Popular Posts

Thursday, August 18, 2022

እምነት ድንገተኛ አይደለም

 


እምነት ከቁሳዊው አለም ባሻገር መንፈሳዊውን አለም የምናይበት እጅግ አስፈላጊ መነፅር ነው፡፡ እኛም ከቁሳዊው አለም ባሻገር መንፈሳዊውን አለም በማየት በእምነት እንድንኖር በእግዚአብሄር መልክና አምሳል ተፈጥረናል፡፡

በእምነት መመላለስ የትጉዎች አካሄድ እንጂ የሰነፎች አካሄድ አይደለም፡፡ እምነት በየእለቱ የምንለማመደው የህይወት ዘይቤያችን እንጂ ረስተንን ቆይተን የሆነ ነገር ሲፈጠር ብቻ ድንገት የምንመዘው ድንገተኛ አይደለም፡፡

እምነት ከትንሽ ጀምረን በየእለቱ በትጋት የምንለማመደውና የምናሳድገው ልምምድ እንጂ አንዳንዴ የምንመዘው መጠባበቂያ መሳሪያ አይደለም፡፡

ከእግዚአብሄር ጋር ባለን ግንኙነት እያንዳንዱ የህይወት እርምጃችን በቃሉ ላይ ባለ እምነት መመስረት አለበት፡፡ በእያንዳንዱ የህይወት እንቅስቃሴያችን ስለእኛ የተፃፈውን የእግዚአብሄርን ቃል ማመን እና መተግበር አለብን፡፡

እርሱም መልሶ፦ ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል አለው። ማቴዎስ 4፡4

ሰው የሚኖረው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ አንድ ቃል አይደለም፡፡ ሰው የሚኖረው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ በእያንዳንዱ ቃል ነው፡፡

እያንዳንዱ የኑሮ አቅጣጫችን የእግዚአብሄርን ቃል ማወቅ ፣ መረዳትና ማመን ይጠይቃል፡፡ የእምነት ልምምድ ሙሉ ጊዜያችንን ፣ ሙሉ ትኩረታችንን እና ሙሉ ህይወታችንን የሚጠይቅ የእለት ተእለት ተግባራችን እንጂ ረስተነው ድንገት የምንመዘው የአደጋ ጊዜ መጠባበቂያ መሳሪያ አይደለም፡፡ 

No comments:

Post a Comment