Popular Posts

Sunday, June 25, 2017

የእውነተኛ ብልፅግና ገፅታዎች

ብልፅግና ክንውም ነው፡፡ ሰው ብልቡ ያለውን ነገር ለመፈፀም መቻል ብልፅግና ነው፡፡ ሰው ማድረግ የሚፈልገውን ነገር ጀምሮ ወደፍፃሜ ማምጣት ብልፅግና ነው፡፡
አንዳንድ ሰው ገንዘብ ብቻ ካገኘ ብልፅግና ይመስለዋል፡፡ ክንውን ከገንዘብ በላይ ነው፡፡ ክንውን የሚጠይቃቸው ገንዘብ ሊያደርገው የማይችል ብዙ ነገሮች አሉ፡፡
ክንውን የሚያስፈልገንን ገንዘብ በሚያስፈልገን ጊዜ ማግኘትን ያጠቃልላል፡፡ ብልፅግና የሚገለጥባቸው ሰባት መንገዶች
1.      ብልፅግና ነገሮችን የማስተዳደር ችሎታ ማግኘት ነው፡፡  
ሰው ሁሉም ነገር ኖሮት እንዴት እንደሚያስተዳድረው ጥበቡ ከሌለው ክንውን ይጎድለዋል፡፡ ሰው የሚያስፈልገውን ገንዘብ ወይም ቁሳቁስ ነገር አግኝቶ ያገኘውን ነገር ለታሰበለት አላማ ማዋል ካልቻለ ክንውን የለም፡፡

2.     ብልፅግና ብክነትን መቀነስ ነው፡፡
ክንውን ብክነትን መቀነስ ነው፡፡ ሰው ያገኘውን ነገር የተወሰነውን እጅ ቢያባክንና የቀረውን እጁን ቢጠቀምበት ልዩነት ያመጣው የብክነቱ መብዛትና ማነሱ እንጂ ያገኘው ገንዘብ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ብክንውን ሲባርክ የብክነትን ቀዳዳውን እንድትረዳና እንድትቀንስ ያደርግሃል፡፡ እግዚአብሄር ሲባርክ ክብደት መስጠት ላለብህ ነገር ቅድሚያ እንድትሰጥ መረዳት በመስጠት ክንውንን ይሰጥሃል፡፡
ጥበብን የወደደ ሰው አባቱን ደስ ያሰኛል፤ ጋለሞቶችን የሚከተል ግን ሀብቱን ያጠፋል። ምሳሌ 29፡3
የከበረ መዝገብና ዘይት በጠቢብ ሰው ቤት ይኖራል፤ አእምሮ የሌለው ሰው ግን ይውጠዋል። ምሳሌ 21፡20
3.     ብልፅግና ከትክክለኛ ሰው ጋር መገናኘት ነው፡፡
በልብህ ላለው ስራ የሚያስፈክግህን ሰው ማግኘት ክንውን ነው፡፡ ሁሉም ነገር ኖሮህ እንደራሱ አድርጎ የሚሰራልህ ትክክለኛውን ሰው ካላገኘህ ልትከናወን አትችልም፡፡ በአለም ላይ ይልቁ ሃብት ሰው ነው፡፡ እግዚአብሄር በታማኝ ሰው ይባርካል፡፡ እግዚአብሄር ሲባርክህ የሚያስፈልግህ ችሎታ ካለው ቁልፍ ሰው ጋር ያገናኝሃል፡፡
እንደ እርሱ ያለ፥ ስለ ኑሮአችሁ በቅንነት የሚጨነቅ፥ ማንም የለኝምና፤ ፊልጵስዩስ 2፡20
4.     ብልፅግና የምትበላውና የምትዘራውን መለየት ነው፡፡
የምትዘራውን ከበላህ ክንውን የለም፡፡ ክንውን የምትበላውን ብቻ እንድትበላና ሌላውን ደግሞ እንድትዘራውና ብዙ እንድታጭድ ያስተምርሃል፡፡ ብልፅግና ለወደፊት ማፍሰስ ያለብህን መዋእለ ንዋይ ወይም ኢንቨስት ማድረግ ያለብህን መረዳቱን ይሰጥሃል፡፡
ለዘሪ ዘርን ለመብላትም እንጀራን በብዙ የሚሰጥ እርሱም የምትዘሩትን ዘር ይሰጣችኋል ያበረክትላችሁማል፥ የጽድቃችሁንም ፍሬ ያሳድጋል፤ 2ኛ ቆሮንቶስ 9፡10
የከበረ መዝገብና ዘይት በጠቢብ ሰው ቤት ይኖራል፤ አእምሮ የሌለው ሰው ግን ይውጠዋል። ምሳሌ 21፡20
5.     ብልፅግና መሰረታዊ ፍላጎትና ቅንጦት የመለየት ችሎታ ነው፡፡
የክርስትያን የመጨረሻ ክንውን መሰረታዊ ፍላጎቱን አማልቶ ጌታን መከተል ነው፡፡ እግዚአብሄር መሰረታዊ ፍላጎታችንን ለማሟላት ቃል ገብቷል፡፡ እግዚአብሄር የምንፈልገውን ሁሉ አያሟላም፡፡ ስለዚህ እግፍዚአብሄር የሰጠንን ሃብት በመሰረታዊ ፍላጎት ላይ ብቻ የማዋል ጥበብ ብልፅግና ነው፡፡ ሰው እግዚአብሄር የሰጠውን ሃብት በቅንጦት ላይ አባክኖት ሊከናወን አይችልም፡፡  
ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤ ወደ ዓለም ምንም እንኳ አላመጣንምና፥ አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፥ እርሱ ይበቃናል። 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡6-8
6.     ብልፅግና እግዚአብሄር የሰጠህን ሰው በሚገባ የመያዝ ችሎታ ነው፡፡
እግዚአብሄር ለሰው የሚሰጠው ታላቁ ሃብት ሰው ነው፡፡ ሰው ብቻውን ያን ያህል ለውጥ ሊያመጣ አይችልም፡፡ ለሰው ሰው ያስፈልገዋል፡፡ ብልፅግና እግዚአብሄር ያመጣልንን እድል የመጠቀም ችሎታ ነው፡፡ ሰውን እንደአቅሙ እንደ ደረጃው እንዴት ማክበርና መያዝ እንዳለበት ካላወቀ ክንውን ከየትም አይመጣም፡፡
ለእያንዳንዱ እንደ ዓቅሙ፥ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠና ወደ ሌላ አገር ወዲያው ሄደ። ማቴዎስ 25፡15
7.     ብልፅግና በህይወት መደሰት መቻል ነው፡፡
ህይወትን ሃላፊነት ብቻ አይደለም፡፡ ህይወት እንድንደሰትበት የተሰጠን ስጦታ ነው፡፡ ሰው ባለበት ደረጃ በደረሰበት ደረጃ ደስ መሰኘት ከቻለ ያ ክንውን ብልፅግና ነው፡፡ ሰው ደስ የመሰኘት ቀጠሮውን "ይህን ሳገኝ እንዲህ ስሆን" እያለ የሚያስተላልፈው ከሆነ ክንውን አይደለም፡፡ ሰው ዛሬ ባለበት ደረጃ ባለበት ሁኔታ በህይወቱ ደስ መሰኘት ካልቻለ የተከናወነ ሰው አይደለም፡፡
እነሆ፥ እኔ ያየሁት መልካምና የተዋበ ነገር ሰው እግዚአብሔር በሰጠው በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ፥ ከፀሐይ በታችም በሚደክምበት ድካም ሁሉ ደስ ይለው ዘንድ ነው፤ ይህ እድል ፈንታው ነውና። እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ ባለጠግነትንና ሀብትን መስጠቱ፥ ከእርስዋም ይበላና እድል ፈንታውን ይወስድ ዘንድ በድካሙም ደስ ይለው ዘንድ ማሠልጠኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። መክብብ 5፡18-19
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ብልፅግና #የብልፅግናወንጌል #መፀለይ #ሞገስ #በረከት #ስኬት #እረኛእግዚአብሄር #ስምረት #መሰረታዊፍላጎት #ሁሉየእናንተነውና #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #የተትረፈረፈህይወት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #መርካት #ደስታ #የልብስፋት #ማስተዳደር #እረፍት

Saturday, June 24, 2017

ከእግዚአብሄር የመቀበል ጥበብ

ብዙ ሰዎች ለእግዚአብሄር እንዴት እንደሚሰጡ ያውቃሉ፡፡ ነገር ግን ከእግዚአብሄር እንዴት እንደሚቀበሉ አያውቁም፡፡ የእግዚአብሄርን የመስጠት መንገድ ስለማይረዱ ከእግዚአብሄር ጋር ይተላለፋሉ፡፡ ወይም ከእግዚአብሄር የመቀበለን መንገድ ስለማይረዱ የእግዚአብሄርን መስጠት በአንድ አቅጣጫ ብቻ ስለሚጠብቁ እግዚአብሄር ቢሰጣቸው እንኳን ከእግዚአብሄር ስለተቀበሉት እውቅናንና ምስጋናን ለእግዚአብሄር አይሰጡም፡፡ ከእግዚአብሄር የመቀበል ጥበቡ ስለሌላቸው ለእግዚአብሄር አብዝቶ ለመስጠት የሚገባቸውን ያህል አይነሳሱም፡፡
ለእግዚአብሄር ገንዘብን ስንሰጠው ገንዘብን ጨምሮ ብዙ የሚሰጠን ነገሮች አሉ፡፡ ለእግዚአብሄር አብልጥን ለመስጠት ከእግዚአብሄር የመቀበልን ጥበብ መማር ያስፈልጋል፡፡ ለእግዚአብሄር ገንዘባችንን ፣ እውቀታችንን ፣ ጊዜያችንንና ጉልበታችንን ስንሰጠው ዘርፈ ብዙ በሆነ መንገድ እግዚአብሄር ይከፍለናል፡፡
ከእግዚአብሄር የማንፈልገው ነገር ስለሌለና እግዚአብሄር በሁሉም የህይወታችን እቅጣጫና በሁሉም ነገራችን ስለሚያፈልገን ከእግዚአብሄር እንዴት እንደምንቀበል ማወቅ አለብን፡፡ 
ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። ዕብራውያን 11፡6
የእግዚአብሄር የአከፋፈል መንገዶች
1.      እግዚአብሄር በሃሳብ ይባርከናል
አንድ ስራ ከሃሳብ ይጀምራል፡፡ አንድ ነገር መስራት እንድንችል እግዚአብሄር ሃሳብን ይሰጠናል፡፡ አንድን ነገር ወደፍፃሜ እንድናመጣ እግዚአብሄር በማስፈፀሚያው ሃሳብ ይባርከናል፡፡ እግዚአብሄር አዳዲስ የፈጠራ ሃሳቦችን ይሰጠናል፡፡ እግዚአብሄር በራእይ ይባርከናል፡፡ ገንዘብ ኖሮን ነገሮችን መረዳትና መፈፀም ካልቻልን ምን ይጠቅመናል?
በሰነፍ እጅ የጥበብ መግዣ ገንዘብ መኖሩ ስለ ምንድር ነው? ጥበብን ይገዛ ዘንድ አእምሮ የለውምና። ምሳሌ 17፡16
ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጎድለው፥ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፥ ለእርሱም ይሰጠዋል። ያዕቆብ 1፡5
2.     እግዚአብሄር በመነሳሳት ይባርከናል
እግዚአብሄር በመፈለግ ይባርካል፡፡ እግዚአብሄር ልባችንን ያነሳሳል፡፡ ምንም ሃሳቡ በሌለን ጊዜ ከመቀፅበት ልባችን አንድን ነገር ለማድረግ ይነሳሳል፡፡ አንድ ነገር ጊዜው ሲሆን እግዚአብሄር ከመቀፅበት ልባችንን ያቀጣጥለዋል፡፡ ይህንን የትኛውም ገንዘብ ሊገዛው የማይችል የእግዚአብሄር የመስጫና የመባረኪያ መንገድ ነው፡፡
ስለ በጎ ፈቃዱ መፈለግንም ማድረግንም በእናንተ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና። ፊልጵስዩስ 2፡13
3.     እግዚአብሄር በድፍረት ይባርከናል
ሌላው ለእግዚአብሔር ሰጥተን እግዚአብሄር ለእኛ የሚሰጥበት መንገድ ድፍረት ነው፡፡ ከእኛ የተሻለ የሚታይ ነገር ኖሯቸው ያልደፈሩትን ነገር ለመፈፀም እንድንደፍር ድፍረትን በመስጠት ጌታ ይባረከናል፡፡ እኛም እንኳን አስኪገርመን ድረስ እንድንደፍር እምነትን ይሰጠናል፡፡ ምንም ያህል ገንዘብ ሊገዛው የማይችል እግዚአብሄር ለእኛ የሚሰጥበትና የሚባርክበት መንገድ ነው፡፡
እምነት ግን መጥቶአልና ከእንግዲህ ወዲህ ከሞግዚት በታች አይደለንም። ገላትያ 3፡25
ለአንዱም በዚያው መንፈስ እምነት፥ ለአንዱም በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታ፥ ለአንዱም ተአምራትን ማድረግ፥ 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡9
4.     የልቦናችንን አይኖች በማብራት ይከፍለናል
ለእግዚአብሄር ስንሰጥ ከእግዚአብሄር የምንቀበልበት ሌላው መንገድ የአይን መከፈት ነው፡፡ እግዚአብሄር አይናችንን ይከፍታል፡፡ እግዚአብሄር እይታን ይሰጠናል፡፡ እግዚአብሄርን የልቦናችንን አይኖች ያጠራል፡፡ እግዚአብሄር ዋጋ መስጠት ላለብን ነገር ብቻ ዋጋ እንድንሰጥ ያሳየናል፡፡ እግዚአብሄር አጥርተን በማየት ይባርከናል፡፡
የክብር አባት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እርሱን በማወቅ የጥበብንና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ እለምናለሁ። ኤፌሶን 1፡17
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እምነት #መስጠት #ማካፈል #መባረክ #ስጡ #ምፅዋት #መቀበል #ጥበብ #ማስተዋል #እይታ #ሃሳብ #መነሳሳት #የእግዚአብሄርሃይል #መንፈስቅዱስ #መዝራት #ከልቡ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #ድሃ #መፅሃፍቅዱስ #በደስታ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Friday, June 23, 2017

የውጤታማ ፀሎት ቁልፍ

በፀሎት ውስጥ የተጠራቀመ አጅግ ታላቅ ሃይል አለ፡፡ ስለፀሎት ያለን መፅሃፍ ቅዱሳዊ መረዳት በፀሎት ህይወታችን ፍሬያማ እንድንሆን ያደርጋል፡፡ ፍሬያማ ፀሎትን ከማየታችን በፊት ፍሬያማ ያልሆነን ፀሎት እስኪ እንመልከት፡፡
የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች። ያዕቆብ 5፡16
ፍሬያማ ያልሆነ ፀሎት ንግግር ብቻ ነው፡፡
ፀሎት ከእግዚአብሄር ጋር መነጋገር ነው፡፡ ፀሎት እግዚአብሄርን መስማትና ለእግዚአብሄር መናገር ነው፡፡ ሲጀመር እስኪጨረስ ለእግዚአብሄር መናገር ጸሎት አይደለም፡፡ እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን ስለማናውቅ ሃሳባችንን ለእግዚአብሄር መናገር ብቻ ንግግር እንጂ ፀሎት አይደለም ፡፡
መክብብ 5፡2 ወደ እግዚአብሔር ቤት በገባህ ጊዜ እግርህን ጠብቅ ለመስማት መቅረብ ከሰነፎች መሥዋዕት ይበልጣልና እነርሱም ክፉ እንዲያደርጉ አያውቁምና። እግዚአብሔር በሰማይ፥ አንተም በምድር ነህና በአፍህ አትፍጠን፥ በእግዚአብሔርም ፊት ቃልን ይናገር ዘንድ ልብህ አይቸኵል ስለዚህም ቃልህ ጥቂት ትሁን።
ፍሬያማ ያልሆነ ፀሎት የፈሪ ዱላ ነው፡፡
ፀሎት የፈሪ ዱላ አይደለም፡፡ ፀሎት እግዚአብሄርን ከእንቅልፉ የምንቀሰቅስበት መጥሪያ ጩኸት አይደለም፡፡ ፀሎት ስለህይወታችን ለእግዚአብሄር ካልነገርነው በስተቀር አያውቅም ብለን ለማሳወቅ የምንጥርበት ጥረት አይደለም፡፡ ፀሎት እግዚአብሄር የሚያስፈልገንን ስለማያውቅ የምናሳውቅበት ማስታወቂያ አይደለም፡፡ ፀሎት እግዚአብሄር የማያውቀውን ነገር በመንገር የምናስደንቅበት መንገድ አይደለም፡፡
ስለዚህ አትምሰሉአቸው፤ ሳትለምኑት አባታችሁ የሚያስፈልጋችሁን ያውቃልና። ማቴዎስ 6፡8
ፍሬያማ ያልሆነ ፀሎት እግዚአብሄርን ማስረጃ ነው፡፡
እግዚአብሄር ከእኛ ፀሎት መረጃን ሰብስቦና ተረድቶ የህይወት እቅዳችንን የሚሰራበት መንገድ አይደለም፡፡ የህይወት እቅዳችን ቀድሞውንም በእርሱ ዘንድ አለ፡፡
ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። ኤርሚያስ 29፡11
ፀሎት በእረፍት እግዚአብሄርን መስማትና ለእግዚአብሄር መናገር ነው፡፡  ፀሎት ከአባታችን እግዚአብሄር ጋር የአባትና የልጅ ህብረት የምናደርግበት መንገድ ነው፡፡ ፀሎት ከእግዚአብሄር ጋር ቁጭ የምንልበት መንገድ ነው፡፡ ፀሎት እግዚአብሄር ከእኛ ምን እንደሚፈልግ የምንጠይቅበት መንገድ ነው፡፡ ጸሎት ምን ላድርግልህ የምንልበት መንገድ ነው፡፡ ፀሎት ምኔን ልስጥህ ብለን የምንጠይቅበት መንገድ ነው፡፡ ፀሎት እግዚአብሄርን ለመስማት ፣ ለመታዘዝና ለማገልገል በፊቱ የምንቀመጥበት መንገድ ነው፡፡
ፀሎት እንደ አስተናጋጅ ሁለት እጃችንን ወደኋላ አጣምረን እግዚአብሄር ከእኛ ምን እንደሚፈልግ የምንጠይቅበትና የምንሰማበት የአምልኮና የህብረት ጊዜ ነው፡፡
እነዚህም ጌታን ሲያመልኩና ሲጦሙ መንፈስ ቅዱስ። በርናባስንና ሳውልን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ አለ። ሐዋርያት 13፡2
የእግዚአብሄር መንፈስ ስለእኛ ወይም ስለሌላው እንዴት እንደምንፀልይ የሚመራን በፊቱ በእረፍት ስንሆን ነው፡፡ እንዴት መፀለይ እንደሚገባን መንፈስ ሲመራን ፀሎታችን አላማውን ይመታል፡፡ በእግዚአብሄር ፊት ቆይተን በምሪት የምንፀልየው ፀሎት ግቡን ይመታል፡፡ በእግዚአብሄር መንፈስ ተደግፈን የምንፀልየው ፀሎት ጊዜ ሳይወስድ ዝም ብሎ እንደማይተኩስ ጠብቆ አነጣጥሮ አላማውን እንደሚመታ ተኳሽ በፀሎት ህይወታችን ፍሬያማ ያደርገናል፡፡
እንዲሁም ደግሞ መንፈስ ድካማችንን ያግዛል፤ እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና፥ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል፤ ሮሜ 8፡26
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

Thursday, June 22, 2017

የመስጠት አለምአቀፋዊ ጥያቄና መልሱ

ስጡ ይሰጣችሁማል፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ተመልሶ ይሰፈርላችኋልና፥ የተጨቈነና የተነቀነቀ የተትረፈረፈም መልካም መስፈሪያ በእቅፋችሁ ይሰጣችኋል። ሉቃስ 6፡38
ሰው መስጠት ማካፈል ይፈልጋል፡፡ ማንም ሰው መስጠትና ማካፈል ትክክል አንደሆነ ያውቃል፡፡ መስጠትና ማካለፈል መልካም ነገር እንደሆነ የማይረዳ ሰው የለም፡፡ ሁሉም ሰው ስለመስጠት አስፈለካጊነት ያውቃል፡፡
ሰው ግን እንዳይሰጥ የሚያደርገው ምንድነው? ሰው ታዲያ እንዳይሰጥ የሚያስፈራራው ምንድነው? ብለን ስንጠይቅ ይህን የሰውን ሁሉ አለም አቀፋዊ ጥያቄ እንደሆነ እንረዳለን፡፡
ይህ ሰው እንዳይሰጥ የሚያደርገው ጥያቄ የሰው ሁሉ ሃቀኛ ጥያቄ ነው፡፡ ሰው ለመስጠትና ለማካፈል ይህ እውነተኛ ጥያቄ በትክክል ሊመለስለት ያስፈልገዋል፡፡ ይህን ጥያቄ ለሰው በሚገባ ሳይመለስለት ሰውን ስጥ ማለት አግባብ አይደለም፡፡
ግን ሰው እንዳይሰጥ የሚያግደው ይህ ጥያቄ ምንድነው፡፡ ሰው ሊሰጥ ካለ በኋላ እንኳን እጁን እንዲመልሰው የሚያደርገው ጥያቄ ምን አይነት ጥያቄ ነው?
ይህን ጥያቄ ማንም ቢጠይቀው ማንም ሊኮንነው የማይገባው ሃቀኛ ጥያቄ ነው፡፡ ሰጥቼ እኔስ ባጣ የሚለው ጥያቄ በትክክል ሊመለስለት የሚገባው እውነተኛ ጥያቄ ነው፡፡ ከሰጠሁ በኋላ እኔስ ቢጎድልብኝ የሚለው ጥያቄ አለም አቀፋዊ መለስ የሚገባው አለምአቀፋዊ ጥያቄ ነው፡፡
ስለዚህ ነው ኢየሱስ ስጡ ብሎ ከተናገረ በኋላ ሰጥቼ ቢጎድልብኝስ የሚለውን የሰውን ጥያቄ መልሰ ሲሰጥ ይሰጣችሁማል ያለው፡፡
ስትሰጡ ይሰጣችኋል፡፡ እንዲያውም አለ መስጠት ማቀበል ብቻ አይደለም፡፡ መስጠት ማስተላለፍ ብቻ አይደለም፡፡ መስጠት መዝራት ነው መስጠት ማበርከት ነው፡፡ ስትሰጡ የሰጣችሁት ብቻ ሳይሆን በመልካም መስፈሪያ ተባዝቶ ይሰጣችኋል፡፡
እንዲያውም መስጠት የሰጣችኋት ብቻ ተልክቶ ተመልሶ የምትሰጣችሁ አይደለም፡፡ ተመልሶ የሚሰጣችሁ የሰጣችሁት ብቻ ሳይሆን የተነቀነቀ የተጨቆነ መስፈሪያ ይሰጣችኋል፡፡
ስጡ ይሰጣችሁማል፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ተመልሶ ይሰፈርላችኋልና፥ የተጨቈነና የተነቀነቀ የተትረፈረፈም መልካም መስፈሪያ በእቅፋችሁ ይሰጣችኋል። ሉቃስ 6፡38
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#እምነት #መስጠት #ማካፈል #መባረክ #ስጡ #ምፅዋት #የእግዚአብሄርሃይል #መንፈስቅዱስ #መዝራት #ከልቡ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #ድሃ #መፅሃፍቅዱስ #በደስታ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

Wednesday, June 21, 2017

ገንዘብን ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ይበልጥ የተባረከበት ዋና ዋና ምክኒያቶች

ገንዘብን መስጠት ጥልቅ የሆነ መነሻ ሃሳብ አለው፡፡ ገንዘብን መስጠት ምክኒያት አለው፡፡ ገንዘቡን የሚሰጥ ሰው ገንዘቡን ለመስጠት በቂ ምክኒያት አለው፡፡ ገንዘብን መስጠት ከጀርባው ጥልቅ ምክኒያቶች አሉት፡፡
መስጠት ጥልቅ የሆነ ትርጉም አለው፡፡ ሰው ገንዘቡን ሲሰጥ በተዘዋዋሪ የሚናገረው ነገር አለው፡፡ ገንዘብን የመስጠት ትርጉምን እንመልከት፡፡
ገንዘብን መስጠት አምልኮ ነው፡፡
ገንዘብን መስጠት እግዚአብሄርን ማምለክ ነው፡፡ እግዚአብሄርን የሚያመልከ ሰው ገንዘብን አያመልክም፡፡ እግዚአብሄርን የሚወድ ሰው ገንዘብን ይጠላል እግዚአብሄርን የሚጠጋ ሰው ገንዘብን ይንቃል፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር መልካም ግንኙነት ያለው ሰው ከገንዘብ ጋር መጥፎ ግንኙነት አይኖረውም፡፡ ለእግዚአብሄር የሚገዛ ሰው ለገንዘብ እንደማይገዛ በድርጊቱ እያወጀ ነው፡፡
ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም። ማቴዎስ 6፡24
ገንዘብን መስጠት ምስጋና ነው፡፡
ገንዘብን ስንሰጥ እግዚአብሄር ነው የሰጠኝ እያልን ነው፡፡ ገንዘብን ስንሰጥ ለእግዚአብሄር አቅርቦት እውቅና እየሰጠን ነው፡፡ ገንዘብን ስንሰጥ አመሰግናለሁ እያልን ነው፡፡  
እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ፥ በኀዘን ወይም በግድ አይደለም። 2ኛ ቆሮንቶስ 9፡7
ገንዘብን መስጠት እምነት ነው፡፡
ገንዘብ መተማመኛ ነው፡፡ ከገንዘብ በላይ መተማመኛ የሌለው ሰው ገንዘብን መስጠት አይችልም፡፡ ከገንዘብ በላይ የሚተማመንበት ያለው ሰው ግን ገንዘብን ይሰጣል፡፡ ገንዘብ ስጋትን ይቀንሳል፡፡ ከገንዘብ በላይ ስጋቱን የሚቀንስለትን አምላኩን የሚያውቅ ብቻ ነው ገንዘብን የሚለቀው፡፡ ገንዘብን መስጠት የማይታየውን ማየት ይጠይቃል፡፡
ብልና ዝገት በሚያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በሚሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብ አትሰብስቡ፤ ነገር ግን ብልም ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በማይሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ፤ ማቴዎስ 6፡19-20
ገንዘብን መስጠት ፍቅር ነው፡፡
ገንዘብን የሚሰጥ ሰው ራስ ወዳድ አይደለም፡፡ ገንዘብን የሚሰጥ ሰው ሌላው ከእኔ ይሻላል ብሎ የሚያስብ ሰው ነው፡፡ ገንዘብን የሚሰጥ ሰው ሌላውን የሚያከብርና ለሌላው ዋጋ የሚሰጥ ሰው ነው፡፡ ገንዘብን የሚሰጥ ሰው ለሌላው መልካም የሚያስብ ሰው ነው፡፡  
ገንዘብን መስጠት ርህራሄ ነው፡፡
ገንዘብን መስጠት ለሌላው እንደምናስብ የምናሳይበት መንገድ ነው፡፡ ገንዘብን መስጠት ለሌላው ርህራሄ እንዳለን ያሳያል፡፡ ገንዘብን መስጠት ለራሳችን ብቻ እንዳማናስብ የምናሳይበት መንገድ ነው፡፡ ገንዘብን መስጠት በምድር ላይ ያለነው ሌላውን ለማገልገን እንደሆነ የምናሳይበት መንገድ ነው፡፡ ገንዘብን መስጠት እግዚአብሄር የሰጠን የምንበላውን ብቻ እንዳልሆነና የምንዘራውንም እንደሰጠን እውቅና የምንሰጥበት መንገድ ነው፡፡  
የሚመክርም ቢሆን በመምከሩ ይትጋ፤ የሚሰጥ በልግስና ይስጥ፤ የሚገዛ በትጋት ይግዛ፤ የሚምር በደስታ ይማር። ሮሜ 12፡8
ገንዘብን መስጠት በእግዚአብሄር መደገፍ ነው፡፡
በገንዘብ የሚደገፍ ሰው ገንዘብን አይሰጥም፡፡ ገንዘብ የህይወት ጥያቄውን ሁሉ የሚፈታለት የሚመስለው ሰው ገንዘብን አይሰጥም፡፡ ገንዘብ ግን ውስን እንደሆነ ገንዘብ ሊገዛ የማይችላቸው ብዙ ነገሮች እንዳሉና እግዚአብሄርን ከገንዘብ ውጭ ስለብዙ ነገሮች እንደምንፈልገው የተረዳ ሰው ገንዘቡን ለመስጠት አይቸግረውም፡፡ የሰው ልጅ ቁልፍ በገንዘብ ውስጥ ሳይሆን በጌታ እጅ እንዳለ ያወቀ በጌታ በመመካት ገንዘበኑን ይሰጣል፡፡  
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጠቢብ በጥበቡ አይመካ፥ ኃያልም በኃይሉ አይመካ፥ ባለ ጠጋም በብልጥግናው አይመካ፤ ነገር ግን የሚመካው፦ ምሕረትንና ፍርድን ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን በማወቁና በማስተዋሉ በዚህ ይመካ፤ ደስ የሚያሰኙኝ እነዚህ ናቸውና፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡ ኤርሚያስ 9፡23-24
ገንዘብን መስጠት መኖሪያዬ ገንዘብ አይደለም ማለት ነው፡፡
ገንዘብን መስጠት መኖሪያዬ ገንዘብ አይይደለም የሚል መልክት አለው፡፡ ገንዘብን መኖሪያቸው የሆነ ሰዎችና ከገንዘብ ኑሮ ያለፈ ነገር የማይታያቸው ሰዎች ገንዘብን አይሰጡም፡፡ ገንዘብ እንደማያኖረውና የእርሱ መኖሪያ እግዚአብሄር እንደሆነ የሚያውቀ ሰው ገንዘቡን ይሰጣል፡፡  
መኖሪያህ የዘላለም አምላክ ነው፥ የዘላለምም ክንዶች ከአንተ በታች ናቸው፤ ዘዳግም 33፡27
ሰውም ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ነገር ሁሉ በሕይወት እንዲኖር እንጂ ሰው በእንጀራ ብቻ በሕይወት እንዳይኖር ያስታውቅህ ዘንድ አስጨነቀህ፥ አስራበህም፥ አንተም ያላወቅኸውን አባቶችህም ያላወቁትን መና አበላህ። ዘዳግም 8፡3
ገንዘብን መስጠት ፀሎት ነው፡፡
ገንዘብን መስጠት እግዚአብሄርን በገንዘብ የምገዛቸውን ነገሮች አንተ አሟላ ማለት ነው፡፡ ገንዘብን መስጠት ስጡ ይሰጣችሁዋል የሚለውን እግዚአብሄርን መለመኛው መንገድ ነው፡፡ መስጠት እግዚአብሄርን ለተጨማሪ ገንዘብ መለመኛው መንገድ ነው፡፡ ገንዘቡን ሰጥቶ የሚጎድልበት ሰው ስለሌለ መስጠት በተዘዋዋሪ አይጉደልብኝ የሚል ልመና ነው፡፡
ስጡ ይሰጣችሁማል፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ተመልሶ ይሰፈርላችኋልና፥ የተጨቈነና የተነቀነቀ የተትረፈረፈም መልካም መስፈሪያ በእቅፋችሁ ይሰጣችኋል። ሉቃስ 6፡38
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እምነት #መስጠት #ማካፈል #መባረክ #ስጡ #ምፅዋት #የእግዚአብሄርሃይል #መንፈስቅዱስ #መዝራት #ከልቡ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #ድሃ #መፅሃፍቅዱስ #በደስታ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

Monday, June 19, 2017

የይቅርታ ክብር

እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፥ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፥ ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ፤ ቆላስይስ 3፥13
ይቅር ማለት ክብር ነው፡፡ ማንም መንገደኛ የበደለው ላይ ይይዝበታል ይቅር ማለት ግን ከፍ ያለ የህይወር ደረጃ ነው፡፡ ይቅር
ይቅርታ የጥበበኞች ነው፡፡ ይቅር የሚልና የሚተው ሰው እነዚህን ወሳኝ ጥበቦች የተረዳ ሰው ነው፡፡ ይቅር የሚልና የሚለቅ ሰው መልካም መረዳት ያለውቀ ሰው ነው፡፡
የይቅርታ እውነተኛ ትርጉም
1.      ይቅር የሚል ሰው ይቅር መባሉን የማይረሳ ሰው ነው፡፡
ይቅር መባሉ የማያደንቅና በልቶ ከገሃዲ የሆነ ሰው ይቅር ለማለት ይቸግረዋል፡፡ ይቅር መባሉን የሚያስታውስና የሚያደንቅ ሰው ይቅር ለማለት ይቀለዋል፡፡ ይቅር የሚል ሰው ታላቁ ሃጢያቱ ይቅር የተባለው ሌሎችን ትንንሽ ሃጢያቶች ይቅር እንዲል መሆኑን የተረዳ ሰው ነው፡፡ ይቅርታ ታላቁን ሃጢያት ይቅር ስለመባላችን ለእግዚአብሄር አድናቆታችንንና ምስጋናችንን የምናሳይበት ወርቃማ አጋጣሚ ነው፡፡
ከዚያ ወዲያ ጌታው ጠርቶ፦ አንተ ክፉ ባሪያ፥ ስለ ለመንኸኝ ያን ዕዳ ሁሉ ተውሁልህ፤ እኔ እንደ ማርሁህ ባልንጀራህ የሆነውን ያን ባሪያ ልትምረው ለአንተስ አይገባህምን? አለው። ማቴዎስ 18፡32-33
2.     ይቅር የሚል ሰው ወደፊትም ይቅርታ እንደሚያስፈልገው የሚረዳ ሰው ነው፡፡
የምንኖረው በእግዚአብሄር ምህረት ነው፡፡ የምንኖረው በሰው ምህረት ወይም በሰይጣን ምህረት አይደለም፡፡ የምንኖረው የእግዚአብሄርን ምህረት ተስፋ በማድረግ ነው፡፡ ወደፊትም የእግዚአብሄር ምህረት እንደሚያስፈልገው የሚረዳ ሰው ምህረት ለማድረግ ይበረታታል፡፡ ነገር ግን ከጥፋት ያለፈ የመሰለውና በትእቢት ራሱን ላይ የሰቀለ ሰው ምህረት ለማድርግ ይኩራራል፡፡  
3.     ይቅር የሚል ሰው ነፃ መሆን የሚፈልግ ሰው ነው፡፡
ይቅር የሚል ሰው የበደለውን ሰው መከታተል ፣ ስለበደለው ሰው የራሱን የህይወት መለወጥ የማይፈልግ ሰው ነው፡፡ ይቅር የሚል ሰው የህይወት አላማውን የተረዳ ከሩጫው ማንም እንዲያደናቅፈው የማይፈልግ ሰው ነው፡፡ ይቅር ማለት የሚፈልግ ሰው የበደለውን ሰው በመከታተል በበደለው ሰው ባተሌ በመሆን ህይወቱን ማባከን የማይፈልግ ነው፡፡ ይቅር የማይል ሰው ስለበደለው ሰው ቀን ከሌሊት ሲያስብ ፣ ስለበደለው ሰው ሲናገር ስለበደለው ሰው ሲንቀጠቀጥና ጉልበቱን ሲፈጅ የበደለውን ሰው ኑሮ ይኖራል፡፡ ይቅር የማይል ሰው ስለማይለቅና ስለማይተው የራሱን ህይወት ትቶ ከበደለው ሰው ጋር በደባልነት ይኖራል፡፡ ይቅር የማይል ሰው የራሱን ህይወት ትቶ በደሉን በበዳዩ ላይ ፅፎ ይዞ በዳዩ በየሄደበት የሚከታተል ሰው ነው፡፡  
4.     ይቅር የሚል ሰው ህይወቱን በራሱ መምራት የሚፈልግ ሰው ነው፡፡
ይቅር ማለት የሚፈልግ ሰው ህይወቱን አቅጣጫ ስለበደለው ሰው ለመለወጥ የማይፈልግ ሰው ነው፡፡ ይቅር የሚል ሰው የህይወት ራእዩን ጥሎ በሌላ ጉዳይ መገኘት የማይፈልግ ሰው ነው፡፡ ይቅር ማለት የሚፈልግ ሰው የራሱን የህይወት አላማ በበደለው ሰው ህይወት መለወጥ የማይፈልግ ሰው ነው፡፡ ይቅር ማለትና የበደለውን መልቀቅ የሚፈልግ ሰው የራሱን ህይወት በራሱ መምራት የሚፈልግ ሰው ነው፡፡ ይቅር ማለት የሚፈልግ ሰው የራሱን ህይወት በበደለው ሰው እጅ ላይ መጣል የማይፈልግ ሰው ነው፡፡  
5.       ይቅር ማለት የሚፈልግ ሰው ለዲያቢሎስ እድል ፈንታ መስጠት የማይፈልግ ሰው ነው
ይቅር አለማለትና ጥላቻ የሰይጣን ለም መሬት ነው፡፡ ጥላቻ ለሰይጣን ሰራ ተስማሚ የአየር ሁኔታ ነው፡፡ ሰው ጥላቻን ካስተናገደ ወደደም ጠላም ሰይጣን ይጠቀምበታል፡፡ የሰይጣን አላማው ደግሞ የሚበድለውንም የሚበደለውንም መስረቅ ማረዳ ማጥፋት ነው፡፡ (ዮሃንስ 10፡10) የሰይጣን መጠቀሚያ መሆን የማይፈልግ ስው ይቅር ይላል፡፡ ቆሻሻ መካከል እየኖሩ ዝምብ አይምጣብኝ ማለት እንደማይቻል ሁሉ ይቅር ሳይሉ ስፍራ እየሰጡት ሰይጣን አይንካኝ ማለት አይቻልም፡፡ በተዘዋዋሪ ሰይጣንን  መቃወሚያው መንገድ ጥላቻን አለማስተናገድና ፈጥኖ ይቅር ማለት በምህረት መመላለስ ነው፡፡
በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፥ ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት። ኤፌሶን 4፡27
6.       ይቅር የሚል ሰው የሰውን ህይወት እንደማይቆጣጠር የተረዳ ሰው ነው፡፡
ይቅር ማለት የሚፈልግ ሰው የራሱ ህይወት እንጂ የሰውን ህይወት መቆጣጠር እንደማይችል ልኩን ያወቀና የተረዳ ሰው ነው፡፡ ይቅር የሚል ሰው ሌላው እንዳይበድለው ማድረግ እንደማይችል ያወቀ ሰው ነው፡፡ ማድረግ የሚችለው ነገር ይቅር ማለት ፣ መተውና  መልቀቅ መሆኑን የተረዳ ሰው ነው፡፡ ይቅር የሚል ሰው ራሱ ተበቃይ እንዳይደለና ፈራጅ ሌላ እንዳለ የተረዳ ሰው ነው፡፡
ተወዳጆች ሆይ፥ ራሳችሁ አትበቀሉ፥ ለቍጣው ፈንታ ስጡ እንጂ፤ በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና። ሮሜ 12፡19
7.       ይቅር ማለት የሚችል ሰው እኔ እሻላለሁ የሚል ሰው ነው፡፡
ይቅር ማለት የሚችል ሰው የበደለው ሰው ስለበደለ ብቻ እንደተጎዳ የሚያስብና ተበዳዩ እንደሚሻል የተረዳ ሰው ነው፡፡ ሰው ከሚበድል መበደል ይሻለዋል፡፡ የሚበድል ሰው አይጠቀምም በከንቱ ይበድላል፡፡ የሚበደል ሰው ግን እግዚአብሄር ይክሰዋል፡፡ ይቅር የሚል ሰው ርህራሄ የሚሰማውና እኔ እሻላለሁ የሚል የአዘኔታ ልብ ያለው ሰው ነው፡፡
እንግዲህ ፈጽሞ የእርስ በርስ ሙግት እንዳለባችሁ በእናንተ ጉድለት ነው። ብትበደሉ አይሻልምን? ብትታለሉስ አይሻልምን? 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ 6፥7
8.       ይቅር የሚል ሰው መበደሉ ምንም እንዳማያመጣ የተረዳ ሰው ነው፡፡
የሰው የወደፊት እድል ፈንታ የተያዘው በሰው እጅ አይደለም፡፡ የሰው ፈራጅ እግዚአብሄር ነው፡፡ በፅድቅ የሚፈርድ እግዚአብሄር በሰማይ አለ፡፡ ሰው ተበደለም አልበደለም ለውጥ አያመጣም፡፡ ሰው ተበደለም አልተበደለም ምንም ማለት አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ነው ፈራጅ፡፡ ይቅር የሚል ሰው ፅድቅን በሚያደርገው በእግዚአብሄር የሚመካ ሰው ነው፡፡ ይቅር ሚል ሰው እግዚአብሄርን ደስ የሚያሰኘው ማስተዋል ያለው ሰው ነው፡፡
ነገር ግን የሚመካው፦ ምሕረትንና ፍርድን ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን በማወቁና በማስተዋሉ በዚህ ይመካ፤ ደስ የሚያሰኙኝ እነዚህ ናቸውና፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡ ኤርምያስ 9፥24
መበደል ሳይሆን ይቅር አለማለቱ ሰውን ይጎዳዋል፡፡ ሰው ሲበድለን እግዚአብሄር ይክሰናል፡፡ ይቅር ካላልን ግን ይቅር ባለማለታችን እንጎዳለን እንጂ እግዚአብሄር የሚያደርግልን ነገር የለም፡፡ ሰውን የሚጎዳው መበደል ሳይሆን ይቅር አለማለት ነው፡፡
9.       ይቅር የሚል ሰው ይቅር አለማለቱ በዳዩን እንደማይጎዳ የተረዳ ሰው ነው፡፡
በደሉ ተፈፅሟል፡፡ ጥፋተኛ ከሆነ እንደበዳዩ ደረጃ የሚፈርደው እግዚአብሄር ነው፡፡ የተበደለ ሰው ይቅር አለማለቱ በፍርዱ ላይ ምንም ተፅእኖ የለውም፡፡ የተበደለ ሰው ግን ይቅር ካላለ በራሱ ህይወት ላይ ጉዳት ያመጣል፡፡ የተበደለ ሰው ቶሎ ይቅር ስላለ እግዚአብሄር የበዳዩን ጥፋት አያቀልለትም፡፡ ለረጅም ጊዜ ስለያዘው ደግሞ ጥፋቱን አያከብድውም፡፡ ይቅር ያላለ ሰው የሚጎዳው ራሱን ብቻ ነው፡፡   
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ይቅርታ #ምህረት #ፍርድ #ጠላት #ዲያቢሎስ #ስፍራ #ኢየሱስ #ጥላቻ #ትእቢት #መራርነት #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ