Popular Posts

Wednesday, May 25, 2022

የዝነኝነት አደጋ


 ለማንም አንዳች እንዳትናገር ተጠንቀቅ፥ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን ስለ መንጻትህ ሙሴ ያዘዘውን አቅርብ አለው። የማርቆስ ወንጌል 144

ለማንም አትንገሩ ብሎ አዘዛቸው እነርሱ ግን ባዘዛቸውም መጠን ይልቅ እጅግ አወሩት የማርቆስ ወንጌል 736

ወደ ቤቱም ሰደደውና፦ ወደ መንደሩ አትግባ በመንደሩም ለማንም አንዳች አትናገር አለው። የማርቆስ ወንጌል 826

ስለ እርሱም ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው። የማርቆስ ወንጌል  830

ከተራራውም ሲወርዱ የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሣ ድረስ ያዩትን ለማንም እንዳይነግሩ አዘዛቸው። የማርቆስ ወንጌል 99

እርሱም ለማንም እንዳይናገር አዘዘው፥ ነገር ግን፦ ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፥ ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን ስለ መንጻትህ ሙሴ እንዳዘዘ መሥዋዕት አቅርብ አለው። የሉቃስ ወንጌል 514

ወላጆችዋም ተገረሙ፤ እርሱ ግን የሆነውን ለማንም እንዳይነግሩ አዘዛቸው። የሉቃስ ወንጌል 856

ኢየሱስ ከፈወሰ እና ድንቅ እና ታእምራት ካደረገ በኋላ ለማንም አትናገሩ ሲል በተከታታይ እናያለን፡፡ ሰዎች የእግዚአብሄርን ድንቅ መናገራቸው መልካም ቢሆንም ነገር ግን ያለጊዜው የሰዎችን ትኩረት መሳብ እና ዝነኛ መሆን በኢየሱስ ላይ የሚያመጣው ጉዳት ስለሚበልጥ ለማንም አትናገሩ ብሎ ድንቅ የተደረገላቸውን ያስጠነቅቅቃአቸው ነበር፡፡

ኢየሱስ የትኩረት እጥረት አልነበረበትም፡፡ የኢየሱስ ትኩረት የእግዚአብሄርን የአባቱን ፈቃድ በምድር ላይ አድርጎ አብን ማክበር ነበር፡፡ በትኩረትም ያለትኩረትም የእግዚአብሄርን ፈቃድ መፈፀም አነደሚቻል ኢየሱስ በአገልግሎቱ አሳትይቶዋል፡፡ የእግዚአብሄርን የልቡን ፈቃድ አድርጎ ለማለፍ የሰውን ትኩረት መሳብ ግዴታ አይደለም፡፡

እነሆ የመረጥሁት ብላቴናዬ፥ ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ወዳጄ፤ መንፈሴን በእርሱ ላይ አኖራለሁ፥ ፍርድንም ለአሕዛብ ያወራል።

አይከራከርም አይጮህምም፥ ድምፁንም በአደባባይ የሚሰማ የለም። ማቴዎስ 12፡18-19

የኢየሱስ ትኩረት ብዙ ሰዎችን መሰብሰብ ሳይሆን ወደ እርሱ የመጡትን በታማኝነት እና  በትጋት ማገልገል ነበር፡፡

የኢየሱስ የምድር ላይ አገልግሎት የሚመዘነው በተከተሉት ሰዎች ብዛት እንዳልነበረ ኦየሱስ ጠንቅቆ ያውቅ ስለነበረ ትኩረቱ ወደእርሱ የመጡትን በታማኝነት እና በትጋት ማስተማር እና መፈወስ ነበር፡፡

እንዲያውም ኢየሱስ ይጠነቀቀ የነበረው ካለጊዜው የመጣ ዝና በአገልግሎቱ ላይ አላስፈላጊ ጫና እንዳይፈጥርበት እና ከአገልግሎቱ እንዳያስተጓጉለው ነበር፡፡  

እግዚአብሄር አብ ብዙዎች በኢየሱስ አገልግሎት የሚጠቀሙበት ጊዜው ሲደርስ የኢየሱስ ዝና እስከ ሶርያ ድረስ እንደ ወጣ መፅሃፍ  ቅዱስ ይናገራል፡፡

ያም ዝና ወደዚያ አገር ሁሉ ወጣ። ማቴዎስ 926

ኢየሱስ ከፈወሰ በሁዋላ ለማንም አትናገሩ ቢልም የኢየሱስ ዝና የሚወጣበት ትክክለፃው ጊዜ ሲመጣ ግን ኢየሱስን ዝነፃ እንዳይሆን ምንም ነገር አላገደውም ነበር፡፡

ጊዜ በጊዜው የሚመጣ ርያ ድረስ ወጣ

ዝናውም ወደ ሶርያ ሁሉ ወጣ፤ በልዩ ልዩ ደዌና ሥቃይም ተይዘው የታመሙትን ሁሉ አጋንንትም ያደሩባቸውን በጨረቃም የሚነሣባቸውን ሽባዎችንም ወደ እርሱ አመጡ፥ ፈወሳቸውም። የማቴዎስ ወንጌል 424

ያም ዝና ወደዚያ አገር ሁሉ ወጣ። የማቴዎስ ወንጌል 926

በዚያ ዘመን የአራተኛው ክፍል ገዥ ሄሮድስ የኢየሱስን ዝና ሰማ፥ የማቴዎስ ወንጌል 141

ዝናውም ወዲያው በየስፍራው ወደ ገሊላ ዙሪያ ሁሉ ወጣ።የማርቆስ ወንጌል 128

ኢየሱስም በመንፈስ ኃይል ወደ ገሊላ ተመለሰ፤ ስለ እርሱም በዙሪያው ባለችው አገር ሁሉ ዝና ወጣ።የሉቃስ ወንጌል 414

ዝናም በዙሪያው ባለች አገር ወደ ስፍራው ሁሉ ስለ እርሱ ወጣ። የሉቃስ ወንጌል 437

ይህም ዝና ስለ እርሱ በይሁዳ ሁሉ በዙሪያውም ባለች አገር ሁሉ ወጣ።የሉቃስ ወንጌል 717

እግዚአብሄር ሞገስን ሲያበዛ ካለምንም ጥረት እና ጭንቀት በጊዜው ስማችንን ያወጣዋል፡፡

እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፤ 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 5፡6

የእግዚአብሄር ሞገስ ህዝቡን በጥረት ሳይሆን በመለኮታዊ መንገድ በቀላሉ ይጠራል፡፡

እነሆ፥ የማታውቀውን ሕዝብ ትጠራለህ፥ የእስራኤልም ቅዱስ አክብሮሃልና ስለ አምላክህ ስለ እግዚአብሔር የማያውቁህ ሕዝብ ወደ አንተ ይሮጣሉ። ትንቢተ ኢሳይያስ 55፡5

ጊዜውን የጠበቀ ዝና ሰዎችን ለፈውስ እና ለነፃነት እንደሚሰበስብ ሁሉ ያለጊዜው የሆነ የሰዎችን ትኩረት መፈለግ በአገልጋዩ ላይ ከፍተኛ ጫና በመፍጠር ከአገልግሎት ሊያስተጓጉል ይችላል፡፡

እግዚአብሄር አንዳንዴ ህይወታችንን ቀለል የሚያደርገው እና ለጊዜው የሚደብቀን ከጊዜው በፊት ያለውን የዝነኝነት አላስፈላጊ ሸክም እንዳንሸከም ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ስራ ለመስራት ትኩረትን መሳብ አስፈላጊ አይደለም፡፡

አገልጋይም ዝና ያለውን ጥቅም ብቻ ካየ እና ከዝናው መምጣት ጋር ተያይዞ የሚመጣውን ሃላፊነቱን ካላየ ዝናውን ብቻ ሲያሳድድ እግዚአብሄር ከሰጠው አገልግሎት ይስተጓጎላል፡፡

ከዝና ጋር አብረው የሚመጡ ብዙ አላስፈላጊ ሸክሞች አሉ፡፡ ሰው ራሱ ፈልጎ ዝናውን ካላመጣው እና እግዚአብሄር በራሱ ጊዜ ካመጣው ከዝና ጋር የሚመጡ ሸክሞችን የሚሸከምበት ፀጋን ራሱ እግዚአብሄር ያበዛለታል፡፡

ነገር ግን ሰው ራሱን የሰዎችን ትኩረት ከሳበ ፣ ራሱን ዝነኛ ካደረገ እና በቅልጥፍናው ራሱን አላግባብ ካስተዋወቀ ዝናውን ለማግኘት ብቻ ሳይሆን ዝናውን ለመጠበቅ አላስፈላጊ ዋጋ ይከፍላል፡፡ በተጋነነው ማስታወቂያ የመጡትን ሰዎች ማርካት ችግር ይሆናል፡፡ አላግባብ ትኩረታቸው የተሳበውን ሰዎች ለማስደሰት እግዚአብሄር ከሰጠው የህይወት አላማ ለመውጣት ይፈተናል፡፡ በራሱ ያመጣውን ታዋቂነት  እና ዝና ለማስጠበቅ እግዚአብሄርን ያማከለ ሳይሆን ህዝብን ያማከለ ሰው ይሆናል፡፡ እግዚአብሄር ህዝቡን እንዲያገለግልበት የሰጠውን አቅርቦት ዝናን ለማስጠበቅ ሊያባክነው ይችላል፡፡

በጊዜው እግዚአብሄር ያመጣውን ዝና የሚጠብቅለት ማንም ሰው እስከማያስፈልገው ድረስ ራሱ እግዚአብሄር ይጠብቀዋል፡፡ ሰው በራሱ ያመጣውን ዝነኝነት ራሱ እንዳመጣው በራሱ ወጭ ይጠብቀዋል እንጂ እግዚአብሄር አይጠብቅለትም፡፡

አገልጋዩ የሚያገለግለውን አገልግሎት አያስተዋውቅ ማለት ሳይሆን የራሱን የስጋ ክንድ በመጨመር ትከረቱ ማስተዋወቁ ላይ አይሁን ነው፡፡ የአገልጋይ ትኩረት መሆን ያለበት እግዚአብሄር የላከለትን ሰዎች በታማኝነት ማገልገል ላይ መሆን አለበት፡፡

በምንም ነገር ላይ ማስተዋወቅ ያለብን ጌታን እንጂ ራሳችንን መሆን የለበትም፡፡ መታወቅም ካለብን ጌታን በማስተዋወቅ እንጂ ራሳችንን ብቻ በማስተዋወቅ መሆን የለበትም፡፡

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa

ለተጨማሪ መጣጥፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/

#ራዕይ #የቅንጦት #አስፈላጊነቱ #ፈቃዱ #መምራቱ #አጀንዳው #ኢየሱስ #ጌታ #ቤተ ክርስቲያን #ስኬት # #ተመስጦ #ስብከት #ትኩረት #ዝና #ማስታወቅ 

No comments:

Post a Comment