Popular Posts

Sunday, May 22, 2022

ቅንጦት በጣም ውድ ነው

 


ቅንጦት በጣም ውድ ነው።
ቅንጦት በጣም ውድ ነው የሚለውን ስታይ እና ታዲያ ቅንጦት ርካሽ አይደለም ልትል ትችላለህ፡፡ ቅንጦት ስል ውድ ነገሮችን ማለቴ አይደለም፡፡ ቅንጦት ስል ከሚያስፈልጉን ነገሮች ውጭ ያሉ ነገር ግን እኛ የምንፈልጋቸው ነገሮች ማለቴ ነው፡፡ 
ጥራት ያላቸው ነገሮች ጥራት ከሚያንሳቸው ነገሮች በበለጠ ዋጋ እንደሚገዙ አውቃለሁ፡፡ የቅንጦትን ነገር ሳነሳ ለህይወት አላማችን በእርግጥ የማያስፈልጉን እኛ ግን የምንፈልጋቸውን ነገሮች ማንሳቴ ነው።
እግዚአብሔር አባታችን ነው። እርሱ ያለማቋረጥ የሚያስፈልገንን ነገር ያዘጋጅልናል። ያ ማለት ግን እኛ የምንፈልገውን ሁሉ ያቀርባል ማለት አይደለም። እግዚአብሄር ፍላጎትህን እንደሚያሟላ የተረጋገጠ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር የምትፈልገውን ነገር ሁሉ እንደሚሰጥህ ዋስትና የሚሰጥ የመፅሃፍ ቅዱስ ቃል የለም። ይልቁንም ቅዱሳት መጻህፍት የሚናገሩት የቅንጦት ኑሮን የሚፈልጉ ሰዎችን ፀሎት እግዚአብሄር እንደማይሰማ ነው፡፡ 
በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ አይደሉምን? ትመኛላችሁ ለእናንተም አይሆንም፤ ትገድላላችሁ በብርቱም ትፈልጋላችሁ፥ ልታገኙም አትችሉም፤ ትጣላላችሁ ትዋጉማላችሁ ነገር ግን አትለምኑምና ለእናንተ አይሆንም፤ ትለምናላችሁ፥ በምቾቶቻችሁም ትከፍሉ ዘንድ በክፉ ትለምናላችሁና አትቀበሉም። የያዕቆብ መልእክት 4፡1-3
በህይወታችን ለሚያስፈልገን ነገር ሁሉ የእግዚአብሄር ፀጋ በቂ ነው፡፡ 
ሰዎች በቅንጦት መኖር ሲፈልጉ እግዚአብሔር ለአላማው ያዘጋጀላቸውን አቅርቦት እግዚአብሔር ላላሰበው ነገር አላግባብ ይጠቀሙበታል። የእግዚአብሔርን አቅርቦት አላግባብ ስናባክን ሌላውን የሕይወታችንን ክፍል እንጎዳዋለን።
እግዚአብሔር በሕይወታችን ያለውን ዓላማ ለመፈጸም የሚያስፈልገንን ሁሉ እንደሚሰጠን ቃል ገብቷል። እግዚአብሄር የሚያቀርበው አቅርቦት ሁሉ ከህይወት ዓላማችን ጋር የተቆራኘ ነው።  "ይህ ነገር ተልእኮዬን ለመፈፀም አስፈላጊ ነው ወይ?" የሚለው ጥያቄ በሕይወታችን ውስጥ ፍላጎትን እና ቅንጦትን ለመለየት ወሳኝ መመዘኛ ነው፡፡ በድፍረት ለአላማዬ መሳካት ግዴታ ያስፈልገኛል ማለት ካልቻልን በስተቀር የምንፈልገው ነገር ቅንጦት እንጂ አስፈላጊ ላይሆን ይችላል። የቅንጦት ፍላጎት ተገቢ ካልሆነ ፉክክር ፣ ከራስ ወዳድነት እና ከስግብግብነት ይመነጫል። ከእኛ ጋር ተመሳሳይ የህይወት ዓላማ ከሌላቸው ከሌሎች ሰዎች ጋር እንድንወዳደር እና እንድንፎካከር አልተጠራንም። በሕይወታችን ውስጥ ልዩ የሆነ የእግዚአብሄር ዓላማ አለ።
የእግዚአብሔር አቅርቦት በሕይወታችን ውስጥ ባለው ልዩ ዓላማ የተገደበ ነው። የእግዚአብሄር አቅርቦት በህይወታችን ላለው አላማ አያንስም አይበዛም፡፡ እግዚአብሄር ያዘጋጀልንን አቅርቦት እግዚአብሔር ላልጠራን ነገር ስናውል እግዚአብሔር የሰጠንን አቅርቦት እናባክናለን። ከዓላማችን ውጪ ለሆነ ነገር የምናጠፋው ነገር ሁሉ የምናባክነው ለዓላማችን ከተሰጠን አቅርቦት ላይ ነው።
የቅንጦት ህይወት እንዲኖረን ከፈለግን ከሰዎች ጋር ጦር እና ጠብ ውስጥ እንገባለን፡፡ እግዚአብሄር ለቅንጦት አቅርቦትን ስለማያዘጋጅ የቅንጦት ፍላጎታችንን ለማሟላት ጠብ ውስጥ በመግባት እግዚአብሄር የሰጠንን እጅግ የከበረውን የህይወት አላማ እናባክነዋለን፡፡ 
ቅንጦትን መፈለግ ሰው በራሱ ዝነኛ ለመሆን ከመፈለግ ይመጣል። እራሳችንን ዝነኛ ካደረግን ዝናችንን ጠብቆ ማቆየት ከባድ ሸክም ይሆንብናል፡፡ እኛ ራሳችን ዝነኛ ለማድረግ ምንም የምናደርገው ነገር ከሌለ ጊዜውን ጠብቆ በተፈጥሮአዊ መንገድ እስከመጣ ድረስ ዝነኛ መሆን ምንም ስህተት የለበትም፡፡ ራስን ዝነኛ ለማድረግ የሚከፈለው እና ዝነኝነቱን ለመጠበቅ የሚከፈለው ዋጋ በጣም ከፍተኛ ብቻ ሳይሆን ሊከፍሉት የማይችሉት ውድ ዋጋን የሚያስከፈል ነገር ነው፡፡
ትርፍ ነገር ስለሌለ ዝናን የምትከተለው የእግዚአብሔር ዓላማ ለመኖር ከተሰጠህ ጊዜ ጉልበት እና እውቀት ላይ ቀንሰህ ነው። በመሠረቱ ዝናን መከተል  በእግዚአብሔር የተሰጠ አይደለም። ዝናን የምትከተል ከሆነ ዝናን የምትከተለው ራስህ ነህ እንጂ እግዚአብሔር የለበትም። ከሌሎች ጋር ከተወዳደርክ እና ከተፎካከርክ እግዚአብሔር ውድድሩን ስፖንሰር አያደርግም፡፡ 
ቅንጦቶቻችንን መፈለግ ካልተውን እና በሚያስፈልገን ነገር ላይ ካልረካን ሌሎችን መድረስ እና እነሱን ማገልገል አንችልም።
በሆንከው ነገር ካልረካህ በምታገኘው ነገር አትረካም።
ለተጨማሪ መጣጥፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/
#ራዕይ #የቅንጦት #አስፈላጊነቱ #ፈቃዱ #መምራቱ #አጀንዳው #ኢየሱስ #ጌታ #ቤተ ክርስቲያን #ስኬት # #ተመስጦ #ስብከት

No comments:

Post a Comment