Popular Posts

Monday, November 14, 2022

የእግዚአብሔር ፈቃድ ወይም ሞት!

 


የእግዚአብሔር ፈቃድ ወይም ሞት!

የተፈጠርኩት ለእግዚአብሔር ክብር እንደሆነ አውቃለሁ፡፡

በስሜ የተጠራውን ለክብሬም የፈጠርሁትን፥ የሠራሁትንና ያደረግሁትን ሁሉ አምጣ እለዋለሁ። ትንቢተ ኢሳይያስ 43፡6-7

በዋጋ እንደተገዛሁ አውቃለሁ፡፡

በዋጋ ተገዝታችኋል፤ የሰው ባሪያዎች አትሁኑ። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 7፡23

እኔ የራሴ እንዳልሆንኩ አውቃለሁ

በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 6፡20

የእግዚአብሔር ፈቃድ መሆኑን ላረጋግጥ እንጂ ምንም ነገር አደርጋለሁ!

የእግዚአብሔር ፈቃድ መሆኑን ላረጋግጥ እንጂ የፈለገውን ያክል ሞኝ ያስብለኝ እንጅ ምንም ነገር አደርጋለሁ፡፡

የእግዚአብሔር ፈቃድ መሆኑን ላረጋግጥ እንጂ ተቃውሞ በሁሉም አቅጣጫ ያስነሳብኝ እንጂ ፈቃዱ እንደሆነ ያመንኩበትን ምንም ነገር አደርጋለሁ፡፡

የእግዚአብሔር ፈቃድ መሆኑን ያላረጋገጥኩት ነገር በወርቅ ቢንቆጠቆጥ ዞር ብዬ እንኳን አላየውም፡፡ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማድረግ የማንንም እሺታ አልጠብቅም፡፡

ወዲያው ከሥጋና ከደም ጋር አልተማከርሁም፥ ወደ ገላትያ ሰዎች 1፡15-16

የእግዚአብሔር ፈቃድ ከሆነ ሰዎች የሚያከብሩትን ነገር ሁሉ እንቃለሁ ሰዎች የሚንቁትን ነገር ሁሉ አከብራለሁ፡፡

አዎን፥ በእውነት ከሁሉ ይልቅ ስለሚበልጥ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ጌታዬ እውቀት ነገር ሁሉ ጉዳት እንዲሆን እቈጥራለሁ፤ ስለ እርሱ ሁሉን ተጐዳሁ፥ ክርስቶስንም አገኝ ዘንድ፥ በክርስቶስም በማመን ያለው ጽድቅ ማለት በእምነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ያለው ጽድቅ እንጂ ከሕግ ለእኔ ያለው ጽድቅ ሳይሆንልኝ፥ በእርሱ እገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጕድፍ እቈጥራለሁ፤ ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 3:8-9

የእግዚአብሔር ፈቃድ መሆኑን ላረጋግጥ እንጂ በሁሉም ዘንድ ያስጠላኝ እንጂ ለሚያስከትልብኝ አደጋ ወይም ሪስክ ራሴን እሰጣለሁ፡፡

ሰውን ወይስ እግዚአብሔርን አሁን እሺ አሰኛለሁን? ወይም ሰውን ደስ ላሰኝ እፈልጋለሁን? አሁን ሰውን ደስ ባሰኝ የክርስቶስ ባሪያ ባልሆንሁም። ወደ ገላትያ ሰዎች 1፡10

የእግዚአብሔር ፈቃድ መሆኑን ላረጋግጥ እንጂ ሁሉን ባጣ እንደክብር እቆጥረዋለሁ፡፡

ከአእላፍ ይልቅ በአደባባዮችህ አንዲት ቀን ትሻላለች፤ በኃጥኣን ድንኳኖች ከመቀመጥ ይልቅ፥ በእግዚአብሔር ቤት እጣል ዘንድ መረጥሁ። መዝሙር 84፡10

የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዳለበት ያወቅኩትን ነገር ምክኒያቱ ባይገባኝም እንኳን አብሬው እሞታለሁ፡፡

እነዚህ ሁሉ አምነው ሞቱ፥ የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል አላገኙምና፤ ዳሩ ግን ከሩቅ ሆነው አዩትና ተሳለሙት፥ በምድሪቱም እንግዶችና መጻተኞች እንዲሆኑ ታመኑ። ወደ ዕብራውያን 11፡13

ለእኔ ሃብት ማለት በእጦትም ቢሆን የእግዚአብሔርን ፈቃድ መፈፀም ነው፡፡ ለእኔ ድህነት ማለት ሁሉም ሞልቶለት የእግዚአብሔርን ፈቃድ መሳት አለመፈፀም ነው፡፡ ለእኔ ዝና ማለት በመደበቅ እና በመጥፋት የእግዚአብሔርን ፈቃድ መፈፀም ነው፡፡ ለእኔ ዝነኛ አለመሆን ማለት በአለም ሁሉ ተከቦ እና ተደንቆ የእግዚአብሔርን ፈቃድ መሳት አለመፈፀም ነው፡፡ ለእኔ ሃያልነት ማለት በድካም የእግዚአብሔርን ፈቃድ መፈፀም እና ጌታን ደስ ማሰኘት ነው፡፡ ለእኔ ድካም ማለት እጅግ ሃያል ሆኖ ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር መተላለፍ ነው፡

ለእኔ ስኬት ማለት አይን ውስጥ የማይገባውን የተደበቀውን የእግዚአብሔርን ፈቃድ መፈፀም ነው፡፡ ለእኔ ውድቀት ማለት የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሌለበትን ታላላቅ ነገር ማድረግ ነው፡፡

የእግዚአብሔር ፈቃድ ከሆነ የሚያስጠላው ያምረኛል፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃድ ከሌለበት የሚያምረው ያስጠላኛል፡፡

የእግዚአብሔር ፈቃድ ካለበት የሚመረው ይጣፍጠኛል፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃድ የሌለበት የሚጣፍጠው ነገር ያቅለሸልሸኛል፡፡

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa 

No comments:

Post a Comment