Popular Posts

Tuesday, December 13, 2016

የእለት እንጀራችንን እለት እለት ስጠን

የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን፤ ማቴዎስ 6፡11
ለአብዛኞቻችን መሰረታዊ ፍላጎት ዋና የህይወት ጥያቄ አይመሰለንም፡፡ ነገር ግን ዋናው የህይወት ጥያቄ የእለት እንጀራ ነው፡፡ የእለት እንጀራ ለኑሮ የሚያስፈልገን መሰረታዊ ፍላጎትን ሁሉ ያጠቃልላል፡፡  
በህይወት ስለብዙ "ትልልቅ" ነገሮች ጌታን ማመን ያለብን ይመስለናል፡፡ ሰው ለመሰረታዊ ፍላጎት እግዚአብሄርን ካመነ አረፈ ማለት ነው፡፡ ምክኒያቱም በህይወት የሚያስፈልገው ዋና ነገር መሰረታዊ ፍላጎትን አማልቶ ጌታን መከተል ነው፡፡
የመኖር አላማችን ጌታን መከተል ፣ ለጌታ መኖርና ኢየሱስን በህይወታችን ማክበር ነው፡፡ የምንኖረው ለመኖር ብቻ አይደለም፡፡ የምንኖረው ኢየሱስን በመምሰል ስለ ኢየሱስ አዳኝነትና ጌትነት በምድር ላይ ለመመስከር ነው፡፡
ስለ ኢየሱስ አዳኝነትና ጌትነት በምድር ላይ ለመመስከር የሚያስፈልገን መሰረታዊ ፍላጎታችን መሟላቱና ነው፡፡
ብዙ ሰው ስለብዙ ነገር ታላቅ እምነት እንዲኖረው ይፈልጋል፡፡ ሰው ኢየሱስ ስለ እርሱ ሃጢያት በመስቀል ላይ እንደሞተ ከማመን ቀጥሎ የመጀመሪያውና መሰረታዊው እምነት ስለ እለት እንጀራው ወይም ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ ጌታን ማመን ነው፡፡
ስው ስለ መሰረታዊ ፍላጎቱ ጌታን ካላመነ ስለምንም ሌላ ነገር አምናለሁ ሊል ይዋሻል፡፡ ሰው ስለመሰረታዊው ፍላጎቱ ካላመነ ስለ ትልልቅ ነገር ጌታን አምናለሁ ቢል ምንም አይጠቅመውም፡፡
ሰው ስለ መሰረታዊ ፍላጎቱ ስለሚበላው ፣ የቤት ኪራይ ስለሚከፍለው ፣ ስለ ልጆቹ ትምህርት ቤት ፣ ስለ መኪናው ነዳጅ ጌታን ካመነ እግዚአብሄርን በነፃነት ማገልገል ይችላል፡፡ የኑሮ ጭንቀት ፊት ከሰጠነው ማናችንንም በቁማችን ሊውጠን ስለሚችል ሰው ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ ጌታን ካላመነ ጌታን ለማገልገል ነፃነት ሊኖረው አይችልም፡፡  
ሰው ብዙ አላስፈላጊ እርምጃ ሲወስድ የሚየታየው ስለመሰረታዊ ፍላጎት ጌታን ባለማመኑ ነው፡፡ ሰው የሚዋሸው ፣ የሚያጭበረብረው ፣ ሌላውን የሚጠላው ስለመሰረታዊ ፍላጎት ጌታን ስለማያምን ነው፡፡
ስለመሰረታዊ ፍሎጎቱ ጌታን ያመነ ሰው ጌታ የእለት እንጀራውን በእለቱ እንደሚሰጠው አጥብቆ የተረዳ ሰው ፀጥና ዝግ ብሎ በመኖር ጌታን ሲያሳይ ለብዙዎች ምሳሌ ሊሆንና በሚቀናበት የክርስትና ህይወት ጌታን በምድር ቆይታው ሲያስከብ እናያለን፡
የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን፤ ማቴዎስ 6፡11
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ጭንቀት #የኑሮሃሳብ #የእለትእንጀራ #የባለግነትምቾት #ዘር #መሰረታዊፍላጎት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

Monday, December 12, 2016

የሙሉ ፍሬ ጠላት

ኢየሱስ በዘር ስለሚመሰለው የእግዚአብሄር ቃል በምሳሌ ያስተምር ነበር፡፡ የዘርን ስኬት የሚወስነው የሚዘራበት የሰው ልብ እንደሆነ በምሳሌ ያስረዳቸዋል፡፡   
በምሳሌም ብዙ ነገራቸው እንዲህም አላቸው፦ እነሆ፥ ዘሪ ሊዘራ ወጣ። ማቴዎስ 13:3
ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፥ እሾህም ወጣና አነቀው። ማቴዎስ 13:7
ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፥ እሾሁም አብሮ በቀለና አነቀው። ሉቃስ 87
በእሾህ መካከል የተዘራውም ይህ ቃሉን የሚሰማ ነው፥ የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት መታለል ቃሉን ያንቃል፥ የማያፈራም ይሆናል። ማቴዎስ 13:22
በእሾህ መካከልም የወደቀ እነዚህ የሚሰሙት ናቸው፤ መንገዳቸውንም ሄደው በሕይወት ዘመን በአሳብና በባለ ጠግነት ምቾት ይታነቃሉ፥ ሙሉ ፍሬም አያፈሩም። ሉቃስ 814
የምንሰማውም የእግዚአብሄር ቃል ሃያል ሆኖ ሳለ በህይወታችን እንዳይሰራ የሚያግደው አስቀድመን ልባችንን የሰጠንለት ነገር ነው፡፡
የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፥ የሚሠራም፥ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፥ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፥ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል፤ ዕብራውያን 4፡12
አስቀድሞ ህይወታችንን የያዘው ነገር የምንሰማው ቃል ሙሉ ፍሬ እንዳያፈራ ያንቀዋል፡፡ የእግዚአብሄር ቃል ለማደግና ለማፍራት በቂ እድል እንዳያገኝ ያስረዋል፡፡
የእግዚአብሄር ቃል ስፍራን አግኝቶ ሙሉ ፍሬ እንዳያፈራ የሚገዳደረው አስቀድመን ልባችንን የሰጠንለት የኑሮ ጭንቀትና የባለጠግነት ምኞት ነው፡፡
ለኑሮ ጭንቀት ራሳችንን በሰጠን መጠን የእግዚአብሄር ቃል በእኛ ላይ ሃይል እንዳይኖረው እናግደዋለን፡፡ ለባለጠግነት ማታለል ራሳችንን ከሰጠን የእግዚአብሄር ቃል በህይወታችን እንዳይሰራ እንበርዘዋለን፡፡ የባለጠግነት ምኞት በህይወታችን ስፍራን ካገኘ የእግዚአብሄር ቃል ሙሉ ፍሬ እንዳያፈራ ያግደዋል፡፡
ፀሎት፡ እግዚአብሄር አባቴ ሆይ ይህንን ቃል እንድሰማ ስለላክልፅ አመሰግንሃለሁ፡፡ ቃልህን ሰምቻለሁ፡፡ የኑሮ ጭንቀት ቃልህ በህይወቴ እንደሚገባው አንዳይሰራ እንደሚያግደው ከቃልህ ተረድቻለሁ፡፡ እግዚአብሄር ሆይ አንተን እታዘዛለሁ፡፡ በህይወቴ ለጭንቀት ፊት አልሰጥም፡፡ ፀጋህ ስለሚረዳኝ አመሰግንሃለሁ፡፡ አሜን
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ጭንቀት #የኑሮሃሳብ #ብልፅግና #የባለግነትምቾት #ዘር #መሰረታዊፍላጎት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

Sunday, December 11, 2016

ዓመቱ ሲመዝን

ክርስትያን በየጊዜው ህይወቱን በእግዚአብሄር ቃል መመዘን አለበት፡፡ በየጊዜው የማይገመገምና የማይፈተሽ ህይወት ከንቱ ህይወት ነው፡፡
ሃዋሪያው የእግዚአብሄርን ስራ ለረጅም ጊዜ ከሰራ በኋላ ተመልሶ በከንቱ ሮጬ እንዳይሆን በማለት ህይወቱን ሲመዝን እናያለን፡፡  
ፈትኖ መልካም እንዲሆን በሚቈጥረው ነገር በራሱ ላይ የማይፈርድ ብፁዕ ነው። ሮሜ 14፡22
ሰዎች በትክክል ህይወታቸውን መመዘን ካልቻሉ ስህተታቸውን ማስተካከል አይችሉም፡፡ ሰዎች እንዴት ህይወታቸውን ከጊዜ ወደጊዜ መመዘን እንዳለባቸው ካላወቁ ለተሻለም ስራ አይነሱም፡፡ ሰዎች ህይወታቸውን በትክክል መመዘን ካልቻሉ ደስታቸውን ያጣሉ፡፡ ሰዎች በትክክል ህየወታቸውን ካልመዘኑ እግዚአብሄር በውስጣው ባስቀመጠው በጎነት እግዚአብሄርን ፈፅመው ማክበር አይችሉም፡፡
ህይወታችንን ግን እንዴት ነው የምንመዝነው፡፡
በክርስትና ህይወታችንን የምንመዝንበት መንገድ ታማኝነታችንን በመመዘን ብቻ ነው፡፡ ከታማኝነት ውጭ ራሳችንን ለመመዘን የምንችልበት ትክክለፃ መመዘኛ አናገፅም፡፡   
ታማኝነት የህይወታችን ብቸኛው መለኪያ ነው፡፡ ሰው ታማኝነቱ የሚታየው ባለው ፣ እግዚአብሄር በሰጠውና በእጁ ባለው ነገር ነው ፡፡ እግዚአብሄር የሚጠይቀን የሰጠንን መክሊት እንዴት እንደተጠቀምንበት ነው፡፡
·         ታማኝነታችን የሚለካው ባለን እወቀት ነው፡፡ 
ታማኝነታችን የሚለካው በሆነ እውቀት ሳይሆን ባለን እውቀት በተሰጠን እውቀት ምን ያህል ታማኝ መሆናችን ነው፡፡
የጌታውንም ፈቃድ አውቆ ያልተዘጋጀ እንደ ፈቃዱም ያላደረገ ባሪያ እጅግ ይገረፋል፤ ያላወቀ ግን መገረፍ የሚገባውንም ያደረገ ጥቂት ይገረፋል። ብዙም ከተሰጠው ሰው ሁሉ ከእርሱ ብዙ ይፈለግበታል፥ ብዙ አደራም ከተሰጠው ከእርሱ አብዝተው ይሹበታል። ሉቃስ 12፡47-48
·         ታማኝነታችን የሚለካው እግዚአብሄር በሰጠን ጊዜ ነው፡፡ 
እግዚአብሄር የሰጠኝን ጊዜ በትክክል ለእግዚአብሄር ክብር አውዬዋለሁ፡፡ እግዚአብሄር የሰጠኝን ጊዜ ቃሉን ለማንበብ በሚገባ ተጠቅሜበታለሁ፡፡ እግዚአብሄር የሰጠኝን ጊዜ ጌታን ለማምለክ ተጠቅሜበታለሁ? እግዚአብሄር የሰጠኝን ጊዜ ፊቱን ለመፈለግ ተጠቅሜበታለሁ?   
·         ታማኝነታችን የሚለካው በሃይል አስተዳደራችን ነው፡፡ 
እግዚአብሄር የሰጠንን ሃይልና ችሎታ ለክፉ ነገር ላለመጠቀም መወሰናችን ታማኞች ያደርገናል፡፡ እግዚአብሄር የሰጠንን ሃይል ግን በጥላቻና በመለያየት ላይ ካጠፋነው በታማኝነት አልተመላለስንም፡፡ 
·         ታማኝነታችን የሚለካው እግዚአብሄር በሰጠን ገንዘብ ነው፡፡
እግዚአብሄር ለመብላት የሰጠንን መብላታችን እግዚአብሄር ለመዝራት የሰጠንን በመዝራታችን ታማኝነታችን ይለካል፡፡
·         ታማኝነታችን የሚለካው የተሰጠንን መክሊት አጠቃቀማችን ነው፡፡
ታማኝነታችን የሚለካው እግዚአብሄር የሰጠንን መንፈሳዊ ስጦታን ለቤተክርስቲያን ጥቅምና ለእግዚአብሄር ክብር እንዴት በታማኝነት እንደተጠቀምንበት ነው፡፡  
አንድ የተቀበለው ግን ሄዶ ምድርን ቈፈረና የጌታውን ገንዘብ ቀበረ። ከብዙ ዘመንም በኋላ የእነዚያ ባሮች ጌታ መጣና ተቆጣጠራቸው። ማቴዎስ 25፡18-19
·         ታማኝነት የሚለካው በተሰጠን ተፅእኖ ነው፡፡
ታማኝነታችን የሚለካው በተሰጠን የተሰጠንን ተሰሚነት ለእግዚአብሄ ክብር ወይም ለራሳችን ጥቅም መጠቀማችን ነው፡፡
ጌታውም፦ መልካም፥ አንተ በጎ፥ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፥ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው። ማቴዎስ 25፡23
ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ የተባለው ባሪያ ለተሻለ ሃላፊነት ይሾማል፡፡ አስተውላችሁ እንደሆነ የጠየቃቸው ያልሰጣቸውንም ሳይሆን የሰጣቸውን አንዴት በታማኝነት እንዳስተዳደሩት ብቻ ነው፡፡ የምንመዝነው ታማኝነታችንን ብቻ ነው፡፡ ታማኝ ከነበርን ፈተናውን አልፈናልና ደስ ሊለን ይገባል፡፡
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ታማኝ #ትጉህ #መክሊት #ትውልድ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ሃሳብ #ገንዘብ #ጊዜ #ትግስት #መሪ

Saturday, December 10, 2016

መንግሥት ያንተ ናትና ኃይልም ክብርም

የኢየሱስን የፀሎት ፍሬ ያየ ከደቀመዛሙርቱ አንዱ ኢየሱስን እንጸልይ ዘንድ አስተምረን ብሎ ጠየቀው፡፡ እውነትም ኢየሱስ ፀሎትን በሙሉ ፍሬያማነት የተጠቀመበት ነበር፡፡ ኢየሱስ የፀሎት ሰው ነበር፡፡ እየሱስ ውጤታማን ፀሎት የኖረውም ያስተማረውም ነበር፡፡
እርሱም በአንድ ስፍራ ይጸልይ ነበር፥ በጨረሰም ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፦ ጌታ ሆይ፥ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱን እንዳስተማረ እንጸልይ ዘንድ አስተምረን አለው። ሉቃስ 11፡1
ኢየሱስ ግን እናንተስ እንዲህ ፀልዩ በማለት ያስተማራቸውን የመጨረሻውን መስመር እንመልከት፡፡
መንግሥት ያንተ ናትና ኃይልም ክብርም ለዘለዓለሙ፤ አሜን። ማቴዎስ 6፡13
ይህ ማለት ይህን ፀሎት የምንፀልየው በአንተ ሃይል በመተማመን ነው፡፡ መንግስት ያንተ ነው ፣ ሃይልም ያንተ ነው ፣ ክብርም ያንተ ነው ፡፡
አንተ ትችላለህ የሚሳንህ የለም፡፡
ስለዚህ የምንፀልየው በእረፍት ነው፡፡
የምንፀልየው በእምነት ነው፡፡
የምንፀልየው በመተማመን ነው፡፡
ስለዚህ ነው መፅሃፍ ቅዱስ ስለፀሎት ሲናገር ከምስጋና ልመናችሁን አስታውቁ የሚለው፡፡
ጌታ ቅርብ ነው። በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። ፊልጵስዩስ 4፡6
ፀሎት ለእግዚአብሄር ሃይል እውቅና በመስጠት መሆን ይኖረበታል፡፡ ፀሎታችን ለእግዚአብሄር ቻይነት እውቅና በመስጠት፡፡
ከእረፍት ያልሆነ ፀሎት እግዚአብሄርን አያስደስተው፡፡ በእግዚአብሄር ላይ የማረፍ ፣ በእግዚአብሄር ላይ የመደገፍ ፣ በእግዚአብሄር የመተማመን ፀሎት እግዚአብሄርን ያስደስተዋል፡፡  
ፀሎታችን በዚህ መረዳት ነው፡፡ ልመናችን ይህን እውቅና በመስጠይት ነው፡፡ ፀሎታችን በእረፍት በመተማመንና በእምነት ነው፡፡
መንግሥት ያንተ ናትና ኃይልም ክብርም ለዘለዓለሙ፤ አሜን። ማቴዎስ 6፡13
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ፀሎት #ምልጃ #ምስጋና #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ደቀመዝመር #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልመና #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እረፍት #መተማመን #እምነት #መደገፍ

Friday, December 9, 2016

ጸጋዬ ይበቃሃል !

በክርስትና ህይወታችን ብዙ የሆኑልን መልካም ነገሮች አሉ፡፡ ስለሆነልን ነገሮች ሁሉ እግዚአብሄርን ሁል ጊዜ እናመሰግነዋለን፡፡ ብዙም እንዲሆኑልን የምንፈልጋቸው ነገሮች ደግሞ አሉ፡፡ ደግሞም ጸልየን ለምነን እንደጠበቅነው ያልሆኑልን ነገሮች ደግሞ እንዳሉ ማመንም ወሳኝ ነው፡፡
በህይወታችን እንዲሆኑልን ጠይቀን እንዳሰብነው ስላልሆኑ ነገሮች ምን ማድረግ እንደሚገባን የእግዚአብሄር ቃል ምን እንደሚል ማወቅ ያሳርፈናል፡፡  
ሃዋሪያው ጳውሎስ በህይወቱ ስለነበረው ድካም እንደፀለየ እንደለመነ እንመለከታለን፡፡ ምንም ቢለምን ሊሆንለት አልቻለም፡፡ ደጋግሞ ስለዚያ ነገር እግዚአብሄርን ሲለምን እናየዋለን፡፡
ስለዚህ ነገር ከእኔ እንዲለይ ሦስት ጊዜ ጌታን ለመንሁ። 2ኛ ቆሮንቶስ 12፡8
ደስ የሚለው ነገር ግን ለምነን ነገሩ ባይሆንም እንኳን በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ ሁል ጊዜ መንገድ አለ፡፡ እግዚአብሄር ለሁሉ መፍትሄ አለው፡፡ ከፊታችን ያላነሳውን ተራራ እንዴት እንደምናልፈው የሚያበረታበት መንገድ አለው፡፡
በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ ያበቃና የተቆረጠ ተስፋ የሌለው ነገር የለም፡፡ ወደ እግዚአብሄር ፀልየን የማይመለስ መልስ የለም፡፡ እግዚአብሄር ሁሉንም ይመልሳል፡፡ እግዚአብሄር ግን የሚመልሰው እኛ በጠበቅነው መንገድ ላይሆን ይችላል፡፡ እግዚአብሄር ግን ሁሌ ይመልሳል፡፡
እርሱም፦ ጸጋዬ ይበቃሃል፥ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና አለኝ። እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ። 2ኛ ቆሮንቶስ 12፡9
በእግዚአብሄር ዘንድ የማይቻል ፣ የማይታለፍና የማይሆን ነገር የለም፡፡ ከፊታችን ያለውን ውሃ ካላደረቀው በውሃ ውስጥ ባለፍን ጊዜ በውሃው የማንሰጥምበትን ፀጋ ሰጥቶናል ማለት ነው፡፡ የእሳቱን ነበልባል ካላጠፋው በእሳት ውስጥ ሳንቃጠል የምናልፍበት ፀጋ በውስጣችን አለ ማለት ነው፡፡ ተራራውን ዘወር ካላደረገው ተራራውን የምንወጣበትና የምናልፍበት የሚያስችል ሃይል ተሰጥቶናል ማለት ነው፡፡
እንደ እኛ አጠባበቅ እግዚአብሄር ላልመለሳቸው ፀሎቶች የእግዚአብሄ አምላካዊ መልስ "ጸጋዬ ይበቃሃል፥ ኃይሌ በድካም ይፈጸማል" የሚል ነው፡፡
ደስ የሚለው ነገር በሁለቱም አሸናፊው እኛ ነን፡፡ እግዚአብሄር ለእኛ ነው፡፡ እግዚአብሄር ከእኛ ጋር ነው፡፡ እግዚአብሄር ባእኛ  ወስጥ ነው፡፡
ጸጋዬ ይበቃሃል!
ጸጋዬ ይበቃሃል!
ጸጋዬ ይበቃሃል!
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #መሪ #ፀጋ #የሚያስችልሃይል #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ፅድቅ #እግዚአብሄርንመምሰል #ራስንመግዛት #ልብ

Thursday, December 8, 2016

የንስሃ ህይወት

በአዳም ምክኒያት የሰው ልጅ ሁሉ በሃጢያት እስራት ውስጥ ወድቆዋል፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ለመኖር ንስሃ መግባት አለበት፡፡
የአለም የአሰራር ስርአትና የእግዚአብሄር መንግስት አሰራር ፍፁም የተለያዩ ናቸው፡፡
የአለም አሰራር በፍፁም በራስ ወዳድነትና በስጋ ምኞት ላይ የተመሰረተ አሰራር ነው፡፡ የእግዚአብሄር መንግስት አሰራር ደግሞ በፍቅር ላይ የተመሰረተ ነው፡፡
ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም። 1ኛ ዮሐንስ 2፡15-16
ሰው በአለም ሲኖር ራሱ በራሱ ላይ ጌታ ሆኖ ነው የሚኖረው፡፡ ያመረውን ያደርጋል ያላመረውን አያደርግም፡፡ እግዚአብሄርን ያስደስታል ወይ? እግዚአብሄርን ያስቆጣል ወይ? ብሎ አያስብም፡፡ ምክኒያቱም በአለም የሚኖር ሰው እግዚአብሄር ጌታው አይደለም፡፡ በህይወቱ የእግዚአብሄርን ጌትነት ጥሎታል፡፡
የእግዚአብሄር መንግስት አሰራር ደግሞ በፍቅርና በፍቅር ላይ ብቻ የተመሰረተ ነው፡፡ የአለም አስተሳሰብና የእግዚአብሄር መንግስት አስተሳሰብ ፍፁም የተለያዩ ናቸው፡፡
አንተም በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም አሳብህ በፍጹምም ኃይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ የምትል ናት። ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ሁለተኛይቱም፦ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የምትል እርስዋን የምትመስል ይህች ናት። ከእነዚህ የምትበልጥ ሌላ ትእዛዝ የለችም። ማርቆስ 12፡30-31
በእግዚአብሄርት መንግስት ውስጥ የሚኖር ሰው በራሱ ላይ ጌታው እርሱ ራሱ ሳይሆን ጌታ ኢየሱስ ነው፡፡ እርሱ ያመረውን ሳይሆን ጌታ የወደደውን ነው የሚያደርገው፡፡ ጌታ አድርግ የሚለውን ያደርጋል፡፡ ጌታ ተው የሚለውን ይተዋል፡፡
የአለም አሰራርና ክርስትና አብረው የማይሄዱ በጣም የተለያየ አሰራር ስላላቸው ጌታን የሚቀበል ሰው ንስሃ መግባት አለበት፡፡ ጌታን የሚቀበል ሰው የአስተሳሰብ ለውጥ ካላመጣ በአለም በሚኖርበት አስተሳሰብ በእግዚአብሄር መንግስት ልኑር ካለ የማይሆን ነገር እየሞከረ ነው፡፡ ሰው ጌታን ሲቀበል የእግዚአብሄርን ቃል በመቀበል ከአለማዊ አስተሳሰብ ቀኝ ኋላ ዙር ብሎ ወደ ኋላ ካልዞረ እግዚአብሄር ያዘጋጀለት በረከት ውስጥ መግባት ያቅተዋል፡፡
ንስሃ ማለት ባዶ ሃይማኖታዊ ስርአት መፈፀም ሳይሆን አለማዊ አስተሳሰብ መለውጥ መንገድን መለወጥ ነው፡፡ ሰው በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ እንደ አለማዊነት አሰራር በመኖር ሊሳካለት አይችል፡፡
ሰው ወደጌታ ሲመጣ መጀመሪያ መረዳት ያለበት ሁለቱ መንግስታት ፍፁም የተለያዩ እንደሆኑና በአለማዊ አሰራር በእግዚአብሄረ መንግስት መቀጠል እንደማይቻል አስተሳሰቡን መለወጥ እንዳለበት ነው፡፡
እውነተኛ ንስሃ ያልገባና የአለምን አሰራር ጥሎ በእግዚአብሄር መንግስት አሰራር በቃሉ ለመኖር ልቡን ያላዘጋጀ ሰው በክርስትናው ሊዘልቅ አይችልም፡፡
ንስሃ ጌታን ስንቀበል የምናደርገው የአንድ ጊዜ ድርጊት ሳይሆን የህይወት ዘይቤ ነው፡፡ ንስሃ ጌታን ሲቀበል ብቻ የሚገባው ነገር ሳይሆን አለማዊ ሃሳቡን በእግዚአብሄር ቃለ ለመለወጥ ልብን ሁል ጊዜ ማዘጋጀት ነው፡፡ የንስሃ ህይወት አለማዊ አስተሳሰብን ጥሎ የእግዚአብሄርን ቃል ለመቀበል ትሁት መሆን ማለት ነው፡፡
ጌታ ኢየሱስን ተቀብሎ ለዳነ ሰው ወደበረከት መግቢያው ብቸኛው መንገድ የንስሃ ህይወት ነው፡፡ ሰው በማንኛውን ጊዜ እንደቃሉ ያልሆነውን ሃሳቡን ትቶ ለእግዚአብሄር ቃል የሚገዛ ልብ ከሌለው በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ ሊባረክ አይችል፡፡
ሰው በማንኛውም ጊዜ የሚያውቀውን እውቀት ለእግዚአብሄር መንግስት እውቀት ለመተው የንስሃ ህይወት ያስፈልገዋል፡፡ ሰው በአለም ከኖረበት አስተሳሰብ ወደ እግዚአብሄር መንግስት አስተሳሰብ ለመለወጥ ሁሌ በትህትና ሊኖር ይገባዋል፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ንስሃ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #አለም #ሃጢያት #ድምፅ #ቅባት #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #የህይወትፍሬ #መናገር #ቅባት #ትግስት #መሪ

Wednesday, December 7, 2016

የህይወት ዛፍ ፍሬ

እግዚአብሄር ሰውን ሲፈጥረው በራሱ መልካምና ክፉን እንዲያውቅ አድርጎ አልነበረም የፈጠረው፡፡ ሰው ሲፈጠር እግዚአብሄርን እየሰማ እየታዘዘ እንዲኖር ነው፡ ሰው ሲፈጠር በየዋህነት እግዞአብሄርን እየተከተለ እንዲኖር ነው የተፈጠረው፡፡
ሰው የተፈጠረው በህይወት ዛፍ ፍሬ እንዲኖር ነው፡፡ ሰው የተፈጠረው አንድ ምሪት ብቻ በየዋህነት እንዲከተል ነው፡፡
እግዚአብሔር አምላክም ሰውን እንዲህ ብሎ አዘዘው፦ ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና። ዘፍጥረት 2፡16-17
ሰው በሃጢያት ሲወድቅ መልካምና ክፉውን በራሱ እየመረጠ እንዲኖር ተገደደ፡፡ ሰው በራሱ ሆነ፡፡ ሰው በግምት ለመኖር ተገደደ፡፡ ሰው ለእግዚአብሄር አንድ ምሪት በየዋህነት የመመራትን እድሉን ሊያገኘው አልቻለም፡፡
ሰው ክፉና መልካምን በራሱ ለመለየት ስለመረጠ ከእግዚአብሄር ክብር ወደቀ፡፡ ሰው በእግዚአብሄር ብቻ የመመራት እድሉን አጣው፡፡ ሰው በአንዱ የህይወት ዛፍ ፍሬ የመኖር ነፃነቱን ተነፈገ፡፡ የሰው ህይወቱ ተከፋፈለ፡፡ የሰው ህይወቱ ተሰነጠቀ፡፡ ሰው የእግዚአብሄርን አላማ ሳተ፡፡
ሰው መልካም ነው ብሎ የሚያስበው ሁሉ መልካም አይደለም፡፡ ሰው ክፉ ነው ብሎ የሚያስበው ሁሉ ደግሞ ክፉ አይደለም፡፡ ስለዚህ ሰው በራሱ ምርጫ ባሪያ ሆነ፡፡
አሳቤ እንደ አሳባችሁ መንገዳችሁም እንደ መንገዴ አይደለምና፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡ ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፥ እንዲሁ መንገዴ ከመንገዳችሁ አሳቤም ከአሳባችሁ ከፍ ያለ ነው። ኢሳይያስ 55፡8-9
ኢየሱስ የሃጢያታችንን እዳ ከከፈለ በኋላ ግን እግዚአብሄር ወደ ቀድሞ አንዱ ምሪት ሊመልሰን የሚያስፈልገውን የሃጢያት እዳ ሁሉ በልጁ በኢየሱስ በኩል ከፈለ፡፡ አሁንም ኢየሱስን ስንቀበለው በልባችን መኖር ይጀምራል፡፡
የእግዚአብሄር ህይወት በልባችን ሲኖር በአእምሮዋችን "ይህ ክፉ ነው" "ይህ መልካም ነው" በሚል ብቻ በራሳችን ከመኖር እንወጣለን፡፡ በውስጣችን ያለውን የእግዚአብሄርን ህይወትን በየዋህነት ከተከተልን የእግዚአብሄር ወዳዘጋጀልን የክብር ደረጃ እንደርሳለን፡፡
በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ አርነት አውጥቶኛልና። ሮሜ 8፡2
"ይህ ክፉ ነው" "ይህ መልካም ነው" ብለን መምረጥ ሳያስፈልገን በውስጣችን ያለውን መንፈስ በመከተል ብቻ የእግዚአብሄርን ፈቃድ በሙላት በመፈፀም እግዚአብሄርን እናስደስተዋለን፡፡
እናንተም ከቅዱሱ ቅባት ተቀብላችኋል፥ ሁሉንም ታውቃላችሁ። እናንተስ ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በእናንተ ይኖራል፥ ማንም ሊያስተምራችሁ አያስፈልጋችሁም፤ ነገር ግን የእርሱ ቅባት ስለ ሁሉ እንደሚያስተምራችሁ፥ እውነተኛም እንደ ሆነ ውሸትም እንዳልሆነ፥ እናንተንም እንዳስተማራችሁ፥ በእርሱ ኑሩ። 1ኛ ዮሐንስ 2፡20፣27
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #መንፈስቅዱስ #የእውቀትዛፍፍሬ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #ምሪት #ድምፅ #ቅባት #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #የህይወትፍሬ #መናገር #ቅባት #ትግስት #መሪ