Popular Posts

Monday, May 23, 2022

እግዚአብሄርን ማገልገል የሚችለው ባለው ነገር የሚረካ ሰው ብቻ ነው


 እግዚአብሄርን ማገልገል የሚችለው ባለው ነገር የሚረካ ሰው ብቻ ነው

በህይወት የምንፈልገው ገደብ የለሽ ነው። የሆነ ነገር እንዲኖርህ ትመኛለህ እና ልክ ስታገኘው በፊትህ ክብሩን ያጣል። አንድን የተሻለን ነገር የሚፈልጉ ሰዎች ባገኙት ጊዜ የተለየ ነገር መፈለግ ይጀምራሉ፡፡ እና ከፍተኛውን ነገር ላይ እንደደረሱ ነገሩ የበፊት ክብሩን ያጣል፡፡ አሁንም የተሻለ እና የበለጠ ነገር እንዲኖራቸው ይመኛሉ እና አሁንም ልክ እንዳገኙት ያንስባቸዋል።

ይህ በተቻለ ፍጥነት መውጣት መላቀቅ ያለብን የሕይወት ክፉ አዙሪት ነው። በዚህ ዑደት ውስጥ ከወደቁ እግዚአብሔርን ማገልገል አይቻልም።

አትሳሳቱ እኔ የተሻለ እና የበለጠ አልቃወምም፡፡ እኔ ጥያቄዬ "የተሻለ እና የበለጠ" ለመፈለግ ያነሳሳን መነሻ የልብ ሃሳብ /motive/ ላይ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ  "ለተሻለ እና ለበለጠ" ያለን ግምት የተሳሳተ ነው። የተሻለ እና የበለጠ" አቅሙ የተገደበ ነው፡፡ "የተሻለ እና የበለጠ" የማይሰጠን በጣም ብዙ ነገር አለ። "የተሻለ እና የበለጠ" ሲገኝ እኛ የምንጠብቀውን ነገር ሊሰጠን ስለማይችል ያሳዝነናል። "የተሻለ እና የበለጠ" ከአለአቅሙ በላይ ብዙ ነገር እንጠብቅበታለን።

ሌላው ጥያቄ "ባለን ነገር ምን እየሰራን ነው?" የሚል ጥያቄ ነው፡፡ "የተሻለ እና የበለጠ" ን ነገር የምንከተለው እንዲያው "የተሻለ እና የበለጠ" ነገር ለመከተል ያህል ብቻ ነው ወይስ "በተሻለ እና በበለጠ" ነገር ሌሎችን በመድረስና እና ባለን ነገር ሌሎችን በማገልገል አላማ ነው?

ባለን ካልረካን እና ባለን ካልተጠቀምን ሁል ጊዜ "የተሻለ እና የበለጠ" የምንፈልግ ከሆነ "የተሻለ እና የበለጠ" ለማግኘት ስንል ምንም ሳናደርግ ህይወታችንን በከንቱ እናባክነዋለን። በተሳሳተ መልኩ "የተሻለ እና የበለጠን" ነገር የሚፈልጉ ሰዎች ሲያገኙትም አይደሰቱበትም፡፡ ሲያገኙት ወዲያው ይንቁታል፡፡ ምክንያቱም በመጀመሪያ ደረጃ  "የተሻለ እና የበለጠ" የመፈለግ ተነሳሽነታቸው /motive/ የተዛባ ነው።

ስላላችሁ ነገር አመስጋኝ ከሆናችሁ እና ከረካችሁ ከራሳችሁ ህይወት አልፋችሁ ሌሎችን መድረስ እና ማገልገል ትችላላችሁ።

ሐዋርያትም ጌታን፦ እምነት ጨምርልን አሉት። 

ጌታም አለ፦ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ፥ ይህን ሾላ፦ ተነቅለህ ወደ ባሕር ተተከል ብትሉት፥ ይታዘዝላችሁ ነበር። ሉቃስ 17፡5-6

አብዛኛዎቹ ችግሮቻችን "የተሻሉ እና የበለጡ" ነገሮች ከማጣት አይመጡም። አብዛኛው ችግሮቻችን የሚመነጩት ያለንን ነገር ካለመጠቀም ነው። ትርጉም ያለው ነገር ለማድረግ የሚያስችለን ነገር ሁሉ እያለን አሁንም "የተሻለ እና የበለጠ" ነገር እንጠብቃለን፡፡ ባለን ነገር አንድ ነገር ለማድረግ ዛሬ መወሰን አለብን፡፡

ሁልጊዜ ልዩነት የሚያመጣው “የተሻለ እና የበለጠ” ጉዳይ እንዳልሆነ ብንረዳ የጸሎት ሕይወታችን ይለወጥ ነበር።

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa 

ለተጨማሪ መጣጥፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/

#ራዕይ #የቅንጦት #አስፈላጊነቱ #ፈቃዱ #መምራቱ #አጀንዳው #ኢየሱስ #ጌታ #ቤተ ክርስቲያን #ስኬት # #ተመስጦ #ስብከት #እናማጥናለን

No comments:

Post a Comment