲያቅተው ይስታል፡፡
እንደ ባለ አእምሮ እንዲያስብ እንጂ ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ በተሰጠኝ ጸጋ እናገራለሁ። ወደ ሮሜ ሰዎች 12፡3
ከሰው ውስጥ ፍርሃት ከጠፋና ሰው በትእቢት ካሰበ የጊዜ ጉዳይ ብቻ ነው እንጂ መውደቁ አይቀሬ ነው፡፡
ትዕቢት ጥፋትን፥ ኵሩ መንፈስም ውድቀትን ይቀድማል። መጽሐፈ ምሳሌ 16፡18
እንዳይወድቁ መፍራትና ራስን በትህትና ማዋረድ መልካም ነገር ነው፡፡ ሰው ራሱን ማዋረድ ካልቻለ ሁኔታዎች ያዋርዱታል፡፡ ሰው ክቡር ነው፡፡ ሰውን ሌላ ሰው ሲያዋርደው መልካም አይደለም፡፡ ሰውን ሁኔታ ሲያዋርደው መልካም አይደለም፡፡ የተሻለው ነገር ሰው እንዳይወድቅ መፍራቱና ራሱን ማዋረዱ ነው፡፡
ብልህ ሰው ክፉን አይቶ ይሸሸጋል፤ አላዋቂዎች ግን አልፈው ይጐዳሉ። መጽሐፈ ምሳሌ 22፡3
ፍራ እንጂ የትዕቢትን ነገር አታስብ። ወደ ሮሜ ሰዎች 11፥20  
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ክብር #ትእቢት #ኩራት #እግዚአብሄር #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ትህትና #ራስንማዋረድ #ፅናት #ትግስት #መሪ

Thursday, March 7, 2019

እግዚአብሔርም ቤት ይፈልጋል !

እግዚአብሔርም ቤት ይፈልጋል !
ኢየሱስም መለሰ አለውም፦ የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን። የዮሐንስ ወንጌል 14፡23
ሰው በተፈጥሮው ቤቴ የሚለው ማረፊያ ቦታ ይፈልጋል፡፡ ሰው ከዚያ እየተነሳ የሚሰራበት የሚማርበት የሚንቀሳቀስበት መነሻ ቤት ይፈልጋል፡፡ ሰው ሰዎች ሌሎች ሰዎች ሲፈልጉት የሚገኝበት እንግዳውን የሚቀበልበት የሚያስተናግድበት ቤት ይፈልጋል፡፡
እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው ለእርሱ ማረፊያ መኖሪያ ቤት እንዲሆን ነው፡፡
እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው የሚናከትረብት መድረክ እንዲሆንለት ነው፡፡
እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው መልካምነቱን የሚያሳይበት ቦታ እንዲሆንለት ነው፡፡
እግዚአብሄር ሰው በሰራው ቦታ ውስጥ አይኖርንም፡፡ እግዚአብሄር ደስ ብሎት የሚያርፈው እና የሚኖረው ራሱ በሰራውና በፈጠረው ሰው ውስጥ ነው፡፡
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሰማይ ዙፋኔ ነው፥ ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት፤ የምትሠሩልኝ ቤት ምን ዓይነት ነው? የማርፍበትስ ስፍራ ምንድር ነው? እነዚህን ሁሉ እጄ ሠርታለችና እነዚህ ሁሉ የእኔ ናቸው፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ነገር ግን ወደዚህ ወደ ትሑት፥ መንፈሱም ወደ ተሰበረ፥ በቃሌም ወደሚንቀጠቀጥ ሰው እመለከታለሁ። ትንቢተ ኢሳይያስ 66፡1-2
ሰው በተፈጥሮው ንፁህ ቤት ውስጥ መኖር እንደሚፈልግ ሁሉ እግዚአብሄርም የሚኖርበት ንፁህ ቤት ንፁህ ህይወት እንዲሆንለት ይፈልጋል፡፡ 
ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 6፡19-20
መፅሃፍ ቅዱስ ለእግዚአብሄር መኖሪያ ሆናችሁ ተሰሩ በማለት ያዘናል፡፡
እናንተ ደግሞ እንደ ሕያዋን ድንጋዮች ሆናችሁ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕትን ታቀርቡ ዘንድ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ። 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 2፡5
ባደግን ፣ በሰፋንና በነፃን መጠን ለእግዚአብሄር ይበልጥ የሚመች መኖሪያና ማገልገያ ቤት ሆን እንሰራለን፡፡
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ትህትና #የእግዚአብሔርቤት #በቃሉመንቀጥቀጥ #ማረፊያ #መኖሪያ #የተሰበረልብ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ማደሪያ #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  #የዋህነት #ንፁህ

Monday, March 4, 2019

ለመውደድና ለመወደድ

ሰው ለመውደድና ለመወደድ ፍቅር በሆነው በእግዚአብሄር ተፈጥሮአል፡፡ ሰው ካልወደደና ካልወደደ የተፈጠረበትን አላማ ስቷል ማለት ነው፡፡
እኛም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር አውቀናል አምነንማል። እግዚአብሔር ፍቅር ነው፥ በፍቅርም የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል። 1ኛ የዮሐንስ መልእክት 4፡16
ሰው ሲፈጠር ለሌላው ሰው ከሚያካፍለው መልካም ስጦታ ጋር ተፈጥሮአል፡፡ በሰው ውስጥ ያለው ነገር ለሌላው ሰው የሚጠቅም ነገር ነው፡፡
ሰው ያለምክኒያት ለመውደድ ዲዛይን ተደርጎ ስለተፈጠረ ሰው ሌላውን ካልወደደ ፣ በውስጡ ባለው ነገር ሌላውን ካልጠቀመና ካላገለገለ የተፈጠረበትን አላማ ይስታል፡፡
በተሰጠንም በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለ ፈሰሰ ተስፋ አያሳፍርም። ወደ ሮሜ ሰዎች 5፡5
ሰው ሌላውን ለመውደድ ብቻ ሳይሆን ለመወደድም ደግሞ ተፈጥሮአል፡፡ ሰው እርሱን የሚወደውና የሚፈልገው ሰው ይፈልጋል፡፡ ሰው ሲፈጠር ከከበረ ነገር ጋር ስለተፈጠረ ያለውን የከበረ ነገር እውቅና የሚሰጠው ሰው ይፈልጋል፡፡ ሰው አስፈላጊነቱንና ጠቃሚነቱን እውቅና የሚሰጠውን ሰው ይፈልጋል፡፡ ሰው ህይወቱ ለሌላው ሰው አስፈላጊ እንደሆነ ማወቅ ይፈልጋል፡፡ ሰው መፈለግ መወደድ ይፈልጋል፡፡     
ሰው ህይወቱ ለሌሎች የሚጠቅም ትርጉም ያለው ህይወት እንዲሆን ይፈልጋል፡፡ ሰው ህይወቱ ለሌሎች የሚጠቅም አስፈላጊ እንደሆነ ማወቅ ይፈልጋል፡፡ ሰው ለሌላው ጠቃሚና አስፈላጊ እንደሆነ ካላወቀ የህይወት ጣእሙን ያጣዋል፡፡
ሰው በእግዚአብሄር እንደተወደደ ካወቀ በሌላ በማንም ሰው ሊወደድ እንደሚችል ማመን አያቅተውም፡፡ ሰው በእግዚአብሄር እንደተወደደ ካወቅ የመወደድ ፍላጎቱ ይረካል፡፡ ሰው በእግዚአብሄር እንደተወደደ ማወቁ ብቻ በሰው ያለመወደዱን ፈተና ተቋቁሞ እንዲያልፍ ይረዳዋል፡፡ በምድር ላይ መኖሩ ለእግዚአብሄር ትርጉም እንዳለው ካወቀ ሰው በምድር ላይ መኖሩ ለሌላው ሰው ትርጉም እንዳለው ማወቅ አያቅተውም፡፡
እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ፥ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ። የዮሐንስ ወንጌል 13፡34
ሰው በእግዚአብሄር እንደተወደደ ካወቀ ሌላውን ለመውደድ ፣ ለመጥቀምና ለማገልገል አቅም ያገኛል፡፡ የሰው ህይወቱ ትርጉም የሚያገኘው በእግዚአብሄርና በሰው መወደዱን ሲረዳና እግዚአብሄርን እና ሰውን ሲወድ ነው፡፡ 
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ፍቅር #መውደድ #መወደድ #ማስተዋል #እግዚአብሔርንመፍራት #ጥበብ #ክፉ #መልካም #መጥቀም #እውቅና #ፍፁም #ማገልገል #መፍትሄ #አላማ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ  #እምነት #ቃል  #ማደስ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ