Popular Posts

Sunday, December 15, 2019

ዕውር ነውና፥ በቅርብም ያለውን ብቻ ያያል



እነዚህ ነገሮች የሌሉት ዕውር ነውና፥ በቅርብም ያለውን ብቻ ያያል፥ የቀደመውንም ኃጢአቱን መንጻት ረስቶአል። 2ኛ የጴጥሮስ መልእክት 1፡9
የሰው ብስለት እና በእግዚአብሄር መንግስት ጠቃሚነት ደረጃ ከሚለካባቸው መመዘኛዎች አንዱ የእይታ ርቀት ነው፡፡ ሰው እይታው ቅርብ ከሆነ አልተረዳም ህፃን መማር አለበት ማለት ነው፡፡ ሰው እይታው ሩቅ ከሆነ ብስለት አለው በብዙ ይጠቅማል ማለት ይቻላል፡፡
ዛሬ ስለሚበላውና ስለሚጠጣው ብቻ የሚያስብና ለሩቁ ዋጋ የማይሰጥ ሰው ከእግዚአብሄርም ከሰውም ጋር ዘለቄታዊ ወዳጅነት ሊኖረው አይችልም፡፡
እንደ ሰው በኤፌሶን ከአውሬ ጋር ከታገልሁ፥ ሙታንስ የማይነሡ ከሆነ፥ ምን ይጠቅመኛል? ነገ እንሞታለንና እንብላና እንጠጣ። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 15፡32
እግዚአብሄር ለታላላቅ ነገር አጭቶን እያለ እይታው ቅርብ ብቻ የሆነ ሰው ምስኪን ነው፡፡
አንተ ታናሽ መንጋ፥ መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ በጎ ፈቃድ ነውና አትፍሩ። የሉቃስ ወንጌል 12፡32
ለጊዜያዊ ለቅርቡ ብቻ እግዚአብሄርን ተስፋ የሚያደርግ ሰው ምስኪን ሰው ነው፡፡  
በዚች ሕይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ ያደረግን ከሆነ፥ ከሰው ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ነን። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 15፡19
ሰው እይታው ራቅ ሲል የዛሬ ደስታውን ገድቦ ለነገ ፍሬያማነቱ በትጋት ይሰራል፡፡
የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና። ወደ ዕብራውያን 12፡1-2
ሰው መንገዱ እይታው ሩቅ ሲሆን በህይወቱ ኢንቨስት የሚያደርገው ነገር ብዙ ይሆናል፡፡
ሰው እይታው ራቅ ሲል ጊዜያዊ ደስታን ይንቃል ለዘላቂው ደስታ ዋጋ ይከፍላል፡፡
ከግብፅም ብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለ ጠግነት እንዲሆን አስቦአልና ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ፤ ብድራቱን ትኵር ብሎ ተመልክቶአልና። ወደ ዕብራውያን 11፡25-26
ሰው እይታው ቅርብ ሲሆንና ለሩቁ የእግዚአብሄር ሃሳብ ሲታወር በጊዜያዊው ነገር ዘለቄታዊውን ክብር ያጣዋል፡፡  
እናንተ እርስ በርሳችሁ ክብር የምትቀባበሉ ከአንዱም ከእግዚአብሔር ያለውን ክብር የማትፈልጉ፥ እንዴት ልታምኑ ትችላላችሁ? የዮሐንስ ወንጌል 5፡44
እይታው ቅርብ የሆነ ሰው ህይወቱን የሚያባክነው በሚጠፋው መብል ላይ ነው፡፡  
ለሚጠፋ መብል አትሥሩ፤ ነገር ግን ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር መብል የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ሥሩ፤ እርሱን እግዚአብሔር አብ አትሞታልና። የዮሐንስ ወንጌል 527
እይታው ሩቅ የሆነ ሰው የሚተጋው ስለእምነት ስራ በአይን ስለማይታየው ነገር ነው፡፡
እንግዲህ፦ የእግዚአብሔርን ሥራ እንድንሠራ ምን እናድርግ? አሉት። ኢየሱስ መልሶ፦ ይህ የእግዚአብሔር ሥራ እርሱ በላከው እንድታምኑ ነው አላቸው። የዮሐንስ ወንጌል 5፡28፣29
እይታው ሩቅ የሆነ ሰው
መጨረሻቸው ጥፋት ነው፥ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፥ ክብራቸው በነውራቸው ነው፥ አሳባቸው ምድራዊ ነው። እኛ አገራችን በሰማይ ነውና፥ ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን፤ ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 3፡19፣20
እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ፥ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ እሹ፤ በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም። ወደ ቆላስይስ ሰዎች 3፡1-2
እይታው ቅርብ ያልሆነ ሰው በምድር ላይ በትጋት የሚሰራው እና የምድሩን መከራ የሚታገሰው ለዘላማዊው ሽልማት ነው፡፡
እነሆ፥ ቶሎ ብዬ እመጣለሁ፤ ማንም አክሊልህን እንዳይወስድብህ ያለህን አጽንተህ ያዝ። የዮሐንስ ራእይ 3፡11
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #እይታ #ተስፋ #መፀለይ #መንፈስ #በረከት #መዝገብ #ሰማይ #እንግዶች #ዘላለም #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #እምነት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እይታ #ምድራዊ #ሰማያዊት #ማየት #ቅርብ

Friday, December 13, 2019

በስራ ቦታ ቀኑን ሙሉ ቁጭ ማለት የሚያስከትለውን መተሳሰር ለማፍታታት የሚሰራ እንቅስቃሴ::

አስተማማኝ ድጋፍ



ህይወትህ ብትንትን ያለና ምንም ቅርፅ የሌለው መስሎሃል?
የምትፈልግው ተስፋ ርቆ እንደተሰቀለ ያህል ተሰምቶሃል?
አለኝ ብለህ የተማመንከብተ ነገር እየፈረሰ እንዳለ ተሰምቶሃል?
ያለፈው ህይወትህ መላው ህይወትህን ሁሉ እንዳበላሸው እና ሊስተካከል እንደማይችል ተሰምቶሃል?
በህይወት ያለህ ጊዜ እና ማድርግ የምትፈልገው ነገር እንዳልተመጣነ ተሰምቶሃል?  
የህይወት መንገድህ ተግዳሮት እንደተራራ ገዝፎብሃል?
ሰው ሊታመን እና ለጨበጥ እንደማይችል ተሰምቶሃል?  
ጊዜ እያለፈብህ እንደሆነ ከህይወት ወደኋላ እንደቀረህ ተሰምቶሃል?
ካለህበት አስቸጋሪ ነገር ውስጥ የመውጫው መንገድ እንደሌለው ተሰምቶሃል?
በልብህ ወደምታየው ደረጃ እየሄድክ እንዳለሆንክ ተሰምቶሃል?  
እዛው አንድ ቦታ እየረገጥክ እንደሆነና ህይወትህ ለውጥ የሌለው ድግግሞሽ እንደሆነ ተሰምቶህ ይሆን?
እንግዲያውስ በእግዚአብሄር ለመደገፍ ትክክለኛው ቦታ ላይ ነህ፡፡
እንግዲያውስ በእግዚአብሄር መደገፍ ብቻ የሚጠቅምበት ትክክለኛ ቦታ ላይ ነህ፡፡
እንግዲያውስ ሲጀመር በእግዚአብሄር መደገፍ ያስፈለገበት ትክክለኛ ቦታ ላይ መጥተሃል፡፡  
እንግዲያውስ በእግዚአብሄር መደገፈ የሚባለው ነገር የተሰራበት እና የታለመበት ትክክለኛው ቦታ ላይ ደርሰሃል፡፡
እውቀታችን ሙሉ አይደለም፡፡ ሁሉንም ከመጀመሪያው እስከመጨረሻው እንደ ነጭና ጥቁር በፍፁም የምንረዳና እውቀታችን ሙሉ ቢሆን ኖሮ በእግዚአብሄር ላይ መደገፍ አይጠበቀብንም ነበር፡፡ ሁሉን በሚያውቀውና እኛን ከምናስበው በላይ በሚወደን በእግዚአብሄር ላይ መደገፍ ያስፈለገው እውቀታችን ውስን ስለሆነ ነው፡፡
በራሳችን ሁሉንም ነገር ማድረግ የምንችል ብንሆን በእግዚአብሄር ላይ መደገፍን አያስፈልግም ነበር፡፡ በሃይልም በችሎታም ከእኛ እጅግ ከፍ ባለው በእግዚአብሄር ላይ የምንደገፈው ጉልበታችን ውስን ስለሆነና በራሳችን ማድረግ የማንችለው ነገር ስላለ ነው ፡፡
ደግሞም በእግዚአብሄር ላይ ያለን መደገፍ ለዚህ ወሳኝ ጊዜ ካልጠቀመን መቼ ሊጠቅመን ነው?
እምነት የሚጠቅመው ሁሉ ነገር ቦታ ቦታውን ሲይዝ እና ሲሰምር አይደለም፡፡ እምነት የሚጠቅመው የምንፈልገውን ነገር ሁሉ በእጃችን ስናስገባ አይደለም፡፡ እምነት የሚጠቅውመው ሁሉም ነገር በታሰበው ጊዜና ሁኔ ሲሄድ አይደከለም፡፡ እምነት የሚያስፈልገው በስኬት ተራራ ላይ የወጣን ሲመስለን አይደለም፡፡ እምነት የሚያስፈልገው ሁሉንም የህይወትህ አቅጣጫ ቅርፅ ሲይዝ አይደለም፡፡ እምነት እና በእግዚአብሄር ላይ ተስፋ ማድረግ የሚያስፈልገው የምትፈልገው ነገር በእጅህ ለመግባት ሲፈጥን አይደለም፡፡
ነገር ግን ተስፋ የሚደረግበቱ ነገር ቢታይ ተስፋ አይደለም፤ የሚያየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል? ወደ ሮሜ ሰዎች 8፡24
እምነትና በእግዚአብሄር ላይ መደገፍ የሚጠቅመው ማድረግ የሚገባህን ነገር ለማድርግ አቅም ሲያንስህ ነው፡፡ በእግዚአብሄር ላይ መደገፍ የሚጠይቀው እንዴት ሊሆን እንደሚችል መውጫና መግቢያው ሲጠፋህ ነው፡፡ በእግዚአብሄር ላይ መደገፍ የሚጠይቀው የህይወት ክር ውስብስብ ብሎ ውሉ ሲጠፋብህ ነው፡፡ በእግዚአብሄር ላይ መደገፍ የሚጠይቀው ህይወት እንደቆመ ሲመስልህ ነው፡፡ በእግዚአብሄር ላይ መደገፍ የሚጠይቀው በህይወት ማድረግ የምትፈልጋቸው ነገሮችና ያለህ ጊዜ ሳይመጣጠን ሲቀር ነው፡፡ በእግዚአብሀር ላይ መደገፍ የሚጠይቀው ማድርግ አለብኝ ብለህ የምታስበውና ማድርግ የምትችልበት አቅምህ ልዩነት ሲያመጣ ነው፡፡ በእግዚአብሄር ላይ መታመን የሚጠይቀው ጊዜ እያለፈብህ እንደሆነ እና ወደኋላ እንደቀረህ ሲሰማህ ነው፡፡ በእግዚአብሄር ላይ መታመን የሚያስፈልገው በህይወትህ የሚሆኑት ነገሮች ለምን እንደሆኑ ምክኒያትን ስታጣላቸው ነው፡፡ በእግዚአብሄር ላይ መታመን የሚጠይቀው ለዚህ አልፌ አልሰጠም ላልከው ነገር አልፈህ ስትሰጥ ነው፡፡ በእግዚአብሄር ላይ መታመን የሚጠይቀው በህይወትህ የሆነው ነገር ምክኒያቱ ነገር ሁሉ ለበጎ ስለሚደረግ ብቻ እንደሆነ ከማመን በቀር ሌላ ምክኒያትን ስታጣ ነው፡፡
አላወቅህምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፥ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው፤ አይደክምም፥ አይታክትም፥ ማስተዋሉም አይመረመርም። አላወቅህምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፥ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው፤ አይደክምም፥ አይታክትም፥ ማስተዋሉም አይመረመርም። ኢሳይያስ 40፡28፣31
በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ ምሳሌ 35
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#እምነት #ማየት #አለማየት #ቃል #መታመን #መገደፍ #መተማመን #የእግዚአብሄርሃይል #መንፈስቅዱስ #ቃሉንመስማት #እወጃ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መደገፍ #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #መታመን #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ 

Thursday, December 12, 2019

ለምን ግን ?



በእግዚአብሄር ፈቃድ ውስጥ ለመገኘትና በምድር ላይ የእግዚአብሄርን አላማ ለማስፈፀም ምን እያደረኩኝ ነው የሚለው ጥያቄ ብቻ ሳይሆን የማደርገውን ነገር የማደርገው ለምንድነው የሚለውን ጥያቄ መመለስ ወሳኝ ነው፡፡ የምናደርግው ነገር እስካልተቋረጠ ድረስ የምናደርግበትን ምክኒያት በትጋት መመርምር መቋረጥ የለበትም፡፡
ምን እያደረኩኝ ነው ከሚለው ጥያቄ ከመመለስ ያላነሰ የማደርገውን የማደርገው ለምንድነው የሚለውን ጥያቄ መለመለስ አስፈላጊ ነው፡፡  
እግዚአብሄር ምን እንድምታደርግ ብቻ ሳይሆን ለምን እንደምታደረገው ማወቅ ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሄር ምን እንደምታደርግ ብቻ ሳይሆን ለምን እንድምታደርገው ግድ ይለዋል፡፡ 
የምታደርገው ትክክል ቢሆንም የምታደርግበት የልብህ መነሻ ሃሳብ ስህተት ሊሆን ይችላል፡፡ የምታደርገው ነገር መልካም ቢሆንም የልብህ ሃሳብ ክፉ ሊያደርገው ይችላል፡፡ የምታደርገው የተቀደሰ ቢሆንም የምታደርገበት ምክኒታት ሊያረክሰው ይችላል፡፡
መፀለይን የመሰለ የተቀደሰ ነገረ የለም፡፡ የምንፀልይበት የልባችን መነሻ ሃሳብ መፀለይን ሊያረክሰው ይችላል፡፡
ስትጸልዩም እንደ ግብዞች አትሁኑ፤ ለሰው ይታዩ ዘንድ በምኩራብና በመንገድ ማዕዘን ቆመው መጸለይን ይወዳሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። የማቴዎስ ወንጌል 6፡5
ምጽዋት ማድረግ የተባረከ ነገር ነው ነገር ግን ምጽዋት የምናደርግበት የልባችን መነሻ ሃሳብ የተረገመ ሊያደርገው ይችላል፡፡ 
እንግዲህ ምጽዋት ስታደርግ፥ ግብዞች በሰው ዘንድ ሊከበሩ በምኩራብ በመንገድም እንደሚያደርጉ በፊትህ መለከት አታስነፋ፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። የማቴዎስ ወንጌል 6፡2
የፀሎት እርዝማኔ ለሰው ካለን ርህራሄና ፍቅር ሳይሆን ከልባችን ስስትና ለጥቅም ያለ ስግብግብነት ሊመነጭ ይችላል፡፡
የመበለቶችን ቤት የሚበሉ ጸሎታቸውንም በማስረዘም የሚያመካኙ፥ እነዚህ የባሰ ፍርድ ይቀበላሉ አለ። የሉቃስ ወንጌል 20፡47
የምናደርገው ምንም መልካም ነገር በፍቅር ካልተደረገ ምንም አይጠቅመንም፡፡
በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ ጸናጽል ሆኜአለሁ። ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ፥ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፥ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም። 1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 13፡1-3
ይህንን የማደርገው ለምንድነው ብለን በቅንነት ራሳችንን እንጠይቅ፡፡ ለራሳችን ግልፅ እንሁን፡፡ እውነተኛ መነሻ የልብ ሃሳባችንን እንጋፈጠው፡፡ ቢያንስ ለራሳችን ሃቀኛ እንሁን፡፡ ለራሳችን እውነተኞች እንሁን፡፡
በመጨረሻ ለዘመናት የገነባነው ህይወታችንና አገልግሎታችን በልብ የመነሻ ሃሳብ መበላሸት ከንቱ እንዳይሆን ልባችንን እንመርምር፡፡
ስለዚህም በጨለማ የተሰወረውን ደግሞ ወደ ብርሃን የሚያወጣ የልብንም ምክር የሚገልጥ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ጊዜው ሳይደርስ አንዳች አትፍረዱ፤ በዚያን ጊዜም ለእያንዳንዱ ምስጋናው ከእግዚአብሔር ዘንድ ይሆናል። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 4፡5
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#እምነት #ሃሳብ #መነሻሃሳብ #ልብ #ንፁህ #ፍቅር #ፉክክር #ቃል #ክብር #የእግዚአብሔርቃል #ቃሉንመስማት #እወጃ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Wednesday, December 11, 2019

የሰላም ምንጭ



በእኔ ሳላችሁ ሰላም እንዲሆንላችሁ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ። የዮሐንስ ወንጌል 16:33
የመጀመሪያው የሰላም ምንጭ መከራ እንደለ መረዳት ነው፡፡ መጀመሪያ ሰላሙን የሚያጣው መከራ እንዳለ የማይረዳ ሰው ነው፡፡ መጀመሪያ ሰላሙን የሚያጣው የተሳሳተ ከመከራ የፀዳ የአለም ምስል በአእምሮው ያለው ሰው ነው፡፡ መጀመሪያ ሰላሙን የሚያጣው መከራን የማይጠብቅ ሰው ነው፡፡
በአለም መከራ መጀመሪያ የሚሰናከለው በአለም ሳለን ከመከራ ነፃ እንደምንሆን የሚያስብ ሰው ነው፡፡ በአለም ሳለን መከራ እንዳለብን የሚረዳ ሰው አሸናፊ ነው፡፡  
የአለምን መከራ ለማሸነፍ የመጀመሪያው ደረጃ መከራ የአለም ኑሮ አንዱ ክፍል እንደሆነ መረዳት ነው፡፡ የአለምን መከራ የማሸነፍ ቅድም ሁኔታው በአለም ሳለን መከራ እንደሚገጥመን መጠበቅ ነው፡፡
መከራ ሊገጥመኝ አይችልም ብሎ የሚያስብ ሰው ሞኝ ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ሃሳብ ሳደርግ ተግዳሮት አይገጥመኝም የሚል ሰው ስለህይወት ያለተረዳ ሰው ነው፡፡
በሳል ሰው በሁኔታዎች ውስጥ የእግዚአብሄርን አሰራር የሚረዳ ሰው ነው፡፡ በሳል ሰው የእግዚአብሄርን አላማ ስናስፈፅም በመንገዳችን የሚቆመውን የሰይጣንን አካሄድ የሚረዳ ሰው ነው፡፡  
በሰይጣን እንዳንታለል፤ የእርሱን አሳብ አንስተውምና። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 2፡11
ጥያቄው እንዴት መከራን እንለፈው እንጂ መከራ አለ የለም አይደለም፡፡ ወደ ፈተና ላለመግባት ለመከራ የምንዘጋጀው በሰላሙ ቀን በፀሎት ነው፡፡
ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተነሥታችሁ ጸልዩ አላቸው። የሉቃስ ወንጌል 22፡46
ጥያቄው መከራን ለማለፍ ህይወታችን የእግዚአብሄርን ቃል በመታዘዝ መሰረት ላይ እንገንባ እንጂ መከራ አለ የለም አይደለም፡፡
ስለዚህ ይህን ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው ሁሉ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራ ልባም ሰውን ይመስላል። ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንም ቤት ገፋው፥ በዓለት ላይም ስለ ተመሠረተ አልወደቀም። የማቴዎስ ወንጌል 7፡24-25
ጥያቄው መከራን የምናልፈው የእግዚአብሄርን ጥበብ በመቀበል ነው የሚል እንጂ መከራ አለ የለም አልነበረውም፡፡
ወንድሞቼ ሆይ፥ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፥ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቍጠሩት . . . ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጎድለው፥ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፥ ለእርሱም ይሰጠዋል። የያዕቆብ መልእክት 1፡2-5
ጥያቄው መከራ አለ የለም ሳይሆን መከራ በህይወታችን የሚሰራውን የፍፁምነት ድንቅ ስራ ነው፡፡
ወንድሞቼ ሆይ፥ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፥ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቍጠሩት ትዕግሥትም ምንም የሚጎድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን ትሆኑ ዘንድ ሥራውን ይፈጽም። የያዕቆብ መልእክት 1፡2-4
የሰላም ምንጭ በአለም ሳለን መከራ እንዳለብን መረዳትና መከራን እንዴት ማስተናገድ እንደለብን እንደምናሸንፈው ከእግዚአብሄር ቃል መማር ነው፡፡
በእኔ ሳላችሁ ሰላም እንዲሆንላችሁ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ። የዮሐንስ ወንጌል 16:33
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ክብር #መዋረድ #መከራ #ፈተና #መፅናት #መታገስ #ሰላም #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና #እምነት #አንድነት #ፀጋ  #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Tuesday, December 10, 2019

እግዚአብሄር የሚረዳበት ብቸኛው መንገድ



እግዚአብሄር መንገዱ ብዙ ነው፡፡ እግዚአብሄር አሰራሩ ልዩ ልዩ ነው፡፡ እግዚአብሄር ባላሰብነው መንገድ ሲረዳን አይተናል፡፡ እግዚአብሄር ብዙዎችን በተለያ መንገድ ይረዳል፡፡
እግዚአብሄር ቢፈልግም እንኳን በብዙ መንገድ ሊረዳው የማይችለው ሰው አለ፡፡ እግዚአብሄር ቢፈልግ እንኳን በአንድ መንገድ ብቻ ሊረዳው የሚገደድበት ሰው አለ፡፡
የሚማር ልብ የሌለው ሰው የመዳን ተስፋ የሌለው ሰው ነው፡፡
በቃሉ የሚቸኵለውን ሰው ብታይ፥ ከእርሱ ይልቅ ለሰነፍ ተስፋ አለው። መጽሐፈ ምሳሌ 29፡20
ሁሉን አውቃለሁ የሚል ሰው ለመለወጥ ተስፋው የመነመነ ሰው ነው፡፡  
ለራሱ ጠቢብ የሆነ የሚምስለውን ሰው አየኸውን? ከእርሱ ይልቅ ለሰነፍ ተስፋ አለው። መጽሐፈ ምሳሌ 26፡12
እግዚአብሄር በአንድ መንገድ ብቻ ሊረዳው የሚችል ሰው ደግሞ አለ፡፡
እግዚአብሄር ሰውን የሚረዳበት በጣም ብዙ መንገድ ቢኖውርም ትእቢተኛን ግን ሊረዳው የሚችለው በአንድ መንገድ ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄር ሰውን የሚገናኝበት ብዙ መንገድ ቢኖረውም ከትእቢተኛ ጋር በአንድ መንገድ ብቻ እንዲገናኝ ይገደዳል፡፡
እግዚአብሄር ትእቢተኛውን የሚገናኘው በተቃራኒው ጎን ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄር ትእቢተኛውን የሚገናኘው ትእቢተኛውን ፊትለፊት በመግጠም ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄር ትእቢተኛውን የሚገናኘ ትእቢተኛውን በማሳየት ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄር ትእቢተኛውን የሚገናኘው በመጋፈጥ ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄር ትእቢተኛውን  የሚገናኘው በተቃውሞ ብቻ ነው፡፡
ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሄር መልክና አምሳል ነፃ ፈቃድ ያለው ተደርጎ ነው፡፡ ሰው ትእቢትን ከመረጠ ማንም ከምርጫው ሊመልሰው አይችልም፡፡ የፈጠረን እግዚአብሄር እንኳን በእኛ ፋንታ አይመርጥልንም፡፡ እግዚአብሄር እንኳን ሊያደርግ የሚችለው የትህትናና የትእቢትን ምርጫዎች መስጠትና ትህትናን እንዲመርጥ  መምከር ብቻ ነው፡፡
በፊታችሁ ሕይወትንና ሞትን በረከትንና መርገምን እንዳስቀመጥሁ እኔ ዛሬ ሰማይንና ምድርን በአንተ ላይ አስመሰክራለሁ፤ እንግዲህ አንተና ዘርህ በሕይወት ትኖሩ ዘንድ ሕይወትን ምረጥ፤ ኦሪት ዘዳግም 30፡19
እግዚአብሄር ለትሁታን ፀጋ ቢሰጥም ለትእቢተኛው ግን ከተቃውሞ ውጭ ምንም ሊሰጠው አይችልም፡፡  
ነገር ግን ጸጋን አብልጦ ይሰጣል፤ ስለዚህ፦ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል ይላል። የያዕቆብ መልእክት 4፡6
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ትህትና #መዋረድ #ባህሪ #ዝቅታ #ትዕቢት #ትምክህት #መመካት #ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መጋቢ #እምነት #ጥፋት #ውድቀት #ኩሩ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ