Popular Posts

Wednesday, December 2, 2020

አለቅጥ መደሰትና አደጋዎቹ

 


ስሜት ስለአንድ ሁኔታ የሚጠቁመን በረከት ነው፡፡ በምድር ላይ የእግዚአብሄርን ሃሳብ መፈፀም ካለብን ስሜታችንን በሚገባ መቆጣጠር ግድ ይላል፡፡

አንድ ነገር ሲሆንልን መደሰት መልካም ነው፡፡ ነገር ግን መፅሃፍ ቅዱስ ሁሉን በልክ አድርግ እንደሚል ለደስታም መጠን አለው፡፡

አንተ ግን ነገርን ሁሉ በልክ አድርግ፥ መከራን ተቀበል፥ የወንጌል ሰባኪነትን ሥራ አድርግ፥ አገልግሎትህን ፈጽም። 2ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 4፡5

ከመጠን ያለፈ ደስታ የራሱ አደጋዎች አሉት፡፡ ከመጠን ያለፈ ደስታ ከደስታነቱ ባሻገር የሚያመለክተው የህይወት ችግሮች ነው፡፡

አንድ ነገር ሲሆንልን ከመጠን ያለፈ ደስታን ማሳየት በሁኔታው ላይ ያለንን መደገፍ ያሳያል፡፡ ከመጠን በላይ መፈንጠዝ የሚያመለክተው ከሁኔታው ጋር ያለንን ጤናማ ያልሆነ ግንኙነት ነው፡፡ ከመጠን ያለፈ ደስታ በእግዚአብሄር ላይ ሳይሆን በሁኔታው ላይ ያለንን አደገኛ መደገፍ ያሳያል፡፡

በእግዚአብሄር የሚደገፍ ሰው በእግዚአብሄር እንጂ በሁኔታ ከመጠን በላይ አይፈነጥዝም፡፡

በሁኔታዎች ከመጠን በላይ የሚደሰት ሰው ሃዘኑ ቅርብ ነው፡፡ ልጆች ሆነን ከመጠን በላይ ስንፈነጥዝ ወላጆቻቸን ተዉ ይህ ደስታ ወደለቅሶ እንዳይለወጥ ይሉን ነበር፡፡ ደግሞም ካልተመለስንና ካልሰማናቸው ወደሃዘን ይለወጣል፡፡ ወላጆቻችን ይህ ከመጠን በላይ የሆነ ደስታ ከመጠን በላይ የሆነ ዘና ማለት ከመጠን በላይ የሆነ መፈንጠዝ ጤናማ እንዳልሆነና ወደሀዘንና እንደሚለወጥ ከልምድ ያውቁታል፡፡

ስለአንድ ነገር ከመጠን በላይ የሚጓጓ ሰው እንዲሁ የሚጠብቀው ነገር ሳይሆን ቀርቶ ሳያዝን አይቀርም፡፡ ስለአንድ ነገር ከመጠን በላይ የሚጓጓ ሰው ስለነገሩ ያለውን የተሳሳተ  ግምት ያሳያል፡፡ ሰው ለምንም ነገር ከሚገባው በላይ ግምት ከሰጠው ያ የጓጓለት ነገር ሳያሳዝንው አይርም፡፡ እኛ ሰዎች ብዙ ጊዜ ከሚገባው በላይ ግምት የምንሰጣቸው ጥበብ ፣ ሃይልና  ባለጠግነት እንደጠበቅናቸው የህይወታችንን ጥያቄያችንን ስለማይፈቱ ያሰናክሉናል፡፡

እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጠቢብ በጥበቡ አይመካ፥ ኃያልም በኃይሉ አይመካ፥ ባለ ጠጋም በብልጥግናው አይመካ፤ ነገር ግን የሚመካው፦ ምሕረትንና ፍርድን ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን በማወቁና በማስተዋሉ በዚህ ይመካ፤ ደስ የሚያሰኙኝ እነዚህ ናቸውና፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡ ትንቢተ ኤርምያስ 9፡23-24

በህይወት አላስፈላጊ ጉዳት እንዳያገኘን ከመጠን ያለፍ ደስታንም ሆነ ከመጠን ያለፈ መጓጓትን ከህይወታችን ውስጥ በትጋት ማስወገድ አለብን፡፡

ብልህ ሰው ክፉን አይቶ ይሸሸጋል፤ አላዋቂዎች ግን አልፈው ይጐዳሉ። መጽሐፈ ምሳሌ 27፡12

አይናችንን ከሁኔታዎች ላይ አንስተን በማይለዋወጥ አስተማማኝ በሆነ በእግዚአብሄር ሁልጊዜ ደስ መሰኘትን መማር ብልህነት ነው፡፡

ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፥ ደስ ይበላችሁ። ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 4፡

ሃዋርያው ጳውሎስ ከሁኔታዎች ከአቅማቸው በላይ እንዳንጠብቅባቸው እና አላፊና ተለዋዋጭ በሆኑት በሁኔታዎች ከመጠን በላይ እንዳንደሰት በዚያም እንዳንሰናከል የሚመክረን ስለዚህ ነው፡፡

ዳሩ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እናገራለሁ፤ ዘመኑ አጭር ሆኖአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሚስቶች ያሉአቸው እንደሌላቸው ይሁኑ፥ የሚያለቅሱም እንደማያለቅሱ፥ ደስ የሚላቸውም ደስ እንደማይላቸው፥ የሚገዙም ምንም እንደሌላቸው፥ በዚችም ዓለም የሚጠቀሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙባት ይሁኑ፤ የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነውና። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 7፡29-31

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ተመልክተን #እይታ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ቃል #አሸናፊ #ደስታ #የእግዚአብሄርእቅድ #የእግዚአብሄርፈቃድ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment