Popular Posts

Thursday, February 25, 2021

የበለጠ የተሻለ ከፍ ያለ

 

ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ። ሴቲቱም ዛፉ ለመብላት ያማረ እንደ ሆነ፥ ለዓይንም እንደሚያስጎመጅ፥ ለጥበብም መልካም እንደ ሆነ አየች፤ ከፍሬውም ወሰደችና በላች፤ ለባልዋም ደግሞ ሰጠችው እርሱም ከእርስዋ ጋር በላ። ኦሪት ዘፍጥረት 3፡5-6

እግዚአብሄር ሰውነ ሲፈጥረው የሚያስፈልገውን ሁሉ አሟልቶ ነው፡፡ ሰው ግን የተሰጠውን ነገር ሳያይ ሲቀር ፣ ሲያናንቅና የተሻለ ነገር ሲፈልግ ይሳሳታል ከእግዚአብሄርም መንገድ ይወጣል ፡፡ በየትኛውም አለም ያለው ሰው የሚፈተነው በዚህ ነው፡፡

ሰው እንዴት ሙሉ ተደርጎ እንደተፈጠረ ሳይረዳ ሲቀር የሚፈተነውና የሚወድቀው የተሰጠውን ትቶ የተሻለ ፣ የበለጠ ፣ ከፍ ያለ ነገር ለራሱ ሲፈልግ ነው፡፡

እግዚአብሄር ሔዋንን ሙሉ አድጎት ፈጥሯት እያለ የሰይጣንን ንግግር ሰምታ የተሻለ እውቀትንና የበለጠ ሃይልን ፈለገች፡፡ ሔዋን ግን የሚያስፈልጋት ባላት ሃይል መርካትና ያላትን ሃይል በሚገባ መጠቀም ብቻ ነበር፡፡

አሁን በየእለት ህይወታችን የምንፈተነው በዚሁ ፈተና ነው፡፡

በተለይ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነን የእግዚአብሄር ልጆች የሆንን ሁላችን እግዚአብሄር አባታችን ሆኗል፡፡ እግዚአብሄር የሚያስፈልገን ሁሉ በክርስቶስ ሰጥቶናል፡፡ እግዚአብሄር የሰጠንን መረዳት ሳንችን ስንቀር ሙሉ የሆነውን የእግዚአብሄርን አቅርቦት ልናሻሸለው የሚበልጥ ፣ የተሻለና ከፍ ያለ ነገር ለማግኘት ስንሞክር እንሳሳታለን፡፡

አሁን የሚያስፈልግን ተጨማሪ ገንዘብ ሳይሆን የተሰጠንን ገንዘብ ተረድተን የምንጠቀምበት ጥበብ ነው

ለእያንዳንዱ እንደ ዓቅሙ፥ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠና ወደ ሌላ አገር ወዲያው ሄደ። አምስት መክሊትም የተቀበለው ሄዶ ነገደበት ሌላም አምስት አተረፈ፤ እንዲሁም ሁለት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ። አንድ የተቀበለው ግን ሄዶ ምድርን ቈፈረና የጌታውን ገንዘብ ቀበረ። ማቴዎስ 25፡15-18

አሁን የሚያስፈልገን ተጨማሪ እምነት ሳይሆን ያለንን እምነት ማሰራት ብቻ ነው፡፡

ሐዋርያትም ጌታን፦ እምነት ጨምርልን አሉት። ጌታም አለ፦ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ፥ ይህን ሾላ፦ ተነቅለህ ወደ ባሕር ተተከል ብትሉት፥ ይታዘዝላችሁ ነበር። ሉቃስ 17፡5-6

አሁን የሚያስፈልገን ተጨማሪ ዝና ሳይሆን ባለን ዝና ተጠቅመን ሰዎችን ማገልገል ነው፡፡

አሁን የሚያስፈልገን ተጨማሪ ሃብት ሳይሆን የተሰጠንን ሃብት ለእግዚአብሄር መንግስት ጥቅም እንዴት እንደምናውለው ምሪት መፈለግ ነው፡፡

የሰይጣንም ፈተና ያለንን ርስት እንዳናይ ፣ በሌለን ላይ እያተኮርን "በምስኪንነት" አስተሳሰብ ህይወታችንን ለምንም የማይጠቅም ሽባ ማድረግ ነው፡፡

ሰይጣን ያለንን እስከናቅን ድረስ ፣ ባለን ነገር ላይ እርምጃ እሰካልወሰድን እና ሁልጊዜ ለተጨማሪ ፣ ለሚሻልና ለሚበልጥ ሃይል ፣ ስልጣን ፣ ሃብትና ዝና ብንሮጥ ግድ የለውም፡፡

የመለኮቱ ኃይል፥ በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ፥ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ ስለ ሰጠን፥ በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ። 2 የጴጥሮስ መልእክት 1፡2-3

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እረፍት #ቅድሚያ #እምነት #መደገፍ #ሰንበት #አስቀድማችሁ #ፅድቁን #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #እምነት #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ምህረት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ


No comments:

Post a Comment