Popular Posts

Wednesday, January 18, 2017

የየዋህነት ክብር

የጌታም ባሪያ ለሰው ሁሉ ገር ለማስተማርም የሚበቃ ለትዕግሥትም የሚጸና ሊሆን እንጂ ሊጣላ አይገባውም። ደግሞም፦ ምናልባት እግዚአብሔር እውነትን ያውቁ ዘንድ ንስሐን ይሰጣቸዋልና ፈቃዱን ለማድረግ በዲያብሎስ ሕያዋን ሆነው ከተያዙበት ወጥመድ ወጥተው፥ ወደ አእምሮ ይመለሳሉ ብሎ የሚቃወሙትን በየዋህነት ይቅጣ። 2ኛ ጢሞቴዎስ 2፡24-26
የዋህነት የመንፈስ ፍሬ እንደሆነና መንፈሳዊ ውጤታችንና ፍሬያማነታችነ የሚለካበት ወሳኝ ባህሪ እንደሆነ መፅሃፍ ቅዱስ ያስተምራል፡፡
የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት ራስን መግዛት ነው። ገላትያ 5፡22
በነገር ሁሉ ምሳሌያችን የሆነው ኢየሱስ የዋህ ነበረ፡፡ ከእኔም ተማሩ ብሎ ያስተምረናል፡፡ 
ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤  ማቴዎስ 11፡29
የዋህነት የጥሪያችን ደረጃ ነው፡፡ ከየዋህነት ያነሰ ኑሮ እንድንኖር አልተጠራንም፡፡  ለጥሪያችን እንደሚገባ መኖር በየዋህነት መኖር ነው፡፡
እንግዲህ በጌታ እስር የሆንሁ እኔ በተጠራችሁበት መጠራታችሁ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እለምናችኋለሁ፤ በትሕትና ሁሉና የዋህነት በትዕግሥትም፤ እርስ በርሳችሁ በፍቅር ታገሡ፤ ኤፌሶን 4፡1-2
ስለየዋህነት መፅሃፍ ቅዱስ ብዙ ያስተምራል፡፡ ለምሳሌ ያህል ይህን ያህል ስለ የዋህነት አስፈላጊነት ካየን የየዋህነትን ትርጉም እንመልከት፡፡
ግን የዋህነት ምንድነው?
የዋህነት በብዙ ቃላት ሊተረጎም የሚችል ቃል ነው፡፡ የየዋህነትን ትርጉም እንመልከት፡-
ቸር
መልካምና ርህሩህ አዛኝ ስለሌላው ግድ የሚለው
ክፉና ግፈኛ ያልሆነ  
ለሰው የሚጠነቀቅ ፣ ግዴለሽ ያልሆነ ፣ ራስ ወዳድ ያልሆነ ፣ የሰውን ፍላጎት የሚያከብር
ልከኛ  
ለጥቅም የማይስገበገብ ፣ በቃኝ የሚል ፣ ለመኖር ብዙ ነገር የማይጠይቅ
የተከበረ  
ሰዎች የሚያከብሩት ፣ ክብሩን ጠብቆ የሚኖር ፣ የሚያዋርደውንና የሚያስንቀውን ክፉ ነገር የማያደርግ
ጨዋ
የተገራ ፣ ለጥቅም የማይጣላ ፣ በራስ ወዳድነት የማይከራከር
ሰላማዊ
ሰላም ያለው ፣ ለሌላም ሰላም የሚሰጥ ፣ አስጊ ያልሆነ
አክባሪ
ሰውን አክባሪ ፣ ሰውን የማይንቅ ፣ ለሰው ትልቅ ስፍራ ያለው
ጭምት
ረጋ ያለ ፣ የማይቸኩል ፣ ቁጥብ ፣ ስሜቱን የሚገዛ
በተራ ነገር ላይ የማይገኝ
በትክክለኛው መንገድ የማይመጣን ጥቅም የሚንቅ ፣ ነውረኛ ረብ የማይወድ
ደረጃው ከፍ ያለ
መልካም ባህሪ ያለው በሚሉት ቃላት ሊገለፅ ይችላል፡፡
በጣም ልቤን የነካኝ ይህን ሁሉ ሃሳብ ይበልጥ ሊገልፅ የሚችል የሚርያም ዌብስተር የመዝገበ ቃላት ትርጉምን ላካፍላችሁ፡፡  
Gentleman a :  a man of noble or gentle birth d :  a man of independent means who does not engage in any occupation or profession for gain  
Gentleman የዋህ ፡- የነገስታት ቤተሰብ አባል የሆነ ጥቅም ለማግኘት ማንኛውንም ሥራ ወይም ሙያ ለመሰማራት የማይፈልግ ነፃ ሰው ማለት ነው፡፡
እኛ ኢየሱስን አንደአዳኝና ጌታ የተቀበልን ክርስቲያኖች ይህ መግለጫ በትክክል ይገልጠናል፡፡ አሁን የእግዚአብሄር ልጆች ሆነናል፡፡ የምንሰራው ለመኖር አይደለም፡፡ ለመኖር አንጨነቅም፡፡ ለኑሮዋችን የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ የሚያዘጋጀው አባታችን እግዚአብሄር ነው፡፡
እኛ የምንሰራው ከፍ ላለ ነገር ነው፡፡እኛ የምንሰራው ለመንግስቱ ነው፡፡ እኛ የምንፈልገው የእግዚአብሄርን ፅድቅ ነው፡፡ ሌላ ሁሉ በእግዚአብሄር የሚጨመርልን የእግዚአብሄር ቤተሰብ አባላት ነን፡፡
እንግዲህ፦ ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ማቴዎስ 6፡31-33
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos


Tuesday, January 17, 2017

የልጅነትን ስልጣን መረዳት

ሰው ሲፈጠር በእግዚአብሄር ክብር ነው የተፈጠረው፡፡ ሰው ሲፈጠር በእግዚአብሄር መልክና አምሳል ነው የተፈጠረው፡፡ ሰው በሃጢያት ምክኒያት ስልጣኑን ለሰይጣን አሳልፎ ሰጥቶ ነበር፡፡ ኢየሱስ የሃጢያታችንን እዳ በመስቀል ላይ በመሞት ለመክፈል ወደ ምድር መጣ፡፡
ኢየሱስ የሞተውና ከሙታን የተነሳው ስለእኔ ሃጢያት ነው ብሎ ኢየሱስን እንደ አዳኙና የህይወቱ ጌታ አድርጎ የሚቀበለውን ማንኛውም ሰው እግዚአብሄር ልጅ አድርጎ ወደ ቤተሰቡ ይቀበለዋል፡፡ የልጅነት ስልጣኑን ይመልስለታል፡፡
ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ ዮሐንስ 1፡12
ግን የእግዚአብሄ ልጅነት ስልጣን ምንድነው?
1.      የእግዚአብሄር ልጅነት ስልጣን ከእግዚአብሄር ጋር ለዘላለም የመኖር ስልጣን ነው፡፡
ሃጢያት የሰውን ልጅ ከእግዚአብሄር ተልይቶዋል፡፡ የሃጢያት ደሞዝ ሞት በመሆኑ ሰው ከእግዚአብሄር ለዘላለም ተለይቶዋል፡፡ የሰው ልጅ ሁሉ በሃጢያት ውጤት በዘላለም ሞት ፍርድ ስር ወድቆዋል፡፡ ኢየሱስን የተቀበለ ሰው እግዚአብሄር ስለሚቀበለው ለዘላለም ከእግዚአብሄር ጋር የመኖር ስልጣን አለው፡፡
በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዮሃንሰ 3፡16
2.     የእግዚአብሄር ልጅነት ስልጣን የእግዚአብሄር መኖሪያ የመሆን ስልጣን ነው፡፡

ኢየሱስን በተቀበለ ሰው ውስጥ እግዚአብሄር ይኖራል፡፡ ኢየሱስን የሚከተለ ሰው መንፈስ ቅዱስ ቤተመቅደስ ነው፡፡

የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን? 1ኛ ቆሮንቶስ 3፡16

3.     የእግዚአብሄር ልጅነት ስልጣን የመንፈሱን መያዣ የመቀበያ ስልጣን ነው፡፡

ሰው አንድ እቃ ለመግዛት ፈልጎ ገንዘብ ቢጎድለው እቃውን መግዛት እንደሚፈልግ ማረጋገጫ ቀብድ ይከፍላል፡፡ ቀብድ የከፈለው ሰው እያለ እቃው ለሌላ ሰው አይሸጥም፡፡ ያን ቀብድ የከፈለ ሰው ሌላ ጊዜ መጥቶ የቀረውን ዋጋ ሲከፍል እቃው የእርሱ ይሆናል፡፡

ነገር ግን ለዚሁ የሠራን እግዚአብሔር ነው እርሱም የመንፈሱን መያዣ ሰጠን። 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡5

እንዲሁንም እኛ የእግዚአብሄር መሆናንችንን ደግሞም በመጨረሻው ዘመን እግዚአብሄር ጠቅልሎ የራሱ እንደሚያደርገንም ማረጋገጫ መንፈሱን እንደቅድሚያ ክፍያ ቀብድ ሰጭጥቶናል፡፡ የእግዚአብሄ ልጅ የሆነ ሰው የቤተሰቡ መንፈስ መንፈስ ቅዱስን የመሞላት ስልጣን አለው፡፡

4.     ለሚበላና ለሚጠጣ ከመጨነቅ በላይ እንድንኖር ስልጣን ተሰጥቶናል

እግዚአብሄር  አባታችን ነው፡፡ አባታችን እግዚአብሄ ከእኛ የሚፈልገው የእግዚአብሄርን መንግስትና ፅድቁን እንድንፈልግ ነው፡፡ አህዛብ የሚፈልጉትን እንዳንፈልግ ስልጣን ተሰጥቶናል፡፡ እኛ እንድንፈልግ የታዘዝነው የእግዘኢአብሄርን ፅድቅና መንግስቱን ነው፡፡ ሌላው እንዲጨመርልን ስልጣን ተሰጥቶናል፡፡

5.     በእግዚአብሄር ልጅነታችን በሃጢያት ላይ ስለጣን ተሰጥቶናል

የእግዚአብሄር ልጆች ከሆንን በኋላ ሃጢያት አይገዛንም፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሲሞት የሃጢያተኛ ስጋችንን በመስቀል ላይ ሰቅሎታል፡፡ ስለዚህ አሁን ከሃጢያት ሃይል ነፃ ወጥተናል፡፡ በሃጢያት ላይ ሃይል ተሰጥቶናል፡፡

ኃጢአት አይገዛችሁምና፤ ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች አይደላችሁምና። ሮሜ 6፡14

6.     በሰይጣል ላይ የእግዚአብሄር ልጅነት ስልጣን አለን

ኢየሱስ በምድር ላይ ሰይጣንን ድል ነስቶታል፡፡ ኢየሱስ ሰይጣንን ድል የነሳው በእኛ ምትክ ለእኛ ነው፡፡

አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው። ቆላስይስ 2፡15

እንዲህም አላቸው ሰይጣንን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ። እነሆ፥ እባቡንና ጊንጡን ትረግጡ ዘንድ፥ በጠላትም ኃይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፥ የሚጐዳችሁም ምንም የለም። ሉቃስ 10፡18-19

7.     የእግዚአብሄር ልጅነት ስልጣን ከሁኔታዎች በላይ እንድኖር የሚያስችል ታላቅ ስልጣን ነው፡፡

እግዚአብሄር በህይወታችን ካስቀመጠው አላማ ሊያደናቅፈን በሚመጣ በማንኛውም ሁኔታ ላይ ስልጣን ተሰጥቶናል፡፡

በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥ ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ።  ሮሜ ሰዎች 8፡37-39
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ክብር #ስልጣን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና #እምነት #ሃይል #ልጅነት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Monday, January 16, 2017

በመዋረዳችን እንጠቀማለን

ጌታን ኢየሱስን የምንከተል ሁላችን በእግዚአብሄር ፊት የከበርን ነን፡፡
ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤ አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው። ሮሜ 8፡29-30
ስለዚህ ነው በምድር ላይ የምናልፍባቸው ከፍታዎችና ዝቅታዎች ሊያሸንፉን የማይችሉት፡፡ ጠላት እኛን ለመጣል የሚያመጣውን እንኳን እግዚአብሄ ለከፍታችን ይጠቀምበታል፡፡
በአንድም በሌላም መልኩ የሚዋርዱ ነገሮች በህይወታችን ይመጣሉ፡፡ ነገሮች ሊያዋርዱን በጉድለት በመጡ መጠን እግዚአብሄር የሚክስበት የራሱ መንገድ አለው፡፡ በጎደለን ቅፅበት የሚሞላ የእግዚአብሄር ፀጋ በህይወታቸን ይሰራል፡፡
በሳይንስ ስንማር አንድ ምንም ውሃ ያልያዘ ብርጭቆ ባዶ አይደለም ተብለን ተምረናል፡፡ ባዶው ብርጭቆ ውሃ ባይኖረውም ውሃው የጎደለበትን ቦታ ሁሉ የሚሞላ በባዶ አይናችን የማናየው አየር አለ፡፡
የእግዚአብሄርም አሰራር እንዲዚሁ ነው፡፡ ሰይጣን ሊያጠቃን የሚችለው በሚታየው ነገር ብቻ ነው፡፡ በሚታየው ነገር ሊያዋርደን ሲመጣ እግዚአብሄር በማይታየው በከበረው በተሻለው ነገር ጉድለታችንን ይሞላል፡፡ በሚታየው ነገር ተዋረድን ማለት በማይታየው ነገር ከበርን ማለት ነው፡፡  
በሚታይ ነገር 100 እጅ ሞልቶልኛል የሚያዋርደኝ ምንም ነገር የለም የሚል ማንም ሰው እንደሌለ ሁሉ ሁላችንም ዘወትር የሚያበረታውን የእግዚአብሄርን ፀጋ እንፈልጋለን፡፡ በጎደለን በማንኛውም እጅ የእግዚአብሄ ፀጋ ስለሚሞላብን ሁልጊዜ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን፡፡ ለእኛ መዋረዳችን እንኳን በሌላ መልኩ ጥቅም ነው፡፡
እርሱም፦ ጸጋዬ ይበቃሃል፥ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና አለኝ። እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ። 2ኛ ቆሮንቶስ 12፡9
አዳምና ሄዋን በሃጢያት ከመውደቃቸው በፊት ምንም ልብስ ባይለብሱም ራቁትነታቸው አይታይም ነበር፡፡ ራቁትነታቸውን የሚሸፍን የእግዚአብሄርምን ፀጋ ለብሰው ነበር፡፡  
የሚታይ ነገር ሲጎድል የእግዚአብሄር ፀጋ የሚያስችለን ሃይሉ ቦታውን እየያዘ ይመጣል፡፡ የሚታይ ነገር ሲጎድል የማይታየው የእግዚአብሄር ሃይል እያበረታን ይመጣል፡፡ በነገሮች ስንዋረድ በእግዚአብሄር አሰራር ከፍ ከፍ እንላለን፡፡ በመዋረዳችን በሚያበረታ ፀጋ ለእኛ ማሸነፍ ሁልጊዜ ነው፡፡
ነገር ግን በክርስቶስ ሁልጊዜ ድል በመንሣቱ ለሚያዞረን በእኛም በየስፍራው ሁሉ የእውቀቱን ሽታ ለሚገልጥ ለአምላክ ምስጋና ይሁን፤ 2ኛ ቆሮንቶስ 2፡14
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ክብር #መዋረድ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና #እምነት #አንድነት #ፀጋ  #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Sunday, January 15, 2017

የፍላጎት ማጣት ሶስቱ ምክኒያቶች

በክርስትና ህይወት የእግዚአብሄርን ነገር መራብና መጠማት ወሳኝ ነው፡፡ ፅድቅን መራብና መጠማት የመንፈሳዊ ጤንነት ምልክት ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ነገር የሚራቡና የሚጠሙ ሰዎች ብፁአን ናቸው፡፡
ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፥ ይጠግባሉና። ማቴዎስ 5፡6
በክርስትና ህይወታቸው ፅድቅን መራብ ጀምረው ሲቆይ ወደኋላ ያሉ ብዙ ሰዎችን እናውቃል፡፡ በመልካም ጀምረው የፅድቅ ረሃብና ጥማታቸው በመንገድ ላይ የጠፋባቸው አያሌ ሰዎች ታዝበናል፡፡ የጌታን ቃል ሰምተው የማይጠግቡ የነበሩ በኋላ ግን ያንን ወሳኝ ረሃብና ጥማት የጣሉ ሰዎችን ታዝበናል፡፡
ረሃባችንንና ጥማታችንን የማጣት አደጋ በሁላችንም ላይ አለ፡፡ ፍላጎት ማጣት ሁላችንንም ሊፈትንና ሊጥል የሚችል ፈተና ነው፡፡ ዝለን የእግዚአብሄርን ነገር በትጋት ከመፈለግ ዘወር እንድንል እንፈተናለን፡፡
በነፍሳችሁ ዝላችሁ እንዳትደክሙ፥ ከኃጢአተኞች በደረሰበት እንዲህ ባለ መቃወም የጸናውን አስቡ። ዕብራውያን 12፡3
ይህንን ወሳኝ በረከት እንድናጣው የሚያደርገን ነገር ምን እንደሆነ ማወቅ በዚያ ወጥመድ ውስጥ እንዳንወድቅ ይረዳናል፡፡
1.      ቃሉን በሚዛናዊነት አለመጠበቅ

ለፅድቅ ያለንን ረሃብና ጥማት ሊያጠፋውና ከሩጫችን ሊገታን የሚችለውና ነገር አንድን የእግዚአብሄር ሃሳብ ብቻውን በከፍታ ይዞ ሌላውን መጣል ወይም ማሳነስ ነው፡፡ አንዱን የእግዚአብሄ ቃል ለማጠናከር ሌላውን ማሳነስ የለብንም፡፡ የእግዚአብሄር ቃል ሙሉ ነው፡፡ ሁሉም የእግዚአብሄር ቃል ጠቃሚ ነው፡፡ ሙሉ የእግዚአብሄር ቃል ነው ሙሉ የሚያደርገን፡፡

ሰው ድንችን ብቻ በየእለቱ በመመገብ ጤናማና ብርቱ ሊሆን አይችልም፡፡ እንዲሁም ሰው ያልተመጣጠነና ሚዛኑን ያልጠበቀ ትምህርት በመመገብ ለእግዚአብሄር ነገር ያለውን ጤናማ ፍላጎት ሊያጣው ይችላል፡፡

ለሰው መንፈሳዊ ጤንነት ሙሉ የእግዚአብሄ ምክር አስፈላጊ ነው፡፡ ሰው ፍሬ የሚያፈራው ሙሉውን የእግዚአብሄን ቃል ምክር በመረዳት ብቻ ነው፡፡ ሰው አንዱን ወይም ጥቂት ቃል ብቻ በመያዝና በማጋነን ጤናማ መንፈሳዊ ረሃቡንና ጥማቱን ሊጠብቀው አይችልም፡፡

አንዱ የእግዚአብሄር ቃል ተነጥሎ ብቻውን ስለማይሰራ ሰው አጋኖ በያዘው ቃል ተስፋ ይቆርጣል፡፡ ቃሉ ይሰራል ሃያልም ነው፡፡ በቃሉ ምንም ችግር የለም፡፡ ሙሉውን ቃል በሚዛናዊነት ካልያዝነው እውነተኛውን መንፈሳዊ ፍላጎት እናጣዋለን፡፡

የእግዚአብሔርን ምክር ሁሉ ነግሬአችኋለሁና፥ ምንም አላስቀረሁባችሁም። ሐዋርያት 20፡27

2.     ለደረጃችን ከሚመጥነን በላይ የእግዚአብሄን ቃል ለመረዳት መሞከር

ህፃን ምግብ መብላት የሚጀምረው በወተት ነው፡፡ ወተቱ ያጠነክረዋል ለጠንካራ ምግብ ያዘጋጀዋል፡፡  በወተት ላልተፈተነ ህፃን ጠንካራ ምግብ መስጠት አደገኛ ነው፡፡ ህፃንን ካለጊዜው ስጋ ካበላነው ጤንነቱ ይዛባል፡፡ ለወተት ያለው ተፈጥሮአዊ ፍላጎት ይቀንሳል፡፡

እንዲሁም አንዳንድ ሰዎች  በፍጥነት ማደግ ይጓጓሉ፡፡ መሰረታዊ የክርስትና ትምህርት ከመማራቸው በፊት ጠንካራ ምግብ ለመብላት ሲሞክሩ ጤንነታቸው ይዛባል፡፡ በፍጥነት ማደግ ከመፈለጋቸው የተነሳ የእግዚአብሄርን የማሳደግ ሂደት አይታገሱም፡፡

ቃሉን በአእምሮዋቸው ስለሚያቁት ብቻ የደረሱበት ይመስላቸዋል፡፡ ሰው ግን ደረሰበት የሚባለው በህይወቱ ሲተገብረው ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ አዳዲስ መገለጦች ለማግኘት እንደመፈለጋችን በምናውቀው ቃል ለመኖር ራሳችንን ማስለመድ ይገባናል፡፡

ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ። ያዕቆብ 1፡22
እነዚህ አይነት ሰዎች ሁሉንም ባንድ ጊዜ አውቀው ለመጨረስ ያላቸው ፍላጎት ስለማይሟላ ይሰናከላሉ ለመንፈሳዊ ነገር ያላቸው ፍላጎት ይጎዳል፡፡

3.     በቀዳሚነት ከእግዚአብሄር ቃል መፍትሄን አለመፈለግ

ህፃናት ልጆች ሰውነታቸውን ስለሚጠቅማቸውና ስለማይጠቅማቸው መረዳቱ ስለሌላቸው በምግብ ወላጆችን ያስቸግራሉ፡፡ ህፃን ከረሜላ ካገኘ ጣፋጭ ስለሆነ ብቻ የቻለውን ያህል መምጠጥ ይፈልጋል፡፡ ከረሜላው ጣፋጭ ነው እንጂ ያለው የምግብ ይዘት በጣም ውስን ነው፡፡ ስለዚህ ህፃኑ ያንን ከረሜላ እንደበላ የምግብ ፍላጎቱ ይዘጋል፡፡ ስለዚህ ህፃኑ የሚጠቅመውን ተመጣጣኝ ምግብ መብላት አይችልም፡፡ ህፃኑ ጥቅሙ ጥቂት በሆነ ጣፋጭ ነገር የምግብ ፍላጎቱ በመዘጋቱ ለሰውነቱ የሚጠቅመውን የተመጣጣነ ምግብ ሳያገኝ ይቀራል፡፡

እንደዚሁ በክርስትና የእግዚአብሄርን ቃል አንበብን ተረድተን ታዘነው በህይወታችን ፍሬ እንዲያፈራ በቃሉ ከመፅናትና ከመታገስ ይልቅ ፈጣን መፍትሄን ለመፈለግ እንፈተናለን፡፡ ስላለንበት ሁኔታ እግዚአብሄር በፈጣን ምልክቶችን እንፈልጋለን፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር ይጠቀምባቸዋል ብለን ወደምናስባቸው ሰዎች በመሄድ እግዚአብሄ ስለእኔ ምን ይልሃል ብለን ለመጠየቅ እንፈተናለን፡፡ እውነተኛንና ዘላቂ መፍትሄ ለማግኘት በቀዳሚነት በእግዚአብሄር ቃል ውስጥ መፍትሄን መፈለግ ይገባናል፡፡  

በቀዳሚነት መፍርትሄ መፈለግ ያለብን ከቃሉ ውስጥ ስለሆነ በራሳችን መፀለይና እግዚአብሄር እንዲናገረን ጊዜ መስጠት አለብን፡፡ ለመፍትሄ በእግዚአብሄር ቃል ላይ ያለን ትኩረት ሲነሳ ህይወታችን ለብዙ ነገር ይጋለጣል፡፡

በዚህም ምክኒያት ላለንበት ሁኔታ በቀዳሚነት ከትንቢት አገልግሎት መፍትሄን ለማግኘት እንፈልጋለን፡፡ የጠበቅነው ነገር ሳይሆን ሲቀር የትንቢት አገልግሎት አይሰራም ብሎም የእግዚአብሄር ነገር አይሰራም ወደማለት እንሄዳለን፡፡

በዚያም ሁሉንም የእግዚአብሄርን ነገር እርግፍ አድርገን ለመተው እንፈተናለን፡፡ ነገር ግን እውነተኛ ነቢያትም አሉ እግዚአብሄርም በዚህ ዘመን በትንቢት ይሰራል ነገር ግን እግዚአብሄር ለልባችን በቀዳሚነት ከሚናገረን ይልቅ እግዚአብሄር በቀዳሚነት በትንቢት እንደሚናገር ከጠበቅን ስለማይሰራልን ለእግዚአብሄ ነገር ያለንን ፍላጎት ረሃብና ጥማት ይጎዳዋል፡፡

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #መጠማት #መራብ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና #እምነት #አንድነት #ፀጋ  #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Saturday, January 14, 2017

ከአካላችን ብልቶች ምን እንማራለን ?

በአንድ አካል ብዙ ብልቶች እንዳሉን፥ የብልቶቹም ሁሉ ሥራ አንድ እንዳይደለ፥ እንዲሁ ብዙዎች ስንሆን በክርስቶስ አንድ አካል ነን፥ እርስ በርሳችንም እያንዳንዳችን የሌላው ብልቶች ነን። ሮሜ 12፡4-5
መንፈሳዊ እውነትን ለማስጨበጥ ተፈጥሮአዊ አካላችን በምሳሌነት ሲጠቀስ ብዙ ጊዜ እንመለከታለን፡፡ አካላችንን በመመልከት ብቻ ብዙ መንፈሳዊ ትምህርትን ልንቀስም እንችላለን፡፡
ሃዋሪያው ጳውሎስ “ተፈጥሮ እንኳ አያስተምራችሁም “1ኛ ቆሮ 11፣14 በማለት ተፈጥሮን በመመልከት ብቻ የምንማራቸው ድንቅ ትምህርቶች እንዳሉ ያስተምረናል፡፡
ለምሳሌ የእኛ የክርስትያኖች ህብረት እንደ አካል እያንዳንዳችን ደግሞ እንደ አካል ክፍል ወይም ብልቶች በምሳሌነት ተጠቅሶ እናገኘዋለን፡፡
ከአካል ምን እንማራለን?
አካል አንድ ነው
አካል አንድ ነው፡፡ ብልቶች ብዙ ቢሆኑም አካል ግን አንድ ነው፡፡ የአካል ብልቶች የተለያዩ መሆናቸው የተለያየ አላማ እንዲኖረንና ለተለያየ መንግስት እንድንሰራ ፈቃድ አይሰጠንም፡፡ ለተለየ መንግስት ከሰራን ለእግዚአበሄር መነግስት ሳይሆን ለራሳችን መንግስት ነው እያሰታን ያለነው ማለት ነው፡፡  ስለዚህ ነው ለተለያየ አላማ የመስራት ጥሪ የሌለን፡፡ ሁላችንም የምንሰራው ለአንድ መንግስት ለአንድ ግንብ ነው፡፡
ብልቶች የተለያዩ ናቸው
የብልቶችን ልዩነት መቀበል የአካልን አንድነት እንደመቀበል አስፈላጊ ነው፡፡ አንዳንድ ሰው ከእርሱ የተለየ ሰው ሁሉ ስህተት ይመስለዋል፡፡ ሌላው ጃካለእርሱ ሌላው ጌታ የሚሰራበት አይመስለው፡፡ ለዌላው ደግሞ በእርሱ መንገድ ያልገሄድ ነበትክክለፃ መንገድ እንዳልሄደ ይመስለዋል፡፡
የብልቶች ልዩነት ውበት ነው
የብልቶች ውበት በልዩነታቸው ውስጥ ነው፡፡ ብልቶች ካልተለያዩ ምንም ዋጋ የለውም፡፡ ሁሉም ነገር አንድ አይነት ቢሆን እንዴት ያለ ውድቀት ነው? ሁላችንም አንድ አይነት ከሆንን እንዴት ያለ አሰልቺ ነው፡፡  
አካል ሁሉ ዓይን ቢሆን መስማት ወዴት በተገኘ? ሁሉም መስማት ቢሆን ማሽተት ወዴት በተገኘ? 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡17
ከእኛ ለተለየ ሰው ልባችንን ልናሰፋ ይገባል፡፡ ከእኛ የተለየ ሰው ይጠቅመናል፡፡ ከእኛ የተለየ ሰው የእኛን ጉድለት ይሞላል፡፡ ከእኛ የተለየ ሰው እኛ ማድረግ የማንችለውን መነገር ያደርግልናል፡፡ ከእኛ የተለየ ሰው ውበታችን ነው፡፡
አካልም አንድ እንደ ሆነ ብዙም ብልቶች እንዳሉበት ነገር ግን የአካል ብልቶች ሁሉ ብዙዎች ሳሉ አንድ አካል እንደ ሆኑ፥ ክርስቶስ ደግሞ እንዲሁ ነው፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡12
በሁላችንም የሚሰራ አንድ እግዚአብሄር ነው
የጸጋም ስጦታ ልዩ ልዩ ነው መንፈስ ግን አንድ ነው፤ አገልግሎትም ልዩ ልዩ ነው ጌታም አንድ ነው፤ አሠራርም ልዩ ልዩ ነው፥ ሁሉን በሁሉ የሚያደርግ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው። 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡4-6
ማንም እንዲህ ላገልግል ብሎ በራሱ የሚያገለግል የለም፡፡ የሚያገለግል ከሆነ እግዚአብሄር ነው በውስጡ ያስቀመጠው እግዚአብሄርም ነው በፀጋው የሚያስታጥቀው፡፡ አንተን እግር ያደረገህ እግዚአብሄር ነው ሌላውን አይን ያደረገው፡፡
የብልቶች ውድድር ሞኝነት ነው
ብልቶች እያንዳንዳቸው የተለየ ጥሪ አላቸው፡፡ የተለያየ ጥሪ ያላቸውን ለማወዳደር እንደማይቻል ሁሉ በብልቶች መካከል ያለ ውድድር ከንቱ ነው፡፡ የሚታገል ሰውንና ሯጭን ማፎካከር እንደማይቻል ሁሉ የተለያየ ጥሪ ያለንን ማወዳደር አይቻልም፡፡ አንዱ ከሌላው ጋር ለመፎካከር የራሱን ጥሪ ጥሎ ያልተጠራበትን ጥሪ ማድረግ ይኖርበታል ፡፡ ስለዚህ ነው ፉክክር የህይወት ብክነት የሚሆነው፡፡ ሰው ከጎረቤቱ ጋር ከተፎካከረ ስቷል ማለት ነው፡፡
አንዱ አንዱን ይነካዋል
የአንዱ መደከም የሌላው መድከም ነው የአንዱ መጠንከር የሌላው መጠንከር ነው፡፡ አንዱ አንዱን እንዲያሟላው እንጂ እንዱ አንዱን እንዲፎካከረው አልተሰራም፡፡ አንዱ በሌላው ውድቀት ካልታመመ አንዱ በሌላው ስኬት ካልተደሰተ ከአካል ብልትነት ውጭ እየኖረ ነው ማለት ነው፡፡   
አንድም ብልት ቢሣቀይ ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሣቀያሉ፤ አንድ ብልትም ቢከበር ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል። 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡26
አንዱ አንዱን ይሞላዋል
እጅ ውስጥ የተቀመጠው ችሎታ እና በረከት ለእግር ጥቅም ነው፡፡ የአይን ፀጋ ለጆሮ ያስፈልገዋል፡፡ የአንዱ ጥንካሬ ለሌላው ድካም የታቀደና የተሰራ ነው፡፡ አካል ሙሉ የሚሆነው ሁሉም ብልቶች በትክክል ሲሰሩ ነው፡፡
ነገር ግን ደካሞች የሚመስሉ የአካል ብልቶች ይልቁን የሚያስፈልጉ ናቸው፤ከአካልም ብልቶች ያልከበሩ ሆነው የሚመስሉን በሚበዛ ክብር እናለብሳቸዋለን፥ በምናፍርባቸውም ብልቶቻችን ክብር ይጨመርላቸዋል፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡22-23
አንዱ ለሌላው ያስፈልጋል
ዓይን እጅን፦ አታስፈልገኝም ልትለው አትችልም፥ ወይም ራስ ደግሞ እግሮችን፦ አታስፈልጉኝም ሊላቸው አይችልም። 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡21
አንዱ ብልት ለሌላው ብልት ይጠቅማል፡፡ የአንዱ ብልት መሳካት በሌላው ብልት መሳካት ላይ የተመሰረት ነው፡፡ አንዱ ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለሌላውም ያስፈልጋል፡፡ አያስፈልግም የምንለው የአካል ብልት የለም፡፡ ከሚታየው እስከ ማይታየው ከትልቁ እስከ ትንሹ የአካል ብልት ጠቃሚ ነው፡፡ የአለማችን ሳይንቲስቶች ስለአካችን ክፍሎች ጥቅም በክፍለ ዘመናት እየተመራመሩ ይገኛሉ ግን ሁሉንም የአካል ክፍል ጥቅም አውቀው አልጨረሱትም፡፡ እንዲሁም የማይጠቅም የሚመስለን የአካል ብልት ካለ ራሳችንን ትሁት እናድርግ፡፡ ይ-ጠ-ቅ-ማ-ል፡፡  
ይህን ሁሉ በስፍራው የሚያስይዘው የእኛ ትህትና ነው፡፡
እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ የእምነትን መጠን እንዳካፈለው፥ እንደ ባለ አእምሮ እንዲያስብ እንጂ ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ በተሰጠኝ ጸጋ እናገራለሁ። ሮሜ 12፡3
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ልዩነት #አካል #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #አንድነት #ፀጋ #ብልት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Friday, January 13, 2017

በእግዚአብሔር እመኑ

ልባችሁ አይታወክ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፥ በእኔም ደግሞ እመኑ። ዮሐንስ 141
ኢየሱስ አለ "በእግዚአብሄር እመኑ"፡፡ በእግዚአብሄር የማያምን ሰው አለ ወይ የሚል ጥያቄ ይጠየቅ ይሆናል፡፡ ምክኒያቱም ሁሉም ሰው በእግዘኢአብሄር እንደሚያመን ይናገራል፡፡ እግዚአብሄርን የሚያምን ሰው አለ፡፡ እግዚአብሄርን የማያምን ሰው አለ፡፡ ሁሉም ሰው እግዚአብሄርን አያምንም፡፡
እምነት የሚለካው በስራ ነው፡፡ ሰው አግዚአብሄርን አምናለሁ እያለ እግዚአብሄርን የሚያምን ሰው ስራን ካልሰራ ወይም እግዚአብሄርን እንደሚያምን ሰው ካልኖረ እግዚአብሄርን እንደማያምን ግልፅ ነው፡፡ 
እምነት በአይን የሚታይ ነገር አይደለም እምነት ግን በድርጊት ይገለፃል፡፡ በእግዚአብሄር የሚያምን ሰው የሚያደርገው ነገር አለ፡፡ በእግዚአብሄር የማያምን ሰው የሚያደርገው ነገር ደግሞ አለ፡፡ በእግዚአብሄር የሚያምን ሰው የማያደርገው ነገር አለ፡፡ በእግዚአብሄር የማያምን ሰው የማያደርገው ነገር አለ፡፡
እግዚአብሄርን ማመናችንና አለማመናችን የሚያሳዩ ምልክቶች
በእግዚአብሄር የሚያምን ያርፋል
ሰው በእግዚአብሄር አምናለሁ እያለ ካላረፈ በእግዚአብሄር አላመነም፡፡ ያመነ ሰው ልቡ አይታወክም፡፡ ያመነ ሰው ሰላሙን አያጣም፡፡
ስለዚህ ምድር ብትነዋወጥ፥ ተራሮችም ወደ ባሕር ልብ ቢወሰዱ አንፈራም። መዝሙር 46፡2
ሰው የራሱን ደረጃ በራሱ ከፍ አድርጎ ከሰቀለ በእግዚአብሄር አያምንም፡፡ የሰውን ክብር የሚፈልግ ሰው እግዚአብሄርን አላመነም፡፡ 
እናንተ እርስ በርሳችሁ ክብር የምትቀባበሉ ከአንዱም ከእግዚአብሔር ያለውን ክብር የማትፈልጉ፥ እንዴት ልታምኑ ትችላላችሁ? ዮሐንስ 5፡44
ያመነ ሰው ራሱን ለማዋረድ አይከብደውም
ኢየሱስ አብ ሁሉን በልጁ እንደ ሰጠው ከእግዚአብሔርም እንደ ወጣ ወደ እግዚአብሔርም እንዲሄድ አውቆ፥ ከእራት ተነሣ ልብሱንም አኖረ፥ ማበሻም ጨርቅ ወስዶ ታጠቀ፤ በኋላም በመታጠቢያው ውኃ ጨመረ፥ የደቀ መዛሙርቱንም እግር ሊያጥብና በታጠቀበትም ማበሻ ጨርቅ ሊያብስ ጀመረ። ዮሐንስ 13፡3-5
ሰው በሁኔታዎች ሰላሙን ካጣ በእግዚአብሄር አላመነም፡፡
ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም። ዮሐንስ 14፡27
በአንዳንደ ነገሮች እግዚአብሄር እንደማያስፈልገው የሚያስብ ሰው በእግዚአብሄር አልታመነም፡፡
እግዚአብሔርን ፈልጉት ትጸናላችሁም፤ ሁልጊዜ ፊቱን ፈልጉ። መዝሙር 105፡4
ሰው ከሰው እድገትን ከጠበቀ በእግዚአብሄር አላመነም፡፡ ሰው ሰውን እንዲያነሳው ተስፋ ካደረገ እግዚአብሄርን አልታመነም፡፡ ሰው በአንድ ጊዜ በሰውም ላይ በእግዚአብሄር ላይ ሊታመን አይችልም፡፡
ክብር ከምሥራቅ ወይም ከምዕራብ ወይም ከምድረ በዳ የለምና፤ መዝሙር 75፡6
ሰው ስለስኬቱ በሰው ላይ ልቡን የሚጥል ሰው በእግዚአብሄርን አላመነም፡፡
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በሰው የሚታመን ሥጋ ለባሹንም ክንዱ የሚያደርግ ልቡም ከእግዚአብሔር የሚመለስ ሰው ርጉም ነው። ኤርምያስ 17፡5
ሰው ለእግዚአብሄር ላለመስራት ከሰሰተ በእግዚአብሄር አላመነም፡፡ ሰው ሲያምን ለእግዚአብሄር ሁሉን ነገሩን ይሰጣል፡፡ ሰው ለእግዚአብሄር ከመስጠት የሚሰስተው ነገር ካለ አልታመነም ማለት ነው፡፡
አንድ መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ፦ ጌታ ሆይ፥ ካልዘራህባት የምታጭድ ካልበተንህባትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፤ ፈራሁም ሄጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤ እነሆ፥ መክሊትህ አለህ አለ። ማቴዎስ 25፡24-25
ያመነ ሰው ጌታን በትግስት ይጠብቃል
ሰው እግዚአብሄርን ለመጠበቅ ትግስት ካጣ በእግዚአብሄር አላመነም፡፡ ሰው የእግዚአብሄርን አመጣጥ ካልታገሰ እምነት ጎድሎታል፡፡
የታመነ ሰው እጅግ ይባረካል፤ ባለጠጋ ለመሆን የሚቸኵል ግን ሳይቀጣ አይቀርም። ምሳሌ 28፡20
እጦትን የሚፈራ ሰው በእግዚአብሄር አልታመነም 
የታመነ ሰው እጦትን አይፈራም፡፡ የታመነ ሰው እጦት እንዳይደርስበት የማይገባውን አያደርግም፡፡ የታመነ ሰው እጦትን ይንቃል፡፡ የታመነ ሰው እጦት ምንም እንደማያመጣና ሁሉን የሚችለው ኃይልን በሚሰጠው በክርስቶስ እንደሆነ ያምናል፡፡
መዋረድንም አውቃለሁ መብዛትንም አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም መብዛትንና መጉደልን ተምሬአለሁ። ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ። ፊልጵስዩስ 4፡12-13
ስለህይወቱ የሚጨነቅ ሰው እግዚአብሄርን አልታመነም
እግዚአብሔር ግን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን የሜዳን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፥ እናንተ እምነት የጎደላችሁ፥ እናንተንማ ይልቁን እንዴት? እንግዲህ፦ ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ማቴዎስ 6፡30-31
ባለጠግነት ጥበብና ሃይል ሀይወቴን ያቃኑታል ብሎ የሚያስብ ሰው በእግዚአብሄር አልታመነም፡፡
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጠቢብ በጥበቡ አይመካ፥ ኃያልም በኃይሉ አይመካ፥ ባለ ጠጋም በብልጥግናው አይመካ፤ ነገር ግን የሚመካው፦ ምሕረትንና ፍርድን ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን በማወቁና በማስተዋሉ በዚህ ይመካ፤ ደስ የሚያሰኙኝ እነዚህ ናቸውና፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡ ኤርምያስ 9፡23-24
ልባችሁ አይታወክ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፥ በእኔም ደግሞ እመኑ። ዮሐንስ 14፡1
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ሃሳብ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #ቃል #አእምሮ #ማደስ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ