Popular Posts

Tuesday, December 6, 2016

መዝገብህ ባለበት ልብህ

ልብህ የሚሄደው መዝገብህ ባለበት ቦታ ነው፡፡ ሰው በተፈጥሮው ሃብቱና ልቡ ተነጣጠለው አይኖሩም፡፡ መዝገብህ ባለበት ልብህ በዚያ ይሆናል፡፡
መዝገብህ በሌለበት ቦታ ልብህ በዚያ አይኖርም፡፡ ትኩረትህ ሁሉ የሚኖረው የኔ የምትለው የምትጠነቀቅለት ነገር ባለበት ቦታ ነው፡፡ ስለዚህ አለ ኢየሱስ ልባችሁ በሰማይ እንዲያተኩር ወሳኙ መንገድ ፣ ልባችሁ በሰማይ እንዲቀር የሚረዳው ነገር ፣ ልባችሁ በሰማይ ትኩረት እንዲያዝ ከፈለጋችሁ መዝገባችሁን በሰማይ አስቀምጡ እያለን ነው፡፡
በምድር ላይ የምንደገፍበት ነገር ሲጠፋ ልባችን ወደ ሰማይ መዝገብ ያዘነብላል፡፡ ነገር ግን የምድር ሃብታችን ሲበዛና በዚያም ለመታመን ስንፈተን ልባችንም በምድር ላይ ይቀራል፡፡ ልባችንን የምንጥልበት ሃብታችን በምድር ላይ እየበዛ በሄደ መጠን ልባችን ከሰማይ ላይ እየተነሳ ይሄዳል፡፡ መዝገባችን በምድር ሲሆን ልባችንም በምድር ይሆናል፡፡ መዝገባችን በሰማይ ሲሆን በቅፅበት ልባችንም በሰማይ ይሆናል፡፡
ብዙ ጊዜ ልባችን ከሰማይ በመነሳት እንፈተናልን፡፡ በዚህ ፈተና ያለመውደቅ መንገዱን ኢየሱስ ያስተምራል፡፡ መዝገብን በምድር የመሰብሰብ ጉዳቱ ልባችንን ከሰማይ ላይ እንዲነሳ ሰማይ ትኩረታችን እንዳይሆን ያደርጋል፡፡ መዝገብን በሰማይ የመሰብሰብ ጥቅሙ ልባችንን በሰማይ ይሰበስብልናል፡፡
ብልና ዝገት በሚያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በሚሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብ አትሰብስቡ፤ ነገር ግን ብልም ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በማይሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ፤ መዝገብህ ባለበት ልብህ ደግሞ በዚያ ይሆናልና። ማቴዎስ 6፡19-21
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #መዝገብ #ሃብት #ሰማይ #መሰረታዊፍላጎት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ጥሪ #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

Monday, December 5, 2016

የአእምሮ ብስለት ይጠይቃል

አንዳንድ ጊዜ ከምናስበው በላይ በአእምሮ ያለመብሰል በህይወታችን ሲንፀባረቅ ይታያል፡፡ ችግሩ ደግሞ አብዛኛው ሰው በሳል የሆነ ይመስለዋል፡፡ በሳል የሆነ የመሰለው ሰው ከእግዚአበሄር ቃል የብስለቱን መጠን መለካትና በእግዚአብሄር ቃል ወደከፍ ያለ የብስለት ደረጃ ለማደግ መትጋት ይገባዋል፡፡
ወንድሞች ሆይ፥ በአእምሮ ሕፃናት አትሁኑ፤ ለክፋት ነገር ሕፃናት ሁኑ እንጂ በአእምሮ የበሰሉ ሁኑ። 1ኛ ቆሮንቶስ 14:20 ብስለታችንን የምንለካባቸው መንገዶችና በሳል ሰው ያለው አመለካከት ተዘርዝረዋል፡፡

  • · በሳል ሰው ለልዩነት አክብሮት ያለው ነው
ያልበሰለ ሰው ከእርሱ የተለየ ማንኛውም ነገር ስህተት ይመስለዋል፡፡ ሰውን ሁሉ ተመሳሳይና አንድ አይነት ለማድረግ ይሞክራል፡፡ ሰው ግን ክቡር ነው እያንዳንዱ ሰው እንደ የሁኔታው ሊያዝ ይገባዋል፡፡ ስለዚህ ያልበሰለ ሰው ከእርሱ ለተለየው ሰው ምንም ቦታ የለውም፡፡

  • · በሳል ሰው ለትንንሽ ሰዎች ባለው አክብሮት ይታወቃል

በሳል ሰው ራሱን በሚገባ ስሚያውቅ ሌሎችን ለመድረስ ሰዎችን አይመርጥም፡፡ በሳል ሰው ሰውን በሰውነቱ እንጂ በሌላ በምንም ነገር አይመዝንም፡፡ በሳል ሰው ሰውን የሚያውቀው በክርስቶስ እንጂ በሌላ አይደለም፡፡
እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማሙ፤ የትዕቢትን ነገር አታስቡ፥ ነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ። ልባሞች የሆናችሁ አይምሰላችሁ። ሮሜ ሰዎች 12፡16

  • · በሳል ሰው የራሱን ሃሳብ ብቻ አይፈልግም

በሳል ሰው የሌሎችም ሃሳብ ቢደረግ እንደሚሳካ ያምናል፡፡ በሳል ሰው በሌሎችም እግዚአብሄር እንደሚጠቀም ያምናል፡፡ በሳል ሰው ለአንድነት ራሱን ትሁት ያደርጋል፡፡
በክርስቶስም አንዳች ምክር ቢሆን፥ የፍቅር መጽናናት ቢሆን፥ የመንፈስ ኅብረት ቢሆን፥ ምሕረትና ርኅራኄ ቢሆኑ፥ ደስታዬን ፈጽሙልኝ፤ በአንድ አሳብ ተስማሙ፥ አንድ ፍቅር አንድም ልብ አንድም አሳብ ይሁንላችሁ፤ ፊልጵስዩስ 2፡1-2

  • · በሳል ሰው በደረሰበት ቦታ ሁሉ ላለው ስልጣን እውቅና ይሰጣል፡፡

በሳል ሰው የስልጣንን ጥቅምና አላማ ስለሚረዳ ለስልጣን አክብሮት አለው፡፡ በሳል ሰው ስልጣንንየሚያከብረው ለታይታ ሳይሆን ሁልጊዜ ነው፡፡
እኔ ደግሞ ለሌሎች ተገዥ ነኝና፥ ከእኔም በታች ጭፍራ አለኝ፤ አንዱንም፦ ሂድ ብለው ይሄዳል፥ ሌላውንም፦ ና ብለው ይመጣል፥ ባሪያዬንም፦ ይህን አድርግ ብለው ያደርጋል አለው። ማቴዎስ 8፡9

  • · በሳል ሰው ለቁሳቁስ ዝቅተኛ አመለካከት ያለው ሰው ነው፡፡

ቁሳቁስን የሚያከብር ሰው በሳል ሰው አይደለም፡፡ በሳል ሰው ቁሳቁስ ካላቸውን ደረጃ በላይ አጋኖ አያያቸውም፡፡ በሳል ሰው ከቁስና ከውጭ እይታ በላይ ለልብ እውቅና ይሰጣል፡፡
ወደ ዓለም ምንም እንኳ አላመጣንምና፥ አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፥ እርሱ ይበቃናል። 1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 6፡7-8
እርስዎም ስድስተኛውን ይጨምሩበት ?
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ልብ #ቁሳቁስ #አላማ #መሰረታዊፍላጎት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ጥሪ #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አንድነት #ትህትና #አክብሮት #ስልጣን #መሪ

Sunday, December 4, 2016

የህይወት ጥያቄ መልስ

ጥበብ ዓይነተኛ ነገር ናትና ጥበብን አግኝ፤ ከሀብትህም ሁሉ ማስተዋልን አትርፍ። ምሳሌ 4፡7
በህይወታችን ያሉትን ጥያቄዎች ሁሉ ገንዘብ ሊመልሳቸው የሚችል ይመስለናል፡፡ ስለዚህ ትኩረታችን ከአስፈላጊው ነገር ላይ ተነስቶ ወደ አላስፈላጊው ነገር ላይ ይሆናል፡፡ አብዛኛው የህይወታችን ጥያቄ የሚመለሰው ተጨማሪ ገንዘብ ስናገኝ ሳይሆን ባለን ነገር እንዴት መኖር እንደምንችል ጥበብ ስናገኝ ነው፡፡ ከእኛ ያነሰ ገንዘብ ኖሮዋቸው ከእኛ የተሻለ የሚኖሩ ሰዎች አሉ፡፡ ለህይወት ስኬት ሁሌ ተጨማሪ ገንዘብ በፈለግን ቁጥር ህይወትን እንደሚገባው ማጣጣም አንችልም፡፡
በአብዛኛው ለህይወት ስኬት የሚጠቅመን ነገር ብዙ ገንዘብ ማከማቸት ሳይሆን ባለን ነገር ለመኖር ማስተዋልን ማግኘት ነው፡፡ አንዳንዳንዱ የህይወት ጥያቄው በገንዘብ እንጂ በሌላ በምንም ነገር እንደማይፈታ አእምሮውን የዘጋው ሰው ይህንን ንግግር አይታገሰውም፡፡
ጥበብ አይነተኛ ነገር ነች፡፡ ጥበብን የሚገባዋን ክብር ካልሰጠናትና ካልተከተልናት ጥበበኞች አንሆንም፡፡ ክጥበብና ከህይወት እንጎድላለን፡፡ የጠቢቡ ምክር ከሃብትህም በላይ ማስተዋልን አትርፍ ነው፡፡ ለሃብት ከጥበብ ያነሰ ክብር ስጠው፡፡ ሃብትን አጋንነህ የጥበብ ያህል እትፈልገው፡፡ ሃብትህን ብታጣ ይሻላል ጥበብን ከምታጣ፡፡ ሃብት ውስጥ ሁሉ ነገር የለም፡፡ ጥበብ ውስጥ ግን ሁሉ ነገር አለ፡፡
ብልጥግናና ክብር በእኔ ዘንድ ነው፥ ብዙ ሀብትና ጽድቅም። ፍሬዬም ከምዝምዝ ወርቅ ይሻላል፥ ቡቃያዬም ከተመረጠች ብር። ምሳሌ 8፡18-19
በህይወታችን ያለው ጥያቄ የገንዘብ ፣ የሃይልና የዝና ማነስ ሊመስለን ይችላል፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ ግን ገንዘቡም ሃይሉም ዝናውም የማያደርገውን ጥበብ ለነገስታት እንዲሚያደርገው ይናገራል፡፡ ጥበብ አይነተኛ ነገር ነው፡፡
ምክርና መልካም ጥበብ የእኔ ነው፤ ማስተዋል እኔ ነኝ፥ ብርታትም አለኝ። ነገሥታት በእኔ ይነግሣሉ፥ ሹማምቶችም የቀናውን ነገር ይደነግጋሉ። ምሳሌ 8፡14-15
መፅሃፍም ማንም በህይወት ሲፈተን ከፈተናው መውጫ ጥበብን ይለምን ነው እንጂ ገንዘብን አይደለም ይለምን አይደለም ያለው፡፡
ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጎድለው፥ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፥ ለእርሱም ይሰጠዋል። ያዕቆብ 1፡5
ጥበብ አይነተኛ ነገር እንደሆነች ስንረዳ አብዛኛው የፀሎት ርእሳችን ይቀየራል፡፡ ጥበብ አይነተኛ ነገር እንደሆነች ከልባችን ስንረዳ ትኩረታችን በትክክለኛው ቦታ ላይ ይሆናል፡፡ ጥበብ አይነተኛ ነገር እንደሆነች ስንረዳ ባለንበት ደረጃ ህይወትን በሚገባ መኖር እንጀምራለን፡፡ ጥበብ አይነተኛ ነገር እንደሆነች ስንረዳ ለህይወት ጥያቄያችን መልስ የምንፈልገው ጥበብን ሊሰጠን የሚችለው መፅሃፍ ቅዱስ ጋር ይሆናል፡፡ ጥበብ አይነተኛ ነገር እንደሆነች ስንረዳ ለህይወት ጥያቄያችን ዘወር የምንለው በውስጣችን ወዳለው የጥበብ መንፈስ መንፈስ ቅዱስ ይሆናል፡፡
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes


#ኢየሱስ #ጌታ #ጥበብ #ማስተዋል #መረዳት #ቤተክርስትያን #መንፈስቅዱስ #ብርታት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Saturday, December 3, 2016

የሌለኝ የማያስፈልገኝ ነው

እግዚአብሄር ለአላማ ፈጥሮናል፡፡ የመፈጠራችን አላማ ደግሞ ከመኖር ያለፈ አላማ ነው፡፡ እግዚአብሄር የሰራን ለራሱ ነው፡፡ እግዚአብሄር የፈጠረን ለክብሩ ነው፡፡ እግዚአብሄር በምድር ላይ የሚያኖረን የእርሱን ክብሩንና በጎነቱን እንድናሳይለት ነው፡፡
ወደ ምድር የመጣነው ድንገት አይደለም፡፡ ወደ ምድር የመጣነው እግዚአብሄር ስለፈለገን ነው፡፡ እግዚአብሄር ክብሩን ሊገልጥብን እንድናገለግለው ለፈቃዱ እንድንኖር ወደ ምድር አምጥቶናል፡፡
እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን። ኤፌሶን 2፡10
ለመኖር የሚያስፈልገንን የማሟላት ሃላፊነት ያለበት እግዚአብሄር ሲሆን ለእግዚአብሄር ክብር የመኖር ሃላፊነት ያለብን ደግሞ እኛ ነን፡፡ የእኛ ሃላፊነት የእግዚአብሄን መንግስት ጥቅምና በጎነት መፈለግ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ሃላፊነት የሚያስገልገንን ሁሉ ማሟላት ነው፡፡
እንግዲህ፦ ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ማቴዎስ 6፡31-33
ስለዚህ ነው ሐዋሪያው ጳውሎስ ለህይወት የሚያስፈልገንን ሁሉ እግዚአብሄር በክብር እንደሚሞላብን የሚያስተምረው፡፡ አምላኬም እንደ ባለ ጠግነቱ መጠን በክብር በክርስቶስ ኢየሱስ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ ይሞላባችኋል። ፊልጵስዩስ 4፡19
ስለዚህ ነው መዝሙረኛው እረኛው እግዚአብሄር ስለሆነ ከሚያስገልገው ነገር አንዱንም እንደማያሳጣው የዘመረው፡፡ እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፥ የሚያሳጣኝም የለም። መዝሙር 23፡1
አንድ የማከንብራቸው የእግዚአብሄር ሰው "የሌለኝ ነገር ሁሉ የሌለኝ ስለማያስፈልገኝ ነው" አሉ፡፡
እውነት ነው እግዚአብሄር እረኛችን ሆኖ የሌለን ነገር ካለ ቢያንስ ቢያንስ ለአሁን አያስፈልገንም ማለት ነው፡፡ ወደፊት የሚያስፈልገን ከሆነ እግዚአብሄር በጊዜው ውብ አድርጎ ሰርቶታል፡፡ ለአሁን ግን የሌለኝ ሁሉ የማያስፈልገኝ ነው፡፡ እግዚአብሄር ለእኛ መልካም የሚያደርግ ሆኖ መልካም ለማደርግ ሙሉ ችሎታ ኖሮት ሳለ የሌለን ነገር የማያስፈልገን ነው፡፡
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ራእይ #እረኛ #አላማ #መሰረታዊፍላጎት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ጥሪ #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

Friday, December 2, 2016

የአስቸኳይ ጊዜ ፀሎት

ፀሎት ሁል ጊዜ የምናደርገው ደስ የምንሰኝበትና የምንረካበት የህየወት ዘይቤ እንጂ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አይደለም፡፡ ሁል ጊዜ ወደእርሱ እንድንቀርብ እግዚአብሄር ይፈልጋል፡፡
በመፅሃፍ ቅዱስ የእግዚአብሄርና የህዝቡ ግንኙነት እንደባልና ሚስት ግንኙነት ጊዜ ተጠቅሶ እናገኘዋለን፡፡ ይታያችሁ ሚስት ባልዋን የምትፈልገውና ከባልዋ ጋር የምታወራው ከባልዋ የሆነ ነገር ስትፈልግ የሆነ ፣ ልክ የፈለገችውን ስታገኝ ደግሞ ብትለየው ፣ እንደገና ባልዋን የምትፈልገው ደግሞ ከባልዋ የምትፈልገው ሌላ ነገር ሲገኝ ብቻ ቢሆን ይህ ጤናማ ትዳር አይደለም፡፡
ባልና ሚስት ከሁሉም በላይ ወዳጆችና ጓደኛሞች ናቸው፡፡ የባልና ሚስትን ትልቁን ድርሻ የሚይዘው አብሮነትና ፣ ማውራትና መነጋገር ነው፡፡ አንድ ልጅ አባቱን የሚያናግረው ከአባቱ የሆነ ነገር ሲፈልግ ብቻ ቢሆን ይህ የተበላሸ የአባትና የልጅ ግንኙነት እንደሆነ በቀላሉ እናስተውላለን፡፡ ምክኒያቱም ልጅ አባቱን የሚፈልገው ለአንድ ነገር ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ነገር ሁልጊዜም ነው፡፡ አባት ልጁን ማየት ይፈልጋል ፣ ከልጁ ጋር ማዋራት ይፈልጋል ፣ ከልጁ ጋር መጫወት ይፈልጋል፡፡ ከልጁ ጋር አብሮ መቀመጥ ጊዜ ማሳለፍ ይፈልጋል፡፡ አባት ልጁን ይራበዋል ይናፍቀዋል፡፡
እንደዚሁ እግዚአብሄር እኛን ልጆቹን ይራበናል ይጠማናል ይናፍቀናል፡፡ ለእርሱ ጊዜ እንድንሰጥ ይፈልጋል፡፡ እርሱና እኛ ብቻ የምንገናኝበትን ጊዜ እንድናዘጋጅለት ይፈልጋል፡፡ ትኩረታችን እንድንሰጠው ይፈልጋል፡፡ በእኛና በእርሱ መካከል ምንም ነገር ጣልቃ እንዲገባ እግዚአብሄር አይፈልግም፡፡
እነዚህም ጌታን ሲያመልኩና ሲጦሙ መንፈስ ቅዱስ፦ በርናባስንና ሳውልን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ አለ። ሐዋርያት 13፡2
ከዚህ የመፅሃፍ ቅዱስ ክፍል እንደምንረዳው እነዚህ ሰዎች የተለየ የፀሎት ርእስ እንደነበራቸው የሚያሳይ ምንም ነገር የለም፡፡ ራሳቸውን ለይተው በእግዚአብሄር ፊት ነበሩ፡፡ እግዚአብሄርን ይጠብቁ ነበር፡፡ ለእግዚአብሄር ሙሉ ትኩረታቸውን በመስጠት ከእርሱ ጋር ህብረት ያደርጉ ነበር፡፡ አንድ አስተናጋጅ ተመጋቢ ጋር ቀርቦ ምን ይጠጣሉ ምን ይበላሉ እንዴት ይሁንሎት ብሎ እንደሚጠይቅና ተመጋውን ለማስደሰት እንደሚጠብቅ እንደሚያገለግለውም እነርሱም በእግዚአብሄር ፊት ይቆዩ ይጠብቁ ነበር፡፡
እግዚአብሄር የሚፈልገውን ለማድረግ ተዘጋጅተው ይሰሙት ነበር፡፡ ጊዜያቸውን ለእግዚአብሄር ሰጥተው በፊቱ ነበሩ፡፡ እግዚአብሄርን ያመልኩ ነበር ከፍ ከፍ ያደርጉት ያወድሱት ነበር፡፡
የምንጠይቀው ነገር ሲኖር ብቻ መሆን የለበትም እግዚአብሄርን መፈለግ ያለብን፡፡ ከመሬት ተነስተን የእግዚአብሄርን ፊት መፈለግ አለብን፡፡ የፀሎት ጥያቄ ባይኖረንም እግዚአብሄርን ማምለክና በፊቱ መቆየት ይጠበቅብናል፡፡ ከእርሱ ጋር ህብረት ለማድረግ ብቻ ከእርሱ ጋር መሆን ያስፈልገናል፡፡ በሌሎች ነገሮች ላይ ባተሌ በመሆን እግዚአብሄርን አለመፈለግ በቂ ምክኒያት አይደለም፡፡ ለእግዚአብሄር ጊዜ ላለመስጠት ለምናቀርበው ማንኛውም ምክኒያት እግዚአብሄር አያጨበጭብልንም፡፡ ለምንም ነገር ባተሌ ብንሆን ለእግዚአብሄር ባተሌ መሆን ተቀባይነት የሌለው ሰንካላ ምክኒያት ነው፡፡
የእኛን ኑሮ ለማሸነፍ በሚል እግዚአብሄርን ችላ ማለት እግዚአብሄር የማይቀበለው ሰንካላ ምክኒያት ነው፡፡ ኑሮህን ለማሸነፍ የምረዳን እኔን ፈልገኝ ነው የሚለው እግዚአብሄር፡፡ ሌላ የምንፈልገውን ትተን እግዚአበሄርን ስንፈልግ ሌሎች ፍላጎቶቻችን ይሟላሉ፡፡ እግዚአብሄርን መፈለግ ትተን ሌሎች ነገሮችን ስንፈልግ የህይወት አላማችን እንጎድላለን፡፡
እግዚአብሄር የፈጠረን ለእርሱ ክብር ነው፡፡ እግዚአብሄ የፈጠረን ዋናው አላማ ከእርሱ ጋር ህብረት እንድናደርግ ነው፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር ህብረት እንዳናደርግ ምንም ምክኒያት ካገኘን ከህይወት ዋናው ግባችን እንደወደቅን ማረጋገጫው ነው፡፡
እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው ቤተሰብ ፈልጎ ነው፡፡ እግዚአብሄር ሰውንም በመልኩና በአምሳሉ የፈጠረው ካለምንም እንቅፋት ከሰው ጋር ህብረትን ለማድረግ ነው፡፡
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ራእይ #ፀሎት #እግዚአብሄርንመፈለግ #መሰረታዊፍላጎት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ጥሪ #አላማ #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ግብ #ትግስት #መሪ

Thursday, December 1, 2016

ፍቅር እና "ፍቅር"

እንደ ፍቅር በጣም አስፈላጊ ነገር የለም፡፡ እንደ ፍቅር ደግሞ ትርጉሙ የተዛባ ነገር በአለም ላይ ምንም ነገር የለም፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎች ፍቅር የሚሉት ምኞታቸውን ነው፡፡ የፍቅርንና የምኞትን ባህሪያት ከእግዚአብሄር ቃል በመመልከት ልዩነታቸውን እስኪ እንመልከት፡፡
ፍቅር የሚያተኩረው ሌላው ላይ ነው፡፡ ፍቅር ሌላውን በመጥቀም ሌላውን በማንሳት ሌላውን በማገልገልና በሌላው ላይ ዋጋን በመጨመር ላይ ያተኩራል፡፡
ምኞት የሚያተኩረው ራስ ላይ ነው፡፡ ምኞት በማንኛውም ግንኙነት የሚያስበው እርሱ ምን እንደሚያገኝና እንደሚያተርፍ ብቻ ነው፡፡ ፍቅር የሌላውን ፍላጎት ለማሟላት ሲሄድ ምኞት ግን የራሱ ፍላጎት ብቻ ለማሟላት ይሄዳል፡፡
ፍቅር ሌላውን ሲያስቀድም ምኞት ራሱን ያስቀድማል፡፡ ፍቅር የራሱን ፍላጎት ስለሌላው ፍላጎት ያዘገየዋል፡፡ ምኞት ግን ስለሌላው ፍላጎት የሚያዘገየው ምንም ጥቅም የለም፡፡
ሁሉን ይታገሣል፥ ሁሉን ያምናል፥ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፥ በሁሉ ይጸናል። 1ኛ ቆሮንቶስ 13፡7
ፍቅር በመረዳት የሚደረግ ሲሆን ምኞት በስሜት የሚመራ ነው፡፡ ፍቅር ሌላውን እንዳይወድ የሚፈትኑትን አሉታዊ ስሜቶች ሰምቶ ፍቅርን ከመከተል አይመለስም፡፡ ምኞት ግን ስሜቱን ብቻ ይከተላል፡፡
ፍቅራችሁ በእውቀትና በማስተዋል ሁሉ ከፊት ይልቅ እያደገ እንዲበዛ ይህን እጸልያለሁ። ፊልጵስዩስ 1፡9
ፍቅር እኔ እበልጣለሁ ፣ እኔ ይገባኛል ፣ እኔ የእኔ ለእኔ ነው ሁልጊዜ የሚለው፡፡ ፍቅር ግን አንተ ይገባሃል ፣ አንተ ትሻላለህ ፣ አንተ ትበልጣለህ ብሎ ሌላውን በትህትና ይቆጥራል፡፡
ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፥ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር፤ ፊልጵስዩስ 2፡3
ፍቅር ምክኒያታዊ ያልሆነ ሲሆን ምኞት ምክኒያታዊ ብቻ ነው፡፡ ፍቅር እንካ በእንካ አይደለም፡፡ ፍቅር የሌላውን ሁኔታ ሳያይ የራሱን ሌላውን የማክበር ሃላፊነት ይወጣል፡፡ ምኞት ቀድሞ እንኳን መልካም ካደረገ ያደረገው የተሻለ ጥቅምን ፈልጎ ብቻ ነው፡፡ ወይም መልካም ላደረጉለት ብቻ ነው መልካም የሚያደርገው፡፡ ምኞት ምንም ጥቅም ያላገኘበት ወይም ወደፊት የማያገኝበት ከሆነ ዞር ብሎ አያየውም፡፡
የሚወዱአችሁን ብትወዱ ምን ዋጋ አላችሁ? ቀራጮችስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? ወንድሞቻችሁንም ብቻ እጅ ብትነሡ ምን ብልጫ ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? ማቴዎስ 5፡46-47
ዓይን ስለ ዓይን ጥርስም ስለ ጥርስ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ክፉውን አትቃወሙ፤ ዳሩ ግን ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙርለት፤ ማቴዎስ 5፡38-39
ፍቅር የህይወት ዘመን ሃላፊነት ሲሆን ምኞት የአንድ ሰሞን ጊዜያዊ ነው፡፡ ፍቅር የእውነተኛ ሰው ህይወቱ ነው፡፡ ሰው ፍቅርን የሚከታተለው በውሳኔ ስለሆነ ሰው ከፍቅር መቼም አይለወጥም፡፡ ምኞት ግን ከሌላው በሚገኘው ጥቅም ላይ ስለተመሰረተ ጥቅሙ በቆመ ጊዜ ለመቀጠል አቅም አይኖረውም፡፡
እንዲህም ከሆነ፥ እምነት ተስፋ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው። 1ኛ ቆሮንቶስ 13፡13
ፍቅር ሌላውን ለማገልገል በሌላው ላይ የማይደገፍ ሲሆን ምኞት የራሱን ስለሚፈልግ በሌላው ላይ ያለመጠን የሚደገፍ ነው፡፡ ፍቅር ለሰው መልካም ለማሰብ መልካም ለመናገርና መልካም ለማድረግ የማንም ፈቃድ አያስፈልገውም፡፡ ምኞት ግን ሌላውን ለማስወጣት በሌላው ላይ ከመጠን ያለፈ መደገፍ ይኖርበታል፡፡ ስለዚህ ምኞት ሁልጊዜ ያዝናል ተስፋ ይቆርጣል፡፡
ፍቅር ሌላውን በማርካት ብቻ ይረካል ምኞት ራሱን በማርካት ብቻ ይረካል፡፡ ፍቅር የምሰጠው አለኝ ባለጠጋ ነኝ ስለሚል ለሌላው በመስጠት ይረካል፡፡ ምኞት ግን ምስኪን እኔ አስተሳሰብ ስላለው እኔ ምንም የለኝም ፣ የምሰጠው የለኝም ፣ ደሃ ነኝ የሚሰጠኝ እፈልጋለሁ ስለሚል የሚረካው በመቀበል ብቻ ነው ፡፡
ፍቅር ሌላውን ለመንከባከብ እንዲያስችለው ሌላውን ለመረዳት ይጥራል፡፡ ፍቅር ትጉህ ነው፡፡ ፍቅር ሌላውን በተሻለ ለመንከባከብ እንዲያስችለው የሌላውን ፍላጎትና ባህሪ በትጋት ያጠናል፡፡ ምኞት ለሌላው ግድ ስለሌለው ሌላውን ለማጥናት ስንፍና ስለአለበት የራሱን ስሜት ብቻ ያዳምጣል፡፡ ፍቅር በስንፍና እይመጣም ፍቅር ጥረትና ድካም ይጠይቃል፡፡
በጸሎታችን ጊዜ ስለ እናንተ ስናሳስብ፥ የእምነታችሁን ስራ የፍቅራችሁንም ድካም በጌታችንም በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን የተስፋችሁን መጽናት በአምላካችንና በአባታችን ፊት ሳናቋርጥ እያሰብን፥ እግዚአብሔርን ሁል ጊዜ በሁላችሁ ምክንያት እናመሰግናለን፤ 1ኛ ተሰሎንቄ 1፥2-3
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልዕክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ፍቅር #ምኞት #አላማ #መሰረታዊፍላጎት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ጥሪ #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ