Popular Posts

Monday, September 7, 2020

የደቦ ይቅርታ

 


በአገራችን ጳጉሜ 1 የይቅርታ ቀን ተብሎ ታውጆዋል፡፡ ይቅርታ ደግሞ ብዙ በረከቶችን የተሸከመ ድንቅ መፅሃፍ ቅዱሳዊ ልምምድ ነው፡፡ ነገር ግን ማንኛውም የመፅሃፍ ቅዱስ መርህ የሚባርከን እንደሃይማኖት ስርአት ሳይሆን ተረድተነው ስንለማመደው ብቻ ነው፡፡

እንደው እንደ ሃይማኖት ወግ የምናደርገው ነገር በህይወታችን የታለመለትን አላማ እና ግብ ሊመታ አይችልም፡፡ እንደው ሌላው ሰው ስላደረገው ብቻ የምናደርገው ሃይማኖታዊ ልምምድ ሊባርከን አይችልም፡፡ እንደው ከዚህ የይቅርታ በረከት እጎድላለሁ ብሎ በመፍራት ብቻ እንደ ሃይማኖታዊ ወግ የምናደርገው ነገር እውነተኛውን ይቅርታ እንዳንለማመድ ራሳችንን ያታልለናል እንጂ የሚጠቅመን ነገር አይኖርም፡፡  

እግዚአብሄር የፈጠረን ተባብረን ለአንድ አላማ እንድንሰራ እና አንዳችን አንዳችንን እንድንባርክ ነው፡፡

ይቅርታ ደግሞ በሁለት ሰዎች መካከል የነበረን የአንድነትና የትብብር ግንኙነት መበላሸት የምናስተካክልበት መፅሃፍ ቅዱሳዊ መርህ ነው፡፡

ይቅርታ መጠየቅ በደቦ የማይሰራና በጣም ጥንቃቄ የሚፈልግ ነገር ነው፡፡

ሰውን እንደበደልነው ስናውቅ ይቅርታ ወደ በደልነው ሰው ሔደን መጠየቅ አለብን፡፡ ይቅርታ ስንጠይቅ እንደው ይቅርታ ብቻ ለመጠየቅ ሳይሆን ይቅርታ ከጠየቅንበት መንገዳችን ለመመለስ ነው፡፡ ይቅርታ ስንጠይቅ ተሳስቻለሁ ከዚህ በኋላ አላደርገውም እያልን ለበደልነው ሰው ቃል እየገባን ነው፡፡

የበደለን ሰው ወደእኛ መጥቶ ይቅርታ ሲጠይቀን ደግሞ ይቅር ማለት አለብን፡፡

በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ ወደ እርሱ ቀርቦ፦ ጌታ ሆይ፥ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ልተውለት? እስከ ሰባት ጊዜን? አለው። ኢየሱስ እንዲህ አለው፦ እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ አልልህም። የማቴዎስ ወንጌል 18፡21-22

ሳላውቅ በስህተት ሚለው የደቦ ይቅርታ አጠያየቅ መፅሃፍ ቅዱሳዊ ነው ብዬ አላምንም፡፡ አውቀን ስላልሰራነው ነገር እንጠየቃለን ብዬ አላምንም፡፡ አውቀን ስላለሰራነው ነገር እልፍ ጊዜ ይቅርታ ብንጠይቅ ስህተታችንን ስለማናውቅው ተመልሰን እንዳማናደርገው ማረጋገጫ የለውም፡፡

ሰውን መበደላችንን እርግጠኛ ካልሆንን ወደ ሰውየው ሔደን መነጋገር መፅሃፍ ቅዱሳዊ ግንኙነትን የማስተካከያ መንገድ ነው፡፡

እንግዲህ መባህን በመሠዊያው ላይ ብታቀርብ፥ በዚያም ወንድምህ አንዳች በአንተ ላይ እንዳለው ብታስብ፥ በዚያ በመሠዊያው ፊት መባህን ትተህ ሂድ፥ አስቀድመህም ከወንድምህ ጋር ታረቅ፥ በኋላም መጥተህ መባህን አቅርብ። የማቴዎስ ወንጌል 5፡23-24

ስህተት እንደሰራን እርግጠኛ ባልሆነው ነገር ሳላውቅ በስህተት ብሎ በደፈናው ማለፍ ከእውነተኛው መፅሃፍ ቅዱሳዊ በረከት ያጎድለናል፡፡ እንዲሁም ስህተት እንደሰራን ለማረጋገጥ ሔደን ባልተነጋገርነው ነገር ሳላውቅ በስህተት ብሎ በደፈናው ማለፍ እውነተኛውን መፅሃፍ ቅዱሳዊ በረከት ሊያስገኝልን አይችልም፡፡  

በየትኛውም የመፅሃፍ ቅዱስ ክፍል ማንም ሰው ሳላውቅ በስህተት የሰራሁትን ይቅር በለኝ በሚለው መርህ ይቅርታ ሲጠይቅም ሆነ ሌሎች ይቅርታ እንዲጠይቁ ሲተያስተምር አይቼ አላውቅም፡፡  

ሳላውቅ በስህተት ተብሎ የሚጠየቅ ይቅርታ ባዶ ሃይማኖታዊ ወግ እንጂ ምንም አይነት መፅሃፍ ቅዱሳዊ መሰረት እና ጥቅም የሌለው የሰው ስርአት ነው፡፡

ራሳችንን ትሁት አድርገን ወደ በደልነው ሰው ሔደን ወይም ደውለን ይቅርታ ከመጠየው ይልቅ እንዲሁም በጅምላ የበደልኩዋችሁ ሁሉ ይቅር በሉኝ ማለት ከዋናው የመፅሃፍ ቅዱስ በረከት የሚያጎድለን መንፈሳዊ የሚመስል ባዶ ሃይማኖታዊ ወግ ብቻ ነው፡፡ በጅምላ ይቅርታ ከምንጠይቀው ህዝብ ይልቅ የበደልነውን ሶስት ሰው በግል ይቅርታ መጠየቅ ህይወታችንን ይለውጠዋል፡፡ ካልበደልክና ወይም በደልህን ካልተረዳኸው እግዚአብሄርም ሰውም አይፈርድብህም፡፡ የምትጠየቀው ስለምታውቀው ብቻ ነው፡፡ ከበረከት ላለመጉደል እንደ አጠቃላይ ምርመራ የምታደርገው የይቅር በሉኝ ጥሪ ከፍርሃት እንጂ ከእምነት አይደለም፡፡ አትፍራ ካልበደልክ ወይም በደልህን ካልተረዳኸው ከየትኛውም የእግዚአብሄር በረከት አትጎድልም፡፡  

መልካም የይቅርታ ቀን ! መልካም የይቅርታ ወር ! መልካም የይቅርታ አመት !

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ህይወት #የሚፈርድ #የሚያማ #ወንጌል #መውደድ #ፍቅር #የህይወትምስክርነት #መታዘዝ #ይቅርታ #መውደድ #እውነት #ትህትና #ትንሳኤ #ህይወት #ምህረት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ  #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ 

No comments:

Post a Comment