Popular Posts

Thursday, September 3, 2020

የተሸነቆረ ሸክላ

 


እኛ በክርስቶስ ኢየሱስ አዳኝነት አምነን የዳንን ሁላችን እግዚአብሄር በምድር ላይ ለሰጠን የቤት ስራ በእግዚአብሄር መንፈስ ተቀብተናል፡፡ ካለ እግዚአብሄር መንፈስ እርዳታ  የእግዚአብሄርን ስራ መስራት አይቻልም፡፡ የእግዚአብሄር አላማ በምድር ላይ መፈፀም ካለበት የእግዚአብሄር መንፈስ አብሮን ሊሰራ ይገባዋል፡፡

በክርስቶስም ከእናንተ ጋር የሚያጸናንና የቀባን እግዚአብሔር ነው፥ 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1፡21

ታዲያ ችግሩ ቅባቱን ጠብቆ ለሚፈለገው አላማ ማዋል እንጂ መቀባቱ አይደለም፡፡ ምንም ያህል ብንቀባ ቅባቱን በመልካም የእግዚአብሄራዊ ባህሪ ጠብቀን ካላቆየነው ለታለመለት አላማ ሊውል አይችልም፡፡

የቅባቱ መያዣ ሸክላው በባህሪ ጉድለት የተሸነቆረና በክርስቶስ ባህሪ ካልተጠበቀ በስተቀር ቅባቱን ያባክነዋል፡፡

እግዚአብሄር ብዙ ጊዜ የሚፈጅበት እኛን መቀባት አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ብዙ ጊዜ የሚፈጅበት የተቀባነውን ቅባት ለረጅም ጊዜ አቆይተን ለታለመለት አላማ ሁሉ መጠቀም እንድንችል የቅባቱን መያዣ ሸክላውን መስራት ነው፡፡ እኛን መቀባት ለእግዚአብሄር የሰከንድ ስራ ነው፡፡ ነገር ግን  የቅባቱን አስተዳዳሪ እኛን እግዚአብሄርን በመምሰል መስራት ግን የብዙ ጊዜ ስራ ነው፡፡

ህይወታችን ትእግስት ፣ የዋህነት እና ፍቅር ከጎደለው የተቀባነውን ቅባት ለታለመለት አላማ ሳይውል እናባክነዋለን፡፡

ስለዚህ ነው ቅባት ወደከፍታ ይወስድሃል ባህሪ በከፍታው ላይ ይጠብቅሃል የሚባለው፡፡

ብዙ ሰዎች ግን ስለመቀባታቸው ሃይል ስለማግኘታቸው እንጂ ሃይሉን ለረጅም ጊዜ ስለሚያቆየው ስለባህሪያቸው አያስቡም፡፡ እኛ መቀባት ከምንፈልገው በላይ እኛ እንድንቀባ እግዚአብሄር ይፈልጋል፡፡ የእኛ ድርሻ ቅባቱን ለረጅም ጊዜ እና ለታለመለት አላማ ሁሉ ለመጠቀም የሚያስችለንን የቅባቱን መያዣ ባህሪያችንን በእግዚአብሄር ቃል ለመስራት እንትጋ፡፡

 ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes

#ኢየሱስ #መንፈስቅዱስ #ቅባት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #ምሪት #ድምፅ #ሃይል #ሰላም #ደስታ #ሃዋርያውአቢይ #ሃዋርያውአቢይዋቁማ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #መውደድ #መናገር #የዋህነት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment