Popular Posts

Sunday, February 14, 2021

ወዳጄ ማነው ?

 

እነሆም፥ አንድ ሕግ አዋቂ ሊፈትነው ተነሥቶ፦ መምህር ሆይ፥ የዘላለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ? አለው። እርሱም በሕግ የተጻፈው ምንድር ነው? እንዴትስ ታነባለህ? አለው። እርሱም መልሶ፦ ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም ኃይልህም በፍጹም አሳብህም ውደድ፥ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ አለው። ኢየሱስም፦ እውነት መለስህ፤ ይህን አድርግ በሕይወትም ትኖራለህ አለው። እርሱ ግን ራሱን ሊያጸድቅ ወድዶ ኢየሱስን፦ ባልንጀራዬስ ማን ነው? አለው። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ፦ አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ወረደ በወንበዴዎችም እጅ ወደቀ፤ እነርሱም ደግሞ ገፈፉት ደበደቡትም በሕይወትና በሞት መካከልም ትተውት ሄዱ። ድንገትም አንድ ካህን በዚያ መንገድ ወረደ አይቶትም ገለል ብሎ አለፈ። እንዲሁም ደግሞ አንድ ሌዋዊ ወደዚያ ስፍራ መጣና አይቶት ገለል ብሎ አለፈ። አንድ ሳምራዊ ግን ሲሄድ ወደ እርሱ መጣ አይቶትም አዘነለት፥ ቀርቦም ዘይትና የወይን ጠጅ በቍስሎቹ ላይ አፍስሶ አሰራቸው፥ በራሱ አህያም ላይ አስቀምጦት ወደ እንግዶች ማደርያ ወሰደው ጠበቀውም። በማግሥቱም ሁለት ዲናር አውጥቶ ለባለቤቱ ሰጠና፦ ጠብቀው፥ ከዚህም በላይ የምትከስረውን ሁሉ እኔ ስመለስ እከፍልሃለሁ አለው። እንግዲህ ከነዚህ ከሦስቱ በወንበዴዎች እጅ ለወደቀው ባልንጀራ የሆነው ማንኛው ይመስልሃል? እርሱም፦ ምሕረት ያደረገለት አለ። ኢየሱስም፦ ሂድ አንተም እንዲሁ አድርግ አለው። የሉቃስ ወንጌል 10፡25-37

ኢየሱስ እግዚአብሄርንና ሰውን ውደድ ስለሚለው ስለቀዳሚው ህግ እየተናገረ ነበር፡፡ አንድ የህግ መምህር እኔስ ሰውን እወዳለሁ ነገር ግን መልሶ የሚወደኝ ሰው የለም አይነት አስተያየት አቀረበ፡፡ መልካም አደርጋለሁ ነገር ግን መልሶ መልካም የሚያደርግልኝ ሰው አላገኘሁም፡፡ ሰው መልካም እንዲደረግለት እንጂ መልካም ላደረገለት ሰው መልሶ መልካም ማድረግ አይፈልግም አይነት ቅሬታን አቀረበ፡፡

እንደ ኢየሱስ ግን ፍቅር ማለት መልካም ለሚያደርግልህ መልካም ማድረግ አይደለም፡፡ ፍቅር ማለት መልካም ላደረገልህ መልሶ መልካም ማድረግ ሳይሆን መልስ ሳይጠብቁ መልካም ማድረግ ብቻ ነው በማለት ይህን ታሪክ ነገረው፡፡  

ወዳጅ የሚገኝ አይደለም፡፡ ወዳጅ የምናፈራው ነው፡፡ ወዳኝነት የምንገነባው እንጂ በአጋጣሚ የሚገኝ አይደለም፡፡ ሰውን ወዳጅ የምናደርገው መልካም በማድረግ ብቻ ነው፡፡ ወዳጅ የምናፈራው ወደፊት መልካም ለሚያደርግልን ሰው መልካም በማድረግ አይደለም፡፡ ወዳጅ የምናፈራው ማልካ ላደረገልን ሰው መልካም በማድረግም አይደለም፡፡ መልካም ለማድረግ እስከተዘጋጀን ደረስ ብዙዎችን ወዳጅ ማድረግ እንችላለን፡፡ ወዳጅ ማግኘት የተቸገረን ሰው እንደ ማግኘት ቀላል ነው፡፡ ለተቸገረ ሰው ምህረት ስናደርግና መልካም ስናደርግ ለዚያ ሰው ወዳጁ እንሆናለን፡፡

የጠራውንም ደግሞ እንዲህ አለው፦ ምሳ ወይም እራት ባደረግህ ጊዜ፥ እነርሱ ደግሞ በተራቸው ምናልባት እንዳይጠሩህ ብድራትም እንዳይመልሱልህ፥ ወዳጆችህንና ወንድሞችህን ዘመዶችህንም ባለ ጠጎች ጎረቤቶችህንም አትጥራ። ነገር ግን ግብዣ ባደረግህ ጊዜ ድሆችንና ጕንድሾችን አንካሶችንም ዕውሮችንም ጥራ፤ የሚመልሱት ብድራት የላቸውምና ብፁዕ ትሆናለህ፤ በጻድቃን ትንሣኤ ይመለስልሃልና። የሉቃስ ወንጌል 14፡12-14

ወዳጅነት መልካም ስናደርግለት መልሶ መልካም ለሚያደርግልን መልካም ማድረግ አይደለም፡፡ ወዳጅነት መልካም ላደረገልን መልሶ መልካም ማድረግ አይደለም፡፡

ባልንጀራ ወይም ወዳጅ ከፈለግክ አንተው ባልንጀራ ወይም ወዳጅ ሁን፡፡ ወዳጅ ከፈለግህ ወዳጅነትህን የሚፈልግን ሰው ውደድ መልካምን አድርግ፡፡

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ፍቅር #መውደድ #ማድረግ #መስጠት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #ቸርነት #ሳምራዊ #ሌዋዊ #ካህን #ባልጀራህን #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #ወንጌል #ፅናት #ትግስት #መሪ


No comments:

Post a Comment