Popular Posts

Wednesday, August 24, 2022

የድህነት ድንጋጤን ማሸነፍ

 


እያንዳንዳችን በተለያየ ጊዜ በማጣት እና በድህነት ተፈትነን እናውቃለን፡፡ እጦቱ ቢያልፍም በጊዜው ያለፍንበት እጦት በውስጣችን ድንጋጤን ሊተው ይችላል፡፡ የእጦት ድንጋጤ በውስጣችን ቀርቶ አንዳንዴ "ወደዚያ ድህነት ውስጥ ልትመለስ ነው" ብሎ ያስፈራራናል፡፡

እጦት ውስጥ ልገባ ነው እንዴ? የሚል ፍርሃት መሰማት ተፈጥሮአዊ ስሜት ነው፡፡ በፍፁም የፍርሃት ስሜት እንዳይሰማን ማድረግ አንችልም፡፡

የፍርሃት ስሜት በራሱ ጥሩ ወይም መጥፎ አይደለም፡፡ ማንኛውም ስሜት በህይወታችን የራሱ አላማ እና ስፍራ አለው፡፡

ጠቢብ ሰው ይፈራል ከክፉም ይሸሻል፤ ሰነፍ ግን ራሱን ታምኖ ይኰራል። መጽሐፈ ምሳሌ 1416

ብልህ ሰው ክፉን አይቶ ይሸሸጋል፤ አላዋቂዎች ግን አልፈው ይጐዳሉ። መጽሐፈ ምሳሌ 22:3

የህይወት ድንጋጤ ትዝታው ከጊዜ ወደጊዜ ሊመጣ ይችላል፡፡ የህይወትን ድንጋጤ ሊያነሳሱ የሚችሉ ነገሮች በህይወታችን ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ የድንጋጤውን ስሜት ሊያስቆም የሚችለው ምንም ነገር የለም፡፡ ማድረግ የምንችለው አንድ ነገር ድንጋጤው አሉታዊ ተፅእኖ አሳድሮብንና በድንጋጤው ተነሳስተን እርምጃ አለመውሰድ ነው፡፡

ያለፍንበት የማጣት ድንጋጤ እና ህመም ለረጅም ጊዜ በውስጣችን ሊቆይ ይችላል፡፡ በዚያ በማጣት ህመም ተነሳስተን የማይገባንን ነገር አለማድረግ ይኖርብናል፡፡

አንዳንድ ሰው የማጣትን ህመማ ከሚገባው በላይ ከመፍራቱ እና ከማክበሩ የተነሳ እጦት እንዳይገጥመው በድህነት ፍርሃት ተነሳስቶ የማይገባውን ነገር ሁሉ ያደርጋል፡፡ እንዳያጣ በመፍራት ይዋሻል ይሰርቃል ይቀማል ይጠላል ይበድላል እንዲሁም ይገድላል፡፡

ልዩነት የሚያመጣው ፍርሃቱ መሰማቱ ሳይሆን የፍርሃቱን ስሜቱን የምንይዝበት መንገድ ነው፡፡ የፍርሃትን ስሜት የምንይዝበት መንገድ ፍርሃቱነ አሸንፈን እንድንወጣ ወይም ደግሞ በፍርሃቱ ተሸንፈን እንድንቀር ሊያደርገን ይችላል፡፡

በፍርሃት መንፈስ አስጠንቃቂነት ተረድተን ወደ ድህነት እንዳንገባ የሚገባንን እርምጃ መውሰድ የራሱ የሆነ ጥቅም አለው፡፡ በህይወታችን ለስንፍና ስፍራን ባለመስጠት መትጋት ይጠበቅብናል፡፡ነገር ግን የኑሮ ፍርሃት እኛን የኑሮ ፍርሃት በማስፈራራት የማይገባንን ነገር እንድናደርግ አያድርገን፡፡ በህይወታችን ኪሳራ የሚገጥመን የፍርሃት ስሜቱ ስለተሰማን ሳይሆን ፍርሃት ከህይወት አላማችን ካስቆምን ብቻ ነው፡፡

የድህነት ፍርሃት የህመም እና የድንጋጤው ስሜት ሳይጠፋ የፍርሃቱ ስሜት እያለ የህይወት አላማችንን ካደረግነው ስኬታማ እንሆናለን፡፡

የፍርሃት ስሜት የሚሳካለት ከህይወት ፊት ካልሰጠነው እና አላማችን ካስቆመን ብቻ ነው፡፡

መዋረድንም አውቃለሁ መብዛትንም አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም መብዛትንና መጉደልን ተምሬአለሁ። ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ። ፊልጵስዩስ 4፡12-13

በህይወታችን ያለፈው የድህነት ወይም የማጣት ታሪክ የወደፊት ህይወታችን ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እንዲያደርግ እና ከህይወት አላማችን እንዲያስተጓጉለን አንፍቀድለት፡፡ 

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa 

No comments:

Post a Comment